Print this page
Monday, 19 June 2017 09:16

“አላውቃትም እንዳትለኝና እንዳልጮህ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የመድረኩ ቲያትር አልቆ መጋረጃ ይዘጋል፡  አንዱ ተዋናይም ጓደኛውን ያገኝና…
“ትወናዬ እንዴት ነበር?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
“ምንም አትል…” ይላል ጓደኛው፡፡
“ሦስቱንም ትዕይንት ብጫወት ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ትንሽ ቅር ያለኝ ገና በመጀመሪያው ትዕይንት በጥይት ተመትቼ መሞቴ ነው…” ይላል ተዋናዩ፡፡ ጓደኝየው ምን ቢለው ጥሩ ነው…
“ጥሩ ነበርክ፣ ግን ተመተህ መሞት የነበረብህ መጋረጃው ከመከፈቱ በፊት ነበር፣” አለውና አረፈው፡፡ ይሄኔ ተዋናዩ እኮ…አለ አይደል… “አገር ምድሩ የሚያውቀኝ ‘ሴሌብሪቲ’ ነኝ…” ምናምን ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል፡፡
ስሙኝማ… ታዋቂዎች በዙ፣ የምር፡፡ በቃ በምን ፍጥነት እንደሆነ አንድዬ ይወቀው...መሽቶ ሲነጋ የታዋቂ መአት ይፈለፈላል ነው የምላችሁ። እንደው ‘ምን ይመስለሀል’ ብትሉኝ…ወደፊት እውቅናን ኤክስፖርት ማድረግ እንችላላን፡፡ ልክ ነዋ… ከተራዎቹ ዜጎች ይልቅ ታዋቂዎች ሲበዙ ተረፈ ምርቱን ምን እናድርገው! ቂ…ቂ…ቂ…  ታዋቂ መሆን እንዴት ነው እንዲህ ቀላል የሆነው!
እናማ ማን ታዋቂ እንደሆነ መለየቱ የዜግነት ግዴታ አይነት ነገር የሆነ ይመስላል፡፡
የሆነ ቦታ ከሰዎች ጋር ተቀምጣችኋል፡፡ የሆነች ልጅ ትገባለች፡፡
“ያቺን ልጅ አየሀት?…” ይላችኋል አንዱ፡፡
“ያቺኛዋ ሚኒስከርት ያደረገችው፣ ደረቷን የገለጠችው…”
“አየኋት…” ቶሎ ታቋርጡታላችሁ፡፡ አለበለዛ ቀሚሷን አሳጥሮ፣ ደረቷን ገልጦ፣ ቀስ በቀስ ምስኪኗን እርቃኗን ሊያስቀራት ይችላላ! “ማናት?”
“ማናት! አላውቃትም እንዳትለኝ! አላውቃትም እንዳትለኝና እንዳልጮህ…”
“ከፈለግህ ጩህ፣ ግን አላውቃትም፡፡”
“እንዴት አታውቃትም! እዚሁ አገር ላይ አይደል እንዴ የምትኖረው!””
“የእኔ ጌታ፣ አላውቃትም አልኩህ፣ አላውቃትም፡፡”
“የፊልም ተዋናይት ነች እኮ!”
እናስ! እናስ ምን ይጠበስ! እሷ የፊልም ተዋናይ ስለሆነች የማወቅ ግዴታ አለባችሁ እንዴ!
ሊያጭላችሁ አስቦ ከሆነም ፊት ለፊት መናገር ነው፣ ቂ…ቂ…ቂ…!
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ለሚስቱ ”ውዴ፤የ300‚000 ብር የህይወት ዋስትና ገብቻለሁ፣” ይላታል፡፡ “እኔ አንድ ነገር ቢገጥመኝ ምን እሆናለሁ ብለሽ እንዳትጨነቂ፡፡”
“ጥሩ አድርገሀል፣ የእኔ ውድ፣” አለች ሚስቱ። “ከእንግዲህ በታመምክ ቁጥር ሀኪም ቤት ለሀኪም ቤት መንጦልጦል የለብንም፡፡” ነገርዬው እንዲህ ከሆነ ማን ተናገር አለው! አሁን እኮ ቤቱ ውስጥ ሰንደል በተለኮሰ ቁጥር “ኡፋ ልትገድለኝ ነው፣” እያለ ሲሳቀቅ ሊኖር ነው፡፡
ይቺን ደግሞ ስሙኝ…ሴትዮዋ ሀብት አንገቱ የደረሰ ባለቤቷ ይሞታል፡፡ እናላችሁ…አንድ ቀን እናቷ፤
“ለመሆኑ የውርስን ጉዳይ የሚፈጽምልሽ ደህና ጠበቃ አዘጋጅተሻል?” ትላታለች፡፡ ሚስት ሆዬ ምን ብትል ጥሩ ነው…
“እማዬ የጠበቃዎቹ ነገር ሊያሳብደኝ ነው። አንዳንዴማ ምነው ባሌ ባልሞተ ኖሮ እላለሁ፣” አለችና አረፈችው፡፡
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ኮሚክ ነገር እኮ ነው፡፡ ሥራን እያሳመሩ፣ እያሻሻሉ ከመሄድ ይልቅ አንዴ የሆነ መድረክ ወይም ስክሪን ላይ ‘ብልጭ’ ከተባለ…በቃ የታዋቂነት ‘አክሬዲቴሽን’ ምናምን ነገር የተሰጠ እናስመስለዋለን፡፡ የሚያውቅ ይወቅ፣ የማያውቅ … በቃ አላወቃትም፡፡ እሷን የማያውቅ ጸረ—ምናምን ተብሎ ይፈረጃል የሚል የውስጥ ሰርኩላር ነገር አለ እንዴ!
“ስማ…እንትን ሬድዮ ላይ ቶክ ሾው የሚያቀርብ፣ እንትን ጋዜጣ ላይ ስፖርት የሚጽፍ ታዋቂ ጋዜጠኛ እኮ ነው…”
እናስ! እናስ ምን ይጠበስ!
“የታወቀ ደራሲ እኮ ነው…”
እናስ! እናስ ምን ይጠበስ!
ኮሚክ እኮ ነው…እንኳን እኛ ራሱ፣ ዘፈን መዝፈኑን የማያውቅ ዘፋኝ፣ የመጀመሪያ ‘ሲንግሉን’ ሲለቅ…
“በናፍቆት ሲጠበቅ የነበረው…” በሚባልበት ዘመን እውቅና የእውነትም ቅርብ ነች፡፡
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ገና በጠዋቱ የምስጋናችንን ልክ ሰማየ ሰማያት እያደረስነው፣ የመጀመሪያ ጊዜ ዘፋኙን ከጥላሁን፣ የመጀመሪያ ጊዜ ገጣሚውን ከጸጋዬ ገብረ መድህን፣ የመጀመሪያ ጊዜ ደራሲውን ከበዓሉ ግርማ ጋር እያነጻጸርን፣ ሥራውን የሠሩት ላይ..አለ አይደል… የማይሆን ሀሳብ እንተክልባቸዋለን፡፡ ለራሳቸው ያላቸው ስሜት፣ ሰሜን ኮሪያ ከምታስወነጭፋቸው ሚሳይሎች ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር ቀድመው ይስፈነጠራሉ፡፡  
እናማ አንዴ ራስን በሌለ መሰላል እዛ ላይ ከሰቀሉ በኋላ ወደ እውነተኛው ስፍራ ተመልሶ መውረዱ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
እናማ…በዚህ የተነሳ ብዙ ተስፋ የነበራቸው ወጣቶች መንገድ ላይ ቀርተዋል፡፡ ብዙ ደረጃ ላይ ሊደርሱ ይችሉ የነበሩ ልጆች ከአቅማቸው በላይ…
“ጉደኛ ነህ እኮ፣ እኔ እንዲህ አይነት ችሎታ አለህ ብዬ በህልሜም አስቤ አላውቅም… ”
“እስከዛሬ የት ተደብቀህ ነበር!”
“የግጥም መጽሐፍ ገና ዘንድሮ ተጻፈ…”
ምናምን እያልን እውቅና ቀላል ነው፡፡ የክብር ዶክተርነት እንደ ማዕረግ ስም ሆኖ “የክብር ዶክተር እከሌ እከሌ…” በሚባልበት አገር እውቅና ቀላል ቢሆን አይገርምም፡፡ አንድ ግጥም መጽሐፍ ወርወር አድርጎ “ታዋቂው ባለቅኔ’ ቢባል ችግር የለም፡፡
ደግሞላችሁ…በተለይ በትወናው ዓለም …አለ አይደል… ራሳቸው በራሳቸው “እኔ እኮ ታዋቂ ነኝ” ሊሉ የሚዳዳቸው ሰዎች እየበዙ ግራ እያጋባን ነው፡፡ በግድ እወቁኝ ትንሽ ይከብዳል። በየተሰማራበት መስክ እኮ ስንትና ስንት ጎበዝ አለ! ጎበዝ አካውንታት፣ ጎበዝ የህክምና ዶክተር፣ ጎበዝ አስተማሪ…በየቦታው አለ፡፡ ታዲያላችሁ… ልክ ሌላ ሰው ምድሪቷ ላይ ያልተፈጠረ ይመስል ‘ለታዋቂው ገጣሚ ገለል በሉለት’ አይነት ነገር አሪፍ አይደለም፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ከዚህ በፊት ያነሳናትን አንዲት ታሪክ እንድገማትማ፡፡ ‘በሌላ ስርአት’ ወቅት ነው፡፡  ካዛንቺስ በነበረ አንድ ቡና ቤት ውስጥ ታዋቂው ድምጻዊ ባንኰኒ ላይ ‘ተሰቅሎ’ ይጠጣል፡፡ አጠገቡ አንድ ኮስመን ያሉና በእድሜ ገፋ ያሉ ሰው ነበሩ፡፡  ድንገትም…
“እኔን አታውቀኝም?” ይላቸዋል፡፡ እሳቸውም አየት አድርገውት…
“ይቅርታ አላውቅህም፣” ይሉታል፡፡ ድምጻዊው ይበሽቃል፡፡
“እንዴት አታውቀኝም፣ እኔ እኮ እከሌ ነኝ” ይላል፡፡ ይሄኔ ሰውየው አተኩረው አዩትና ምን ቢሉት ጥሩ ነው…
“ኳስ ተጫዋች ነህ?”
የተለመደች አባባል ለመጠቀም ድምጻዊው ‘ነርቭ ሆነ፡፡’ ለካስ ሰውየው ስም ያላቸው የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ነበሩ፡፡
አንድ ሰሞን “የራስሽ ጉዳይ” የምትል ዘፈን ነበረች፡፡ “የራስሽ ጉዳይ”…አለቀ፡፡ ምን ሌላ ነገር ያስፈልጋል…
“ቀላል ባቡር ፊት ተገትሬ የምሆነውን እሆናለሁ፡፡”
“አንድ ጀሪካን በረኪና እጠጣለሁ…” ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡
እና ምናልባትም…ከመሬት ተነስቶ ”እንዴት አታውቃትም!” ለሚለን ሰው “የራስህ ጉዳይ…” ብለን አጄንዳው ሳይከፈት ልንዘጋው እንችላለን፡፡
እናማ… እውቅና መፈለግ በራሱ ምንም ክፋት የለውም፡፡ መደነቅ፣ መመስገን የማይፈልግ ቢኖር ጥቂት ነው፡፡ ግን እውቅናው በራሱ መንገድ ቢመጣ፣ ሥራው ሳይኖር እውቅናውን ከመፈለግ መልካም ሥራው ቀድሞ፣ እውቅናው ቢከተል አሪፍ ነው፡
አሁንም ትልቁ አደጋ ወጣቶቹ ላይ ነው፡፡ በተከታታይ ድራማ፣ በፊልም፣ በማስታወቂያ---- ብቅ ሲሉ…አለ አይደል…
“የኢትዮጵያዋ አንጄሊና ጆሊ…”
“የሀበሻው ብራድ ፒት…”
ምናምን ማለቱ ቁልቁል ይደፍቃቸዋል እንጂ ሽቅብ እንዲያዩ አያደርጋቸውም፡፡ ‘አንጀሊና ጆሊ’ ከተባለች በኋላ እንዴት ብላ ነው ሽቅብ የምታየው!
‘ብራድ ፒት’ ከተባለ በኋላ እንዴት ብሎ ነው ሽቅብ የሚያየው! በቃ ‘ሽቅብ’ የሚባል ነገር እንዳይኖር ጣራው ተዘጋ እኮ!
እናማ… “አላውቃትም እንዳትለኝና እንዳልጮህ…” የምንል ሰዎች፤ በተለይ በታዳጊ የጥበብ ሰዎች ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ልብ እያልን ይሁንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5865 times