Monday, 19 June 2017 09:04

ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች የሚደራደሩባቸውን አጀንዳዎች እያፀደቁ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(24 votes)

   ገዥው ፓርቲ “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ” ላይ አልደራደርም አለ “ኢትዮጵያ” የሚለው ወደ “ኩሽ ምድር” እንዲለወጥ….
              “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን›› ገደብ እንዲበጅለት “የመገንጠል ጥያቄ›› ተቀባይነት አላገኘም
                    ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች ሊደራደሩባቸው በሚሿቸው አጀንዳዎች ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ ውይይት፤ የምርጫ ህግና ስርአትን በማሻሻል ጉዳይ ላይ ለመደራደር የተስማሙ ሲሆን ኢህአዴግ የ“አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ” ላይ አልደራደርም አለ፡፡ ገዢው ፓርቲ፡፡ “የፍትህ ስርአቱ እንደገና ይዋቀር” በሚለው አጀንዳ ላይ ግን ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ቀደም ብሎ ለድርድር የቀረቡት 17 ፓርቲዎች፤ ከ30 በላይ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን ለድርድር ያቀረቡ ሲሆን ኢህአዴግ በበኩሉ፤ ‹‹መደራደር የምፈልገው ለቀጣዩ ምርጫ መደላደል በመፍጠር ጉዳይ ላይ ነው›› በማለት አንድ አጀንዳ ብቻ ይዞ መቅረቡ ተጠቁሟል፡፡
የድርድር አጀንዳ አደራጅ ኮሚቴውም፤ ከፓርቲዎቹ የቀረቡትን ርዕሰ ጉዳዮች ጨምቆና ተመሳሳዮችን አጠጋግቶ፣ 13 አጀንዳዎች ለድርድር እንዲቀርቡ አመቻችቷል፡፡
በኮሚቴው በተመረጡ 13 አጀንዳዎች ላይም ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ባለፈው ረቡዕ መወያየት የጀመሩ ሲሆን “የምርጫ ህግ እና ስርአትን ማሻሻል” የሚል አጀንዳ ለቀጣይ ድርድር እንዲቀርብ ስስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በረቡዕ ውይይት ከአጀንዳዎቹ በ2ኛነት የቀረበውና ፓርቲዎቹ ተነጋግረውበት መቋጫ ሳያበጁለት ለሰኞ ሰኔ 12 በይደር ያቆዩት የተለያዩ አዋጆችን የተመለከተው ርዕሰ ጉዳይ ነበር፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ስር የፀረ ሽብር አዋጁ፣ የሚዲያ አዋጅ፣ የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅና የታክስ አዋጅ … ድርድር እንዲደረግባቸው የተጠየቀ ሲሆን ኢህአዴግ በአዋጆቹ ላይ ለምን መደራደር እንደፈለጉ ፓርቲዎቹ እንዲያስረዱት ማብራሪያ ጠይቋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለድርድር እንዲቀርብ በሚል ለቀረበው ሃሳብ በሰጠው ምላሽም፤ ‹‹በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆነን፣ ስለ አዋጁ መደራደር ስለማንችል ለድርድር መቅረቡን አልቀበልም›› ያለው ገዥው ፓርቲ፤ የንግድ ኢንቨስትመንት ህግን በተመለከተ የቀረበው አጀንዳም፤ ህጉ ገና ያልፀደቀ በመሆኑ፣ ፓርቲዎች ሀሳብ ካላቸው ማዋጣት እንደሚችሉ ጠቁሞ ለድርድር መቅረብ የለበትም ብሏል፡፡
የፀረ ሽብር አዋጁ ለምን ለድርድር ሊቀርብ እንደሚገባ ገዥው ፓርቲ ላቀረበው የማብራሪያ ጥያቄ፤ የኢዴፓ ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ በሰጡት ምላሽ፤ ‹‹አዋጁ ሙሉ ለሙሉ ይሰረዝ የሚል ጥያቄ የለኝም፤ ነገር ግን በአዋጁ የትርጉም ይዘት የተነሳ የሰብአዊ መብት ጥሰት እያጋጠመ በመሆኑ ድርድር ሊደረግበት ይገባል›› ብለዋል፡፡ የመኢአድ ተወካይ አቶ አዳነ ጥላሁን በበኩላቸው፤ “ህዝባችን በህጉ እየተሳበበ የሚንገላታበትና ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በህጉ ምክንያት የሚታሰሩበት ለስደት የሚዳረጉበት ሁኔታ እንዳለና ለሰብአዊ መብት ጥሰት መነሻ የሆኑ አንቀፆችን በማካተቱ ድርድር ሊደረግበት ይገባል” ብለዋል፡፡ ህጉ ዜጎችን ለመጠበቂያ እንጂ ዜጎችን ለማሸማቀቂያ መዋል እንደሌለበትም አስታውቀዋል።
ተቃዋሚዎች ላቀረቡት ማብራሪያ የኢህአዴግ አቋምና ምላሽ የፊታችን ሰኞ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ቀሪዎቹ አጀንዳዎች  ለድርድር “ይቅረቡ አይቅረቡ” በሚለው ላይም በእለቱ ውይይት እንደሚደረግበት ታውቋል፡፡ ለሰኞ በይደር ከተላለፉ አጀንዳዎች መካከል ስለ ህገ መንግስቱ መሻሻል፣ የፌደራሊዝም አወቃቀር፣ የመሬት ስሪት፣ የመገናኛ ብዙኃን ጉዳይ የመሳሰሉትይገኙበታል፡፡
በርካታ ተቃዋሚዎች ‹‹ለድርድር ብለን ያቀረብናቸው አጀንዳዎች ተቆርጠው ቀርተውብናል›› የሚል አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን ቀርተዋል ተብለው ከተጠቀሱት ጉዳዮች መካከልም ‹‹ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ሳይቀር ብሄራዊ መግባባት ማድረግ ያስፈልጋል›› የሚለው ሃሳብ ይገኝበታል፡፡ አሁን ያለው ባለአርማ ሰንደቅ አላማ ጉዳይም ህዝብን እያግባባ ባለመሆኑ ድርድር ሊደረግበት ይገባል የሚል መከራከሪያ ቀርቧል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን እድሜ ሊገደብ ይገባል፣ ኢህአዴግ በስልጣን ለመቀጠል የህዝብ መተማመኛ ድምፅ ማግኘት አለበት፣ የውጭ ግንኙነታችን መመርመር ያስፈልገዋል፣ የሀገሪቱ አለማቀፍ የድንበር ወሰንን እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት የመንግስት ጣልቃ ገብነት - ለድርድር እንዲቀርቡ ከፓርቲዎች ቢጠይቅም ከተመረጡት 13 አጀንዳዎች ውስጥ አለመካተታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የመላ ኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ “የኦሮሞ ህዝብ የመገንጠል ጥያቄ ለህዝብ ውሳኔ መቅረብ አለበት” የሚል ሀሳብ ያቀረበ ሲሆን የገዳ ስርአት አራማጅ ፓርቲ ደግሞ “ኢትዮጵያ” የሚለው የሀገሪቱ ስያሜ “ወደ ኩሽ ምድር መቀየር አለበት” የሚል አቋም አንፀባርቋል፡፡ የባህር ወደብ ጉዳይም ለድርድር እንዲቀርብ ተጠይቋል፡፡ መቅረቡ ታውቋል፡፡ እንደውም የሶማሌ ላንድ በርበራ ወደብን ወደኛ ማምጣት አለብን ተብሏል፡፡
ለተነሱት ጉዳዮች ምላሽ የሰጡት የኢህአዴግ ዋነኛ ተደራዳሪ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፤ ‹‹የኦሮሞ ህዝብን ህዝበ ውሳኔ፣ የኢትዮጵያን ስያሜ፣ የሶማሌ ላንድ በርበራ ወደብን በተመለከተ ፓርቲዎች የመደራደር ስልጣን ስለሌላቸው በአጀንዳው ላይ አንደራደርም›› ብለዋል፡፡ በመድረኩ ላይ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች በታዛቢነት ተገኝተዋል፡፡

Read 7558 times