Monday, 19 June 2017 08:55

በቀሩ ቀናት ዜጎችን ከሳኡዲ አጠናቆ ማስወጣት እንደማይቻል መንግስት አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

    · ሚድሮክ 10 ሚ.ብር ድጋፍና ለ300 ነፃ የትምህርት ዕድል ቃል ገብቷል
                      - በሃይል ተባረው ለሚመጡ ስደተኞች፤ 11 ሆስፒታሎች ተዘጋጅተዋል

      የምህረት አዋጁ ሲጠናቀቅ ከሳኡዲ አረቢያ በኃይል የሚባረሩ ዜጎችን ለመቀበል መንግስት አጣዳፊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልፃ ተቋማት ከወዲሁ የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታ ማቅረብ እንደ ጀመሩ አስታውቋል፡፡
እስካሁን ከ82 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ መመዝገባቸውን ያመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት፤ የዜጎች አመጣጥ ሁኔታ የተጠበቀውን ያህል ባለመሆኑ አዋጁ ሲጠናቀቅ በኃይል ተባረው የሚመጡ ዜጎች እንደሚኖሩ ጠቁሟል፡፡
ለዚህም ሲባል ከወዲሁ ድጋፍና እርዳታ እየተሰባሰበ ሲሆን የሼህ አላሙዲን ኩባንያ ሚድሮክ፤ 10 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል ከመግባቱ በተጨማሪ ለመቶ ህፃናት ከአፀደ ህፃናት እስከ 8ኛ ክፍል ነፃ የትምህርት እድል፣ መቶ ለሚሆኑ ወጣቶች በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ነፃ የትምህርት ዕድል እንዲሁም መቶ ለሚሆኑ በሚድሮክ ኩባንያዎች የስራ ዕድል ለማመቻቸት ቃል ገብቷል ተብሏል፡፡
የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና ኦሎምፒክ ኮሚቴ 5 ሚሊዮን ብር ለመለገስ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሴቶች ነጋዴዎች ማህበር ለህፃናት ተመጣጣኝ ምግብ ለማቅረብ ቃል የገቡ ሲሆን የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ብርድልብስና የተለያዩ እርዳታዎችን ለማቅረብ ቃል ገብተዋል ተብሏል፡፡
በኃይል ወደ ማስወጣቱ ሲገባ የተጎዱና የታመሙ ሰዎች ሊመጡ ይችላሉ በሚል ስጋትም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በአዲስ አበባ 11 ሆስፒታሎችን ለህክምና ዝግጁ አድርጓል ተብሏል፡፡
“የዜጎች እንግልት ከወዲሁ አሳስቦኛል፤ ያለው መንግስት ‹‹ህብረተሰቡ ለወገኖቹ ጥሪ ያቅርብ” ሲል ተማፅኗል፡፡
በሳኡዲ የሚገኙ ህገ ወጥ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በውል ባይታወቁም የተለያዩ መረጃዎች ከግማሽ ሚሊዩን እንደሚልቁ ጠቁመዋል፡፡    

Read 4247 times