Monday, 12 June 2017 06:52

ኳታር እንዴት ሰነበተች?

Written by 
Rate this item
(3 votes)

    ሳኡዲ አረቢያንና ግብጽን ጨምሮ ስድስት የአረብ አገራት፣ አሸባሪ ቡድኖችን በመደገፍ ሽብርተኝነትና ጽንፈኝነት እንዲስፋፋ፣ አካባቢውም እንዳይረጋጋ አድርጋለች በሚል ከኳታር ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጣቸውን በሳምንቱ መጀመሪያ በይፋ አስታውቀዋል፡፡
አገራቱ ኳታር አይሲስና አልቃይዳን ጨምሮ ለተለያዩ አሸባሪና ጽንፈኛ ቡድኖች ድጋፍ ታደርጋለች በሚል ቢወነጅሏትም፣ አገሪቱ ግን ውንጀላውም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማቋረጣቸው መሰረተ ቢስና በተጨባጭ መረጃ ላይ ያልተመሰረቱ ናቸው ስትል ምላሽ መስጠቷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ባህሬንና ሳኡዲ አረቢያ ብሄራዊ ደህንነታቸውን ከሽብርተኝነትና ከጽንፈኝነት ለመከላከል በሚል ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን ባለፈው ሰኞ ማለዳ በይፋ ያስታወቁ ሲሆን፣ በነጋታውም የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ፣ ግብጽ፣ የመንና ሊቢያ ተመሳሳይ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ አገራቱ የየብስና የባህር ድንበርን እንዲሁም የአየር ክልልን ከመዝጋት ባለፈ፣ አምባሳደሮቻቸውንም ከዶሃ አስወጥተዋል፡፡
የአረብ አገራቱ ተማክረው ፊት ለነሷት፣ ተባብረው ላገለሏት ኳታር መጪው ጊዜ እጅግ ፈታኝና ዘርፈ ብዙ ቀውስ የምታስተናግድበት የፈተና ወቅት እንደሚሆን እየተነገረ ነው፡፡ ቀውሱ ከእለት ጉርስ እስከ ፖለቲካዊ ቀውስ ስር ሰድዶ አገሪቱን የከፋ አደጋ ውስጥ ሊከታት እንደሚችል እየተነገረ ሲሆን፣ የአገራቱ ውሳኔ ይፋ በተደረገ በሰዓታት ዕድሜ ውስጥ ነበር ይህንን እውነታ የሚያጠናክሩ አደገኛ ክስተቶች መታየት የጀመሩት፡፡
ከዕለት ጉርስ እስከ ስርዓት ለውጥ?…
2.7 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ኳታር ምንም እንኳን ቢዝቁት የማያልቅ የነዳጅ ባህር የታደለች ባለጸጋ አገር መሆኗ ባይታበልም፣ የምግብ ዋስትና ወሳኝ ክፍተቷ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አገሪቱ 40 በመቶ ያህሉን የምግብ ፍጆታዋን ከሳኡዲ አረቢያ ጋር በሚያዋስናት የየብስ ድንበር በኩል ነበር በየዕለቱ በመቶዎች በሚቆጠሩ ከባድ ተሸከርካሪዎች እያስጫነች በገፍ  የምታስገባው፡፡
የሰሞኑ ድንገተኛ ውሳኔም ታዲያ፣ ይህ ወሳኝ የምግብ አቅርቦት የሚገባበትን የሳኡዲ አረቢያ ድንበር የሚዘጋ በመሆኑ፣ የምግብ እጥረት በመፍጠር አገሪቱንና ህዝቧን የከፋ ችግር ውስጥ ይጥላቸዋል እየተባለ ነው፡፡ የአገራቱን ውሳኔ ተከትሎ መጪው ጊዜ ያሰጋቸው በርካታ የኳታር ዜጎች፣ ለክፉ ቀን የሚሆን የምግብና የውሃ ስንቅ ለመያዝ ከማክሰኞ ማለዳ ጀምሮ ወደ ሱፐር ማርኬቶች በመጉረፍ ላይ እንደሚገኙም ዶሃ ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ ገልጧል፡፡
የምግብ አቅርቦቱ ወደ አገሪቱ የሚገባበት ይህ የየብስ ትራንስፖርት መስመር ከመዘጋቱ ጋር በተያያዘም፣ በኳታር የምግብ ሸቀጦች ዋጋ መናር ይከሰታል፤ የህዝቡ የዕለት ከዕለት ኑሮም ወደ ቀውስ ያመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የአገሪቱ መንግስት ግን የምግብ እጥረት እንደማይከሰት በመግለጽ ተረጋግተው የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን እንዲገፉ ለዜጎቹ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
ከኳታር ጎን የቆመቺው ኢራንም የተባለው የምግብ እጥረት እንዳይከሰት ለማድረግ አስቸኳይ የምግብ እህል ወደ ኳታር መላኳ ተነግሯል፡፡ የቱርክ ባለሃብቶችም ለኳታር የምግብና የውሃ አቅርቦት ለማድረስ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ከትናንት በስቲያ አስታውቀዋል፡፡
አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኞች ግን፣ ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ሊቀሰቀስ የሚችለው የህዝብ ምሬት ከዕለታዊ የፍጆታ ጥያቄነት አልፎ የስርዓት ወይም የመንግስት ለውጥን ወደ መሻት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴና ጫና ከፍ ሊልና አገሪቱን ወደ ብጥብጥ ሊያስገባት እንደሚችል አስተያየታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
አደጋ ላይ የወደቀ ንግድና ኢንቨስትመንት
እነ ሳኡዲ ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ የአቡ ዳቢው ኢትሃድ ኤርዌይስ እና የዱባዩ ኤሜሬትስ አየር መንገድ ከማክሰኞ ማለዳ ጀምሮ ወደ አገሪቱ መዲና የሚያደርጉትን በረራ ሙሉ ለሙሉ ማቆማቸውን አስታውቀዋል፡፡
አገራቱ በዚህም አላበቁም፡፡ የአየር ክልላቸውን ለታዋቂው የአገሪቱ አየር መንገድ ኳታር ኤርዌይስ ዝግ ማድረጋቸው ተነግሯል፡፡ በየቀኑ ወደ እነዚህ አገራት በርካታ በረራዎችን ሲያደርግ የነበረውና በትርፋማነቱ የሚታወቀው ኳታር ኤርዌይስ፣ በአረብ አገራቱ ውሳኔ ሳቢያ በታሪኩ እጅግ የከፋውን ኪሳራ እንዳያስተናግድም ተሰግቷል፡፡ የአገራቱ ውሳኔ በኳታር ይሰሩ የነበሩ ታላላቅ ኩባንያዎች ስራቸውን እንዲያቆሙ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ እየተነገረ ሲሆን፣ ታዋቂው የሳኡዲ የእግር ኳስ ቡድን አል አህሊ ከኳታር ኤርዌይስ ጋር የነበረውን የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ማፍረሱም ተዘግቧል፡፡
በኳታር እየተከናወኑ ከሚገኙ ታላላቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል የ2022 የአለም የእግር ኳስ ዋንጫን ሊያስተናግዱ የተወጠኑት ግዙፍ ስታዲየሞች፣ ወደብና የምድር ውስጥ የባቡር ትራንስፖርት መስመር ግንባታ ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡
ኮንክሪትና ብረትን ጨምሮ ለእነዚህ ታላላቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች በግብዓትነት የሚውሉት ወሳኝ ጥሬ ዕቃዎች ከጎረቤት ሳኡዲ በየብስና በውሃ ትራንስፖርት የሚገቡ መሆናቸውን የጠቆመው ቢቢሲ፤ የየብስ ድንበሩ መዘጋቱ እንደ ምግቡ ሁሉ በግንባታ ግብዓቶች አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ዕጥረትና የዋጋ ንረት እንዲከሰት እንዲሁም ግንባታዎቹ እንዲጓተቱ ምክንያት መሆኑ እንደማይቀር ዘግቧል፡፡
የሰው ሃብት ቀውስ
የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ በግዛቷ ውስጥ የሚገኙ የኳታር ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ እንዲለቅቁ አዝዛለች፡፡
ሳኡዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስና ባህሬንም ከኳታር ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ መወሰናቸውን ከማስታወቃቸው ባለፈ፣ በኳታር የሚኖሩ ዜጎቻቸው በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ ማስቀመጣቸው ተነግሯል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፤ በአገራቱ ውስጥ የሚኖሩ ወይም ለጉብኝት የመጡ የኳታር ዜጎችም በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ እንዲወጡ ቀነ ገደብ ተቀምጦላቸዋል፡፡  በኳታር 180 ሺህ ያህል ግብጻውያን እንደሚኖሩና አብዛኞቹም ምህንድስናና ህክምናን በመሳሰሉ ቁልፍ የሙያ መስኮች ላይ የተሰማሩ እንደሆኑ የዘገበው ቢቢሲ፤ ግብጽም የእነ ሳኡዲን ፈለግ ተከትላ ዜጎችን የማስወጣት እርምጃ ከወሰደች በኳታር የሚፈጠረው የባለሙያ እጥረት ቀውስ እጅግ የከፋ እንደሚሆን መነገሩን ገልጧል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የፊሊፒንስ መንግስት የአገሪቱ ዜጎች ወደ ኳታር እንዳይሄዱ የሚከለክል ጊዚያዊ እግድ ባለፈው ረቡዕ ማውጣቱን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ይሄም ሆኖ ግን የአገሪቱ መንግስት በኳታር በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ከ200 ሺህ በላይ ዜጎቹን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የያዘው እቅድ እንደሌለም ጠቁሟል፡፡
 ኳታርን ማግለሉ ወደ አፍሪካም ተዛምቷል
በእነ ሳኡዲ የተጀመረውን የማግለል እርምጃ የሚደግፉ ብቻ ሳይሆን ከኳታር ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጣቸውን የሚያስታውቁ አዳዲስ አገራት ብቅ እያሉ ነው፡፡ የአረብ ሊግ አባል የሆነቺዋ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሞሪታኒያ ኳታርን፣ እንዳንቺ ካለው የሽብር ደጋፊ ጋር ህብረት የለኝም፤ በቃሽኝ በማለት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ማቋረጧን በይፋ አስታውቃለች፡፡
ሴኔጋልም እነ ሳኡዲ በኳታር ላይ የወሰዱት እርምጃ አግባብ ነው፣ እኔም ከዛሬ ጀምሮ ከኳታር ጋር ያለኝን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጫለሁ በማለት ባለፈው ረቡዕ አቋሟን የገለጸች ሲሆን፣ በኳታር የሚገኘው አምባሳደሯ በአፋጣኝ ወደ አገሩ እንዲመለስ ጥሪ አስተላልፋለች፡፡
ቻድ በበኩሏ ከትናንት በስቲያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ባወጣቺው መግለጫ፤ የኳታርን ቀውስ ለመፍታት አገራቱ የውይይትን አማራጭ እንዲወስዱ ብትመክርም፣ አምባሳደሯን ከኳታር እንዲመለሱ ከማድረግ ወደ ኋላ አላለቺም፡፡
ሌላኛዋ አፍሪካዊት አገር ጋቦንም ከትናንት በስቲያ ባወጣቺው መግለጫ፤ ኳታርን “ለሽብርተኝነት ድጋፍ የምትሰጥ ያለመረጋጋት አጋር” ስትል ለመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ማጣት ምክንያት በማድረግ አውግዛታለች፡፡
የመታረቅ ዕድል
ማግለል መፍትሄ አይደለም የሚል አቋም የያዙት ቱርክንና ኩዌትን የመሳሰሉ አገራት፤ እነ ሳኡዲ ከኳታር ጋር ያላቸውን ችግርና አለመግባባት በውይይት እንዲፈቱና ያቋረጡትን ግንኙነት እንዲቀጥሉ ጥሪ እያቀረቡ ሲሆን የኩዌቱ ኢምር ሼክ ሳባህ አል አህመድአል ሳባህም ከሳኡዲ አረቢያ መንግስት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከርና መፍትሄ ለመሻት ባለፈው ማክሰኞ ወደዚያው ማቅናታቸው ተዘግቧል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በአንጻሩ፣ ኳታርን ማግለል የሽብርተኝነት ሰቆቃ ፍጻሜ ጅማሬ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው በማለት እነ ሳኡዲ የወሰዱትን እርምጃ ማድነቃቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ባለፈው ረቡዕ ዘግቧል፡፡ በነጋታው ግን፣ ትራምፕ ለኳታሩ ኢሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃመድ አል ጣኒ ስልክ በመደወል፣ ከአገራቱ መካከል የተከሰተውን ልዩነት በውይይት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ አሜሪካ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልጸውላቸዋል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የሳኡዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ኳታር በአካባቢው አገራት የደረሰባት መገለል እንዲያበቃ ከፈለገች፣ ከፍልስጤሙ “ሃማስ” እና ከግብጹ “ሙስሊም ብራዘርሁድ” ቡድኖች ጋር ያላትን ግንኙነት ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ማቋረጥ ይገባታል ብሏል፡፡
የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንዋር ሞሃመድ ጋርጋሽ በበኩላቸው፤ አገራቸው ከኳታር ጋር ወደነበራት የቀድሞ መልካም ግንኙነት የመመለስ አማራጭን ማጤን የምትጀምረው የኳታር መንግስት ከሽብርተኛና ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር ያለውን ግንኙነት በተጨባጭ እንደሚያቆም የሚያረጋግጥ አስተማማኝ ፍኖተ ካርታ ሲያቀርብ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

Read 3729 times