Monday, 12 June 2017 06:49

ከስደት ተመላሾች ምን ይላሉ?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  “ላይቭ አዲስ” የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም የተቋቋመ ነው፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የተቋቋመበት ዋና አላማ ለችግር የተጋለጡ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶችን ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወታቸውን መለወጥ እንደሆነ የድርጅቱ ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ተሾመ ይገልፃሉ፡፡ ድርጅቱ እስካሁን ከውጭና ከአገር ውስጥ ለጋሽ ድርጅቶች ከ16.ሚ ብር በላይ በማሰባሰብ 14 ሺህ
ለሚጠጉ ወገኖች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ “ላይቭ አዲስ” በተለይ ከስደት ተመላሽ
ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በርካታ እገዛዎችን እያደረገ ሲሆን ባለፈው እሁድ በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ (ማዘጋጃ ቤት) በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን 104 ከስደት ተመላሽ ወጣቶች አስመርቋል፡፡ ስልጠናው ያተኮረው በምግብ ዝግጅት፣ በልብስ ስፌትና የውበት ሙያዎች ላይ ነው ተብሏል፡፡ በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ምክትል ቢሮ ሀላፊን ጨምሮ በርካታ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ ለጋሽ ድርጅቶችና የተመራቂ ቤተሰቦች ታድመው ነበር፡፡ በሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከተመራቂዎች መካከል ጥቂት የስደት ተመላሾችን በስደት ህይወታቸውና በሥልጠናቸው ዙሪያ ያነጋገረች ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ምክትል የቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ አበባ እሸቴን ደግሞ አስተዳደሩ ለሳኡዲ ተመላሾች ምን እንዳቀደ ጠይቃቸዋለች፡፡

                  “በስደት ህይወቴን የሚቀይር ነገር አላገኘሁም”
                     ዙበይዳ አወል (ከስደት ተመላሽ)

    ጉራጌ ዞን ጉመር የተባለ ቦታ ነው የተወለድኩት። በ1997 ዓ.ም ወደ ዱባይ ሄጄ አራት የመከራ አመታትን አሳልፌያለሁ፡፡ ከአራት ዓመታት በኋላ መጥቼ፣ የሆነ ስራ ለመስራት ሳስብ ምንም አማራጮች አላገኘሁም፡፡
ሰርቼ ያመጣሁትም ብር ይሄን ያህል የሚያኮራ አልነበረም። እንደገና ተመልሼ ሳዑዲ አረቢያ ሄድኩና ሌላ ሶስት የእንግልት አመታትን አሳልፌ ተመለስኩኝ፡፡
በአጠቃላይ ሰባት ዓመታትን በስደት አሳልፌ መጥቼ፣ አሁንም ምንም መስራት አልቻልኩኝም። ሥራ አጥቼ ተቀምጬ በነበረበት ወቅት ነው ላይቭ አዲስን አግኝቼ ወደዚህ ስልጠና የመጣሁት፡፡ ሙሉ የፀጉርና የውበት ስልጠና ወስጃለሁ፡፡
አሁን የምፈልገው የራሴ ቦታ ቢኖረኝ የራሴን የውበት ሳሎን ከፍቼ፣ ጎን ለጎን ሌሎች የውበት መጠበቂያዎችን እየሸጥኩ ራሴን ለመለወጥ ነው፡፡

------------------

                          “በሰው አገር ሲኖር መብት ተነጥቆ፤ ክብር ተዋርዶ ነው”
                          ሜሮን ሙሴ (ከስደት ተመላሽ)

     አዲስ አበባ ውስጥ ልደታ አካባቢ ነው የተወለድኩት:: ራሴንና ቤተሰቤን እለውጣለሁ ብዬ ወደ አረብ አገር የሄድኩት ገና የ17 ዓመት ታዳጊ እያለሁ ነው፡፡ ቤይሩት ለአንድ ዓመት ሰራሁኝ:: ይህ አንድ ዓመት በስንት መከራና ስቃይ እንዳለፈ፣ እኔና ፈጣሪ ነን የምናውቀው፡፡ ከዚያ ሌላ ጊዜ ተመልሼ 3 ዓመታትን በስቃይ አሳልፌ፣ በመጨረሻ ተይዤ ነው ወደ አገሬ የገባሁት፡፡ በሰው አገር ስትኖሪ መብትሽን ተነጥቀሽ፣ ተረግጠሽና ሰብዕናሽ እየተንቋሸሸ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ብትበይም አትወዢም፣ ብትለብሺም አያምርብሽም፡፡ በአጠቃላይ የበታችነት ስሜት ነግሶብሽ፤ አንገት ደፍተሽ ነው የምትኖሪው፡፡ ይህም ሆኖ መብትሽንም ተነጥቀሽ፣ ያለምሽውና ያቀድሽውም ሳይሳካ ሲቀር፣ ስቃዩ እጥፍ ይሆናል፡፡ እኔም የዚህ ስቃይ ገፈት ቀማሽ ከሆኑት አንዷ ነኝ፡፡
አሁን በአገሬ ላይ እየኖርኩ ነው፡፡ በተለይ ይህን የፀጉር ሙያ ስልጠና የሰጠንን ላይቭ አዲስን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡  አገሬ ላይ ያገኘሁትን እየሰራሁ፣ ትዳር ይዤ ሁለት ልጆች ወልጄ በደስታ እየኖርኩ ባለሁበት ወቅት፣ ላቭሊ የውበት ማሰልጠኛ ተቋም፣ ከስደት ተመላሾችን ለማሰልጠን ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ተመዝግቤ የፀጉር፣ የሜካፕ፣ የጥፍርና የአጠቃላይ የውበት ሙያ  ለ8 ወራት እየተከፈለልኝ ሰልጥኜ ለምርቃት በቅቻለሁ። ከመመረቄ በፊት ግን ስራ አግኝቼ እየሰራሁ ነው፡፡ የማገኘውን ደሞዝ በአግባቡ ከተጠቀምኩበት በቂ ነው፡፡ አገሬ ላይ ተከብሬ፣ ቤተሰብ መስርቼ በመኖሬ እድለኛ ነኝ እላለሁ፡፡ ይህን ህይወቴን ሳስብ፤ አንድ ጊዜ ቤይሩት እያለን አሰሪዎቻችን ሲያሰቃዩን፣ ጠፍተን ቤት ተከራይተን ስንኖር፣ ፖሊሶች መጥተው ሊይዙን ሲሉ፣ አንዷ ከሰባተኛ ፎቅ ላይ ራሷን ወርውራ ሞታለች፡፡ ያቺን ቀን ብታልፋት፣ እንደኔ ይህ አይነት እድል ይገጥማት ነበር (እያለቀሰች)፡፡ እኛ ከእሷ አስክሬን ጋር ለሁለት ወራት እስር ቤት ቆይተናል፡፡ ብቻ ብዙ ስቃይ አለ፡፡ እንደኔ እንደኔ አሁንም እህት ወንድሞቻችን እየተሰደዱ ነው፡፡ ስደቱን ትተው አገር ውስጥ ያሉ የስራ አማራጮችን ቢጠቀሙና መለወጥ ቢችሉ ደስ ይለኛል፡፡ ለዛሬው ቀን ያበቃኝን ላይቭ አዲስን በጣም አመሰግናለሁ፡፡

---------------------

                 ‹‹አገር ድሃም ብትሆን አገር ናት››
                  አማርሽ ወርቁ (ከስደት ተመላሽ)

    ተወልጄ ያደግሁት ሰሜን ሸዋ አካባቢ ነው። ወደ ካርቱም የሄድኩት በ2003 ዓ.ም ነበር፡፡ ዘጠኝ ወራትን በስደት አሳልፌያለሁ፡፡ በህገ ወጥ መንገድ ሱዳን ስለገባን፣ ብዙ ጊዜ በረሀ ለበረሀ እየተንከራተትን ስራ እንፈልጋለን እንጂ ወደ ከተማ የመውጣት እድል አልነበረንም፡፡ ውጣ ውረዱ በቃላት የሚገለፅ አይደለም፡፡ እኛ ሀሳባችን ሱዳን ለመቆየት ሳይሆን ሱዳንን እንደ መሸጋገሪያ ተጠቅመን፣ ወደ ሌላ አገር ለመሄድና ሰርተን፣ ራሳችንንና ቤተሰባችንን ለመለወጥ ነበር፡፡ ግን አንዱም እንዳሰብነው አልሆነም፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ አገራችን ተመለስን። የአመላለሳችን ሁኔታ ጠረፍ ላይ ሉግዲ የምትባል ጊዜያዊ የስደተኞች ካምፕ አለች፡፡ የሚወስድሽ ሱዳን መዝግቦ እዛ ቦታ የመውሰድ ግዴታ ስላለበት እዛ አደረሰን። የተመዘገብንበት ወረቀት በሰላም ወደ አገራችን ለመመለስ አግዞናል፡፡ ያ ወረቀት ባይኖረን ኖሮ፣ ለእስር እንዳረግ ነበር፡፡
ከስደት የተመለስኩት በ2004 ዓ.ም ነው። ከዚያ በኋላ ኑሮዬን የካ ክ/ከተማ አድርጌ፣ የቀን ስራ ስሰራ ነው የቆየሁት፡፡ ላይቭ አዲስ፤ የካ ወረዳ 11 ላይ ማስታወቂያ አውጥቶ አይቼ ተመዘገብኩኝ። እኔ መንጃ ፈቃድ ለመማር ነበር የተመዘገብኩት፡፡ ያ ሳይሳካ ሲቀር ሌላ ሀሳብ አቅርቡ ተብለን፣ የንግድ ስልጠና ወሰድን፡፡ እኔ በፊትም የልብስ ስፌት ችሎታ ስለነበረኝ መጠነኛ ስልጠና ጨምሬበት፣ የልብስ ስፌት ማሽን አስገዝቼ፣ አሁን በልብስ ስፌት ሙያ ላይ ተሰማርቻለሁ፡፡ ጥሩ ገቢ አለኝ፡፡ የቀን ወጪዬን ሳይጨምር በትንሹ በወር ከ3-4 ሺህ ብር ገቢ አለኝ፡፡ በዚህ አንድ ልጄንና ባለቤቴን በጥሩ ሁኔታ አስተዳድራለሁ፡፡ ከመሰደድ እንግልት፣ የሞራል ውድቀትና ከዚያም ሲያልፍ ሞት እንጂ የሚገኝ ነገር የለም፡፡ እኔም በዘጠኝ ወር ቆይታዬ ብዙ ለሞት የሚያበቁ ችግሮችን በፈጣሪ ፈቃድ አልፌ ለዚህ በቅቻለሁ፡፡ በቃ አገር ድሀም ይሁን ሀብታም አገር ነው፡፡ ኩራት ነው፡፡ አገራችን ላይ ችግርን እንጋፈጥ እንለወጥ እላለሁ፡፡
በስደት ኩዌት ዱባይና ቤይሩት ኖሬያለሁ። በሰባት ዓመት የስደት ቆይታዬ የሰራሁበትን አብዛኛውን ለራሴ ነው የኖርኩበት፡፡ ይህ ማለት ምንድን ነው? ሰው ቤት እየሰራን ስቃዩ ሲብስብን ወጥተን እንጠፋና ቤት እንከራያለን፡፡ የቤት ኪራዩ፣ ቀለቡ፣ ልብሱ ወጪ ስለሚያስወጣን ተርፎን የምንቋጥረው ነገር አልነበረንም፡፡ ከዚያ ታስረን ወደ አገራችን እንመጣለን፡፡ የእኔም ህይወት ይህ ነበር። መጨረሻ ላይ ተይዤ የመጣሁት በ2007 ዓ.ም ነበር።እንደዛም ሆኖ አርፌ አልተቀመጥኩም። በድጋሚ ወደ ኳታር ሄድኩኝ፡፡ ከዚያ ታስሬ ወደ አገሬ መጣሁ፡፡
አሁን ወደ ዱባይ ልሰደድ ስል ነው፤ላይቭ አዲስ ባወጣው ማስታወቂያ ሃሳቤን የቀየርኩት፡፡ በላቭሊ የውበት ማሰልጠኛ ተቋም ሙሉ የውበት ስልጠና እንዳገኝ አድርጎ ከስደት ታድጎኛል፡፡ አሁን ልጄን በአግባቡ እያሳደግኩ ነው፡፡ እኔ በቅጥር ላይ መቆየት አልፈልግም፡፡ ቢዝነሱን ካወቅሁት በኋላ የራሴን የመክፈት ሀሳብ አለኝ፡፡  

-----------------

                         “በሦስት ወራት የስደትን አስከፊነት አይቻለሁ”
                      ሰይድ ሸምሱ (ከስደት ተመላሽ)

     ተወልጄ ያደኩት መርካቶ ተክለሃይማኖት አካባቢ ነው፡፡ ወደ ሱዳን የሄድኩት ከአካባቢዬ የሚሰደዱ ሰዎችን በማየት ነው፡፡ ከጎረቤት አካባቢ የሄዱ ሰዎች አንዳንዶቹ ተሳክቶላቸው ተለውጠው ስመለከት፤ ባለኝ የወጣትነት ጉልበት ለትንሽ ጊዜ ሰርቼ እለወጣለሁ በሚል ተስፋ ነው ከአገሬ የወጣሁት፡፡ የሄድኩት በጎንደር፣ በመተማ አድርጌ ነው፡፡ ከዚያ ካርቱም የቆየሁት ደላሎች ጋ ነው፡፡ ደላሎቹ በየጊዜው ብር አምጡ ይላሉ፤ እኛ ‹‹ብር ከየት አምጥተን እንስጣችሁ ወይም ስራ አስገቡንና ሰርተን እንሰጣችኋለን›› ስንል የሚጥሉልንን ቁራሽ ዳቦም ይከለክሉንና በረሀብ አለንጋ እንገረፋለን፡፡ ከቤተሰቦቻችሁ ብር አስመጡ ይሉናል፤ቤተሰባችን ብር ቢኖረው እኛ እንዴት እንሰደዳለን? ስቃዩ ሲበዛብን ከደላሎች ጠፍተን ወጥተን ለሱዳን ጠባቂዎች ራሳችንን አሳልፈን ሰጠን፡፡ እነዚያ ጠባቂዎች ከያዙን በኋላ ወደ አገራችን እንድንመለስ ለቀቁን፡፡ በስንት ስቃይ ወደ ቤተሰብ ተመለስኩኝ፡፡
 ገና የ23 ዓመት ወጣት ነኝ፤ 10ኛ ክፍል ተፈትኜ ውጤት ስላልመጣልኝ ነበር የተሰደድኩት፡፡ በሶስት ወራት ውስጥ ብዙ ተምሬ፣ ስደትን ተጠይፌ ተመልሻለሁ፡፡ ላይቭ አዲስ ያወጣውን ማስታወቂያ አይቼ ተመዘገብኩና ሰለጠንኩኝ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ጥሩ ደሞዝ እየተከፈለኝ፣ የውበት ማሰልጠኛ አስተማሪ ሆኛለሁ፡፡ ይሄ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ገና ደሞዜ ያድጋል፤ከዚህም አልፎ የራሴን የውበት ሳሎን የመክፈት የቅርብ ጊዜ እቅድ አለኝ፡፡

------------------------------------------------------------------

                                 “አስተዳደሩ 20 ሺህ የስደት ተመላሾችን ለማቋቋም አቅዷል”
                                   ወ/ሮ አበባ እሸቴ (የአ.አ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ም/የቢሮ ሃላፊ)

      ከሁሉም የአገራችን ክፍሎች ወደ ሳዑዲ አረቢያ የተሰደዱ ከ400 ሺህ በላይ ወገኖች አሉ። እነዚህን ወገኖች ለመቀበል የፌደራል መንግስት፣ በተለይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በራሱ፣ ከተማ አስተዳደሩም ኮሚቴ በማዋቀር እየሰራ ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በኩል ደግሞ ሁለት አይነት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ አንደኛው፤ አጠቃላይ ከስደት የሚመለሱትን ወገኖች ከፌደራል መንግስት ጋር በመሆን የመቀበል ስራ መስራት ነው፡፡ ይህንን አቀባበል ስናደርግ ተመላሾቹ ቢያንስ 3 ቀን፣ ቢበዛ ደግሞ 5 ቀን እዚህ ከተማ ላይ ይቆያሉ፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት ይዘው የሚመጡት የራሳቸው ንብረት ስለሚኖር ይህንን ንብረታቸው በአግባቡ ተረክበው እስኪወስዱ ድረስ እነሱን ለማስተናገድ የሚደረግ ዝግጅት አለ፡፡
ሁለተኛና ለአዲስ አበባ ብቻ የተሰጠና ክልሎችም በየራሳቸው የሚሰሩበት የአዲስ አበባ ነዋሪ የስደት ተመላሾችን መልሶ የማቋቋም ስራ ነው። ከተማ አስተዳደሩ ከ20 ሺህ የማያንሱ የስደት ተመላሾችን መልሶ የማቋቋም ስራ ለመስራት በከፍተኛ ዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያ ስራ የሚሆነው አጠቃላይ ስደተኞቹ መጥተው፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎቹ ከተለዩ በኋላ በየመኖሪያ ቤታቸው ሄዶ የመመዝገብ  ስራ  ነው።
በምን ፕሮጀክት መሠማራት እንደሚፈልጉና ምርጫቸው ምን እንደሆነ ይጠየቃሉ፡፡ ከዚህ በመቀጠል ከ3 ቀን ያላነሰ የሥነልቦና ግንባታ ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡
ይህ ስልጠና አገራቸው ላይ ሰርቶ የመለወጥን አስተሳሰብ በውስጣቸው ያሰርፃል ተብሎ ታምኖበታል፡፡ ከዚህ ስልጠና በኋላ በምዝገባ ወቅት በመረጡት ሙያ ስልጠና ይወስዳሉ፡፡ ስልጠናውን የሚሰጠው በከተማችን የሚገኘው የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ነው፡፡
የስልጠናው ቀን ርዝማኔ እንደመረጡት የሙያ አይነት የሚወሰን ቢሆንም ቢያንስ 20 ቀን፣ ቢበዛ ደግሞ 30 ቀን ይወስዳል ተብሎ ታቅዷል፡፡
በከተማችን ፋብሪካዎች ‹‹ሰው አቅርቡ›› እያሉን ያላቀረብንባቸው በርካታ የሙያ ዘርፎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በጨርቃ ጨርቅ ስራ፣ በቆዳ ስራና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ብዙ የሰው ሃይል እየተጠየቀና እኛም የተሻለ ደሞዝ የሚያገኙበትን መንገድ እየተደራደርን እንገኛለን፡፡ የስደት ተመላሾችም በነዚህ ዘርፎች ስልጠና ወስደው፣ ወደ ስራው እንዲገቡ እንመክራለን፡፡
ነገር ግን ‹‹አይ እኛ እነዚህን ስራዎች አንፈልግም›› ለሚሉ አናስገድድም፡፡ በሌላ መልኩ ከአዲስ ብድርና ቁጠባ፤ ብድር የሚያገኙበትን መንገድ በማመቻቸት፣ ቦታዎችን በማዘጋጀት እየተደራጁ እንዲሰሩና ራሳቸውን እንዲቀይሩ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ። ይህንን ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ከተለያዩ አገራት የሚመለሱ ዜጎች ላይ በመስራት፣ ከተማ አስተዳደሩ ጥሩ ተሞክሮ አዳብሯል፡፡ ለ20 ሺህ ያህል ተመላሾች ይህን ድጋፍ ለማድረግ እቅድ አፅድቀናል፡፡ የሚያስፈልጉ ኮሚቴዎች ተዋቅረው እየተንቀሳቀሱም ይገኛሉ፡፡
ከመንግስት ምን ያህል በጀት ያስፈልገናል የሚለውን ፕሮፖዛል ቀርፀን፣ ለቀጣዩ 2010 የበጀት አመት እንዲፀድቅልን እየሰራን ነው፡፡

Read 2355 times