Monday, 12 June 2017 06:34

“ቅብጥብጧና ሌሎች አጫጭር ድርሰቶች” ሲፈተሹ

Written by  በታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(17 votes)

 (የአዲስ መጽሐፍ አስተያየት)
                    
     ድርሰቶቹ የአንቶን ፓቭሎቪች ቼሆቭ ሲሆኑ ከሩሲያኛ ወደ አማርኛ የተረጎሙት ወ/ሮ ትዕግሥት ፀዳለ ኅሩይ ናቸው፡፡ በፊት ሽፋን የቅብጥብጧን እመቤት የሚያመለክት ሥዕል ይታያል፡፡ ተርጓሚዋ በውስጥ ገጾች የታላቁንና የተወዳጁን  ደራሲ የቼሆቭን ሥነ ሕይወት  የሚጠቁም ማለት የራሱንና የቤተሰቡን፤ ከኒኮላይ ቶልስቶይና ከማክሲም ጎርኪ ጋር የተነሣቸውን ፎቶግራፎች አካትተዋል። እንዲሁም በተወለደበት ታጋንሮጌ ከተማ፤ የተማረበት ጂምናዚየም፤ በስሙ የተሰየመው የተወለደበት ቤት ሙዚየም፤ እንዲሁም በሌሎች የሩሲያ ከተሞች የተቋቋሙለት ሙዚየሞች፤ በሀገር ውስጥና በውጭው ዓለም ለመታሰቢያነት የተገነቡለት ልዩ ልዩ ሐውልቶች፤ በሞስኮ ከተማ የሚገኘው የመካነ መቃብሩ ሐውልት እንዲካተቱ አድርገዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር  ተርጓሚዋ ወ/ሮ ትዕግሥት ስለ ዝነኛው ጸሐፌ ተውኔትና የአጫጭር ታሪኮች ደራሲ  የሕይወት ታሪክ  ማለፊያ የሆነ ትንታኔ ሰጥተውናል። በትርጉማቸው ውስጥም  ለትረካው ግርታ ሊፈጥሩ ይችላሉ ብለው ለገመቷቸው ለአንዳንድ ቃላት በግርጌ ማስታወሻ የአብርሆት ሥራ ሠርተዋል፡፡ ይኽም አንባቢና አናባቢ በቀላሉ እንዲግባቡ ያደርጋል፡፡
እንደዚሁም ወ/ሮ ትግሥት የደራሲውን ምርጥ አባባሎች በሥራቸው መጨረሻ ላይ  አስፍረውልናል። ለምሳሌም ከምርጥ አባባሎቹ ውስጥ፡- “ለማክሰኞ ቦታውን የማይለቅቅ ሰኞ የለም”  የሚለው ይጠቀሳል፡፡ ስለ ሩሲያ ስም አወጣጥ፤ የአክብሮት፤ የማዕርግ፤ ቁሳቁስና ወንዝ ስሞች--- ማብራሪያ አቅርበውልናል፡፡
ተርጓሚዋ አድካሚና አሰልቺ፤ አስቸጋሪም የሆነውን የትርጉም ሥራ ለማጠናቀቅ የቻሉት እንደ ስማቸው ትዕግሥተኛ ሆነው  ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በእኔ ትሑት እይታ በሀገራችን ዘመን አይሽሬና ታላላቅ ሥራዎችን ከሌላ ቋንቋ እንደ   ወ/ሮ ትዕግሥት ተርጉመው ያቀረቡልን ሴቶች ቁጥር እምብዛም ነው፡፡
የቼሆቭን ድርሰቶች ለመተርጎም ያነሣሣቸው ገና ተማሪ ሳሉ  የታላቁን ደራሲ የፓቭሎቪችን ሥራ የአማርኛ ትርጉም መጽሐፍ ከአጎታቸው እየተዋሱ ያነብቡ ስለነበር ነው፡፡ ከጊዜ በኋላም በመቅድማቸው መግቢያ ላይ የምስጋናና የመታሰቢያ  ቃል ወደ ለገሥዋት ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ለከፍተኛ ትምህርት ተልከውና ከዚያው የጥበብ ባሕር ውስጥ ገብተው፣ የቼሆቭን ድንቅ  ድርሰቶች ማንበባቸው ለዛሬው የትርጉም ሥራቸው መሠረት እንደሆናቸው ለመገመት ይቻላል፡፡
በዚህ ዓይነት ተርጓሚዋ በትርጉም ረገድ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ መደመር ብለው በሚያስመዘግቡት ሥራቸው ከሩሲያ ሕዝብ ሥነሕይወት፤ ከአዳዲስ የአተራረክ ቴክኒክና አይረሴነት ከአላቸው አዳዲስ ገጸ ባሕርያት ጋር  ያስተዋውቁናል፡፡
ሩሲያውያን፡- “ለእንግሊዞች ሼክስፒር አለላቸው፡፡ ለእኛ ደግሞ ፈጣሪ ቼሆቭን ሰጥቶናል” በማለት ይመኩበታል፡፡ እናም በወ/ሮ ትዕግሥት ከሩሲያኛ ወደ አማርኛ ተተርጉሞና ታትሞ በሩሲያ የሳይንስና ባህል ማዕከል በተመረቀው መጽሐፍ ውስጥ በእውቁ ደራሲ በአንቶን ፓቭሎቢች ቼሆቭ ከተደረሱ አጫጭር ታሪኮች ጋር እንተዋወቃለን። ድርሰቶቹ 22 ሲሆኑ የአማርኛ ትርጉማቸውን ከሩሲያኛው ጋር እያገናዘብኩ ሳነብባቸው የወይዘሮ ትዕግሥት የአማርኛ ትርጉም  ማለፊያ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
ርእሶቹ፡- ቅብጥብጧ (በሩሲያኛ አጠራሩ ፖፕሪጉኒም ረዘም ያለ ይዘት ያለው)፤ ለማኙ፤  የቤተሰብ አባት (አቴትስ ሴሜይስትቫ፤ አቴትስ በሩሲያኛ አባት ማለት ሲሆን በቃና ፊልም አቴትስ የተሰኘ ተዋናይ - ገጸ ባሕርይ መኖሩም ገርሞኛል፡፡)፤ ፈንጠዝያ፤ ሰቆቃ (ቶስካ)፤ ወፍራምና ቀጭን (ቶልስቲ ኢ ቶንኪ)፤ ማስረጃ (ስፕራቭካ)፤ ያልተለመደ ሁኔታ፤ ስለ ፍቅር፤ የቃል አጋንኖ ምልክት፤ ባልተቤቲቱ፤ አስቸጋሪ ሰዎች፤ ክፉ ልጅ፤ ዘማሪዋ፤ አብየ፤ አሮጌው ቤት፤ በዕረፍት ቦታ፤ መተኛት ፈለግሁ፤ አንጸባራቂ ሰብእና፤ ቫንካ፤ ኢኦኒች፤ ልጅ እግሯ ሴት፤ የሚሉት ናቸው፡፡
ቼሆቭ በነዚህና በሌሎች ድርሰቶቹ  የሚያሳየን የድሆችንና የታናናሽ  ሰዎችን ሥነሕይወት ነው። ድሆቹ የመንግሥት ሠራተኞች፤ አርሶ አደሮች፤ ተማሪዎች፤ ወታደሮች በሥራው ላይ ይንጸባረቃሉ። “ቅብጥብጧ” በሚለው ድርሰቱ የተሳሉት በኑሮዋቸው ሻል ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ “ቅብጥብጧ” ለሚለው ርእስ  ዋና  ባለጉዳይ (ገጸ ባሕርይ) ዝነኛ ሠዓሊ ለመሆን የምትፍጨረጨረው ኦልጋ ኢቫኖቭና ናት፡፡ ምንም የሌለው ተራ ሰው  የሆነውንና የሕክምና ባለሙያውን ዶክተር  ኦሲፕ ስቲፓኖቪች ዲሞቭን በማግባቷ ትቆጫለች፤ ታዝናለች፡፡ ለእርሱ ሙያም ክብር አትሰጥም፡፡ የኪነ ጥበብ ፍቅር ያላት ኦልጋ፤ የሥዕል ሙያ ለመለማመድ ብላና ወደ ቮልጋ ወንዝ  ዳርቻ ሄዳ፣ ከታዋቂው ሠዓሊ ከርያቮቭኪ ጋር በፍቅር ትወድቃለች፡፡ እርሱ ግን ሙሉ ልቡን ባይሰጣትም በእርሱ ግፊት  ወደ ባለቤቷ ከተመለሰች በኋላ ልቧ ይከፈልባታል። በስውር የፈጸመችውን የፍቅር ግንኙነት ተጸጽታ ለባለቤቷ ለመንገር ብታስብም ወኔ ይከዳታል፡፡ ከመኻል ባለቤቷ ዲሞቭ ታምሞ ይሞታል፡፡ ኦልጋ ኢቫኖቭናም በጸጸት ትገረፋለች፡፡
“ለማኙ” በሚለው ትረካ፡- “አንድ ቡትቶ ለባሽ  ተማሪና አስተማሪ ነበርኩ፤ ክፍለ ሀገር ሥራ አግኝቼ መሄጃ ገንዘብ አጣሁ” (እዚህ ሀገራችንም እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ሞልተዋል) እያለ ሲያታልል ያገኘው ስክቮርሶቭ የተባለ ደግ አሳቢ ሰው፤ እቤቱ እየወሰደው እንጨት እንዲፈልጥ፤ እንዲረበርብ፤ በረዶ እንዲጠርግ፤ ምንጣፍ እንዲያራግፍ፤ ፍራሽ እንዲያናፍስ ያደርገዋል፡፡ ግን አቅመ ቢስ መሆኑን የቤት ሠራተኛው ስለተረዳች በብዙ ታግዘዋለች። የጽሕፈት ሥራ የሚችል መሆኑን ጠይቆም በጽሑፍ ገልባጭነት እንዲሠራ ወደሚያውቀው ሰው ይልከዋል፡፡ ከዚህ በኋላም  ኑሮው ሲሻሻልለት እናያለን፡፡ “ፈንጠዝያ” በተሰኘው ሥራ ሚትያ ኩልዳሮቭ የተባለ ወጣት በመላ ሩሲያ ታዋቂና ዝነኛ ለመሆን ያለውን ምኞት ይገልጽልናል፡፡ ችግር ደርሶበት በጋዜጣ የወጣን አንድ ሰው ምሳሌ አድርጎ  እንደርሱ ለመታወቅ  ሚትያ ጋዜጣውን በኪሱ ይዞና በየደረሰበት እንኩ አንብቡት እያለ ስለ ታላቅነቱ  ሲናገር እናያለን፡፡
“የቃለ አጋኖ ምልክት” በሚለው ትረካ ፔሬክላዲን የተባለውና ከአምስተኛ ክፍል የዘለለ ትምህርት የሌለው የቢሮ ሠራተኛና ጸሐፊ፤ ለዐርባ ዐመት ሲሠራ የቃለ አጋኖ ምልክት እንዳላጋጠመው ይናገራል፡፡ እንዲያውም ዘልቀው ከተማሩ ሰዎች በበለጠ እንደሚሠራና መማር አላስፈላጊ እንደሆነ  እየተኩራራ ይናገራል፡፡ ነጠላ ሰረዝ፤ ድርብ ሰረዝ፤ ዐራት ነጥብ እነዚህ ሁሉ በሕልሙ ጭምር እየመጡ ሲጨነቅም እናያለን፡፡ በተመሳሳይ መልኩም “ያልተለመደ ሁኔታ” በሚለው ድርሰት፤ የአዋላጅዋን የማሪያ ፔትሮቭናን  የሙያ ሥነ ምግባርና  የኪርያኮቭን ገንዘብ ወዳድነትና  የቤተ ሰብ ፍቅር አልባነቱን  እናስተውላለን፡፡
ይኽ ምልከታ ለቅምሻ ያህል የቀረበ ሲሆን  ጊዜ ላለመፍጀት ቀሪውን ከመጽሐፉ  እናንብብ፡፡
ከአርትዖት ያመለጡና ወደፊት ሊስተካከሉ የሚችሉ አንዳንድ ጥቃቅን የቃላትና የአባባል ዓይነቶችን አስተውያለሁ፡፡ አቶ ያሬድ ገብረ ሚካኤል የተባሉ ሰው አሉ እንደሚባለው፤ ፍየልና ፊደል ተጠብቀው አይቻልም፡፡ በቤተ ክህነቱ ትምህርት ላላለፈ ሰው ሆሄያት በጣም አስቸጋሪዎች ናቸው። በዚህ ረገድ ወ/ሮ ትዕግሥትን ጠንቃቃ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ለምሌም ሥዕል፤ ፀሐይ፤ መሐላ፤ ዓይን፤ ኃጢአት፤ ዓመታት-----የመሳሰሉትን ቃላት እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ የአጻጻፍ ሥርዓት  በመጻፋቸው አንድም፤ የመጽሐፍ ቅዱስ፤ አንድም የቤተ ክህነት ትምህርት ቢኖራቸው ነው ብዬ ገመትሁ፡፡
ነገር ግን ወደ ፊት የሚታዩ  አንዳንድ ጥቃቅን ግድፈቶችን አስተውያለሁ፡፡ ፀሐፊ ተውኔት (ገጽ 12 ጸሐፌ ተውኔት ቢባል)፤ ሙሽራው (ገጽ 25 ሙሺሪት)፤ አርት፤ አርቲስት (ገጽ 25፤ 30) የሚለው በአማርኛ ቢጻፍ፤ ኒሻን ነው ወይስ ሊሻን (ገጽ28)፤ ሩህሩህ (ገጽ 30 ርኅሩኅ)፤ ተዋቶ (ገጽ 32 ተዋጥቶ)፤ ስማዩ (ገጽ 44 ሰማዩ)፤ ዘማናዊው (ገጽ 47 ዘመናዊው)፤ ቀደምቱ (ቀዳሚው፤ ቀደምት የብዙ ቁጥር ነው ቀዳማውያን እንደማለት ነው፡፡ ብዙ ጋዜጠኞች፤ ደራሲዎች፤ ተርጓሚዎች በዚህ ቃል ያለአግባብ ሲጠቀሙ ይስተዋላሉ)፤ ቀደምት (ገጽ 60 ቀዳሚ)፤ መስዋዕት (ገጽ 63 መሥዋዕት)፤ ማስጠሎ (ገጽ 79 አስጠሊታ)፤ ሰቆቃ (ገጽ 86 ሰቆቃው) እኒህ በምሳሌነት የቀረቡ ናቸው፡፡ ለማንኛውም ወይዘሮ ትዕግሥት በጥረትዎ ቼሆቫዊ ከሆነው  ከሩሲያ ሥነ ሕይወት፤ አዳዲስ አስተሳሰብ፤ ገጸ ባሕርያትና የአተራረክ ብልኃት ጋር ስለአስተዋወቁን  ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ የመጽሐፉ ዘመነ ኅትመት 2009 ዓ.ም ሲሆን መካነ ኅትመት አ.አ. ፋር ኢስት ትሬዲንግ ነው፡፡ የመጽሐፉ ዋጋ ብር 65 መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የገጽ ብዛት 256 ነው፡፡

Read 11728 times