Monday, 12 June 2017 06:30

ዘርዐ ያዕቆብን አስቤ እንዲህ አልኩ (ክፍል ፪)

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

  ዘርዐ ያዕቆብ እውነት የሚመስሉንን ነገሮች ሁሉ መመርመር እንዳለብን ያምናል፥ ስለዚህም ቅዱሳት መጻሕፍትንም አልማራቸውም፥ በእውነት እነሱ ውስጥ እውነት አለ ወይ ይላል? ያልተፈተሸ፣ ያልተመረመረ ህይወት ትርጉም አልባ ነው እንዲል ሽማግሌው ሶቅራጥስ።
ያልፈተሽነው ከጥንት አባቶቻችን የተቀበልነው እውነት የሚመስለን ነገር ይበዛልና፥ ትክክለኛ እውነትን አንዲቷን ሃቅ ማን ይጠቁመኝ ይሆን እያለ ይባዝናል፤ ዘርዐ ያዕቆብ፡፡ ‹‹እውነትን የሚፈርድ ከየት አገኛለሁ? ምክንያቱም እውነቱ ለኔ እንደ ሃይማኖቴ እንደሚመስለኝ ለሌላውም እንደዚሁ እውነቱ እንደ ሃይማኖቱ ይመስለዋል። እውነት ግን አንድ ናት›› ሁላችንም ስለ እውነት ያለን ግንዛቤ ከሃይማኖታዊ ትምህርቶቻችን ባለን መረዳት ላይ የተወሰነ ስለሆነ ስለ አንድ ነገር ብንጠየቅ እንደየ ሃይማኖታችን አስተምህሮ ብቻ መልስ እንሰጣለን ይላል፤ ዘርዐ ያዕቆብ፡፡ በዚህ ሃሳቡም ተጽእኖ ስላለበት ሰዎችን መጠየቅስ ምን ያደርግልኛል ብሎ እራሱን ያሳምንና እንዲህ ይጸልያል፡- ‹‹እንዲህ እያሰብኩ አልኩ፡- አስተዋይ አድርገህ የፈጠርከኝ፥የጥበበኞች ጥበበኛ፥ የእውነተኞች እውነተኛ የሆንክ ፈጣሪዬ ሆይ፥አንተ ግለጽልኝ፤ ምክንያቱም ዳዊት፥ ሰው ሁሉ ውሸተኛ ነው ከሚለው በቀር ከሰው ዘንድ ጥበብም ሆነ እውነት አይገኝም››
እንደውስ በሰማይ የሚሰማኝ አለ ወይ? እያለ ሲመጻደቅ የነበረው ዘርዐ ያዕቆብ፤ በሰማይ ያለውን ፈጣሪ አማካሪ አድርጎ ስለ ሰዎች አዋቂነት መመጻደቅ ጀምሯል፡፡ ሰው ሁሉ ውሸታም ነው ብሎ ጠቅልሎ ይደመድማል እዚህ ጋ፡፡ ቲፎዞ እንዲሆነውም ቅዱስ ዳዊትን ከመዝሙረ ዳዊት ይጠቅሰዋል። እንደው ዝም ብሎ ‹‹አላዋቂ ነኝ እና እውቀትን ግለጥልኝ›› ማለት ሲችል፥ እንደ ጦስ ዶሮ አንገቷን ቆርጦ አውራ ጎዳና ላይ የሚወረውራት ይፈልጋል። እዚህ ላይ ግን አንድና ሁለት ሰው ብቻ የሚበቃው አይመስልም፥ ሁሉ ውሸተኛ ነው ይለናል፡፡ ሁሉንም አላዋቂ ውሸተኛ አድርጎ መስዋዕት ያደርጋቸውና ከፈጣሪው ጋር ይታረቃል፥ ‹‹አስተዋይ አድርገህ የፈጠርከኝ፥ የጥበበኞች ጥበበኛ፥ የእውነተኞች እውነተኛ የሆንክ ፈጣሪዬ ሆይ፥ አንተ ግለጽልኝ›› እያለ፡፡ መቼም! ዋና ሰላውዲ፣ ቀሳጢ ነው፤ ዘርዐ ያዕቆብ። ሲጀምር አንተ አታውቅም ሲለው ነበር ፈጣሪውን፥ እንዴውስ ሰማይ ወና ባዶ ሆኖ ነው እንጅ የሰው ልጅ ጸባይ መቼ እንዲህ እንደ ውሻ የከፋ ይሆን ነበር ሲለን እንዳልቆየ፥ አሁን ተቀይሶ የፈጣሪ ጓደኛ፣ ምክረኛ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ አይ! ፈላስፋ። ከአንድ ሃሳብ ወደ ሌላው ሃሳብ መሽከርከር፣ የፈላስፋ ህይወት የተገነባበት ማገርና ግድግዳ ነው መሰለኝ? የካድሬና የፈላስፋ ልዩነትም  ይኸው ነው።
የስጋችንን ውስንነት አምኖ መቀበል፥ ብዙ የማናውቀው ነገር ስለመኖሩ ምስክር ይሆነናልና። ለፍጽምና እንድንበቃ አደረገን እንጂ ፍጹም አድርጎ ፈጣሪ አልሰራንም፡፡ ህፃን ልጅ ከእናቱ ማህጸን ሲወጣ እንኳን መራመድ፣ እየዳኸ እንኳ መሄድ አይችልም፥ በሂደት ግን መሮጥም መዝለልም ይቻለዋል፡፡ እኛንም ፈጣሪ ሲሰራን ብዙ ነገር እንዲቻለን (ፍጽምናም ቢሆን) አድርጎ እንደሰራን ዘርዐ ያዕቆብ ያምናል። ሰብዕናችን ወደ ፍጽምና እንዳያድግ የሚገታው ስናበክተው ነው፤ በውሸት፣ በስርቆት፣ በሙስና፣ የሰው ደም በማፍሰስ ውስጣችን ሲበክት፤ እንኳን ወደ ፍጽምና ከፍ ልንል ከነበረን የልጅነት ክብር ዝቅ እንልና አሳማ እንሆናለን፤ ቆሻሻ የማይጠየፍ፣ ያገኘውን ሁሉ ለሆዱ የሚያግበሰብስ ከርስ ብቻ እንሆናለን፡፡ የዘርዐ ያዕቆብ ጥበበኛነቱ እያደገ መሄዱን የሚያሳየን ተከታዩ ጥቅስ ይመስለኛል፡፡ በሒደት፣ በምርምር፣ በትግል፣ በእምቢ ባይነት ወደ ልዕለ ሰብነት መለወጥ እንደሚችል ያምናልና፥
ዳዊት፥ ልባቸው እንደ ወተት ረግቷል ይላል። እነሱም ከቀደሟቸው (ሰዎች) በሰሙት ልባቸው ረግቶ እውነት ይሁን ሐሰት አልተመራመሩም። እኔም አገዛዝህን አውቅ ዘንድ ያሳመምከኝ በሚገባኝ ነው። አንተ በእውነት ገሥጸኝ፤ በምሕረትም ንቀፈኝ። የኀጢአተኞችንና የሐሰተኞችን መምህሮች ቅባት ግን ራሴን አልቀባም። አስተዋይ አድርገህ ፈጥረኸኛልና ግለጽልኝ አልኩ።
እንደው በጠቅላላው እስካሁን ያነሳናቸውን ሃሳቦችና የእርሱን ሥራ ካነበብኳቸው ክፍሎች ውስጥ ለጊዜው በሦስት ከፍለን ብንሰበስባቸው እንደሚከተለው ይሆናሉ፡፡
፩) ዘርዐ ያዕቆብ - ስለ ፈጣሪ ኅላዌ
ሀ) ፈላስፋው ዘርዐ ያዕቆብ፤ ከዛሬ አምስት መቶ አመታት በፊት ግድም ስለ ፈጣሪ መኖር ተፈጥሮን በመመርመር የሚገኝ ማስረጃ (Cosmological Argument) የፈጣሪን ኅላዌ ለመመስከር እንዲህ ተፈላስፎ ነበር፡፡
እንዴትስ እኔ ወደዚህ ዓለም መጣሁ? ከየትስ መጣሁ? የሕይወቴን ጥንትና የዕውቀቴን ጥንት  ለማወቅ ከዓለም በፊት አልነበርኩም። ታዲያ ማን ፈጠረኝ? እኔው ራሴ በራሴ ተፈጠርኩን? ደግሞ የተፈጠርኩ ጊዜ አልነበርኩም። አባቴና እናቴ ፈጠሩኝ ብል ደግሞ፥ እንደኛ ካልተወለዱት፥ ወላጅ ሳይኖራቸው ወደዚህ ዓለም በሌላ መንገድ ከመጡት ከጥንታውያን እስኪደረስ ድረስ ለወላጆቼና ለወላጆቻቸውም ፈጣሪ ሊፈለግላቸው ነው። እነሱም የተወለዱ ከሆነ የትውልዳቸው ጥንት ከየት ነው? ከሌለ ነገር የፈጠራቸው፥ እሱ ግን ያልተፈጠረ፥ ያለና ለዘላለም የሚኖር፥ የሁሉ ጌታ፥ ሁሉን የያዘ፥ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው፥ የማይለወጥና ዓመቶቹ የማይቆጠሩ አንድ ነባር አለ ከማለት በቀር ሌላ አላውቅም። ፈጣሪስ በውኑ አለ አልኩ፤ ምክንያቱም ፈጣሪ ከሌለ ፍጥረት ባልተገኘም ነበረ። እኛ ስላለንና ፍጡሮች እንጂ ፈጣሪዎች ስላይደለንም የፈጠረን ፈጣሪ አለ ማለት አለብን።
ለ) ፈላስፋው ዘርዐ ያዕቆብ ኅላዌአዊ (Ontological Argument) ሙግትንም ተጠቅሞ ስለ ፈጣሪ ኅልውና እንዲህ ይሞግታል፡- ‹‹አልኩ፡- ከፍጥረት ሁሉ የሚበልጥ ፈጣሪ እንዳለ ይታየኛል። ምክንያቱም ከተትረፈረፈው ትልቅነቱ ትልቆችን ፈጥሯልና፤ ሁሉን የሚያስተውል አስተዋይም ነው፤ ምክንያቱም ከተትረፈረፈው አስተዋይነቱ አስተዋዮች አድርጎ ፈጥሮናልና። ልንሰግድለትም ይገባናል፤ ምክንያቱም የሁሉ ጌታ ነውና። ሁሉን የያዘ ስለሆነ ወደ እሱ ስንጸልይ ይሰማናል›› ይላል፡፡
፪) የዘርዐ ያዕቆብ ሥነ ምግባር
ከግዙፍ ጠላቶች ጋር ከመጋፈጥ መሸሽ (ወንጌል ቢያሳድዷችሁ ሽሹ ይላል)
ከመንጋው በመነጠል በብቸኝነት እራስን ማንፃት
የራስን የሥነ ምግባር መርሆዎች በኑሮ፣ በህይወት መግለጥ፤ ሌሎች ላይ ጫና ከማሳደር መቆጠብ (የህይወት መመሪያዎቹን እስኪሞት ድረስ በጽሑፍ እንዳይገለጡ ይከላከል ነበር)
በአገልግሎት የራስን ስራ እየሰሩ የላብን ዋጋ መጠቀም (መጽሐፍ እየጻፈ ገቢ ያፈራ ነበር)
በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የመደብ ልዩነት አለመቀበል (ያሳዳሪውን ባሪያ አግብቶ ትዳር መስርቷል)
በምርምርና በጥያቄ ላይ የተመሰረተ የህይወትና የግብረ ገብ ግንዛቤ መያዝ:: ፈጣሪ ለፍጽምና እንድንበቃ አደረገን እንጂ ፍጹማን አድርጎ አልፈጠረንም፡፡
፫) ዘርዐ ያዕቆብ ስለ እውቀት
(እንዲህም) አልኩ፡- ጌታ ሆይ፥ አንተ የልቤን ሐሳብ ሁሉ ከሩቁ ታውቃለህ፤ እነሆ አንተ የቀድሞውንም የወደፊቱንም ሁሉ ዐውቀሃልና። መንገዴን ሁሉ አንተ አስቀድመህ ዐውቀሃል። ስለዚህ (ዳዊት) ከሩቅ ታውቃለህ አለ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እኔ ከመፈጠሬ በፊት ሐሳቤን ዐውቋልና። እኔም፥ የኔ ፈጣሪ ሆይ፥ ልብ እንድል አስችለኝ አልኩ።
የልቦና ዳኝነት፣ የልቦና ፍርድ፣ የልቦና ሚዛን
ከዚህ በፊት የሰማናቸውን እውነቶችና እውቀቶች በሙሉ መመርመር፤ ከልቦናችን እንዲጣጣሙ ማድረግ፡፡ ይኸንንም እንዲህ በማለቱ እንረዳለን፡- ‹‹ለተመራማሪ ግን እውነት ፈጥና ትገለጣለች፤ ምክንያቱም ፈጣሪ በሰው ልብ ውስጥ ባስቀመጠው ንጹሕ ልቦና የሚመረምር (ሰው) የተፈጥሮን ሥርዐትና ሕጎች አይቶ እውነትን ያገኛል››
የእውቀት መጣረሶችና አለመስማማቶችን በመፈተሽ ማስወገድ፤ ሰማያዊ ህግጋት የሚመስሉትን ሁሉ፡፡
አብዛኛው ስለተስማሙበት ሳይሆን በእራሳችን ሁሉንም መርምረን እውቀትን መገብየት
የቀድሞ እውቀቶችን መርምሮ ትክክለኛውን መቀበል ሌላውን ማስወገድ፡፡ (ደጋግሞ “አሰብኩ አሰብኩና እንዲህ አልኩ” እያለ ነው ሐሳቦቹን ያካፈለን)
እኛ ስንስማማ ሁሉም ትክክል ይሆናል (universal knowledge)፡፡ እዚህ ላይ ቀደም ብሎ ያነሳቸውን ሐሳቦች የሚንድ አቋም የያዘ ይመስላል፤ ነገር ግን ሁላችንም በቅን ልቦናችንን ከፍተን ከተመራመርን አንዲቷን እውነት ለሁላችንም ማድረግ ይቻለናል ለማለት ይመስላል፡፡ ፈጣሪ በሰው ሁሉ ውስጥ ንጹህ ልቦና አስቀምጧልም ብሎናልና፡፡
ስለ ሙሴ ህግ ዘርዐ ያዕቆብ የሰጠው ነቀፋ፤ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ስለ ትዳር ተጠይቆ ከመለሰው ብዙም የራቀ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ክርስቶስን፤ ‹‹የሙሴ ህግ ‹የፍቺ ደብዳቤዋን ሰጥቶ ይሸኛት› ይላል ስለ ሚስት ጉዳይ›› ብለው ሲጠይቁት፤ ሙሴ የልባችሁን ክፋት አይቶ ይህንን አለ እንጂ እግዚአብሔር መጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ባልና ሚስትስ ሁለቱ አንድ ናቸው ብሎ መልሶላቸዋልና። እኛንስ የልባችንን ክፋት አይቶ የረገመን የየትኛው ሰፈር ሙሴ ይሆን? ለክፋት ተላልፈን የተሰጠነው እርግማን ቢኖርብን ነው? ቸር ያሰንብተን። 

Read 1477 times