Monday, 12 June 2017 06:28

“የስንኞች እንባ” … ለስደተኞቻችን!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

     ይኼን ያገሬን ሰው …
ከባዕድ ባርነት ከአሸዋ ሰብስቦ ለምድሩ
ሚያበቃው
ድፍረትን ተንፍሶ ለድሉ ዝማሬ፣
ከእንቅልፉ ሚያነቃው፣
የታል የእርሱ ሙሴ፣---
የስደተኞች ወገኖቻችንን ዕጣ የሚወስነው፣ የመጨረሻው ደወል እየቀረበ በመጣ ቁጥር ልባችን መምታቱ፣ ውስጣችን መፍራቱ ግድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በስደት ላይ ባሉ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ሰቆቃ፤ በልባችን ያስቀመጠው ጠባሳ፣ ያስቀረው ሀዘን ቀላል አይደለም፣ … ዛሬም ያምመናል፣ … አንገት ያስደፋናል፡፡
ያገር ልጅ ማለት ወንድም ነው፣ ያገር ልጅ እህት ናት፡፡ ወገን ናቸው፡፡ ስለዚህ ከድንጋይ ካልተፈጠረ በቀር፣ ሥጋ የለበሰ ሰው ሁሉ ይህ ግድ ላይለው አይችልም፡፡ … እንባ የማይመልሰው ፀፀት፣ ከንፈር መንከስ የማያቀናው ስህተት እንዳይሆን፣ መመኘታችን መፀለያችንና የቻልነውን ማድረጋችን አይቀርም፡፡ የወላጅ ልብ ደግሞ ምን ያህል እንደሚናጥ አስቡት! ሀዘኑ የሀገር ሀዘን ነው፡፡ ዛሬም ሀገር ያላቸው ወገኖቻችን፣ በስደት እንጀራ ላይ ሲሳቀቁ ማየት መስማት ያሳምማል፤ ሀዘኑም መሪር ነው፡፡ ገጣሚው ፍስሃ ተክሉ እንዲህ ተቀኝቷል፡-
ምን ሸራ ይበቃዋል?
ምንስ ያህል ቋሚ ምንስ ያህል ማገር?
ህዝብ ሀዘን ሲገባው፣ ሀገር ስትቸገር?
እውነት ነው፤ ሀዘኑ ሰፊ ነው፣ የማንም ሰፈር ሳቅ አይሆንም፣ የማንም ጎጆ አይደላውም፡፡ … ማንም ቤት እልልታ አይሰማም! … የድንኳኑ ጣሪያ ሰማይ፣ ወለሉም መላው ሀገር ነው፡፡
የአምላክ ግዞተኛ፣ ተጓዥ ወገኖቹ
በአቁፋዳ ጥሬ፣ በቅል ውሃ ያጡ፣
ችግር ጭራቅ ሆኖ፣ ካገር ያስወጣቸው፣
የሔዱበት ቀዬ፣ ፊት ያዞረባቸው፣
ከሩቅ የሚሰማው፣ የሲቃቸው ጩኸት፣
በቁጭት አብግኖ፣ ቆሽቱን አሳርሮት፣
ይኸው፣
ሀዘን ተቀምጧል፣ ለብሶ ቡሉኮውን፣
ብሶቱን ሊያፍነው፣ ሊጫነው ሀዘኑን፡፡
ይህ ግጥም አሁን ያለንበትን ጊዜ፣ አሁን የሚሰማንን ስሜት፣ ትኩስ አ‘ርጎ ያንተከትከዋል። … በችግር ሀገር የለቀቁ ወገኖቻችን ፊት ሞት ተደቅኗል። ዱላና ስቃይ፣ ታቅዷል፡፡ … የሰቆቃ ድምፃቸው አድማሳት ያስተጋባል፡፡ ወገን በዚህ ሲቃ በርግጓል፤ ቆሽቱ አርሯል፤ አዝኗል፡፡ ሀዘኑ ግን ገመና ነው፣ ካፉ አላወጣውም፣ ጓዳ ውስጥ እየነደደ ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ  በዚህ ልቡ ያልተረበሸ፣ ሆዱ ያልባባ የለም፡፡ ግና ታፍኗል! … ቡሉኮ፣ ገመና መሸፈኛ ነው፡፡
የኛው ይብስ እንደሆነ እንጂ ጎረቤታችንን ኤርትራን ጨምሮ አፍሪካዊያን የስደት ቀለብ ሆነናል፡፡ ሀገር የሌለው የሰው ቀላዋጭ ተደርገናል። ዓለም ፊቱን አጥፎብናል፡፡ … ትራምፕም ሺህ ጊዜ ምላሳቸውን መዝዘውብናል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ወገኖቻችን በስለት ታርደዋል፣ በእሳት ተማግደዋል፡፡ ይህ ነው ሰቆቃ! … ይህ ነው ሀዘን! … ችግሮቻችን ብዙ ናቸው፡፡ ወደ ሥልጣኔው የገባን መስለናል እንጂ ገና ኋላ ነን፡፡ የተሻሻሉና ውድ የህክምና መሳሪያ አጥተን ወገኖቻችን ሲሞቱ፣ በውድ ዕቃዎች የምንቀናጣበት ከፊል ምዕራፍ አለን፡፡
ብቻ አፍሪካዊያን ዘረኝነትና የቡድን አስተዳደርን ጨምሮ፣ … ያለመሰልጠናችን ለማኞች አድርጎናል። እንጀራ ሳንጠግብ መሳሪያ እንታጠቃለን፡፡ ሰዎችን ለማዳን እያቃተን፣ ሆስፒታላችን ውስጥ ሰው እየረገፈ፣ በጠመንጃ እርስ በርስ እንተላለቃለን፡፡ አፍሪካዊያን እንዲህ ነን …!
ገጣሚ ብሩክታዊት ጎሣዬ “ደመኛ ፍቅር” በሚለው የግጥም መጽሐፍዋ የደረደረችው ስንኝ ሆዴን ያባባዋል፤ አንጀቴን ያሳክከኛል፡-
“አፍሪካዊ”
ረሀብ ካልሆነ … ጦርነት ይሆናል
ጦርነት ከጠፋ … እብድ ፖለቲካ
ገርፎ ያስወጣዋል
ሰበብ የሌለውን … እውቀት ይጠራዋል
ሀገሩ ቢወለድ … በሀገሩ አያድግም
ሀገሩ ላይ ቢያድግ … ሀገሩ አያረጅም
አፍሪካዊ ማለት ሲሰራ ከጥንቱ
ተበይኖበታል እንዳይገናኙ
እንጀራና ቤቱ፡፡
እውነት ነው፤ ብዙ ኢትዮጵያዊ ቤቱን ትቶ ልጆቹን ተሰናብቶ ስደት ሄዷል፤ የሄደው እንጀራ ፍለጋ ነው፡፡ … አንዳንዱ ደግሞ በጦርነት ይሰደዳል፣ አፍሪካ ውስጥ ጦርነትና ረሀብ የስደት መነሾ ነው። በዚያ ላይ ዕብድ ፖለቲካ አለ፡፡ እርስ በርስ ተጠማምዶ መተላለቅ! … እርስ በርስ መጠላላት! …. መጠፋፋት! … ሌላው ደግሞ ትምህርት ፍለጋ ይሄዳል-ትላለች ብሩክታዊት፡፡ ስለዚህም ሀገሩ ቢወለድ፣ አያድግበትም፤ ቢያድግበት፣ እርጅናውን ሀገሩ አያጠናቅቅም፡፡ ይህንን አይተነዋል፡፡ ብዙ ሰዎች በሽምግልናቸው ገንዘብ ፍለጋ ሰው ሀገር በስደት ይኖራሉ፡፡ ይህ ሁሉ ግን የድህነት ውጤት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ያለመሰልጠን የሚያስከፍለን ዋጋ ነው፡፡ እናም እንጀራና ቤታችን ማዶ ለማዶ ሆኖዋል።
ለአንዳንዱ እንደ ኩራትና ስኬት ቢታየውም ከራስ ሀገር ወጥቶ መኖር በረከት አይደለም። …. እርግማን ነው፡፡ ከወገን መለያየት፣ ስኬት አይደለም፤ ሰቀቀን ነው፤ ናፍቆት ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ ስደት ከሚባል ሰቀቀን፣ በባዕድ ሀገር ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ ተጥሎ ከመኖር የሚታደገን ማን ይሆን? … ከእነ ክብራችን፣ ከእነ ነፃነታችን እፎይ ብለን ወደ ብልፅግና ከወገኖቻችን ጋር የምንገሰግስበት ጀንበር የምትወጣው መች ይሆን? …
ገጣሚ ትዕግስት ማሞ “የጎደሉ ገፆች” በሚለው መጽሐፍዋ ይህ ቁጭት ያንገበገባት ይመስላል፡፡ …. ስንኞችዋ፣ እንደ እሳት ደም ውስጥ ይነድዳሉ፤ …
ዛሬ ማን …
ባለ ቀን ተጭኖት ተላልፎ ተሰጠ አቅም ጉልበት አጣ፣
ሀገር እንደሌለው ወገን እንደሌለው
ከሜዳ ተሰጣ፡፡
ማንም ታሪክ አልባ ታሪኩን ሲያጠላሽ፣
ስሙን ከል ሲቀባ፣
ዕዩልኝ ወንዱን ልጅ ዘራፉን በትኖ
እንደ ሴት ሲያገባ፡፡
የትዕግስት ቁጭት ይህ ነው፡፡ ማንም ትናንት የተነሳ ሀገር፣ የስልጣኔ ንጋት የሆነችውን ሀገር፣ በጀግኖች ደምና አጥንት የተመሰረተችውን ኢትዮጵያ እንደ ምናምን ሲቆጥራት፣ ልጆችዋን ሲያጉላላ የተሰማትን ህመም ነው ያሰማችው፡፡ ወንዱ ልጅ፣ የጀግና ልጅ “ዘራፍ!” ማለት አቅቶት፣ በሰው ሀገር ባይተዋር ሆኖ ወደቀ፣ ሜዳ ላይ ተሰጣ! ነው ጩኸቷ! ቀጥላ ግን፡-
ይኼን ያገሬን ሰው …
ከባዕድ ባርነት ከአሸዋ ሰብስቦ ለምድሩ ሚያበቃው
ድፍረትን ተንፍሶ ለድሉ ዝማሬ፣
ከእንቅልፉ ሚያነቃው፣     
የታል የእርሱ ሙሴ፣
የታል የኛ ሙሴ? የዝምታችንን ፅልመት የሚገፈው?
ዛሬ ላይ ተቀምጠን የትናንትን ኑረት የኋሊት ሽተናል
ለስማችን ጥልሻት ቀና ‘ምንልበት
ትንሳዔ ናፍቀናል
የታል የኛ ሙሴ? ሙሴ ያስፈልገናል
አለን ብለን እያልን ዐለም ፊት ወድቀናል፡፡
ትዕግሥት እንዳለችው፤ የዛሬ ናፍቆታችን አሸዋ ላይ የተበተኑ ወገኖቻችንን ከሰይፍ ማዳን፣ ከሞት መታደግ ነው፡፡ ልቅሶዋቸውን በዝማሬ መለወጥ መቻል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚያስፈልገን “ጥሩ መሪ” ነው፤ አለሁ ባይ! … እንደተለመደው ብሔራዊ የሀዘን ቀን ማወጅና ባንዲራ መዘቅዘቅ ዋጋ የለውም። አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት፣ የሚቻለውን ሁሉ አድርጎ ወገኖቻችንን መታደግ ይጠበቅበታል። የገጣሚዎቻችን እንባ … መሪር ነው! … እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ድምፅ በምድረ በዳ የሚጮህ! … አፍሪካ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከመቀመቅ ያውጣሽ! …

Read 1945 times