Monday, 12 June 2017 06:24

ሲቄ - የሴቶች የገዳ ሥርዓት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

 ገዳ የጥቁር ሕዝቦች እሴት ነው
                     
      የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት እንደ ሲስተም፣ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን የሚያቀዳጅ፣ በሁሉም የዕድሜ እርከን ገብቶ የሚያስተምር ቋሚና ጠንካራ ተቋም ስላለው፣ የጊዜና የጠፈር ምንነት የተገለጸበት እውነተኛና ቀዳሚ የፍልስፍና መሠረቶች ላይ የተዋቀሩ እሴቶችን ያካተተ በመሆኑ ዩኔስኮ አምና (2016) ‹‹በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት›› (World‘s Intangible Heritage) መዝግቦታል፡፡
የገዳ ሥርዓት አራማጆች፣ ዩኔስኮ በወሰደው እርምጃ ተደስተዋል፤ ሞራላቸውም ከፍ ብሏል። በዚህ ስሜት ይመስላል፤ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስር የተቋቋመው የኦሮሞ ጥናት ማዕከል (Institute of Oromo Studies-IDS) ባለፈው ሳምንት መጨረሻ “Gadaa The Indigenous Knowledge System of Oromo” በሚል ርዕስ ሁለተኛውን ዓለም አቀፍ የኦሮም ጥናቶች ኮንፈረንስ ያካሄደው። አምና አንደኛውን ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ማካሄዱ ይታወቃል፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ የእንግሊዙን ዱርሃም ዩኒቨርሲቲና የኢጣሊያው ቶሬንቶ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት እንዲሁም ከግል የተውጣጡ ተመራማሪዎች የተገኙ ሲሆን 37 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የኮንፈረንሱ ዓላማ በገዳ ሥርዓት ዙሪያ ከሚሠሩና የሚመለከታቸው በርካታ ዘርፈ- ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ማዕከላት፣ የትምህርት ተቋማት፣  የስልጠና ማዕከላት፤ ኮንፈረንስ አዘጋጆች፣ የመዛግብት አያያዝና የስርጭት ባለሙያዎች አንድ ላይ ተቀናጅተው የሚሠሩበት መድረክ መፍጠር ሲሆን በተለይ  ደግሞ የገዳ ሥርዓት፣ በውስጥ አስተዳደር፣ በፖለቲካ፣ በግጭት አወጋገድ ዘዴ፣ በፆታ እኩልነትና በሌሎችም የእውቀት ዘርፎች ያለውን እምቅ አቅም መተንተን እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በጉባኤው ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፅጌ ከተማ፤ “ያለፈ ታሪክ የሌለው ኅብረተሰብ፣ ሁሉም ትዝታዎች እንደጠፉበት ሰው ይቆጠራል፡፡ ከዚህ ጋር ሲነፃፀር  ቅድመ አያቶቻችን እንዲሁ ሕዋ ላይ አልተውንም፡፡ በርካታ ባህላዊ፣ ማኅበራዊ፣ የፍልስፍና፣ የኢኮኖሚና የሌሎች ጉዳዮችን እውነት በሥነ ቃል  አስተላልፈውልናል። እነሱ እነዚህን የእውቀት ሲስተሞች ለእኛ ለማስተላለፍ ይህን ያህል ለጋስ ከሆኑልን እነዚህን የእውቀት ሀብቶች ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ የእኛ ኃላፊነትና ግዴታ ነው” ብለዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ሌማሳ ኮንፈረንሱን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፤ ገዳ ለምን የዚህ ኮንፈረንስ ዋነኛ ማጠንጠኛ ሆነ ብለው በመጠየቅ ሲመልሱ፤ የጊዜና የሕዋ ፍልስፍናዊ አመለካከት በገዳ ማኅፀን ውስጥ በመሆኑ፣ የፈጣን ዕድገት ለውጦች ዋነኛ የገዳ የልብ ትርታ ስለሆኑ፣ ወንዶችና ሴቶች፣ ወጣቶችና አረጋዊያን፣ ራሴና ሌሎች፣ በዴሞክራሲያዊና አግባብ ባለው መንገድ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው የሚለው አመለካከት፣  በመሠረቱ ሁሉም ሕዝብ እኩል ስለሆነ፣ የማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ መብቶችና ጥቅም እኩል ተጠቃሚ መሆን አለባቸው የሚለው egalitarian ዋነኛና ከፍተኛ የገዳ ስርዓት እሴት ስለሆነ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
ከራስ ይልቅ የሌሎችን ጥቅም ማስቀደም ዋነኛ የገዳ ሲስተም እሴት ነው፡፡ ይህም አፍሪካ በቀል ሲስተም፣ የአፍሪካ የጋራ ስሜትና እምነት ነው ያሉት ፕሮፌሰር ፍቅሬ፤ ለዚህ ነው የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ እውቅና ሲሰጠው የካሬቢያን ምሁራን ድምፃቸውን በጩኸት ያሰሙት፡፡ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ  ርቀት ያላቸውን ሁለት አኅጉሮች ያስተሳሰረው ነገር፣ በሰው ልጅነት፣ በእኩልነት፣ ፍትህና ሌሎች እውቀቶች ላይ የተመሰረተው የጥቁር ህዝቦች ዋነኛ እሴት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግግር ያደረጉት ፕሮፌሰር ተሰማ ታአ፣ የገዳ ሥርዓት በየጊዜው እየተለወጠ አዲስ ጉልበት እያገኘ፣ በአዲስ መንፈስ በየ8 ዓመቱ ደግሞ ላይመለስ የሚሸኝ ሥርዓት እንደሆነ ጠቅሰው፣ በየአራት ዓመቱ የሠራውን ነገር እየተከታተሉ (ሞኒተርና ኢቫሉየሽን እያደረጉ) ለኅብረተሰቡ የሚሳውቁ አሉ፡፡ ጥሩ ካልሠራ በአራት ዓመቱ ያቆማል፡፡ በትክክል ሰርቶ ከሆነ አመስግነው፣ እስከ 8 ዓመት  ድረስ ቀጥል ይሉታል፡፡ ከ8 ዓመት በኋላ የነበረው ገዳ ተለውጦ አዲስ የገዳ አስተዳደር ይመረጣል ብለዋል፡፡
“የገዳ ሥርዓት ሕዝብን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ሕይወት… በትክክል ማስተዳደር ነው ያሉት ፕሮፌሰር ተሰማ፤ ሥርዓቱ ሕግ ነው። ያ ሕግ አሁን ‹‹ሩል ኦፍ ሎው›› የምንለው ነው፡፡ ያ ሕግ በፊትም ነበረ፣ አሁንም በቦረናና በቱሉማ አለ፣ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ አሁን የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ ኢንታንጀብል ሄሪቴጅ በሚል ከተመዘገበ በኋላ የሥርአቱ አራማጆች ሞራል ከፍ ብሏል፡፡  ለሕዝቡም ይጠቅማል፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም ነው፡፡ ገዳ ሰላምን የሚሰብክና የሚተገብር ሥርዓት ነው፡፡ ሳፉ (ይሉኝታ) የሚባል ነገር አለ፡፡ ሰውን እንደፈለገው መግደል፣  መጨቆን፣ ማሰር፣… የገዳ ሥርዓት አይደለም” በማለት አብራርተዋል፡፡
“ዘ ሮል ኤንድ ስታተስ ኦፍ ኦሮሞ ውማን ኢን ገዳ ሲስተም” በሚል ርዕስ ጥናታዊ  ጽሑፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር አባል ዶ/ር ታደሰ በሪሶ፤ የገዳ ሥርዓት ሴቶችን አያሳትፍም፣ ያገልላል ይባላል፡፡ ይህ ነገር እውነት ነው ወይ ተብለው ተጠይቀው ሲመልሱ፤ እውነት አይደለም ብለዋል፡፡ ገዳ ሴቶችን አያሳትፍም፣ ያገልላል የሚለው ሐሳብ እንዴት እንደመጣ ዶክተሩ ሲያብራሩ፤ “ቀደም ሲል በገዳ ሥርዓት ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉ እነ ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሠና ሌሎችም በጣም የታወቁ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ምሁራን፤ ገዳ ሴቶችን አያሳትፍም፣ ያገልላል የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው፡፡ ዋናው የገዳ ሥርዓት ችግር ሴቶችን ያለማሳተፉ ነው በማለት ያምኑ ነበር።
“አሁን ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ የገዳ ሥርዓት ጥናቶች ያሳዩን ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ፣ በአርሲና በጉጂ ኦሮሞዎች አካባቢ፣ ሴቶች፣ የራሳቸው የሆነ ከገዳ ጋር ጎን ለጎን እኩል የቆሙ ሲቄና አቴቴ የሚባሉ ወንዶችን የማያካትቱና የሚያገልሉ ተቋማት ወይም ድርጅቶች፤ ገዳ ራሱ የሴቶችን መብት ለማስከበር ያቋቋማቸው ናቸው፡፡ እነ ፕሮፌሰር አስመሮምና ሌሎች ምሁራን እነዚህ ተቋማት መኖራቸውን አላወቁም ነበር፡፡ ምክንያቱም፣ ፕሮፌሰሩ ጥናታቸውን የሰሩት ቦረና አካባቢ ነው፡፡ የሲቄና አቴቴ ኢንስቲትዩቶች በቦረና አካባቢ የሉም ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህ ተቋማት በሌሎች አካባቢዎች መኖር ያለመኖራቸውን ሳያገናዝቡ ነው ገዳ ሴቶችን አያሳትፍም በማለት የጻፉት፡፡
“ሲቄ ኢንስቲትዩሽን  የሴቶችን መብት የሚያስከብር፣ የሴቶችን ንብረት የማፍራትና የመያዝ መብት የሚጠብቅ፣ ሴቶች በሃይማኖትና በፖለቲካ ከወንዶች ጋር ያላቸውን ልዩነቶች በሚገባ የሚተነትን ነው፡፡ ሴቶች በፖለቲካ፣ ሴቶች በሃይማኖት እንዴት መሳተፍ እንደሚችሉ፣ ሴቶች ንብረት ማፍራትና መያዝ እንደሚችሉ በሚገባ የሚተነትን ተቋም ነው፡፡ ሲቄ የሚባለው በትር ነው፡፡ አንዲት ልጃገረድ ስታገባ እናቷ የምትሰጣትና የምትይዘው፣ አባ ገዳ የሆነ ሰው ከሚይዘው በትር ጋር እኩል ዋጋ ያላት በትር ናት፡፡ ለምሳሌ አንዲት ሴት ባገባችበት አካባቢ ወይም በቤተሰቦቿ መካከል መብቷ ቢነካ ወይም ብትደበደብ፣ ለአካባቢው ሴቶች የተፈፀመባትን የመብት ጥሰት ትናገራለች፡፡ ሴቶቹም ሲቄ በትራቸውን ይዘው እልል እልል እያሉ ይወጣሉ፡፡
‹‹በዚህ ጊዜ እልልታውን የሰማች ሴት እቤቷ አትቀርም፡፡ ታማ ቢሆን ወይም አስታማሚ ብትሆን ወይም እቤት ውስጥ ሥራ ይዛም ቢሆን፣ … እቤት ውስጥ አትቀርም፡፡ ሲቄያቸውን ይዘው የተበደለችዋን ሴት ተከትለው አንድ ቦታ ይቀመጣሉ።
የተፈጠረው ችግር በሽማግሌ ተጣርቶ ትክክለኛ መፍትሄ ካልተሰጠው በስተቀር ወደየ ቤታቸው አይመለሱም፡፡ ሥራ ሁሉ ቀጥ የሚልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ወንዶች፣ የተፈጠረው ችግር እንደማይደገም ተንበርክከው ይለምናሉ። ስለዚህ ወንዶች ተመሳሳይ ስህተት ላለመፈፀም ይጠነቀቃሉ። ይኼ መብታቸውን የሚያስከብሩበት መንገድ ነው፡፡
“ሌላው ደግሞ ሴቶች ንብረት የማፍራትና የንብረት ባለቤት የመሆን መብት አላቸው፡፡ አንዲት ልጃገረድ ስታገባ ሕጓን የጠበቀች ጨዋ መሆኗን ለማሳየት ከብት ይሰጣታል፡፡ የተሰጣትን ከብት በሲቄ በትሯ መታ ታደርጋለች፡፡ በተሰጣት ላም፣ ጊደር ወይም ወይፈን ላይ መብት አላት፣ የእሷ ነው ማለት ነው፡፡
“በፖለቲካም ቢሆን ሲቄ የሚመራበት ሕግ (ካስተመሪ ሎው) አላቸው፡፡ የሕጉ መኖር ብቻ ሳይሆን የሚያስፈጽሙበት ዘዴዎች አሏቸው። ዘዴው እርግማን ሊሆን ይችላል፡፡ ሴቶች ሲቄያቸውን ይዘው ወጥተው እርግማን ካደረጉ፣ አንድ ሰው ከተረገመ በራሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በዘር ዘሮች ላይ ይደርሳል ተብሎ ስለሚፈራ ሴቶች እርግማን እንዳያደርጉ በጣም ይፈራል፡፡
“አቴቴ ደግሞ ልጅ የማግኘት አምላክ ነው፡፡ ልጅ የሌላቸው ሴቶች ተሰብስበው እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው የሚለማመኑበት ሥርዓት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ዝናብ፣ ድርቅ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ የመሳሰሉት የተፈጥሮ አደጋዎች እንዳይመጡ፣ ካሉም እንዲቆሙ ሴቶች ወጥተው ፀሎት በማድረግ ፈጣሪያቸውን የሚለማመኑበት ሥርዓት ነው፡፡ ገዳ ሴቶችን ያገልላል ብለው የጻፉ ሰዎች እነዚህን ተቋማት ሳያዩ ነው፡፡ ገዳ ሴቶችን ያገልላል የሚባለውን ያህል ሲቄና አቴቴ ወንዶችን ያገልላሉ፡፡ ነገር ግን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ሁለቱም ሥርዓቶች ጎን ለጎን ተደጋግፈው የሚሰሩ መሆናቸው ነው” በማለት አስረድተዋል፤ ዶ/ር ታደሰ በሪሶ፡፡

Read 5745 times