Monday, 12 June 2017 06:22

ከትንሹ ማርሌይ ‹‹ጁንየር ጎንግ›› ጋር…

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   እንደ መግቢያ
የ38 ዓመቱ፤ የሬጌና ዳንስ ሆል እውቅ አርቲስት ዴሚያን ማርሌይ 21ኛ ኮንሰርቱን ባለፈው ማክሰኞ ግንቦት 29 በአዲስ አበባ  ጊዮን ሆቴል አቅርቧል፡፡ መላው አዲሱ የፈረንጆች ዓመት ከገባ የቦብ ማርሌይ ቤተሰቦች  ወደ ኢትዮጵያ እየቀረበ በመጣባቸው ሁኔታዎች  መደነቅ ይኖርበታል፡፡ በጊዮን ሆቴል ባቀረበው ኮንሰርት መድረክ ላይ ባስተላለፋቸው መልዕክቶች ይህን መገንዘብ ይቻላል፡፡
በነገራችን ላይ ዴሚያን ማርሌይ  በጊዮን ሆቴል ካቀረበው ኮንሰርት በፊት በብሄራዊ ቲያትር ልዩና ታሪካዊ የሙዚቃ ቪድዮ ቀረፃ ነበረው፡፡ ‹‹ስቶን ሂል›› ከተባለው አዲስ አልበሙ አንዱን ዘፈን የሚያጅብ ትእይንት የቀረፀበት አጋጣሚ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን አርበኞች፤ ብሄራዊ ቲያትርን፤ የብሄር ብሄረሰቦች ባህልና አለባበስ ንና የሙዚቃ ባለሙያዎችን በዓለም አቀፍ የማስተዋወቅ ዕድል ይኖረዋል፡፡
 ዴሚያን  ከ12 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ የተመለሰው ለሰባት ሳምንታት በአፍሪካና በአውሮፓ አገራት በተከታታይ በሚያቀርባቸው የኮንሰርቶች እቅዶቹ መሰረት ነበር፡፡ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ “Stone Hill” በሚል ርእስ በጌቶ ዩዝ ኢንተርናሽናል አሳታሚነት ለገበያ የሚበቃውን አምስተኛ የስቱዲዮ አልበም በእነዚህ ኮንሰርቶቹ በዘመቻ ያስተዋውቃል።
በብሄራዊ ቲያትር ማክሰኞ ምሽት ከሰራው የሙዚቃ ቪድዮ ቀረፃ በኋላ በቲያትር ቤቱ የጓሮ በር ደጃፉ ላይ አዲስ አበባ የመጣበትን ሁኔታ አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ፤
‹‹ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው የሙዚቃ ዝግጅት ለማቅረብ ነው፤ ጎን ለጎን ደግሞ በአዲሱ አልበሜ ‹‹ስቶን ሂል›› ለሚገኝ ዘፈን የቪድዮ ቀረፃ ማከናወን ችለናል፡፡›› ብሏል፡፡
ብዙውን ጊዜ የሬጌ ሙዚቀኞችና ራስተፈርያኖች ኢትዮጵያን የአባቶቻችን አገር እያሉ ያወድሷታል። ወደ ተስፋዋ ምድር መመለስ የሚለው አጀንዳ እውን ይሆናል ወይ… በአጠቃላይ ኢትዮጵያን እንዴት አገኘሃት - ሁለተኛው ጥያቄ ነበር፡፡
‹‹እንግዲህ የቦብ ማርሌይ ቤተሰቦችን በመወከል እኛ መጥተናል፡፡ ይህም ወደ ተስፋዋ ምድር የመመለስ ራዕያችን ተግባራዊ መሆን መጀመሩን የሚያመለክት አንድ አጋጣሚ ነው፡፡ የተለያዩ ጉብኝቶች ነበሩን። ቤታችንን የምንገነባበት መሬት ስናፈላልግም ነበር። በአጠቃላይ ጥሩ ጅምሮች አድርገናል፡፡›› ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ታላቅ ክብር ነው፡፡ ቅልል ያለች ውብ አገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ ለመስተንግዷችሁ በጣም እናመሰግናለን፡፡ ፍቅር ብዙ ይሁንላችሁ። ለመላው ኢትዮጵያ የምናስተላልፈው መልዕክት አንድ ፍቅር - ‹‹ዋን ላቭ›› ነው፡፡ ሁልጊዜ፡፡››
አፍሪካ ዩናይት በሚል መሪ ርእስ በ2005 በአዲስ አበባና በ2006 ላይ በጋና የተካሄዱ ሁለት ኮንሰርቶች ነበሩ፡፡ መላው የቦብ ማርሌይ ወንድማማቾችና ቤተሰቦቻቸው ተሳትፈውባቸዋል። በተለይ ዴሚያን በ2005 እኤአ ላይ በአዲስ አበባ የቦብ ማርሌይ 60ኛ ዓመት በተከበረበትና በመስቀል አደባባይ ከ250 ሺ በላይ በታደሙት ኮንሰርት ላይ ከወንድሞቹ ጋር ‹‹ኩድ ዩ ቢለቭድ›› እና ሌሎች ሙዚቃዎችን   በከፍተኛ የመድረክ ብቃት ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡
ለመሆኑ ይህን የመሰለ ደማቅ ኮንሰርት ሌሎቹን የቦብ ማርሌይ ወንድማማቾችና መላው ቤተሰቡን በማሳተፍ አይደገምም ወይ ብዬ ጠየቅኩት…
ዴሚያን ሲመልስ፡-
‹‹የአፍሪካ ዩናይት ኮንሰርትን … አዎ አስታውሳለሁ፡፡ ሊደገም ይችላል ወይ… አላውቅም። ግን በድጋሚ ቢዘጋጅ ደስ ይለኛል፡፡ እኛ ወደ አዲስ አበባ አሁን መጥተናል፡፡ ኮንሰርቱም መላው ቤተሰቦቻችንን በመወከል የምናቀርበው ነው፡፡››
ዴሚያን ወደ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት  በአራት የአፍሪካ አገራት አምስት ከተሞች ኮንሰርቶቹን ካቀረበ በኋላ ነበር፡፡ የመጀመርያ ዝግጅቶቹ በደቡብ አፍሪካ  ሁለት ከተሞች የቀረቡ ነበሩ፡፡  በጆሃንስበርግ ከተማ ኮንሰርቱን ያቀረበው ‹‹ዘ ግሩቭ ላይቭ ኦን ኒው ታውን›› በሚባል ዝግጅት ሲሆን፤ በደርባን ከተማ ደግሞ በ“ዛካፎ ሚዩዚክ ፌስቲቫል” ደማቅ ኮንሰርቱን ሊያቀርብ ችሏል፡፡
ስለ ደቡብ አፍሪካ ሁለት ከተሞች ቆይታውና ስለ አፍሪካ  ሲናገር፡-
‹‹አፍሪካ የሩቅ ዘመዶቻችን ምድር ናት፤ ታላቅ ታሪክ ያለትና መጭው ጊዜ ብሩህ የሆነላት አህጉር›› ብሏል፡፡
ከደቡብ አፍሪካ ሁለት ከተሞች በኋላ  ግንቦት 23 በናይሮቢ ኬንያ ኮንሰርት ነበረው፡፡ የኬንያ ጋዜጦች ዴሚያን ማርሌይ በካርኒቮሬ ግራንድ ‹‹ስትሪት ፊውዠን ኮንሰርት ሊረሳ የማይችል ምርጥ ኮንሰርት ማቅረቡን በስፋት አድንቀው፣ ናይሮቢ የበርካታ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ማካሄጃ ከተማ እየሆነች መምጣቷን፤ ምናልባት በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋና የሙዚቃ መናሐርያ መሆኗን አስተጋብተዋል፡፡ በተጨማሪም በናይሮቢ ከተማ በርካታ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው የሙዚቃ ፕሮሞተሮችና የኮንሰርት ኤጀንቶች ቢሮ እየከፈቱ መሆናቸውን የገለፀ አንድ የኬንያ ሚዲያ ዘገባ፤ ከተማዋን “ዘ ኒውዮርክ ኦፍ አፍሪካ” በሚል ካሞካሻት በኋላ ትልልቅ የሙዚቃ ኮንሰርቶች በከተማው መደጋገማቸው ለአገሪቱ ምርጥ ሙዚቀኞች በጋራ የመስራት እድል መፍጠሩን አድንቆታል፡፡ ዴሚያን በናይሮቢ ቆይታው፤ አንድ ባለቤት የሌላቸው እንስሳዎችና የዱር አራዊቶች የሚሰበሰቡበት ልዩ ማዕከል የጎበኘ ሲሆን አንድ በከተማ ተወልዶ ያደገ አንበሳን በጉዲፈቻ በመረከብ የዜና አውታሮችን ትኩረት ሊያገኝ ችሏል፡፡ ከናይሮቢ በኋላ ሁለት ኮንሰርቶቹን ግንቦት 26 በሴንትፒዬር ዩኒዬን አይስላንድ እንዲሁም ግንቦት 27 በፖርት ሊዊስ ሞሪሽዬስ ያቀረበ ሲሆን አዲስ አበባ የአፍሪካ ኮንሰርቱ የመጨረሻ መድረክ ሆናለች፡፡ ከአዲስ አበባ በኋላ በቀጥታ ወደ አውሮፓ በማቅናት በእንግሊዝ፤ በሆላንድ፤ በስዊዘርላንድ፤ በፈረንሳይና በጀርመን ሌሎች ኮንሰርቶችን እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡
በኮንሰርቱ ዋዜማ… የአዘጋጆቹ ነገር
በዴሚያን ማርሌይ የጊዮን ሆቴል ኮንሰርት ዙርያ የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘትና ለመዘገብ በነበረኝ እቅድ ከአዘጋጆቹ ጋር ለመገናኘት ያልፈነቀልኩት  ድንጋይ አልነበረም፡፡ በጊዮን ሆቴል የተደረገውን ኮንሰርት  ተጣምረው ያዘጋጁት አውሮራ ፕሮዳክሽን፤ ሲግማ ኢንተርቴይመንትና ዛክ ፕሮዳክሽን ነበሩ፡፡ ስለ ኮንሰርቱ እነ ዘለቀ ገሰሰ በተገኙበት የተሰጠው የመጀመርያው መግለጫ ካመለጠኝ  በኋላ በመጨረሻው ሰሞን በተለይ ዋናውን የኮንሰርት አዘጋጅ ለማግኘት የወሰደብኝ ጊዜ የሚገርም ነበር፡፡ በየቀኑ ብዙ ስልኮች ብሞክርም ምላሽ ላገኝ አልቻልኩም፡፡ በመጨረሻም ኮንሰርቱ ሊካሄድ ሁለት ቀናት ሲቀሩት እሁድ እለት የኮንሰርቱ  ዋና አዘጋጅ ስልኩን አነሳልኝ፡፡ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ፤ ግን ያነሳኋቸው ሁለት ጉዳዮችን ነበር፡፡ ዴሚዬን ማርሌይን መምጣቱን አስመልክቶ ምን ምን አዳዲስ መረጃዎች አሉህ፤ ቃለ ምልልስ ማድረግስ ይቻላል ወይ…. በማለት፡፡ ያገኘሁት ምላሽ ያልጠበቅኩት ነበር፡፡ ‹‹ዛሬ እሁድ ነው፡፡ ከቤተሰቤ ጋር እረፍት የማደርግበት ነው›› በሚል በደፈናው ውይይቱን ዘጋብኝ፡፡ በማግስቱ ሰኞ ጠዋት ላይ በድጋሚ ደወልኩለት፡፡  እንደ ሚዲያ ባለሙያ የነበረኝን ፍላጎት ላስረዳው ሞከርኩና ቢያንስ ዴሚያን ማርሌይን ቃለምልልስ ለማድረግ ይቻል እንደሆነ ጠየቅኩት… ለዚህም ምላሹ የሚያበረታታ አልነበረም፡፡ ‹‹ዴሚያን ቃለምልልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ለጥቂት ሰከንዶች ለኢቢኤስ ብቻ ነው ቃለምልልስ የሚሰጠው፡፡››  ነበር ያለኝ። ቃለ ምልልሱን ጭራሽ እንዳታስብ፤ ተወው ነገር ነው፡፡ እንግዲያውስ ለኮንሰርት መግቢያ የሚሆን የሚዲያ ፓስ ተዘጋጅቷል በትህትና፡፡ ‹‹የሚዲያ ፓስን በተመለከተ የሚሰሩት ሌሎች ናቸው፡፡ እነሱን ጠይቀህ ልታገኝ ትችላለህ፡፡ እኔ ጋ ምንም የለም፡፡ ስራ ተከፋፍለን ነው የምንሰራው›› ሲል በመሰላቸት መንፈስ ነበር ያዋራኝ፡፡ የኮንሰርት አዘጋጅ ከሚዲያ ጋ የሚኖረው ግንኙነት በተቻለ መጠን የተሳለጠ መሆን አለበት፡፡
የሙዚቃ ቪድዮ ቀረፃው በብሄራዊ ቲያትር
ሰኞ አመሻሹ ላይ ነው፤ አንድ ወዳጄ ስልክ የደወለልኝ፡፡ ዴሚያን ማርሌይ በብሄራዊ ቲያትር ከአርበኞች፤ ባህላዊ የብሄር ብሄረሰብ አለባበሶችን የሚያስተዋውቁ ወጣት አርቲስቶችና የሙዚቃ ባለሙያዎች በማሳተፍ ልዩና ታሪካዊ የሙዚቃ የቪድዮ ቀረፃ ስለሚያከናውን ተከታትለህ ስለ ጉዳዩ መዘገብ ትችላለህ ብሎ ጥቆማ ሰጠኝ። በቪድዮ ቀረፃውም ልትሳተፍ ትችላለህ አለኝ።  በግዮን ሆቴል የሚቀርበው የዴሚዬን ኮንሰርት ይበልጥ ያጓጓኝ በሙዚቃ ቪድዮ ቀረፃው የምገኝበት አጋጣሚ ከተፈጠረ በኋላ ነበር፡፡
ዴሚዬን ማርሌይ በብሄራዊ ቲያትር የቪድዮ ቀረፃውን ሲያከናውን  ተሳትፎ ለማድረግና ዘገባ ለመስራት ማክሰኞ 11 ሰዓት ላይ ብሄራዊ ቲያትር ቅጥር ግቢ ደረስኩ፡፡ በመጀመርያ በዋና መግቢያ በኩል ለመግባት ያደረግኩት ሙከራ የተሳካ አልነበረም፡፡ በር ላይ የነበሩት ሰዎች በፍፁም ሊተባበሩኝ አልቻሉም፡፡ ከፈለግክ ዞረህ በኋላ በር ጠይቃቸውና ግባ ነበር ያሉኝ፡፡ በኋላ በር ስሄድ ብዙ መጉላላት ገጠመኝ፡፡ በስንት ማስረዳት ገባሁ፡፡
ዴሚያን ማርሌይ ከራሱ ልዑካን ቡድኖች ከኮንሰርት ቀረፃው አስተባባሪዎችና ከሌሎች አጃቢዎች ጋር መጣ ፡፡ በብሄራዊ ቲያትር ደጅ ሆኖ ቀረፃው ተጀምሮ ነበር፡፡ ትያትር ቤቱ ደጃፍ ካለው የአንበሳ ሃውልት ስርም ቀረፃዎች ተደርገው  ነበር ወደ ቲያትር ቤቱ የገባው፡፡
በቪድዮ ቀረፃው የተሳተፉት ስድስት አዛውንት አርበኞች፤ ሌሎች የትያትር ቤቱ ተዋናዮች እንዲሁም ታዋቂ አርቲስቶችና ድምፃውያን ነበሩ፡፡ ከድምፃውያኑ መካከል ሃይሌ ሩት፤ ራስ ጃኒ፤ ኬኒ አለን፤ ራስ ማይኪ፤ ኬኒ አለን፤ ሲድኒ ሰሎሞንና የባንድ አባላቱ… ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡
የሙዚቃ ቪድዮ ቀረፃው የተከናወነው በብሄራዊ ቲያትር ጣራ ላይ በሚገኝ ባንኮኒ ላይ ነበር። ቄጠማ ተጎዝጉዟል ፤ ዙርያ ገብ ክብ ሰርተው የተደረደሩ ወንበሮች ላይ ተሳታፊዎቹ ተቀምጠውና ዙርያውን ከበው ደስ የሚል ድባብ ፈጠሩ፡፡ መሃል ላይ ካምፋየር ተቀጣጠለ፡፡ ከዚያንም በዴሚዬን ማርሌይ ቀረፃ የሚሰሩት ባለሙያዎች በሚያስደንቅ ዝግጅት የቪድዮ ቀረፃውን አከናወኑ፡፡ ወደፊት የሙዚቃ ቪድዮው በኢንተርኔት የሚዲያ አውታሮች ሲሰራጭ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡
ዴሚያን ማርሌይን የሙዚቃ ቪድዮውን ለመስራት ለምን ብሄራዊ ቲያትርን እንደመረጠ … የዘፈኑ መልዕክት ምን እንደሆነ ጠይቄዋለሁ፡፡
‹‹የሙዚቃ ቪድዮው በብሄራዊ ቲያትር እንዲሆን የመረጡት ዲያሬክተሮቹ እንጂ እኔ አልነበረኩም። የመረጡበት ምክንያት ተስማምቶኛል፡፡ የቲያትር ቤቱን ታሪክ፤ ማራኪ የውስጥ ድባብ ከተመለከትኩ በኋላ አስደንቆኛል፡፡ የሙዚቃው መልዕክት እንደሰማኸው ስለ ሰላም፤ ስለ ፍቅርና አንድነት ነው። አፍሪካ ከችግሮቿ ሁሉ ተላቅቃ በሰላምና በእድገት እንድትጓዝ ለማነሳሳት ነው…›› ብሏል፡፡
ኢትዮጵያዊ ጥበብ ያለበሰችው ማፊ
ዴሚያን ማርሌይ፤ በብሄራዊ ቲያትር ባከናወነው የሙዚቃ ቪድዮ ቀረፃ ላይ ከነበሩ ባለሙያዎች ትኩረቴን የሳበችው የፋሽን ዲዛይነር ባለሙያ የሆነችው ማህሌት አፈወርቅ ወይም ማፊ ነበረች። ዴሚያን ቀረፃውን ከመጀመሩ በፊት ቀረፃው እየተከናወነና ከዚያም ከቀረፃው በኋላ አስር ጊዜ ‹‹ማፊ… ማፊ… ማፊ›› እያለ መጣራቱ አስደንቆኛል። ከቀረፃው በፊት የተከናነበው ጋቢና ከውስጥ የለበሰው በሚያም ጥለት የተዋበ በሸማ የተሰራ ሸሚዝ አልተመቸውም እንዴ… በቀረፃው ላይ ለብሶት የነበረው  በመስቀልና በተለያዩ የኢትዮጵያ ጥበቦች የተዋቡት ካባና ሸሚዝ… አልሆኑትም ይሆን? ብዬ ስታዘብ ነበር፡፡ ስለሆነም ማፊን በዚህ ጉዳይ ላይ ጠየቅኳት… ለካስ አስሬ ሲጠራት የነበረው ዲዛይን አድርጋ ያለበሰችው አልባሳት በትክክል ለብሶት እንደሆነ እንድታረጋግጥ ነበር፡፡
ማፊን ለዴሚያን ልብሶችን ዲዛይን አድርጋ የምትሰራበትን እድል የፈጠሩት የሙዚቃ ቪድዮ ቀረፃውን ከሎስ አንጀለስ ድረስ በመምጣት ያከናወኑት ድርጅቶች ባለሙያዎች ናቸው፡፡ በፋሽን ዲዛይነርነት የነበራትን ልምድና ታሪክ ከገመገሙ በኋላ እሷን ምርጫቸው አድርገው የኢትዮጵያን ባህል የሚያንፀባርቅ፣ ባህላዊና ዘመናዊ እሴቶችን ያዋሃዱ አልባሳት፤ በተለያዩ አማራጮች አዘጋጅታ እንድትሰራላቸው ጠየቅኳት፡፡ ከዚያም አራት አይነት የአልባሳት አማራጮችን በመስራት አቀረበችላቸው። ከሙዚቃ ቪድዮ ቀረፃው ጋር በተያያዘ በማፊ የቀረቡለትን ሁለት አልባሳት ዴሚያን በደስታ ነበር የተቀበላቸው፡፡ ከቀረፃ በፊት የለበሰው ሙሉ በሙሉ በሸማኔዎች ከጥጥ የተሰሩ፣ በጥለቶች የተዋቡ ጋቢና ሸሚዝ ነበሩ፡፡ ለሙዚቃ ቪድዮ ቀረፃው የለበሰው ደግሞ  በዘመናዊ ጨርቅ የተሰራ ግን የኢትዮጵያን ታሪክና ባህል የሚያንፀባርቅ፣ በወርቃማ የመስቀልና የባህላዊ ንድፎች የተጠለፉ ካባና ሸሚዝ ነበሩ፡፡ ከአዲስ አድማስ ጋር በዚሁ ስኬታማ ስራዋ ላይ አጭር ቃለምልልስ ያደረገችው ማፊ እንደገለፀችው፤ ዴሚያን የአልባሳት ዲዛይኖቿን ሙሉ ለሙሉ ረክቶባቸዋል፡፡ ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው በአማራጭነት ያቀረበችለትን አራቱንም ዲዛይኖች ሙለ ሙሉ መውሰዱ ሲሆን ከኮንሰርቱ በኋላ ወደፊት ሁሉም የአልባሳት ስራዎችን ለእሱና ለሙዚቃ ቡድኑ የተወሰኑ አባላት በማዘጋጀት እንድታቀርብ መስማማቱን እንደገለፀላት ተናግራለች፡፡
የፋሽን ዲዛይነርዋ ማህሌት አፈወርቅ ወደዚህ ስኬታማ ሙያዋ ከመግባቷ በፊት ገና ከ16 ዓመቷ ጀምሮ በሞዴልነትና በሙዚቀኛነት ለመስራት ሞክራለች ነበር፡፡ ጎን ለጎንም በነርስነት ሙያ እየተማረች ነበር፡፡ ልዩ ፍቅር የነበራት ግን ለፋሽን ሙያ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ሙያ ስኬታማ ለመሆን ከዓመታት ትጋትና ጥረት በኋላ የኢትዮጵያን ባህላዊ አልባሳት ከዘመናዊ ፋሽን ጋር በሚያዋህዱ ዲዛይኖቿ ዓለምአቀፍ ተቀባይነት እያገኘች መጥታለች። በነገራችን ላይ በ2010 የአውሮፓ ህብረት ባዘጋጀው የፋሽን ቀን በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሰስ “የዓመቱ ምርጥ ዲዛይነር” ተብላ ተሸልማለች፡፡ በ2012 ‹‹የኦርጅናል አፍሪካ ዲዛይን አዋርድ›› መጎናፀፏ እንዲሁም በ2012 በኒውዮርክ የአፍሪካ ፋሽን ሳምንት የተሳተፈችበት አጋጣሚ የሚጠቀሱ ናቸው። ለታዋቂ ሰዎች የአልባሳት ዲዛይን ስትሰራም ዴሚያን ማርሌይ የመጀመርያዋ አይደለም፡፡ በተለይ ለቴዲ አፍሮና ለታዋቂው ዓለም አቀፍ ሼፍ ማርክ ሳሙኤልሰን ያበረከተቻቸው ስራዎችም እንዳሏት ይታወቃል፡፡ በቅርቡ ደግሞ በክሬቲቭ ፊውቸርስ አዋርድ ላይ በመሳተፍ ያሸነፈች ሲሆን ከ5 ወራት በኋላ በሚካሄደው የ2017 ሃብ አፍሪካ የፋሽን ሳምንት ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ተሳታፊ ናት፡፡
የኮንሰርት አዘጋጆች ለወደፊቱ…
በጊዮን ሆቴል የቀረበው የዴሚያን ማርሌይ ኮንሰርት ደማቅ ድባብ እንደነበረው እድሉን አግኘተው የገቡ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች እየመሰከሩ ይገኛል፡፡ ይሁንና በአጠቃላይ የኮንሰርቱ ስኬት በተዘጋጀበት የጊዮን መናፈሻ ጥበት ፤ ትኬት የገዙ ታዳሚዎችን በአግባቡ ባላከበረ ሁኔታ የተካሄደው የበር ላይ መስተንግዶ፤  በኮንሰርት ታዳሚዎች በ11ኛው ሰዓት ትኬት የመግዛት ሩጫ የተፈጠሩ ግርግሮች ፤ የኮንሰርት አዘጋጆቹ ለሚዲያ ያነሰ ትኩረት መስጠት፤ የኮንሰርት ሰባሪዎች ጉዳይ፤ ኪስ አውላቂዎችና ጉዳዩን በፕሮፌሽናል መንገድ ባላስተናገዱ ተባባሪዎችና ተራ አስከባሪዎች ልዩ ሞገሱን እንዲያጣ ሆኗል፡፡ በተለይ አዘጋጆቹ ተገቢውን የተጋባዥ እንግዶች ዝርዝር በማዘጋጀት የሙዚቃ  ባለሙያዎች፤ ኢንቨስተሮች፤ የሚዲያ ባለሙያዎች የሚገቡበትን የይለፍ መታወቂያ በበቂ ትኩረትና ፍላጎት አዘጋጅተው ሊያቀርቡ ይገባ ነበር፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያለው ዴሚያን ማርሌይ ከተለያዩ ሚዲያዎች ጋር ሊገናኝበት የሚችልበትን ሰፊ የጋዜጣዊ መግለጫ መድረክ ለማመቻቸት መትጋት ነበረባቸው፡፡ብዙ የሙዚቃ አፍቃሪዎች የትኬት ዋጋ መወደድም አሳስቧቸዋል፡፡ እንደዴሚያን አይነት አርቲስትን ለማየት ምናልባት ከ200 እስከ 300 ብር ብንከፍል ብለው የጠየቁም አሉ፡፡ በርግጥ ኮንሰርቱ በአዲስ አበባ ስታድዬም ወይን በመስቀል አደባባይ ቢዘጋጅ ያን ያህል አይወደድም ነበር፡፡ ስለዚህ የኮንሰርት አዘጋጆች ትልልቅ መድረኮች ምቹ የሚሆንበትን አቅጣጫ በመፍጠር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መስራት ይኖርባቸዋል፡፡
‹‹ለኢትዮጵያ ሙዚቃዎች ልዩ ፍቅር አለን… ለሌላው ዓለም በስፋት እንዲዳረሱ እንፈልጋለን››
ዴሚያን ማርሌይ የኢትዮ ጃዝ አባት በተባለው ክቡር ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ የተሰሩ ሙዚቃዎችን በመጠቀም እና ከራሱ ዜማ እና አዘፋፈን ጋር በማዋሃድ ምርጥ ሙዚቃዎችን ሰርቷል፡፡  በተለይ ‹‹ዲስታንት ሪሌቲቭ›› በተባለውና  ከአሜሪካዊው ራፕር ናስ ጋር በሰራው አልበም የሙላቱን ‹‹የከርሞ ሠው››  ‹‹አስ ዊ ኢንተር›› በሚል ርእስ ተጫውተውታል፡፡ ከሶማሊያዊው ካናን ጋር በሰራው እንድ ሙዚቃ ደግሞ የሳክስፎኑን ንጉስ ጌታቸው መኩርያ  ዜማ በልዩ የራፕና ሂፕሆፕ ስልት ተጫውተውታል፡፡
ይህን አስመልክቶ ዴሚያን የኢትዮጵያን ዜማዎች እየመረጠ ለምን እንደሚሰራ እንዲያብራራልኝ ጥያቄ አቅርቤለት ነበር፡፡
‹‹ ሁሉንም አይነት ሙዚቃ ከልብ እንደምንወድ የኢትዮጵያን ሙዚቃንም በጣም እንወዳለን። ከየትኛው ዓለም ክፍል የመጣን ሙዚቃን እንሰማለን፡፡ በተለይ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ልዩ ፍቅር እያደረብን ነው፡፡  ከናስ ጋ በሰራነው አልበም ብዙ አፍሪካዊ ዜማዎችን ተጠቅመናል፡፡ ዋናው ዓለማችን የአፍሪካን ሙዚቃን መሰረታዊ አስተዋፅኦ እና ተፅእኖ ለማንፀባረቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቀኞች ዜማዎች ‹‹ሳምፕል›› በማረግ በመስራታችን ክብር ይሰማናል፡፡ በዓለም ዙርያ እንዲዳረስ በተሻለ ለማስተዋወቅ ነው፡፡›› የሚል ነበር የዴሚዬን ምላሽ
በመጨረሻም  ለዴሚያን ያቀረብኩት ጥያቄ ብዙዎቹ የሬጌ ሙዚቀኞች ወደ ተስፋዋ ምድር ኢትዮጵያ ለለመለስ ተስፋ እንደሚያደርጉ ከጠቀስኩ በኋላ ኢትዮጵያውያን ቦብ ማርሌይን እንዲሁም መላው ቤተሰቡን እንደሚወዱ ቦብ በህይወት እያለ ሙዚቃውን ካቆመ በኋላ ኑሮውን በኢትዮጵያ የማድረግ ህልም እንደነበረው በመግለፅ ይህ ህልም አንተ እውን ታደርገዋለህ ወይ… የሚል ነበር፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ቤት ቢኖረኝ ከልብ  እደሰታለሁ። በሁሉም ዓለም ክፍል ቤቶች እንዲኖሩኝ እፈልጋለሁ። በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ››

Read 1624 times