Print this page
Saturday, 10 June 2017 14:42

የጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  የተስፋ ብልጭታዎችና የወደፊት አቅጣጫዎች ክፍል 1
       • 445 አትሌቶች (243 ወንድና 202 ሴት) በማስመረቅ ለተለያዩ ክለቦች እና ቡድኖች አዘዋውሯል፡፡
       • 113 አትሌቶች 58 ወንድ 55 ሴት በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች እና የስፖርት ዓይነቶች ለብሄራዊ  ቡድን        ተመርጠዋል፡፡
       • 31 ወንድና 26 ሴት አትሌቶች በአህጉራዊ ውድድሮች፤ 13 ወንድና 11 ሴት አትሌቶች ደግሞ በዓለም አቀፍ                ውድድሮች ተሳትፈዋል፡፡

     የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሲሆን በኢትዮጵያ መንግስት ለግንባታው ብቻ ከ224 ሚሊዮን ብር ላይ ወጭ ሆኖበታል፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ደግሞ በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ማዕከሉ የዓለማችን ታላላቅ ሯጮች መፍለቂያ በሆነችው አርሲ ዋና ከተማ አሰላ ውስጥ በ45.9 ሄክታር ላይ ተገንብቷል፡፡
የግንባታው ተቋራጭ ዛምራ ኮንስትራክሽን ሲሆን በአማካሪነት የሰራው  አልትሜት ፕላን አማካሪ መሐንዲሶች እና አርክቴክቶች ኃ.የተ. የግ. ማ. ነው። በማዕከሉ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ይገኛሉ፡፡  ለአትሌቲክስ እና ሌሎች የሜዳ ላይ ስፖርቶች የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟሉና ትራኮች ከመነጠፋቸውም በላይ   የመለማመጃ ስፍራዎችም ይገኙበታል፡፡ የግንባታ ስራዎቹ በከፍተኛ ጥራት፤ ዓለም አቀፍ ደረጃን በማሟላት እና በልዩ የምህንድስና ጥበብ የተሰሩ ናቸው፡፡ በተጨማሪም የእግር ኳስ ሜዳ፤ ዘመናዊ ጅምናዚዬም ከነመሳርያዎቹ፤ ክሊኒክ፤ ቤተመፅሃፍት፤ የሰልጣኞች መማርያ፤ መመገቢያ አዳራሾች፤ የአሰልጣኞችና ሰልጣኞች መኖርያዎች እንዲሁም የአስተዳደር ቢሮዎችም ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ 19 የተለያዩ ህንፃዎች በደን፤በለምለም መስክ እና በነፋሻ አየር ተከበው በማዕከሉ ግቢ ውስጥ ተገንብተዋል። የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል  ሙሉ በሙሉ ግንባታው አልቆ በመመረቅ ስራ የጀመረው ከ1 ዓመት በፊት ነው፡፡ ይሁንና ማዕከሉን ለማደራጀትና ለማዋቀር በተያዘው አቅጣጫ፤ ሰልጣኞችን በመመልመል እና ልምምድ በማሰራት ከ7 ዓመታት በላይ የዘለቀ ልምድ ነበረው፡፡ የማዕከሉ ግንባታ በሂደት ላይ በነበረባቸው ዓመታት በተለይ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ከኦሮሚያ ክልል 8 ብሎክ ኮንደሚኒዬሞችን በ10 ሚሊዮን ብር ገዝቶ ሲሰራ ነበር፡፡
በአሰላ ከተማ የሚገኘውን የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከልን የጎበኘሁት ባለፈው ሰሞን ሲሆን የስፖርት መሰረተ ልማቶቹን ተዘዋውሬ ተመልክቼ ተደንቄባቸዋለሁ፡፡ ማዕከሉ በኢትዮጵያ የስፖርት መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፉ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል። ግንባታውን በአማካሪነት ካሰራው የአልትሜት ፕላን አማካሪ መሐንዲሶች እና አርክቲክቶች ሬዚዳንት ኢንጅነር መኮንን ዲንሣ በግንባታው ስለቀሰሙት ከፍተኛ ልምድ ተወያይተናል፡፡ የማዕከሉ አሰልጣኞች  ሰልጣኞችን እንዴት እንደሚመለምሉ ፤ ስለሚከተሏቸው ሳይንሳዊ የስልጠና መንገዶች፣ ስለውጤታቸው፣ ስለወደፊት ተስፋቸው ነግረውናል፡፡ ጉብኝቱን ያደረግነው በ46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማግስት በመሆኑ ትኩረት ያደረግነው በማዕከሉ የአትሌቲክስ እንቅስቃሴዎች ላይ ነበር፡፡ የእግር ኳሱን ነገር በሌላ አጋጣሚ የምንመለስበት ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ይህ ፅሁፍ የማዕከሉን የተስፋ ብልጭታዎች እና የወደፊት አቅጣጫዎች የዳሰስንበት ነው፡፡ መልካም ንባብ፡፡
‹‹በስፖርት መሰረተ ልማቶች ግንባታዎች ያለን ልምድና እውቀት ጨምሯል፡፡››
 የአልትሜት ፕላን ‹‹ሬዚዳንት›› ኢንጂነር መኮንን ዲንሣ
የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከልን ዲዛይን የሰራው፤  የግንባታ ቁጥጥሩን ያከናወነው፣ የኮንትራት ውሎችን በማስተዳደር በአማካሪነት የሰራው  አልትሜት ፕላን አማካሪ መሐንዲሶች እና አርክቴክቶች ኃ.የተ. የግል ማህበር ነው፡፡ በግንባታው ወቅት የአማካሪው ተቀማጭ መሃዲስ ሆኖ የሰራው ኢንጅነር መኮንን ዲንሣ ለስፖርት አድማስ እንደተናገረው የአልትሜት ፕላን መሐንዲሶችና ሌሎች ባለሙያዎች በስፖርት መሰረተ ልማቶች ዙሪያ ያላቸው ልምድና እውቀት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በተለይ ደግሞ የጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል እና በወልዲያ ከተማ በሚገኘው የሼክ መሃመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታድዬም ግንባታዎች የላቁ ውጤቶች እንደሆኑም ይገልፃል፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን በማሟላት የተገነቡ በመሆናቸው በየሙያ ዘርፉ ብዙ ልምድና ተመክሮዎችን ተቀስሞባቸዋል፡፡
ማዕከሉን ለመገንባት ከጅምሩ የታቀደው በ1 ዓመት ከ6 ወር  ነበር፡፡ ይሁንና በግንባታው ወቅት ባጋጠሙት ፈታኝ ሁኔታዎች 3 ዓመት ተኩል ፈጅቷል፡፡ ኢንጂነር መኮንን እንደሚለው ማዕከሉ የተገነባበት አካባቢ የነበረው አባጣ ጎርባጣ መልክዓ ምድርን ለማደላደል ያካሄዷቸው ቁፋሮዎች ለ2 ትልልቅ ስታድዬሞች የተካሄደ ይመስል ነበር፡፡ በተለይ የአፈር ቆረጣ ስራው ብቻ ከ6 ወራት በላይ መፍጀቱን ይናገራል፡፡  በርግጥ  ግንባታው የተከናወነበት አካባቢ ለአትሌቶች ተስማሚ መክዓምድርና ንፁህ አየር ስለሚገኝበት ለስፖርት የተመቸ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም ከግዛያዊው የግንባታ ፈተና ይልቅ የማዕከሉን ዘላቂ ጠቀሜታ እዚህ ጋር ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ የምህንድስና ባለሙያዎች ለየትኛውም የስፖርት መሰረተ ሙያው የሚጠይቀውን ትጋት እና ጥረት በማድረግ  መፍትሄ መፍጠር ነበረባቸው  ስለዚህም አስቸጋሪውን መልክዓ ምድር አመቺ እንዲሆን መስራታቸውን  የጠቀሰው መኮንን ዲንሳ ፤  በቀደምት የስፖርት መሰረተ ልማቶች የተገኙ ልምዶች ወደፊት አዳዲስ ለሚሰሩ እንደ ተመክሮ መወሰድ እንዳለባቸው ፤ የግንባታ ስፍራዎች አስፈላጊ ባለሙያዎችን በሚያሳትፉ ቅድመ ጥናቶች መመረጥ እንዳለባቸው አመላክቷል፡፡  
የማዕከሉ አብዛኛዎቹ የግንባታ ግብዓቶች ከአገር ውስጥ መገኘታቸውን የሚገልፀው ኢንጅነር መኮንን፤ በተለይ ከውጭ አገራት የገቡት የትራክ ንጣፎች፤ የፓውዛ መብራቶች፤ የጂምናዚዬም መሳርያዎች መሆናቸውን ጠቃቅሷል፡፡ በአጠቃላይ የስፖርት መሰረተ ልማቶቹ  ፈታኝ የግንባታ ሂደቶች ያለፉባቸው ቢሆንም በኢትዮጵያዊ የምህንድስና ባለሙያዎች የሙያ ብቃት ጥናትና ክትትል መሰራታቸው የገዘፈ የእውቀት ሽግግርና ስኬት የተገኘበት ነው፡፡  
ከ25 እስከ 30 ዓመታት በብቃት የሚያገለግሉት ዘመናዊ ትራኮችና አነጣጠፋቸው
መሐንዲስ መኮንን ዲንሣ ለስፖርት አድማስ  እንደገለፀው በማዕከሉ የተነጠፉት የመሮጫ እና የመለማመጃ ትራኮች  ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ ትራኮቹና ሌሎች ግብዓቶቻቸው ወደ ማዕከሉ ገብተው ከመነጠፋቸው በፊት የግንባታው ባለቤት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር፤ የግንባታው ተቋራጭ ዛምራ ኮንስትራክሽን እና የግንባታው አማካሪ አልትሜት ፕላን በወከሉ ባለሙያዎች የተዋቀረ ኮሚቴ ወደ ውጭ በመጓዝ አስፈላጊውን ግምገማ እና ምርመራ  አድርገዋል። የትራኮቹ  የአገልግሎት ዘመን፤ጥንካሬ፤ ተለጣጭነት፤ ከኦርጅናል ፕላስቲክ መሰራት … እንዲሁም ሌሎች የመለኪያ መስፈርቶችን በመከተል በጥልቀት የመፈተሽ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ከዚህ ሂደት በኋላ ትራኮቹንና አጠቃላይ ግብዓቶቻቸው የ‹‹ሌሱታን››  ብራንድ እንዲሆኑ ተወሰነ፡፡ ተቀማጭነቱን በቻይናዋ ሻንጋይ ከተማ ያደረገ ኩባንያ የሚያቀርበው ምርት ሆነ፡፡ ሌሱታን የተባለው የትራክ ብራንድ በ2008 እኤአ ላይ ለቤጂንግ ኦሎምፒክ በወፍ ጎጆ የተነጠፈ ነው፡፡ ኢንጅነር መኮንን ዲንሳ ለስፖርት አድማስ  እንዳስረዳው የመሮጫ እና የመለማመጃ ትራኮቹ ንጣፍ፤ ደረጃ በደረጃ የተሰራበት ሁኔታ  ምህንድስናው ከፍተኛ ጥበብ የጠየቀ ፤ ቴክኖሎጂው ወቅቱን  የጠበቀ ፤ ደረጃው የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበርን መስፈርት ሙሉ ለሙሉ ያሟላ ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ወደፊት ለሚሰሩ ተመሳሳይ የትራኮች ንጣፍ ተምሳሌት እንደሚሆንም በልበ ሙሉነት ይናገራል፡፡ ትራኮቹ የግልጋሎት ዘመናቸው ከ25 እስከ 30 ዓመት የሚዘልቅ ነው፡፡ ታላላቆቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች እነ ኃይሌ፤ ጥሩነሽ፤ ደራርቱ እና ሌሎች አትሌቶች በተለያዩ አጋጣሚዎች በነበሯቸው ጉብኝቶች እነዚህ ትራኮች ሙሉ በሙሉ አድንቀዋል፡፡ በማዕከሉ አሰልጣኞች እና በሌሎች የስፖርት ባለሙያዎችም ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ ከሩጫ ስፖርቶች ባሻገር በዋናው ትራክ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለተለያዩ የሜዳ ላይ ስፖርቶች ማለትም ለጦር ውርወራ፤ ከፍታ ዝላይ፤ለምርኩዝ ዝላይ፤ ለአሎሎ እና ለዲስከስ ውርወራ የተዘጋጁ ክልሎች አሉ፡፡ የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮና ሚኒማ ለማሟላት የሚያግዙ ናቸው፡፡
የአልትሜት ፕላን ቀጣይ ፕሮጀክቶች የቃሊቲና የአበበ ቢቂላ ስታድዬሞች …
አልትሜት ፕላን አማካሪ መሐንዲሶች እና አርክቴክቶች ኃ.የተ. የግል ማህበር በኢትዮጵያ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ግንባታ በአማካሪነት በመስራት ከፍተኛ ልምድ እያካበተ ቀጥሏል፡፡ በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል እና በወልዲያው የሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታዬም ግንባታዎች የተገኙ ልምዶች ደግሞ ከፍተኛ ናቸው። ከሁለቱ ግዙፍ የስፖርት መሰረተ ልማቶች በኋላ በሌሎች ፕሮጀክቶችም እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በአዲስ አበባ የተለያዩ ዞናል ስታድዬሞችን ዲዛይን የሰራው አማካሪው በአቃቂ ቃሊቲ ከ25 ሺህ በላይ  ተመልካች የሚያስተናግደውን ስታድዬም ግንባታ ጀምሯል፡፡ ይህ ስታድዬም ከወልዲያው ሼክ መሃመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታድዬም ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ ዙርያውን ጥላ ፎቅ የሚገነባለት፤ ባለ ሙሉ መቀመጫ እና ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ ትራክ የሚነጠፍለት ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል አልትሜት ፕላን አማካሪ መሐንዲሶች እና አርክቴክቶች ኃ.የተ. የግል ማህበር የአበበ ቢቂላ ስታድዬም ሁለንታናዊ ጥገና ለማድረግ፤ ትራክ ለማንጠፍ፤ ዙርያ ገብ ጥላ ፎቅ ለመስቀል እና ባለ ሙሉ መቀመጫ ለመስራት  በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡
ይቀጥላል


Read 3749 times