Sunday, 11 June 2017 00:00

“ተዉ አታበላሹ እንጂ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በዛ ሰሞን ነው…በተቆፈረው የከተማው አንድ ክፍል፡፡ በአሥራዎቹ መጀመሪያ የሚሆኑ ልጆች የተቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ ከርቀት ድንጋይ እየወረወሩ ይፎካከራሉ፡፡ ይሄኔ አንድ አዛውንት ምን ቢሉ ጥሩ ነው…
“ልጆች ተዉ አታበላሹ እንጂ፣ ለእናንተ ነው እኮ የተቆፈረው፡፡”
እንግዲህ ምን ያስቡ፣ ምን እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ ግን ነገርዬዋ…አለ አይደል…ለሌላውም ታገለግላለች፡፡
“ተዉ አታበላሹ እንጂ…” ሊባልላቸው የሚገባ መአት ነገሮች አሉ፡፡
ስሙኝማ…ሰኔ ገባ አይደል፣ በጀት መዝጊያ ጊዜ!… እኔ የምለው… ያለአግባብ ምን ሆነ የተባለ ስንት ቢሊዮን ብር ነው! እንዴት ነው…ነገርዬው ሁሉ ሀዲዱን የሳተ ባቡር እየሆነ ያለው! በሚሊዮኖች ስንገረም፣ በመቶ ሚሊዮኖች ስንገረም፣ ጭራሽ ቢሊዮኖች ገባና አረፈው!
እናማ…“ተዉ አታበላሹ እንጂ…” ሊባልላቸው የሚገባ መአት ነገሮች አሉ፡፡
ዘንድሮ…አለ አይደል…ሁሉም ነገሮችን የሚያየው ከራሱ ሆኗል፡፡ እሱ ከደላው ሁሉም ሰው የደላው ይመስለዋል፣ እሱ አሼሼ ገዳሜ ካለ ሁሉም ሰው አሼሼ ገዳሜ የሚል ይመስለዋል፡፡ በሆነ ነገር ‘ሙያተኛ’ የሆኑት ሰዎች ሙያው የሚጠይቀውን ማብራሪያ ከመስጠት እንደራሳቸው ጓዳ ብቻ ሲያስቡት አስቸጋሪ ነው፡፡
“ቲማቲም እንዲህ የተወደደችበትን ምክንያት ልታስረዳኝ ትችላለህ?…”
“መሠረታዊ የሆነ ጥያቄ ነው ያመጣኸው፡፡ ይገርምሀል፣ ይሄን ጥያቄ መቼ ነው የምጠየቀው ብዬ አስብ ነበር፡፡ ዋናው ነገር በመጀመሪያ ቲማቲም ምን አይነት ጥቅም እንደሚሰጥ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡”
ሰውየው ምን ነካው! የቲማቲም እርሻ አለው እንዴ!
ስለ ዋጋው መወደድ ጠየቅሁት እንጂ የካሎሪና የቪታሚን ዝርዝር አቅርብልኝ አልኩት!
“ይቅርታ፣ መቼም ስለ ቲማቲም ጥቅም የማያውቅ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ አሁን ማወቅ የምፈልገው ዋጋው እንደ ጠፈር መንኮራኩር ሽቅብ ለምን እንደተተኮሰ ነው፡፡
“እኮ መወደዱ ከሚሰጠው ጥቅም ጋር መያዝ አለበት፡፡ ቲማቲም ተወደደ ማለት ብቻ ሳይሆን ዋናው ማወቅ የሚገባን ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር ለምን ኪሎ መቶ ብር አይገባም…”
ይቺን  ይወዳል!  “ኧረ አንተኑ መቶ…” ብላችሁ ትጀምሩና ትተዉታላችሁ፡፡ ልክ እኮ ቲማቲም አዲስ የተገኘች ግኝት ሆና ገና “ጉድ! ጉድ!” እየተባለላት ያለች ነገር ያስመስላታል፡፡
“ተዉ አታበላሹ እንጂ…” ሊባልላቸው የሚገባ መአት ነገሮች አሉ፡፡
እናላችሁ… ስንት ዘመን ስንጠቀምባቸው የኖርናቸው ነገሮች…አለ አይደል… በፈረንጂኛ ስለተጻፈላቸው ብቻ የሆነ አዲስ ግኝት የተገኘ ይመስል ስናደርገው የሆነ ችግር አለ፡፡
“ስለ ጤፍስ ምን ታስባለህ?”
“ጤፍማ አሁን ዓለም አቀፋዊ ሆናለች፣ በእውነት ደስ የሚል ነው፡፡”
“ደስ የሚል ነው የሚለውን ብታስረዳኝ…”
“ፈረንጆች ጤፍን መውደዳቸው በጣም ደስ ይላል፣ ይህ ጤፍ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡”
“ፈረንጅ ወደደው አልወደደው የጤፍን ደረጃ የሚቀንሰው ነገር አለ እንዴ! ለምንድነው ስንት ሺህ ዓመት ስንጠቀምበት ኖረን አሁን የምንዘምርለትን ያህል ሳንዘምርለት የኖርነው!”
“አልገባህም፣ ዋናው ነገር ጤፍ ዓለም አቀፍ መሆኗ ለመልካም ገጽታ ግንባታ ያግዛል፡፡ ‘ጤፍ’ የሚለው ነገር ሲነሳ የኢትዮዽያም ስም አብሮ ይነሳል…”
ቆይማ…የኢትዮዽያ ስም እንዲነሳ  የሚያደርጉ መአት ነገሮች አሉ እኮ! ስንት በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት ላያቸው ላይ የተቀመጥንባቸው… አለ አይደል… የፈረደበት ፈረንጅ ‘እስኪያወራላቸው’ የምንጠብቃቸው ስንት ነገሮች አሉ እኮ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይቺ ‘የመልካም ገጽታ ግንባታ’ የሚሏት ነገር እንዴት ነው እንዲህ መጫወቻ የሆነችው! አሸር በአሸር የሆነውን ‘ዲስኩር’ ሁሉ ማሳመሪያ ሆና ‘ኩል፣’ ‘ፋውንዴሽን’ ምናምን አስመሰልናት እኮ!  
“ድርጅታችን የአገሪቱን መልካም ገጽታ በውጪ ለመገንባት አቅዶ እየሠራ ነው…” አይነት ‘ወሬ’ ማሳመሪያ ተለምዷል፡፡ ድርጀቱ እኮ እንኳን የአገር ገዕታ ሊገነባ ራሱ ገጽታ የሚባል ነገር የለውም!  ቂ…ቂ…ቂ… ግን በዚህ የአገር ገጽታ ለመገንባት መካከለኛ ገቢ ለመድረስ ምናምን የሚባሉ ‘ዲስኩር’ ማሳመሪያዎች ላይ “እንዴት?” “ለምን?” አይነት ጥያቄዎች ስለማይነሱ እንደተፈለገው መደጋገም ይቻላል፡፡ እናማ… ይቺ ‘መልካም ገፅታ ግንባታ’ የምትለዋ ሀረግ… ጠቃሚነቷ ሳስቶ ትርጉም አልባ እንዳትሆንማ!”
“እኔ እንዲህ የሚሉ ብዙ ሰዎች ከልባቸው ሳይሆን ‘እነ እከሌ ብለውት እኔ ሳልለው እንዳልቀር’ ብለው ይመስለኛል፡፡ ጤፍን ከአገር መልካም ገፅታ ጋር ማያያዝ…”
“ቆይ!  ቆይ! እንዲህ ስትል ምን ማለትህ ነው? አንተ እንደ ጠላቶቻችን የዚችን አገር እድገት አትፈልግም እንዴ? አንተ…”
አሁን ነገር መጣ! አሁን ገና ዋናው ነገር መጣ! አሁን ገና የአገር በሽታ እየሆነ ያለ ነገር መጣ! በሆነ አቋም ላይ ጠንከር ብላችሁ ከተከራከራችሁ…እንዲህ አይነት ነገር እንደሚመጣ ጠብቁ፡፡ ሀሳቦቻችሁን የምታራምዱ ሳይሆን ከጀርባ ሌላ ዓላማ ያላችሁ አስመስለው ‘ጎመን በጤና’ እንድትሉ ያደርጓችኋል፡፡
“ተዉ አታበላሹ እንጂ…” ሊባልላቸው የሚገባ መአት ነገሮች አሉ፡፡
“እሺ በአጠቃላይ የዋጋ መወደድ ምክንያት ምንድነው ትላለህ?”
“እሱ እንኳን የእድገት ምልክት ነው፡፡”
“ይቅርታ የብዙ ነገሮች ዋጋ ተወደደ፣ ከአቅማችን በላይ ሆነ፣ ኑሮ ከፋ እያልኩህ እኮ ነው!”
“እኮ እኔስ ምንድነው የምልህ…ይሀ ሁሉ ምን ያህል እያደግን እንደሆንን የሚያሳይ ነው፡፡”
“በነገራችን ላይ እየሠራኸው የነበረው ቤት ምን ደረሰ?”
“እሱማ አለቀና አከራየሁት እኮ፡፡ እንደውም ሲ.ኤም.ሲ. የተጀመረ ጂ ፕላስ ቱ ገዝቼ እየሠራሁ ነው፡፡”
“ታዲያ መጀመሪያውኑ እንዲህ አትለኝም!” ትላላችሁ በሆዳችሁ፡፡ ግን ደግሞ ዝም ብሎ ማለፉም አላስችል ይላል፡፡
“ለምሳሌ እኛ ቤት ቁርስ መብላት ትተናል። የምሳ ፍጆታችንም በአርባ ስምንት በመቶ አቆልቁሏል። ይቅርታ እዚህ አገር ሁሉንም ነገር በመቶኛ ማስላት የማይሸረፍ ሰብዊ መብት ስለሆነ ነው ቁጥር የጠቀስኩት፡፡”
“ምን እያልክ ነው…”
“እኔም፣ የማውቃቸውም ሰዎች የምንበላው እየቸገረን እንዴት የእድገት ምልክት ነው ትለኛለህ!”
“እሱ የአንተ ጉዳይ ነው፡፡”
“ለምሳሌ ድሮ ለምሳዬ ሁለት አይነት ምግብ እበላ ነበር፡ ዘንድሮ ግን አልሆነም፡፡”
“እሱ እንግዲህ…”
“ለምሳሌ በፊት ግፋ ቢል ፓራሳይቷ ምናምን ብታስቸግረኝ ነው…አሁን ግን የበሽታ አይነት በሙሉ ሰፍሮብናል፣ ይሄም የእድገት ምልክት ነው?…”
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…ሰዓሊው ሴትዮዋን እየሳላት ነበር፡፡ ሲጨርስም አቀረበላትና…
“ምን ይመስልሻል…” ይላታል፡፡
እሷም ግንባሯን ቋጥራ “ምን በደልኩህ! ምን ብበድልህ ነው እንዲህ አድርገህ የምትስለኝ…” ትለዋለች፡፡
ሰዓሊው ይደነግጥና “ምነው፣ ምን አጠፋሁ!” ይላታል፡፡ እሷ እየተንገሸገሸች…
“ጦጣ ነው እኮ ያስመሰልከኝ!…” ትላለች፡፡
ይሄኔ ሰዓሊው ሳቅ ብሎ ምን ቢላት ጥሩ ነው… “እሱ የእኔ ሳይሆን የወላጆችሽ ጥፋት ነው…” ብሏት አረፈው፡፡
ሰው ከመውቀስ በፊት ጥፋቱ የማን እንደሆነ ይለይማ!
እናማ…“ተዉ አታበላሹ እንጂ…” ሊባልላቸው የሚገባ መአት ነገሮች አሉ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5795 times