Sunday, 11 June 2017 00:00

ሰላማቸው እያሽቆለቆለ ከመጣ 5 ሀገራት፤ ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ሆናለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(25 votes)

  አለመረጋጋትና ግጭት፣የዜጎች የደህንነት ስሜት፣ የሰብአዊ መ ብት አጠባበቅ፣ የፖለቲከኛ እስረኞች ብዛት
         
    በዓለም ላይ ሰላማቸው በእጅጉ እያሽቆለቆለ ከመጣ አምስት አገራት ኢትዮጵያ የመሪነቱን ቦታ የያዘች ስትሆን ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ፣ብሩንዲ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ማሊና ሌሴቶ ይከተላሉ፡፡
 ሰሞኑን ይፋ በተደረገው የዘንድሮ የዓለም ሀገራት የሰላም ሁኔታ ሪፖርት፤ ከ178 አገራት በ134ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ኢትዮጵያ፤ቀድሞ ከነበራት ደረጃ 16 ያህል ደረጃዎችን ዝቅ በማለት ሰላማቸው በእጅጉ ካሽቆለቆለ የዓለማችን አገራት የቀዳሚነቱን ሥፍራ ይዛለች ተብሏል፡፡
የዓለም አገራት የሰላም ይዞታን ለመገምገም 22 መሰረታዊ መስፈርቶች የተቀመጡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አለመረጋጋትና ግጭት፣ የዜጎች የደህንነት ስሜት፣ የሰብአዊ መብት አጠባበቅና በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ እስረኞች ብዛት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
ኢትዮጵያ በግጭት ውስጥ ማለፏና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር መሆኗ ሰላማቸው አሽቆልቆሏል ከተባሉ የዓለም አገራት በቀዳሚነት እንድትሰለፍ አድርጓታል ያለው ሪፖርቱ፤የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለመንግስት ተጨማሪ ጡንቻ በመፍጠሩ ተቃውሞዎች በኃይል እንዲታፈኑ አድርጓል ብሏል። በሀገሪቱ የተከሰተው ግጭትና የቆይታ ጊዜው እንዲሁም ያስከተለው ሰብአዊ ቀውስም ኢትዮጵያን ሰላማቸው በእጅጉ ካሽቆለቆሉ 5 አገራት ግንባር ቀደሟ አድርጓታል፡፡ ፡  
በሰላም ማሽቆልቆል ከኢትዮጵያ ጋር የተጠቀሱት ሌሎች የዓለም ሀገራት፡- ፣ብሩንዲ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ማሊና ሌሴቶ ሲሆኑ ቀድሞ የነበራቸው የሰላም ሁኔታ ተሻሽሏል ተብለው የተጠቀሱ 5 የዓለም ሀገራት ደግሞ፡- የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ስሪላንካ፣ ካምቦዲያ፣ ፖርቹጋልና ጅቡቲ ናቸው፡፡
ላለፉት 9 ዓመታት በዓለም ላይ ሰላማዊ ሀገር በመሆን የቀጠለችው አውሮፓዊቷ አይስላንድ ስትሆን እሷን ተከትለው ኒውዚላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ኦስትሪያና ዴንማርክ ይጠቀሳሉ፡፡ በተቃራኒው ሶርያ፤የዓለማችን  ሰላም አልባ አገር የተባለች ሲሆን አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ደቡብ ሱዳንና የመን ይከተሏታል፡፡
ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው ግሎባል ፒስ ኢንዴክስ፤ በቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን፣ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር እንዲሁም ለሀገራቸው መልካም የሰሩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችን የሚሸልም ድርጅት ባላቸው ኖህ ሳማራና በሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች እንደሚደገፍ ይታወቃል፡፡   

Read 8266 times