Sunday, 04 June 2017 00:00

የስዊድኑ ሆቴል ፍቺ ለሚፈጽሙ ደምበኞቹ ካሳ ሊሰጥ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ካንትሪሳይድ ሆቴልስ ግሩፕ የተባለው የስዊድን ሆቴል ከቅርንጫፎቹ በአንደኛው ለተወሰነ ጊዜ በማረፍ አገልግሎቱን የሚጠቀሙ የተኳረፉ ባለትዳሮች፣ በሆቴሉ ቆይታቸው ችግራቸውን የማይፈቱና በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ፍቺ በመፈጸም ትዳራቸውን የሚያፈርሱ ከሆነ ካሳ እንደሚሰጥ ማስታወቁ ተዘግቧል፡፡
በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በውይይት የመፍታት ባህልን የማዳበር ተልዕኮ ያነገበው ሆቴሉ፤ በተለያዩ ምክንያቶች የተኳረፉ ጥንዶች ከቅርንጫፎቹ ወደ አንደኛው ጎራ በማለት፣ እየተዝናኑ ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱና ትዳራቸውን ከመፍረስ እንዲያድኑ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ሲሆን፣ በቆይታቸው ችግራቸውን መፍታት ካቃታቸውና በ1 አመት ጊዜ ውስጥ የሚፋቱ ከሆነ፣ ለተፋቺዎቹ የሁለት ቀን አዳር ሙሉ ወጪያቸውን በካሳ መልክ እንደሚሰጥ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሆቴሉ ይህንን ያልተመለደ አሰራር የቀየሰው ባለትዳሮች በመካከላቸው ግጭትና አለመግባባት ሲከሰት፣ ከመደበኛው ህይወታቸውና በግርግር ከተሞላው አለም ለተወሰነ ጊዜ በመውጣት ገለል ብለው እየተዝናኑ በትዳራቸው ጉዳይ ላይ በሰከነ መንፈስ እንዲመክሩና ትዳራቸውን ከአደጋ እንዲታደጉ ለማበረታታት ነው ተብሏል፡፡
ከሆቴሉ ቅርንጫፎች በአንደኛው የተወሰነ ጊዜ ቆይተው በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት ለመቅረፍ ያልቻሉና ፍቺ የፈጸሙ ባለትዳሮች፣ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የተሰጣቸውን ህጋዊ ፍቺ መፈጸማቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ  ለሆቴሉ በማቅረብ የተጠቀሰውን የካሳ ክፍያ ማግኘት እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡

Read 1646 times