Sunday, 04 June 2017 00:00

2016 በታሪክ ከፍተኛው የመኪና ሽያጭm የተመዘገበበት ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ቻይና በማምረትም በመሸጥም አለምን ትመራለች

    ያለፈው የፈረንጆች አመት 2016 በአለማችን የመኪና ሽያጭ ታሪክ አዲስ ክብረ ወሰን የተመዘገበበትና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መኪኖች የተሸጡበት እንደነበር የጠቆመው ቢዝነስ ኢንሳይደር ድረገጽ፣ በአመቱ 88.1 ሚሊዮን ያህል መኪኖች መሸጣቸውን ዘግቧል፡፡
በ2016 በአለማቀፍ ደረጃ የተመዘገበው የመኪኖች ሽያጭ መጠን በ2015 አመት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ4.8 በመቶ እድገት ማሳየቱን የጠቆመው ዘገባው፣ የሽያጭ እድገቱ ባለፉት አራት አመታት ከተመዘገቡት ከፍተኛው እንደሆነም ገልጧል፡፡
በአመቱ 24.38 ሚሊዮን መኪኖችን በመሸጥ ከአለማችን አገራት ቀዳሚዋ ቻይና ስትሆን፣ ከአመቱ አለማቀፍ የመኪና ሽያጭ ገበያ የ13 በመቶ ድርሻን የያዘቺው አገሪቱ፣ ባለፈው አመት ከሸጠቻቸው የ3.2 ሚሊዮን መኪኖች ጭማሪ ማሳየቱንም ዘገባው አስረድቷል፡፡
ቻይና በአመቱ ከአለማችን አገራት ከፍተኛውን የመኪና ሽያጭ ለማስመዘገቧ በምክንያትነት ከሚጠቀሱ የተለያዩ ጉዳዮች መካከል በአነስተኛ መኪኖች ላይ የ50 በመቶ የታክስ ቅናሽ ማድረጓ አንዱ እንደሆነም ዘገባው አብራርቷል፡፡
በ2009 የፈረንጆች አመት ከተከሰተው አለማቀፍ የገንዘብ ቀውስ በኋላ በነበሩት አመታት፣ የአለማችን የመኪኖች ሽያጭ መሻሻል እያሳየ መቀጠሉንም አክሎ ገልጧል፡፡ ስታቲስታ የተባለው አለማቀፍ የመረጃ ትንተና ተቋም በበኩሉ፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 በአለማቀፍ ደረጃ 72 ሚሊዮን ያህል የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የተለያዩ አይነት መኪኖች መመረታቸውን ይገልጻል፡፡
የአለማችን የመኪና ምርቱ በ2015 ከነበረው የአምስት በመቶ ያህል እድገት እንዳሳየ የጠቆመው ድረገጹ፣ በአመቱ 24 ሚሊዮን መኪኖችን ያመረተቺው ቻይና ከአለማችን አገራት በአንደኛነት መቀመጧንና ከአለማችን የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መኪኖች ምርት 34 በመቶውን ያህል እንደምትይዝ ገልጧል፡፡
ከቻይና ታላላቅ ትርፋማ የመኪና አምራች ኩባንያዎች መካከል ከታዋቂው የአሜሪካ መኪና አምራች ኩባንያ ጄኔራል ሞተርስ ጋር በጥምረት የሚሰራው ሲያክ ሞተር ኮርፖሬሽን እንደሚገኝበትም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1243 times