Sunday, 04 June 2017 00:00

በደብረማርቆስ በ650 ሚ. ብር የዘይት ፋብሪካ ሊገነባ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 የሀገሪቱን 20 በመቶ የዘይት ፍጆታ ይሸፍናል ተብሏል
                            
     በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረማርቆስ ከተማ በ650 ሚሊየን ብር WA የተባለ የዘይት ፋብሪካ ሊገነባ ነው፡፡ ፋብሪካው ስራ ሲጀምር 20 በመቶ የሀገሪቱን የዘይት ፍጆታ በመሸፈን  ለዘይት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስቀር የWA የዘይት ፋብሪካ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው ዘይቱን ለማምረት ኑግ፣ሰሊጥ ሱፍና አኩሪ አተርን የሚጠቀም ሲሆን በቀን 250 ቶን የእህል ምርት  በመጠቀም 130 ቶን ንፁህ ዘይት የማምረት አቅም እንዳለው የገለጹት ኃላፊዎቹ፤የፋብሪካውን ግንባታ የሚሰራው የቻይና ኩባንያ በ3 ወራት ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ተፈራርሟል ብለዋል፡፡ በ30 ሺ ካ.ሜ መሬት ላይ ያርፋል የተባለው የዘይት ፋብሪካው ስራ ሲጀምር ለ650 ሰራተኞች የስራ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር የምስራቅ ጎጃም ዞን 40 ያህል ሰሊጥ አምራች ባለ ሀብቶችና ገበሬዎች በተሻለ ዋጋ ለፋብሪካው ግብአት የሚሆን ጥሬ እቃ በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ታውቋል፡፡ ወደፊት ፋብሪካው የራሱን ጥሬ እቃ ለመጠቀም የራሱ እርሻ እንደሚኖረውም ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡
WA የዘይት ፋብሪካ ይህንን ፕሮጀክት አጠናቆ ስራ ጀመረ በኋላ የበቆሎ ዘይት ለማምረት እቅድ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 2202 times