Sunday, 04 June 2017 00:00

አትሌት መሰረት በ5ሺ ሜትር የኢትዮጵያን ከፍተኛ ውጤት ይዛለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ባለፈው ሰሞን  ባሳለፈው ውሳኔ አትሌት መሰረት ደፋር  በቤጂንግ ኦሊምፒክ በአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች የወሰደችው የነሐስ ሜዳሊያ ወደ ብር ሜዳልያ እንዲያድግ   ወስኗል፡፡ አትሌት መሰረት በ5ሺ ሜትር በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ በቤት ውስጥ ውድድርና በኦሎምፒክ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበች አትሌት እንደሆነች ይታወቃል፡፡  የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ለአትሌት መሰረት የቤጂንግ ኦሎምፒክ የነሐስ ሜዳሊያው የተቀየረላት በወቅቱ በዜግነት ቱርክን ወክላ ሁለተኛ ወጥታ የነበረችው ትውልድ ኢትዮጵያዊቷ   አትሌት ኤልቫን አብይ ለገሰ የተከለከለ አበረታች መድሃኒት ተጠቅማ መገኘቷ ስለተረጋገጠ ነው። ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት  አትሌት ኤልቫን በዶፒንግ ተጠቃሚነት ጥፋተኛ ሆና በመገኘቷ ከ2007 እስከ 2009 እኤአ ድረስ ያገኘችውን ክብር፣ ጥቅምና ሜዳሊያዎች ተነጥቃለች። በ2008 እኤአ ላይ የቻይናዋ ቤጂንግ ከተማ ባስተናገደችው 29ኛው ኦሎምፒያድ በ5ሺ ሜትር ሴቶች አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በአንደኝነት በማጠናቅቅ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው፡፡ በተመሳሳይ ከወራት በፊት ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ባሳለፈው ውሳኔ ለንአትሌት ሶፍያ አሰፋ በለንደን ኦሊምፒክ በሶስት ሺህ ሜትር መሰናክል ሴቶች ያገኘችው የነሐስ ሜዳሊያ ወደ ብር ማሳደጉ እይዘነጋም፡፡
በዶፒንግ ጥፋቶች በ2008 እኤአ በቤጂንግ ኦሎምፒክ በሴቶች 5ሺ ሜትር እንዲሁም በ2016 እኤአ በሪዮ ኦሎምፒክ በሴቶች 3ሺ ሜትር መሰናክል በኢትዮጵያውያ አትሌቶች ተመዝግበው የነበሩት ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎች በሁለት የብር ሜዳልያዎች በመቀየራቸው ኢትዮጵያ እስካሁን በተሳተፈችባቸው 13 ኦሎምፒያዶች ያስመዘገበችው ውጤት 22 የወርቅ፣ 11 የብርና 20 የነሐስ በድምሩ 53 ሜዳሊያዎች ሆኗል፡፡
ከአትሌት መሰረት ደፋር የውጤት ታሪክ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
2 ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን፤ 1 ጊዜ የብር ሜዳልያ
2 ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን፤ 1 ጊዜ የብር ሜዳልያ፤ 2 ጊዜ የነሐስ ሜዳልያ
4 ጊዜ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር ሻምፒዮን፤ 2 ጊዜ የብር ሜዳልያ፤ 1 ጊዜ የነሐስ ሜዳልያ
2 ጊዜ የኦል አፍሪካን ጌምስ ሻምፒዮን
 1 ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን
 3 ጊዜ የብር ሜዳልያ
 2 ጊዜ የዓለም ኮንትኔንታል ካፕ አሸናፊ
 9 ጊዜ የዓለም አትሌቲክስ ፍፃሜ አሸናፊ
 6 ጊዜ የዳይመንድ ሊግ 6 ጊዜ የጎልደን ሊግ ውድድሮች አሸናፊ
3 ጊዜ የኢትዮጵያ ሻምፒዮን

Read 2571 times