Sunday, 04 June 2017 00:00

ለብርቱካን አካሉ ህክምና ርብርቡ ቀጥሏል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ታዋቂዋ የስፖርት ጋዜጠኛ ብርቱካን አካሉ ለሚያስፈልጋት አስቸኳይ ህክምና  በአገር ውስጥ እና በተለያዩ ዓለም ክፍሎች    ገንዘብ የማሰባሰቡ ሂደት  ቀጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ስራ አስፈፃሚ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ አስቸኳይ ኮሚቴ በማቋቋም ከአባላቱ ገንዘብ ማሰባሰብ ጀምሯል፡፡
የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ሃና ገብረስላሴ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀችው አስቸኳይ ኮሚቴው ከባላቱ በነፍስ ወከፍ 200 ብር መሰብሰብ  የጀመረ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችን በመወከል ሄኖክ አበራ እንዲሁም የኤልፓ ደጋፊዎችን በመወከል ሰለሞን ተሾመ በአገር ውስጥ ከየአቅጣጫ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ እና በአካባቢው አገራት የሚገኙ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እና ስፖርት አፍቃሪዎች እንዲሁም በሰሜን አሜሪካ ደግሞ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር አባላት የሆኑት ታምሩ አለሙ እና አምሃ ፍሰሃ የማሳከሚያ ገንዘቡን ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነም ጨምራ ገልፃለች፡፡  ያለፉትን ሶስት አመታት   በደቡብ አፍሪካና በኬኒያ ማሳለፏን የምትናገረው ብርቱካን ከጨጓራ ጋር በተያያዘው ጋዝትሪክ አልሰር በተባለው ፅኑ ህመሟ በጤናዋ እክል ይገጥማት ነበር፡፡ ህመሙ እየባሰ በመምጣቱ ለህክምና ብዙ ገንዘብ አስወጥቷታል፡፡ ከስፖርት ጋዜጠኝነቷ  በተለያዩ ምክንያቶች በመራቋም ቤት እንኳን  ተከራይታ መኖር አልቻለችም፡፡ ስለዚህም ከነበረችበት ከኬኒያ ወደ ዱባይ ለስራና ለተሻለ ህክምና መሄድ ግድ ሆኖባታል፡፡
ይሁንና ህመሟ ከአቅሟ በላይ ሆኖ አልጋ ላይ ወድቃለች፤ ዱባይ በሚገኙ  ኢትዮጵያዊያን ፈቃደኝነት ከ12 ሰዎች ጋር አብራ እየኖረች ነው፡፡ ከጨጓራ ጋር በተያያዘው ጋዝትሪክ አልሰር በተባለው ፅኑ ህመሟ ምክንያትም ያማራትን መብላት ያቆመች ሲሆን፤ ጥቂት ፈሳሽ ብቻ በየእለቱ እየወሰደች ነው፡፡ ከህመሙ ጋር በተያያዘም ሆዷን ጨምሮ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ዕብጠት ተከስቷል፤በፍጥነት አስፈላጊውን ህክምና ካላገኘችም በሽታው ወደ ካንሰር እንደሚቀየር የህክምና ባለሙያዎች ነግረዋታል፡፡ በተለይ ከሰሞኑ ከፍተኛ ድካም እየተሰማት በመሆኑ ከአልጋ እንደማትወርድና በሳምንት ሁለት ቀን ማስታገሻ ብቻ እንደሚሰጣት የምትናገረው ብርቱካን ለሶስት አመታት ያፈነችውን ህመሟን አሁን ይፋ በማድረግ በማህበራዊ ሚዲያው ለኢትዮጵያዊያን የድረሱልኝ ጥሪ አቅርባለች በአጠቃላይ ለህክምና 6ሺህ ዶላር መጠየቋን በመጠቆም  ነው፡፡ የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ስራ አስፈፃሚ የመሰረተው አስቸኳይ ኮሚቴና የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት  በዚህ ሳምንት የጀመሩትን ገንዘብ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ ውጤት በቀጣይ ሳምንት እንደሚያሳውቁ ይጠበቃል፡፡
ብርቱካን አካሉ በዛሚ ኤፍ ኤም ሬድዮ 90.7 ላይ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በሬድዮ ቀጥታ ስርጭት የሚያስተላለፍ ሃበሻ ሊግ የተባለ ፕሮግራም መስራች ስትሆን፤ ከዚያ በፊት በስፖርት ጋዜጠኝነት በተለያዩ ጋዜጦች ላይ የአገር ውስጥ ዘገባዎችን  በማቅረብ ሰርታለች፡፡ ጋዜጠኛ ብርቱካን አካሉ በሬድዮ የቀጥታ ስርጭት የአገር ውስጥ የሊግ ውድድሮች እና የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎችን በማስተላለፍ የመጀመርያዋ ኢትዮጵያዊ የሴት ኮሜንታተር ናት ማለት ይችላል።
ብርቱካን ከሌሎች እውቅ የስፖርት ጋዜጠኞች ጋር በመስራት የኢትዮጵያን የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች በሬድዮ ስርጭት ሽፋን በመስጠት እና በማሟሟቅም ፈርቀዳጅ ናት፡፡ በተለይ በየክልሉ የሚደረጉ የሊግ ጨዋታዎችን በሬድዮ ስርጭት በቀጥታ በማስተላለፍ ለስፖርት ቤተሰቡ ባለውለተኛ ነች። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ተከትሎ የቀድሞው የእግር ኳስ ፌደሬሽን ለብርቱካን አካሉ አስተዋፅኦ እውቅና ሰጥቶ የምስክር ወረቀት ሸልሟታል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦችም በየትኛውም ስፍራ እና በማናቸውም ጊዜ የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች እንድታስተላልፍ የድጋፍ ደብዳቤ በመስጠት እና በማመስገን አበረታተዋታል፡፡ ኢትዮጵያ ከተሳተፈችበት 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ ብርቱካን አካሉ፤ ኮሜንታተርነቷ ብትራራቅም በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ኦፊሴላዊ ድረገፅ (www.cafonline.com) ላይ የኢትዮጵያን እግር ኳስ የሚመለከቱ ዘገባዎች እያቀረበች ነበር፡፡

       ብርቱካን ለማግኘት በስልክ ቁጥር +971569460828
-----------------------------------------------

Read 704 times