Sunday, 04 June 2017 00:00

“የምሁራን ገዳም” በጣና ሃይቅ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

   “አዲስ አድማስን በፍቅር የማነብ ሰው ነበርኩኝ”

     “----ብዙ ሀሳብ ነበረኝ፤ ከሀሳቦቼና እቅዶቼ መካከል ማስተርሴን ሰርቼ በትምህርት ራሴን ማሳደግ የመጀመሪያው
ነበር፡፡ እንደውም ከስራ ዓለም ወጥቼ ወደ ንግዱ የገባሁትም የተሻለ ገንዘብ ይዤ ትምህርቴን ለመቀጠል ነበር፡፡ በደሞዝ ያንን ማድረግ እንደማልችል በማሰብ ---” በ1268 በጻዲቁ አባ ሂሩት ዓምላክ የተመሰረተው ዳጋ ቅዱስ እስጢፋኖስ አንድነት ገዳም፤ በጣና ሃይቅ ላይ ከሚገኙት የወንዶች ገዳም አንዱ ነው፡፡ በዚህ ገዳም ውስጥ ባለው ሙዚየም የአጼ ዳዊት፣የአጼ ዘርዓያዕቆብ፣የአጼ ሱስኒዮስና የሌሎችም ነገስታት አጽም ሳይፈርስና ሳይበሰብስ ይገኛል፡፡ ይሄን ገዳም ሌላው ለየት የሚያደርገው “ዓለምን የናቁ” ዶክተሮች፣ፓይለቶች፣መምህራንና በተለያዩ ዘርፎች የመጀመሪያ ድግሪ ያላቸው ከ150 በላይ ምሁራን ገዳማውያን የሚገኙበት መሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ባዘጋጀው “ህያው የጥበብ ጉዞ 5 ወደ አባይ ጣና ምድር” የተሰኘ የኪነጥበብ ጉዞ፣ ከተጎበኙት ታሪካዊ ቦታዎች አንዱ ይኸው ጣና ሃይቅ ላይ የሚገኘው የዳጋ ቅዱስ እስጢፋኖስ አንድነት ገዳም ነው፡፡
   በኪነጥበብ ጉዞው የተሳተፈችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ከዓለማዊ ህይወት ይልቅ መንፈሳዊ ህይወትን መርጠው በዚሁ ገዳም የገደሙትን የ30 ዓመቱ አባ ገ/ሥላሴ በላቸውን፤ በቀደመው ዓለማዊ ህይወታቸውና
በቅርቡ በተቀላቀሉት የገዳም መንፈሳዊ ህይወታቸው ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡

       አባ ---- ትውልድዎና ዕድገትዎ የት ነው?
ትውልድና እድገቴ እዚሁ ጎጃም ውስጥ ‹‹መርጦለማሪያም›› የሚባል ቦታ ላይ ነው፡፡ እድሜዬ ለትምህርት ሲደርስ ቤተሰቦቼ ወደ ትምህርት ቤት ልከው አስተምረውኛል፤ እስከ ዩኒቨርስቲ ደርሼ ተመርቄያለሁ፡፡
የት ዩኒቨርሲቲ ነው የተማሩት? በምን ትምህርትስ ነው የተመረቁት?
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቱሪዝም ማኔጅመንት ዲግሬዬን ይዤ በስራ ዓለም ላይም ነበርኩኝ፡፡ ደሴ ወ/ሮ ስህን ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል በመምህርነት አገልግያለሁ፡፡ ተምሬ ራሴንና ቤተሰቤን አሳድጋለሁ የሚለው የታዳጊነት ህልሜ ከማገኘው ደሞዝ ጋር አልመጣጠን ሲለኝ ተቀጥሮ መስራቱን ሳልገፋበት ቀረሁ፡፡
ሥራውን አቁመው ወዴት ሄዱ ?
በወቅቱ የተወሰነ ገንዘብ ስለነበረኝ ወደ ደቡብ ክልል ሄጄ ንግድ ጀመርኩኝ፡፡ በየጠረፉ እየሄድኩ የተለያዩ ንግዶችን ሰርቻለሁ፡፡ ለምሳሌ ቱርካና ሀይቅን ታውቂው እንደሆነ፣ እዚያ ከዓሳ አስጋሪዎች ዓሳ ተረክቤ፣ ወደ ኬንያ እያሻገርኩ ጥሩ ብር መያዝ ችዬ ነበር፡፡
ከዚያስ?
ይህን ስራ በጥሩ ሁኔታ እየሰራሁ ሳለ፣ የመንፈስ ጭንቀት ያዘኝ፤ ምክንያቱም ምን እንደሆነ አላወቅኩም፡፡ ጭንቀቱ  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሄዶ ለአዕምሮ መቃወስ ዳረገኝ፡፡ መጮህ ልብስ መቅደድ ጀመርኩኝ፤ከዚያ አርባ ምንጭ ውስጥ የሚገኝ በረዳ ሚካኤል የሚባል ገዳም ውስጥ ጠበል ገባሁ፡፡ ይህ እንግዲህ 2004 ነሐሴ ወር ላይ ነው የሆነው፡፡ እዚያ ለተወሰነ ጊዜ ጠበል ስጠመቅ ቆይቼ ዳንኩኝ፡፡ ከዚያ የገዳም ህይወት ይማርከኝ ጀመር። እዚያው ለተወሰነ ጊዜ ቆየሁ፡፡ ነገር ግን ቦታው ከገዳምነት ይልቅ ወደ ጠበል ቦታነት ስለሚያመዝን፣ ለጥሞናና ሀሳብን ሰብስቦ ለመቀመጥ አይመችም፡፡ ከዚያ በኋላ ጥሩ ገዳም የሚገኘው የት ነው እያልኩ ስጠይቅ፤ ይህን ቦታ ሰው ጠቆመኝና እዚህ ገባሁ፡፡
መቼ ነው ወደዚህ ገዳም የገቡት?
እዚያ የገባሁት ዘንድሮ የሆሳዕና ዕለት ነው፡፡ ብዙም አልቆየሁም፡፡
 ከመጡ ጥቂት ጊዜ ቢሆንዎትም በዚህ ገዳም ውስጥ ብዙ ልሂቃን እንደሚገኙ ያውቃሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ እስቲ የሚያውቁትን ያህል ይንገሩኝ?
በነገራችን ላይ እዚህ ገዳም ውስጥ ከ150 በላይ ምሁራንና ትልልቅ ሰዎች እንዳሉ እሰማለሁ፡፡ ነገር ግን እርስ በእርሳችን አናወራም፡፡ በዚህ ገዳም ያሉ ትልልቅ ምሁራንና ልሂቃን ስለ ራሳቸው ማንነት፣ በዓለም እያሉ ስላላቸው የእውቀትና የኑሮ ደረጃ አይናገሩም፤ ምክንያቱ ደግሞ ወደ ውዳሴ ከንቱና ወደ ትዕቢት ይመራናል የሚል ነው፡፡ ብዙ የተማሩ የተመራመሩ  ምሁራን እንዳሉ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ከሁሉም አይነት የህብረተሰብ ክፍል ማለትም ከመንግስት ሰራተኛውም፣ በንግድ አለም አንቱ ከተባሉት ሀብታሞችም፣ ከገበሬውም፣ ከምሁራንም ይገኙበታል፡፡ ነገር ግን ሁሉም አይናገሩም፤በቃ ያንን ዓለም ንቀውት እውቀታቸውንም ሀብታቸውንም፣ በዓለማዊ ህይወት የነበራቸው ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነትም እርግፍ አድርገው ንቀውት እዚህ ገዳም ውስጥ ገብተዋል፡፡ አሁን እኔም ይህንን የምነግርሽ እዚህ ልብስ የማጥብበት ቦታ ለመድረስ ከድንጋይና ከውሃ ጋር እየታገልሽ ስለመጣሽ ፍላጎትና ጉጉትሽን አይቼ ነው እንጂ “እንዲህ ነኝ እንዲህ ነበርኩኝ” ለማለትና በዓለማዊ ህይወት የነበረኝን ማንነት ሰው እንዲያውቅልኝ ብዬ አይደለም፤ይህን ግምት ውስጥ እንድታስገቢው፡፡
ድፍረት አይሁንብኝና እርስዎ ገና የ30 ዓመት ወጣት ነዎት፤ እንደው ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ላይ እያሉ ከዚያም ወደ ስራው ዓለም ከገቡ በኋላ ትዳር ወይም የፍቅር ጓደኛ አልነበረዎትም?
ፍቅረኛ የምትባል ነገር አልነበረችኝም፤ ወደዚያ ህይወት አልገባሁም ነበር፡፡
ግን እንዴት? አንደኛ የሀይስኩልና የዩኒቨርስቲ ቆይታ ብዙዎች ለፍቅር የሚፈላለጉበት፣ ዓለማቸውን የሚቀጩበት ነው፤ በዚያ ላይ እርስዎ በጣም ወጣትና መልከ መልካም ነዎት ብዬ ነው?
እርግጥ ያነሳሽው አብዛኛው እውነት ነው፡፡ ወቅቱና እድሜዬ ለዚህ ተፅዕኖ ሊያጋልጥ የሚችል ቢሆንም እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ የሰንበት ት/ቤት ተማሪ ነበርኩኝ፤ ግቢ ጉባኤም እሳተፍ ነበር፡፡ ወደዚህ ህይወት ለመግባት አልተዘጋጀሁም ነበር፤ያንን አይነት ህይወት ሳልጀምር ነው እንግዲህ ማቄን ጨርቄን ሳልል ወደዚህ ህይወት የገባሁት፡፡
ወደዚህ ህይወት  ገዳማዊ ሆኖ ለመግባትና ለመኖር የሚጠየቅ መስፈርት አለ ?
ዋናውና ዋናው መስፈርት ዓለምን መናቅ፣ እርግፍ አድርጎ መተው ነው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ዓለማዊ ነገሮች የሉም፡፡ ለምሳሌ ትዳር መመስረትና ፍቅረኛ መያዝ አይቻልም፣ ሌሎችም በዓለም የምናከናውናቸው ጭፈራ መጠጥና መሰል ነገሮች እዚህ ቦታ ላይ አይሞከሩም፡፡ በአጠቃላይ ከነዚህ ዓለማዊ ሀሴቶች ራሱን ነጥሎ ከመጣ፣አንድ ሰው እዚህ ቦታ ለመኖር የሚከለክለው የለም፡፡
ከዚህ በፊት ትዳር የነበረው፤ ልጆች የወለደ ሰው፤ ዓለም በቃኝ ካለ፣ በዚህ ገዳም መኖር ይችላል?
ምንም የሚከለክለው ነገር የለም፡፡ ዋናው ነገር ዓለምን ከልቡ መተው ነው፡፡ ይሄ የንስሀ ቦታ ነው፡፡ ምንም እንኳን አንድ ሰው በዓለማዊ ህይወቱ በብዙ ሀጢያት ውስጥ ቢያልፍም ዓለም በቃኝ፣ ከእግዚአብሄር ጋር እኖራለሁ፣ እመለሳለሁ ካለ፣ ውሳኔውን ልናከብርለት ይገባል፡፡ ይሄ የንስሀ ቦታ ነው፤ ማንም ደግሞ ከሀጢያት የነፃ ሰው የለም፤ ቃሉም ህመምተኛ እንጂ ጤነኛ መድሃኒት እንደማያስፈልገው ይናገራል፡፡ ስለዚህ ዋናው ነገር ዓለምን መናቅ ነው፡
 እርስዎ ሁለቱንም ኖረውታልና----በአለማዊ ህይወትና በገዳም ህይወት መካከል ያለውን ልዩነት እስኪ ያብራሩልኝ?
 አለም ላይ ብዙ ሁካታና ጫጫታ አለ፡፡ በጣም ብዙ ነገር፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ደግሞ ነፍስ የምታገኘው ሰላማዊ ሀሴት አለ፡፡ ሁለቱ ምንም አይገናኙም። አሁን እዚህ ቦታ ላይ ለአንድ ሳምንት ብትቆዪ አለም ላይ ያለው ሁካታው፣ ጫጫታው፣ ውጣ ውረዱ፣ የዓለም ከንቱነት ያስጠላሻል፡፡ እና እዚሁ የመቅረት፣ በዚህ እረፍት ውስጥ ---- በዚህ ጥሞና ውስጥ የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ያጭርብሻል፡፡ ያኔ ነፍስ የሚሰማት ትልቅ የደስታ ስሜት አለ፡፡ ለምሳሌ በዓለም በቁስ አካል፣ በምግብ፣ በመጠጥና በመሰል ነገሮች የማይገኝ ደስታ እዚህ ይገኛል፡፡ ይህን ደስታ እነማን ያገኛሉ? እንደ እግዚአብሔር መንፈስ፣ ፈቃድ የሚኖሩ ብቻ ናቸው፡፡ ነገር ግን እዚህ ቦታ ሆነው ለአፍታ እንኳን ዓለምንና ውጥንቅጧን ካሳቡ ሁከት ነው፡፡ የመንፈስ ግጭትም ያመጣል፡፡ እንደ መንፈስ ፈቃድ ለሚኖሩ ሰላሙና እርካታው ተዝቆ አያልቅም! እንደውም መፅሐፉ በእንዲህ ዓይነት ገዳማት፣ በየ40 ቀኑ መንፈስ ቅዱስ ይወርዳል ይላል፡፡
በዚህ እድሜዎ አለምን ንቀው፣ ጠቅልለው ገዳም ሲገቡ ከቤተሰብ ተቃውሞና ሙግት አልገጠመዎትም?
ገዳም ከገባሁ ጀምሮ ከቤተሰብ፣ ከዘመድ ወዳጅ፣ ከጓደኛ ተገናኝቼ አላውቅም፡፡ በአሁኑ ወቅት ቤተሰቤ እኔ የትና በምን ሁኔታ ላይ እንዳለሁ አያውቁም፡፡ እኔም ቤተሰቤ ይኑር ይሙት የማውቀውና የምሰማው ነገር የለም፡፡ ማወቅም መስማትም አልፈልግም፡፡ በአጠቃላይ ምንም ግንኙነት የለኝም፡፡
የገዳም ህይወት የቤተሰብ ግንኙነት መቋረጥን ይጠይቃል ወይስ የግል ምርጫዎ ነው?
ገዳሙ ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም ስልክ መደዋወል፣ ስለ ቤተሰብ ሁኔታ መስማት፣ ከዓለም ለሚመጡ መልዕክቶችና ወሬዎች ጆሮን መስጠትን የዛን ሰው የገዳም ህይወትና ጥሞና ይረብሻል ስለሚባል፣እንደነዚህ ዓይነት ግንኙነቶች አይፈቀዱም፡፡ ቤተሰብም እዚህ ቦታ ልኑር ልሙት፤ ልሰደድ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ እኔም ስልክም የለኝም፤ ሬዲዮና ቴሌቪዥን አልሰማም አላይም፤ በአሁን ሰዓት ዓለም ላይ ምን እየተደረገ እንደሆነ፣ ምን ዓይነት ጉዳዮች እየተከናወኑ እንዳሉ የማውቀው ነገር የለም፡፡ የእኔ ግንኙነት እዚህ ገዳም ከሚገኙ አንዳንድ አባቶች ጋር ነው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ጓደኝነትም አይፈቀድም፡፡ ከአንዱ ወደ አንዱ አካባቢ መዞር አይቻልም፡፡ እዚህ ጓደኛ ሊሆኑ የሚችሉት መንፈሳዊ መፅሐፍት ብቻ ናቸው፡፡ በገዳሙ ቤተ መፃህፍት አለ፤መንፈሳዊና የታሪክ መፅሐፍትን አነባለሁ፡፡
እዚህ ገዳም ውስጥ “የዘጉ አባቶች” አሉ ሲባል እሰማለሁ፡፡ “የዘጉ” ማለት ምን ማለት ነው?
“የዘጉ” ማለት ገዳሙ ውስጥ የተሰጣቸው መኖሪያ ውስጥ ሆነው በራቸውን ይዘጋሉ፤ከሰው አይገናኙም፤ አይነጋገሩም፤ ትንሽ ትንሽ ምግብ ያሉበት ድረስ ይሄድላቸዋል፤ ያችን ይቀምሳሉ እንጂ ከሰው ጋር ግንባር ለግንባር አይተያዩም፤ለሽንት እንኳን ሲወጡ ሰው በሌለበት ሰዓት ነው፡፡ ምንም ዓይነት ነገር መስማት አይፈልጉም፤ ግንኙነታቸው ከአምላክ ጋር ብቻ ነው፡፡ ሁሌ ይፆማሉ፤ እነዚህ የበቁ አባቶች ናቸው፤ በዚህ ገዳም ብቻ ሳይሆን እንደነዚህ ባሉ ገዳማት “የዘጉ አባቶች? አሉ፡፡
ገዳሙ የሚተዳደረው በምንድን ነው? ለምሳሌ የቀለብ ወጪ በምን ትሸፍናላችሁ? የምትሰሩት ሥራ አለ?
ከእኔ ብጀምር እኔ በሽመና ስራ ገዳሙን በማገዝ የበኩሌን እወጣለሁ፡፡ እዚህ ገዳሙ በር ላይ ለሽያጭ የሚቀርቡ ፎጣዎችና እስካርፎች በእኛው የሚሰሩ ናቸው፡፡ እኔ ጎበዝ ሸማኔ ነኝ፡፡ ከዚህ በተረፈ የገዳሙ ዋና የገቢ ምንጩ እርሻ ነው፤ ከዚያ የጫካ ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ ለምሳሌ፡- ማንጎ፣ ሙዝና ሌሎችም ይገኛሉ፡፡ በዚህ ይተዳደራል፡፡ በግብርናውም በአትክልተኝነቱም፣ በፅዳቱም----- ሁሉም በሚችለው ገዳሙን ያገለግል፡፡
እንዴት ነው ቦታውን ቱሪስቶች ይጎበኙታል?
 ይጎበኛል ግን ብዙ አይደለም፡፡ ጣና ሀይቅ ላይ ካሉ ገዳማት ውስጥ በጣም የሚጎበኘው ክብራ ገብርኤል ነው፡፡ እዚህ ግን አልፎ አልፎ ነው፤በበቂ ሁኔታ እየተጎበኘ ነው ብዬ አላምንም፡፡
በገዳም ህይወት ውስጥ ያለው የአመጋገብ ስርዓት ምን ይመስላል?
በነገራችን ላይ ገዳም ውስጥ ሁሌም ፆም ነው፡፡ አሁን ጊዜው በአለ ሀምሳ ስለሆነ እንጂ ሁሌም ፆም ነው፡፡ ፆም ተፁሞ ከመበላቱ በፊት ፀሎተ ማዕድ የሚባል አለ፤ ዘጠኝ ሰዓት ላይ አባቶች ፀሎተ ማዕድ አዳራሽ ይገቡና 150ውም ዳዊት ይደገማል፡፡ ከዚያ በኋላ መልከ- ማሪያም፣ መልከ ኢየሱስና ሳልዕከ ተደግሞ 11፡00 ላይ ፀሎተ ማዕድ የተደገመበት ህብስትና ወይን ይቀርባል፡፡ ያ ከተቀመሰ በኋላ ሁሉም እንደየ አቅሙ ዳቤ (መኮሪተ) ይመገባል ማለት ነው፡፡
ስጋ ነክ  ምግቦች ወደ ገዳም አይገቡም ማለት ነው?
በዓመት ሁለት ጊዜ ይታረዳል፤ለትንሳኤና ለገና ስጋ ይበላል፡፡ ከዚያ ውጭ ዳቤ ብቻ ነው የምንመገበው፡፡
በገዳም ህይወት ከመማረክዎ በፊት ለህይወትዎ ምን ያቅዱና የት መድረስ ይፈልጉ ነበር?
ብዙ ሀሳብ ነበረኝ፤ ከሀሳቦቼና እቅዶቼ መካከል ማስተርሴን ሰርቼ በትምህርት ራሴን ማሳደግ የመጀመሪያው ነበር፡፡ እንደውም ከስራ ዓለም ወጥቼ ወደ ንግዱ የገባሁትም የተሻለ ገንዘብ ይዤ ትምህርቴን ለመቀጠል ነበር፡፡ በደሞዝ ያንን ማድረግ እንደማልችል በማሰብ ማለት ነው፡፡ ከትምህርቱ ቀጥሎ እንደ ሰው ደረጃ በደረጃ የሚታሰቡ ነገሮች ይኖራሉ፤ ነገር ግን በመንፈስ መታወክ ሰበብ እኔን ወደዚህ ቦታ ለማምጣት እግዚአብሔር ስራ ሰርቷል፤ የተመረጥኩ ሰው ነኝ፤ በዚህ ደስተኛ ነኝ፡፡
በአሁኑ ወቅት የጥሞና ጊዜ አለዎት ብዬ አስባለሁ፤የተማሩም ነዎትና መፅሐፍትን ከማንበብ ባሻገር የገዳምን ህይወት የመፃፍ ሀሳብ የለዎትም?
እዚህ ከመምጣቴ በፊት አንድ መፅሀፍ ፅፌ አሳትሜ ነበር፡፡
ምን አይነት መፅሀፍ?
አሁን ገበያ ላይ ያለ ይመስለኛል፤ 3 ሺህ ኮፒ መታተሙን አስታውሳለሁ፡፡
የመፅሀፉ ርዕስ ምንድን ነው?
መንፈሳዊ ይዘት ያለው ነው፡፡ ርዕሱ  ‹‹እናስተውል›› ይሰኛል፤ 247 ገፅ ያለው ነው፡፡ ከሞረዳ ሚካኤል እንደወጣሁ ጉራጌ ዞን ቡኢ አካባቢ የሚገኘው ምድረ ከብድ አቦ ቤተክርስቲያን ገዳም ጥቂት ጊዜ ቆይቼ ነበር፡፡ በዚያ ቆይታዬ ነው የፃፍኩት፡፡ መፅሀፉ በአጠቃላይ ዓለምና ህዝቧ ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ፣ መንፈሳዊው አለም ያለውን ትሩፋትና መሰል ሁኔታዎችን የሚያመላክትና በዓለም ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሱ የመጡ ቀውሶችንና መፍትሄዎቻቸውን የሚጠቁም ነው፡፡ በቀጣይም እንደ ፈጣሪ ፈቃድ እፅፋለሁ፤የበፊቱንም የፃፍኩት በየጊዜው ዲያሬዬ ላይ ሳጠራቅም የኖርኳቸውን ነው፡፡
 እርስዎ እዚህ ሆነው “ዓለምን ትቼ መጥቻለሁ” ብሎ ወደ ገዳም ከገባ በኋላ ወደ ዓለማዊ ህይወት የተመለሰ ሰው አጋጥምዎታል?
አዎ አጋጥሞኛል፤ ብዙ ጊዜ በስሜት ተገፋፍተው ይመጡና ልባቸው በደንብ ስለማይወስን ኑሮው ይከብዳቸውና ይመለሳሉ፡፡ በተደጋጋሚ አጋጥሞኛል፤ እዚህ ቦታ ላይ ከልቡ ለወሰነና ላመነ ነው ደስታና እርካታ የሚኖረው፡፡
አባ፤ ፍላጎቴን ተረድተው ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ በመሆንዎ አመሰግናለሁ---  
እሺ እኔም አመሰግናለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የ”አዲስ አድማስ” አንባቢና ተከታታይ ነበርኩኝ፤ ርዕሰ አንቀፁን፣ የኤፍሬም እንዳለን እንጨዋወት፣ ኪነ-ጥበባዊ ይዘቶቹን-----ሁሉ በፍቅር የማነብ ሰው ነበርኩኝ፡፡ አሁንም በሆነ አጋጣሚ ይሄ ጋዜጣ እኔው ጋ ተመልሶ ሲመጣ ገርሞኝ ስለነበር፣ ይሄንን ሳልነገርሽ ብትሄጂ ቅር እንዳይለኝ ብዬ ነው፡፡ መልካም ጉዞ እመኝልሻለሁ፡፡

Read 5017 times