Print this page
Sunday, 04 June 2017 00:00

‘ልጃችሁን ለልጃችን…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

   “---- እናማ… ‘ልጃችሁን ለልጃችን’ የሚል ሽምግልና ከመሄዳችሁ በፊት ቀደም ሲል ከሴቶች ጋር የነበረውን
ግንኙነት በተመለከተ መረጃው በጽሁፍ ይሰጠን በሉ፡፡ እሱ በወለደው እናንተ መሳቀቅ አለባችሁ እንዴ! ----“
                 
     እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰዎቹ ለጓደኛቸው እሷዬዋን ለመጠየቅ ሽምግልና ይሄዳሉ፡፡ የ‘እጩ ሙሽራዋ’ ሰፈር ሲደርሱም የሆኑ ሴትዮ መንገድ ላይ ጠብቀዋቸው ቤት ይዘዋቸው ይገባሉ፡፡ እንደገቡም “ተቀመጡ…” ይባላሉ፡፡ እነሱም “መጀመሪያ የመጣንበትን ጉዳይ ሳንናገር አንቀመጥም” ይላሉ፡፡
“እሺ፣ ጉዳያችሁ ምንድነው?” (‘ለወጉ ያህል’ የሚባለው ይሄ መሆን አለበት፡፡ አሀ… “እሁድ ጧት ልጃችንን በጋብቻ ለመጠየቅ ሽማግሌዎች ይመጣሉ” ተብሎ የሶፋ ዳንቴል በተገዛ በዓመት ከመንፈቁ ፍትግ ተደርጎ ታጥቦ፣ በቁርስ ሰዓት ለምሳና ለእራት በቅቶ የሚተርፍ ምግብ ተዘጋጅቶ “ጉዳያችሁ ምንድነው?” ብሎ ቲራቲር ‘ወግ አይቅርብን’ ነዋ!”
“ልጃችሁን ለልጃችን ለመጠየቅ ነው የመጣነው?”
“የትኛዋን ልጅ?” ብለው ይጠይቃሉ፣ የእሷ ወገኖች፡፡ ሽማግሌዎቹም ‘ስሟን’ ይናገራሉ፡፡ ይሄኔ ነው እንግዲህ ‘ሙቃዲስ’ የምትባለው ሴተዮ ብትሰማው አንድ ሌሊት ሙሉ የምታወራበት ነገር የተፈጠረው፡፡ ክፍሉ ውስጥ ድንጋጤ ይሆናል። ‘ልጃችሁን ስጡን’ ስለተባለ ድንጋጤ አለ እንዴ!  ጓዳ ያ ሁሉ ክትፎና ትሪፓ በሳህን የተደረደረው፣ ልጃቸውን ‘በደስታ ለመስጠት’ አይደለም እንዴ! ችግሩ ምን መሰላችሁ…የተጠራው ስም፡፡ በተለይም አንደኛው ሰውዬ ጣሊያን መውጣቱን ገና ያልሰሙ አርበኛ ነገር አደረጋቸው፡፡
“ስሟን ማን አላችሁ?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ሽምግልና የመጡትም የጠሩትን ስም ይደግማሉ፡፡ ቤቱ ቀውጢ ሆነና አረፈላችሁ፡፡
“ይቺን ይወዳል! እኔ ቆሜ ነው ሞቼ እሷን ለጋብቻ የምትጠይቁት!” ምናምን ሲሉ ከተላኩት አንዱ ወጣ ይልና ወደ ጓደኛው ደውሎ የሆነውን ይነግረዋል፡፡
“እስቲ ድገምልኝ፣ ማንን ብላችሁ ነው የጠየቃችሁት?”
የጠሩትን ስም ይነግረዋል፡፡ ምን አለፋችሁ ጓደኝዬው ትንፋሽ እስከሚያጥረው በሳቅ ፈነዳላችሁ፡፡ ምን ቢል ጥሩ ነው… “የጠራችሁት እኮ መንገድ ያሳዩዋችሁ ሴትዮን ስም ነው!” ብሎት ቁጭ፡፡ ሴትዮዋ ደግሞ ለእኛ ለተቆጡት ሰው አራት ነው ምናምን የወለዱላቸው ናቸው፡፡
ይቅርታ ተጠይቆ ነገሩ መልኩን ያዘ አሉ፡
መጀመሪያ ነገር ሽማግሌ የተባሉ በደንብ እያዳመጡ እንጂ----የምን ጫፍ ይዞ ክትፎው ሳይደርስ እንድረስበት ነው፡፡
የምር ግን… አለ አይደል… የዘንድሮ ትልቅ ችግራችን ነገሮችን ሳናጣራ፣ አውቀን የበቃን አይነት መሆናችን ነው፡፡ ጫፍ ይያዝና… አለ አይደል… መንገድ መሪዋን የአራት ልጆች እናት ለጋብቻ የምትጠየቅ አጎጠጎጤ ምናምን ማድረግ ይመጣል፡፡ እግረ መንገዴን…ሴትዮዋ ስማቸው ሲጠራ አንገታቸውን ደፍተው እንደ ልጅነታቸው ሲሽኮረመሙ ነበር ተብሏል፡፡
ደግሞላችሁ…ከጥቂት ወራት በፊት የሆኑ ሰዎች ‘ልጃችሁን ለልጃችን’ ሊሉ ወደ ልጅት ቤት ይሄዳሉ። ቦታውን በምልክት ያገኙና የግቢውን በር አልፈው ይገባሉ፡፡ ይሄኔ ሙሽርነት ልትጠየቅ ከነበረችው ልጅ ቤት አንድ ሰውዬ ተጣድፈው ይወጣሉ፡ ሰላምታ የለ፣ “ከየት ነው የመጣችሁት?” የለ…ብቻ ምን ቢሏቸው ጥሩ ነው…
“የመጣችሁበትን እናውቃለን፣ የዛሬ አሥራ አምስት ቀን ተመለሱ፣” አሉና ቤት ገብተው በሩን ቀረቀሩት አሉ፡፡ ምን አይነት ዘመድ ናቸው! ደግሞላችሁ…የጋብቻ ጥያቄ ይዘው የመጡ ሽማግሌዎችን ቤተሰቦቿ ከበር ያባረሩ ልጂት…አለ አይደል… እሷ በጫጉላው ምሽት ባሏን ከመኝታ ቤት በር ላለማባረሯ ዋስትናው ምንድነው!  ቂ…ቂ…ቂ… የምር ልጃቸውን አሳልፈው ለመስጠት ባይፈልጉ እንኳን ስንት መንገድ እያለ፣ ነጭ የሰላም ባንዲራ እያውለበለቡ የመጡ ሽማግሌዎችን እንዲህ ማዋረድ ምን ይሉታል! (ለነገሩ ‘ከበር ላይ መመለስ’ ለእኛ አዲስ አይደለም፡፡ በጣም ስለለመድነውም ከመብሸቅ ይልቅ… “በር ድረስ መድረሳችን ራሱ ትልቅ ነገር ነው...” ብለን ለራሳችን ‘ኤ’ እንሰጣለን፡፡)
እናማላችሁ… ሰርጉ ላይ ምን ተብሎ እንደሚዘፈንም ሊያስቸግር ይችላል፡፡ አለ አይደል…በፈቃዷ የመጣችውን… “ይዟት ይዟት በረረ…” ከማለት ይልቅ “ነጥቆ አወጣት ከጓዳ… ምናምን የሚል የሰርግ ዘፈን ሊፈጠር ይችላል፡፡
እኔ የምለው ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ሰርግ ላይ…  “የታማንብሽ ወጣቷ እንዴት ነሽ!” የሚለው ግጥም…እንዴት ነው እስከዛሬ ‘ጥልቅ ማስተካከያ’ ያልተደረገበት! እንዴ… ልጇት እየተሞሸረች እያለ “ታምተንብሽ ነበር፣ አሁን አገባሽ ወይ፣” አይነት ዘፈን የጠብ ይመስላላ! “የታማንብሽ…” ተባለ እንጂ፣ “ሙሽራው የታማብሽ…” አልተባለም! አስቸጋሪ እኮ ነው… ሙሽራው የሚያውቀው ‘የሰርግ ዘፈን’… “አይ አም ኤ ቨርጂን” የሚለውን ብቻ ከሆነ (ቂ…ቂ...ቂ…) “ውሽሞችሽ ጭራሽ ሠርግሽ ላይ መጥተው የታማንብሽ ይበሉ! እንዴት ብትንቁኝ ነው!” ምናምን ብሎ የሆነ ሰበር ዜና ይፈጥር ነበር። በእርግጥ “የታማንብሽ” አይበሉ እንጂ… ውሽሞች ውሽሚቶች ሰርግ ላይ እንደሚሄዱ የታወቀ ነው፡፡
ስሙኝማ… የድሮ ገርል ፍሬንድ ምናምን ስታገባ ሠርጓ ላይ መሄድ እኮ እንዴት አይነት ‘ሪያሊቲ ሾው’ ይወጣዋል መሰላችሁ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ያው “ለሰርጓ ጠራችኝ፣ ሄድኩኝ አልቀረሁም…” ምናምን ማለት ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… “…ሽቶው ውሀ ነው” የሚባለው ነገርስ! ማለትማ፣ ነገርዬው ‘ሚዜው ቺስታ ነው፣ አንድ ቦምቦሊኖ ለሁለት የሚያዝ ነው’ አይነት ነው፡፡ ግን ጊዜው ተለውጧሏ! አሀ… ዘንድሮ ሽቶው ውሀ የሚሆነው ሚዜው ‘ድሀ’ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ሽቶው ‘ፎርጅድ’ ስለሆነ ሊሆን ይችላላ! እናማ…
ኸረ ሚዜው ቡፋ ነው
ሽቶው ፎርጅድ ነው
ምናምን ተብሎ ይስተካከልልንማ፡፡
እናላችሁ….ፍቺው በዛ፣ ዓመት እንኳን ሳይደፈኑ ዓይንህ/ሽ ለአፈር መባባል በዛ በሚባልበት ዘመን የሰርግ ዘፈን ግጥሞች ‘መዋቅራዊ ማሻሻያ’ ያስፈልጋቸዋል፡፡ (ምን ላድርግ… “…ያለበት ሁኔታ ነው ያለው…” ከሚለው ሀረግ እኩል “መዋቅራዊ ማስተካከያ ይደረጋል” ምናምን የሚባል ነገር ስሰማ ስለከረመኩ ነው!) እናማ…መፋታት እንዲህ ከባሰበት…አለ አይደል…
አይዞሽ ሙሽሪት አይበልሽ ከፋ
ሁሉም ያገባል በየወረፋ
የሚለው ግጥም ይለወጥልን፡፡ በምትኩ…
አይዞሽ ሙሽሪት አይበልሽ ከፋ
ይህ ካልተስማማሽ ሌላም አይጠፋ
ይባልልንማ፡፡ (‘ተገጠመና’ ቁጭ!)
ደግሞላችሁ…ሌላ ጊዜ እንዲሁ ልጃችሁን ለልጃችን ሊሉ ይሄዳሉ፡፡ ታዲያላችሁ… ከልጅት ቤተሰቦች አንዱ ምን ይላል… “እሱ ሰውዬ አግብቶ የለም እንዴ!” ሽምግልና የመጡት ግራ ይጋባሉ፡፡ እነሱ የሚያውቁት አንዴ አገንፍቶ ፍሪጅ የከተተውን ማካሮኒ ለዓለም ሬከርድ በሚያበቃ ድግምግሞሽ እያሞቀ የሚበላ ‘ሰርቲፋይድ ወንድላጤ’ መሆኑን ነው፡፡ ከመሀላቸው አንዱ ግን ለካስ የሚያውቀው ነገር አለ፡፡
“አዎ፣ አግብቶ ነበር፡፡”
ሽምግልና የሄዱት መደንገጥ፡፡
“ደግሞም ልጅ አለው፣ አይደል!”
ልጅ! ጭራሽ ልጅ! ይሄኛው እንኳን ዝም ብሎ አሉባልታ መሆን አለበት፡፡
“አዎ የዘጠኝ ዓመት ልጅ አለው፣” ተባለና አረፈላችሁ፡፡ እናማ… ‘ልጃችሁን ለልጃችን’ የሚል ሽምግልና ከመሄዳችሁ በፊት ቀደም ሲል ከሴቶች ጋር የነበረውን ግንኙነት በተመለከተ መረጃው በጽሁፍ ይሰጠን በሉ፡፡ እሱ በወለደው እናንተ መሳቀቅ አለባችሁ እንዴ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5263 times