Saturday, 27 May 2017 14:07

በ46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  • ወደፊት የሚያድግባቸው ሁኔታዎች ተስተውለዋል
                 • የስፖንሰርሺፕ ገቢ የሚጠናከርበት ተስፋ ተፈጥሯል
                 • ከክለቦች መከላከያና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፤ ከክልሎች ኦሮሚያና ደቡብ ተምሳሌት ይሆናሉ
                 • የዓለም ሻምፒዮና እጩና ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት የሚያመች ሆኖ ይቀጥላል፡፡
                 • በሜዳ ላይ ስፖርቶች መነቃቃቶች ተፈጥረዋል፤ መቀጠል አለባቸው
                 • 10 አዳዲስ የኢትዮጵያ ክብረወሰኖች ተመዝገበዋል

     ባለፈው ሰሞን በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደው 46ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ስኬታማ ነበር፡፡  በታዋቂ አትሌቶች የተደራጀው ፌደሬሽን የተገበረው የላቀ የውድድር  አመራር፤ ታዋቂ አትሌቶች ሻምፒዮናን በመታደም፤ ለአሸናፊዎች ሽልማት በማበርከት እና ለተተኪ አትሌቶች ሞራል በመስጠት የነበራቸው ተሳትፎ፤ ለሻምፒዮናው አዲስ አብይ ስፖንሰር በማግኘት የሚያስገኘው ገቢው መጠናከሩ፤ ከሩጫ ውጭ ባሉ ሌሎች የሜዳ ስፖርቶች የተፈጠሩ መነቃቃቶች እና በርካታ አዳዲስ ክብረወሰኖች መመዝገባቸውን እንደማስረጃ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ በቀጣይ ዓመታት ሻምፒዮናው በከፍተኛ የተመልካች ብዛት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚካሄዱ ትልልቅ ውድድሮች ሚኒማ ለማሟላት በሚቻልበት ስታድዬም፤ በተጨማሪ ስፖንሰሮች ተጠናክሮ ልዩ እድገት በማሳየት እንደሚቀጥል ተስፋ ሰጭ ሁኔታዎች ተስተውለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ስለሺ ብስራት ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ በሻምፒዮናው ክለቦች፤ ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች በተሟላ ስልጠና እና ዝግጅት በስፖንሰርሺፕ ተጠናክረው የፉክክር ደረጃቸውን እንዲያሳድጉ በሚያስችል ስትራቴጂ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ለዚህም ፌደሬሽኑ በስፖርት የዩኒቨርስቲ ምሁራን፤ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች የተሰባሰቡበት ልዩ የሱፕርቪዥን ቡድን በማቋቋም በመላው አገሪቱ በመዘዋወር ጥናት አድርጎ በሪፖርቱ መሰረት በመፍትሄ ርምጃዎች ለመስራት ወስኗል፡፡
የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ስለሺ በዝርዝር እንደገለፀው ዘንድሮ በአትሌቲክስ ሻምፒዮናው የዋንጫ ተሸላሚዎች የተለዩት የሜዳልያ ስብስብ እና እስከ 8 ለሚያገኟቸው ደረጃዎች  ነጥብ በመስጠት ነው፡፡ ስለሆነም ለወርቅ ሜዳልያ 9 ነጥብ፤ ለብር ሜዳልያ 7 ነጥብ ለነሐስ ሜዳልያ 6 ነጥብ፤ ለአራተኛ 5 ነጥብ፤ ለአምስተኛ 4 ነጥብ፤ ለስድስተኛ 3 ነጥብ፤ ለሰባተኛ 2 ነጥብ እንዲሁም ለስምንተኛ 1 ነጥብ በመስጠት በየፆታ መደቡ እና በአጠቃላይ ውጤት የዋንጫ ተሸላሚዎቹ ተለይተዋል፡፡ በድምር ውጤት በሁለቱም ፆታዎች አጠቃላይ አሸናፊ ሆኖ ዋንጫ የተሸለመው ብቁ እና የተሟላ ተሳትፎ ያደረገው የመከላከያ አትሌቲክስ ክለብ ሲሆን 371 ነጥብ በማግኘት ነው፡፡ ኦሮሚያ ክልል በ331 ነጥብ በሁለተኛ ደረጃ ፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ181 ነጥብ በሶስተኛ ደረጃ ጨርሰዋል፡፡  በወንዶች ምድብ አጠቃላይ አሸናፊ ሆኖ ዋንጫ ሊወስድ የበቃው አሁንም የመከላከያ አትሌቲክስ ክለብ በ220 ነጥብ ሲሆን ኦሮሚያ ክልል በ174 እንዲሁም ሲዳማ ቡና በ85 ነጥብ በሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ጨርሰዋል፡፡ በሴቶች ምድብ ደግሞ ኦሮሚያ ክልል 157 ነጥብ በመሰብሰብ የዋንጫ ተሸላሚ ለመሆን ሲበቃ መከላከያ በ151 ነጥብ እንዲሁም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ184 ነጥብ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ደረጃ ጨርሰዋል፡፡
በሻምፒዮናው ከተሳተፉ 30 ክለቦች መካከል  የመከላከያ  እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  አትሌቲክስ ክለቦች  እንደነባር ተሳታፊነታቸው ለሻምፒዮና ድምቀት ፈጥረዋል፡፡  እነ ሲዳማ ቡና በአዲስ ተሳታፊነት ያመዘገቡት ውጤት የሚደነቅ ነው፡፡ ከ11 ክልሎችና ሁለት የከተማ  ኦሮሚያ እና ደቡብ ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ ሻምፒዮናውን ፉክክር የበዛበት ማድረጋቸው ተምሳሌት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ በአጠቃላይ ከላይ የተዘረዘሩት ክለቦች እና ክልሎች በየቡድኖቻቸው ለሻምፒዮናው በቂና የተሟላ ዝግጅት በማድረግ፤ ለአትሌቶች በቂ ትጥቅ በማሟላት፤ በበቂ ጊዜ ስልጠና እና  ልምምድ ሰርቶ በሻምፒዮናው ላይ በመሳተፍ ውጤታማ ሊሆኑ ከመቻላቸውም በላይ የላቀ ተፎካካሪነታቸውን አሳይተዋል፡፡
በአትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከ30 በላይ ክለቦች እንዲሁም 11 ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተካፈሉት ከ1000 በላይ ስፖርተኞችን በማሳተፍ ሲሆን በተለይ በክለቦችና በማሰልጠኛ ማዕከላት ለሚገኙ ታዳጊ እና ወጣት አትሌቶች የውድድር ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡  ከሩጫ ውድድሮች ባሻገር በሜዳ ላይ በሚካሄዱ የተለያዩ ስፖርቶች በአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን ሊወክሉ የሚችሉ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት እንደሚቻል በገሃድ ተረጋግጧል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በሁለቱም ፆታዎች ከ800 ሜትር ጀምሮ እስከ 10 ሺህ ሜትር አሸናፊ የሆኑ አትሌቶች፤ ከ4 ወራት በኋላ ለንደን ላይ በሚካሄደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለመካተት በእጩነት ተመርጠዋል። በተለይ የረጅም ርቀት ሩጫ ላይ የሚወዳደሩት አትሌቶች አስፈላጊውን ሚኒማ ማሟላት በሚችሉበት ብቃት ላይ እንደሚገኙ ሊያስመሰክሩ የቻሉበት ነው፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ሻምፒዮኖች በቀጣይ  በኔዘርላንድ ሄንጌሎ ላይ በሚዘጋጀው ልዩ ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ሄንግሎ ላይ አሸናፊ የሆኑና ሚኒማውን የሚያሟሉ አትሌቶች በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሀገራቸውን ወክለው ይወዳደራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡
የኢትዮጵያ አትሌቲከስ ሻምፒዮናው  በበርካታ የሜዳ ላይ ስፖርቶች ከመቼው ጊዜ በላቀ ሁኔታ ተስፋ ሰጭ ሁኔታዎች ታይተውበታል፡፡ በተለይ በሻምፒዮናው የመጨረሻ ሁለት ቀናት ፍጻሜያቸውን ባገኙት የዝላይ ስፖርቶች የተመዘገቡት ውጤቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳታፊ ሊያደርግ ከሚችለው ሚኒማ ጋር የተጠጋጉ ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል  በውርወራ ስፖርቶችም በተመሳሳይ ጥሩ ውጤት መታየቱ የሚጠቀስ ሲሆን  በሌሎች የሜዳ ተግባር ውድድሮች ብሄራዊ ክብረወሰኖችም መሻሻላቸው ሌላው ስኬት ነው፡፡ ሻምፒዮናው ላይ ከዚህ ቀደም በልኬት ላይ  የነበረው  ችግር በአዲስ መልክ በተደራጀ እንቅስቃሴ በመከናወኑና በቴክኖሎጂ መታገዙ ሻምፒዮናውን በአንድ ደረጃ አሳድጎታል።
46ኛውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ልዩ ካደረጉት ሁኔታዎች ዋንኛው በ10 የተለያዩ ስፖርቶች አዳዲስ የኢትዮጵያ ክብረ ወሰኖች መመዝገባቸው ነው፡፡ በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች ፤ በሴቶች የ1 ሺህ 500 ሜትር፣ በመሰናክል፣ በስሉዝ ዝላይ፣ በጦር ውርወራና በ20 ኪሎ ሜትር እርምጃ ውድድሮች የተመዘገቡት ይገኙበታል፡፡ በሻምፒዮናው ታሪክ 10 ክብረወሰኖች መሰበራቸውም ከረጅም ጊዜ በኋላ ሊሳካ የቻለ ነው፡፡ ከ46ኛው በፊት በ43 ኛው እና በ44 ኛው ሻምፒዮና በ 7 ውድድሮች ክብረ ወሰን መሻሻሉ ሲታወስ፤ በ2008 በተካሄደው 45ኛው ሻምፕዮና 6 ክብረ ወሰን ተሻሽለው ነበር፡፡ በዘንድሮው ሻምፒዮና 10 ክብረ ወሰኖችን ሊያሻሽሉ የበቁት ስፖርተኞች ከሜዳልያ እና የገንዘብ ሽልማታቸው ባሻገር ከፌደሬሽኑ፤ ከኃይሌ ገብረስላሴ እና ከአራራት ሆቴል በድምሩ እያንዳንዳቸው 22ሺ ብር አግኝተዋል፡፡ በተለይ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት  ኃይሌ አዲስ ክብረ ወሰን ላስመዘገቡ አትሌቶች በግሉ ለእያንዳዳቸው 10 ሺህ ብር ሽልማት ማበርከቱ ያልተጠበቀ ነበር፡፡  ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዲስ ክብረወሰን ላስመዘገቡት  10 ሺ ብር እንዲሁም አራራት ሆቴል ተጨማሪ 2 ሺ ብር  ሸልመዋል።
በ46ኛው አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተመዘገቡት 10 ክብረ ወሰኖች ከዚህ በታች የቀረቡት ናቸው፡፡
በወንዶች ስሉስ ዝላይ  - አትሌት አዲር ጉር- ከመከላከያ -   15.79 ሜትር
በሴቶች ስሉስ ዝላይ - አትሌት አርአያት ዲቦ -ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  12.94 ሜትር
በወንዶች ምርኩዝ ዝላይ-  አትሌት መዝገቡ ቢራራ -ከመከላከያ - 4.40 ሜትር
በሴቶች ከፍታ ዝላይ - አትሌት አርአያት ዲቦ - ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ - 1.74 ሜትር
በሴቶች 400 ሜ መሠናክል-  አትሌት ደሜ አቡ- ከኦሮሚያ ክልል -58.74 ሰከንዶች
በሴቶች 20 ኪ.ሜ እርምጃ - አትሌት የኋልዬ በለጠው- ከፌዴራል ማረሚያ -1፡32፡39.7
በሴቶች 1500ሜ -አትሌት ፋንቱ ወርቁ -ከኦሮሚያ ክልል - 4:07.80
በሴቶች 4X400 ሜትር - የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡድን - 3፡37.23
በሴቶች ጦር ውርወራ -አትሌት ሹራ ኡቱራ- ከኦሮሚያ ክልል - 45.76 ሜትር
በሴቶች 5000 ሜ  - አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ- ከፌዴራል ማረሚያ - 15:12.16
የሻምፒዮናው ኮከብ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ አትሌት አርያት ዲቦ በ3 የወርቅ ሜዳልያዎችና በሁለት አዳዲስ ክብረወሰኖች  ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ  የሻምፒዮናው ኮከብ ለመሆን በቅታለች፡፡ አትሌት አርያት   በስሉዝ፣ በከፍታና በርዝመት ዝላዮች ሶስት ወርቆችን ማምጣቷ ብቻ ሳይሆን በስሉዝና በከፍታ ዝላዮች ላይ ሁለት አዲስ ክብረወሰኖቿ አስመዝግባለች፡፡
ሁለት ወርቅ ያመጡ አትሌቶች
ኤፍሬም መኮንን- ከኢትዮ ኤሌትሪክ -በወንዶች 4X400ሜ እና 400ሜ
በድሩ መሀመድ- ከመከላከያ-በወንዶች100 ሜ እና 200 ሜ
አዲር ጉር -ከመከላከያ -በወንዶች ርዝመት ዝላይ እና ስሉስ ዝላይ
ሕይወት ወንዴ  -ከኢት/ንግድ ባንክ - በሴቶች 400 ሜትር እና 4X400ሜ.
ማህሌት ሙሉጌታ -ኢት/ንግድ ባንክ- በሴቶች  800 ሜትር 4X400ሜ.
ገበያነሽ ገዴቻ- ከ መከላከያ-በሴቶች 100 ሜ መሠናክል እና 4X100ሜ.

Read 818 times