Sunday, 28 May 2017 00:00

ቅዱስ ጊዮርጊስ ለ3 ነጥብ መትጋት አለበት

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

በ2017 ቶታል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ  ሊግ  ኢትዮጵያን በመወከል እየተሳተፈ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከምድቡ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለማለፍ በተለይ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች  3 ነጥብ ለማግኘት መትጋት እንዳለበት አስተያየቶች ተሰጡ፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊጉ የምድብ 3 ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ባለፈው ማክሰኞ እና ሐሙስ ተደርገው ቅዱስ ጊዮርጊስ  በአዲስ አበባ ስታድዬም  የቱኒዚያውን ኤስፔራንስ በማስተናገድ  ቅዱስ  0ለ0 በሆነ ውጤት ሲለያይ፤ በኪንሻሳ ማርታዬርስ ስታድዬም የደቡብ አፍሪካውን ሜመሎዲ ሰንዳውንስ ያስተናገደው ኤኤስ ቪታ ክለብ 3ለ1 ተሸንፏል፡፡
በአፍሪካ ክለቦች ሻፒዮንስ ሊግ የምድብ ፉክክር በመግባት አዲስ ታሪክ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሁለቱ ዙር ጨዋታዎች 2 ነጥብ ማግኘቱ አበረታች ቢሆንም በተለይ በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በጥንቃቄ እና በትኩረት በማድረግ ተገቢውን 3 ነጥብ መሰብሰብ እንደሚኖርበት ተገልጿል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በአዲስ አበባ ስታድዬም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኤስፔራንስ የተገናኙበት ጨዋታ ላይ የመጀመሪያው አጋማሽ 20 ደቂቃዎች በሁለቱም ክለቦች በኩል የተቀዛቀዘ ፉክክር የታየበት ነበር፡፡  የቅዱስ ጊዮርጊሱ  ግብ ጠባቂ  ሮበርት ኦዶንካራ  ባጋጠመው ጉዳት 15ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ መውጣቱ ብቸኛው  ክስተት ነበር፡፡  ተቀይሮ የገባው  ዘሪሁን ታደለ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ 38ኛው ደቂቃ ላይ  ሙከራ ተደርጎበት በጥሩ ሁኔታ ማዳን ችሏል ፡፡ በኤስፔራንስ በኩል ተጨዋቾቹ አየሩ ስለከበዳቸው ብዙ ጫና የፈጠሩ እንቅስቃሴዎች ያልነበሩ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩልም ከፍተኛ ጥንቃቄ ከማብዛት፤ እና ግልፅ የሆነ የጨዋታ እቅድ ካለመተግበር ጋር በተያያዘ  በሜዳቸው እንደመጫወታቸው የሚያረኩ አልነበረም፡፡  በሁለተኛው ግማሽ በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል ተጋጣሚያቸውን አስጨንቆ በመጫወት ረገድ የተሻሉ ነበሩ፡፡ ለዚህም በ49ኛው ደቂቃ ላይ በሳልሃዲን ሰኢድ እና በ55ተኛ እና በ90ኛው ደቂቃ ላይ በአብዱልከሪም ኒኪማ የተደረጉ ሙከራዎች  ይጠቀሳሉ፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ  ዋና አሰልጣኝ ኔዘርላንዳዊው ማርቲን ኖይ በህመም ምክንያት ቡድኑን  አለመምራታቸው በክለቡ የጨዋታ እቅድ እና ታክቲክ ላይ ተፅእኖ ሳያሳድር አልቀረም፡፡ የማርቲን ኖይ ምክትሎች ዘሪሁን ሸንገታና ፋሲል ተካልኝ  ከጨዋታው ነጥብ ይዘው ለመውጣት በሚያደርጉት ጥረት ከተጨዋች ቅያሪ አንፃር ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ በሁለተኛው ግማሽ ሌላው ተጠቃሽ ክስተት በኤስፔራንስ በኩል ሲሆን ጋሌኒ ቻላሊ የተባለው ተጨዋች በቅዱስ ጊዮርጊሱ ፕሪንስ ላይ በሰራው ጥፋት 68ኛ ደቂቃ ላይ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሊሰናበት መቻሉ ነበር፡፡  ኤስፔራንሶች በምድባቸው ሁለት ዙር ጨዋታዎች ሁለት ቀይ ካርዶች ማስመዝገባቸው ነው፡፡ ከ30 ደቂቃዎች በላይ በ10 ተጫዋች የተጫወቱት ኤስፔራንሶች የአዲስ አበባ የየር ሁኔታ ከባድ ተፅእኖ ቢፈጥርባቸውም በመልሶ ማጥቃት ውጤቱን ለመቀየር  ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡  በተለይ 80ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ቢያስቆጥሩም  ኳስ በእጅ በመነካቷ ጎሏን ሽረዋታል።
የኤስፔራንስ ምክትል አሰልጣኝ ከጨዋታ በኋላ በሰጡት አስተያየት‹‹ በጣም ከባድ ጨዋታ ነበር፡፡ ከ30 በላይ ደቂቃዎችን በ10 ተጨዋቾች መጫወታችን ፈትኖናል፡፡ ምናልባትም ቡድናችን ባለፉት 3 ሳምንታት ያለፈባቸው ተደራራቢ ጨዋታዎች ጫና ሳይፈጥሩ አልቀረም፡፡ በማንኛውም ጨዋታ ዋና ግባችን 3 ነጥብ ማግኘት ነው፡፡ ካልቻልን ቢያንስ በአቻ ውጤት 1 ነጥብ ማግኘታችን ያስደስታል›› ብለዋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ  በበኩሉ ከጨዋታ በኋላ በሰጠው አስተያየት “የጨዋታው እንቅስቃሴ በመጀመሪያው 45 መልካም አልነበረም፡፡ ከእረፍት ስንመለስ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል የቁጥር ብልጫውን አልተጠቀምንም ነገር ግን በ90 ደቂቃ ውስጥ በልጆቻችን እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ ፤ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል”።  ሲል ተናግሯል፡፡
ከምድብ 3 የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች በኋላ የቱኒዚያው  ኤስፔራንስ በ4 ነጥብ በ3 የግብ ክፍያ በመሪነቱ ሲቀጥል፤   የአምና ሻምፒዮናው የደቡብ አፍሪካ ሜመሎዲ ሰንዳንስ በ4 ነጥብና በሁለት የግብ ክፍያ በሁለተኛ ደረጃ ይከተላል፡፡  ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን ሲይዝ የዲ.ኮንጎው ኤኤስ ቪታ ክለብ ያለምንም ነጥብ በ5 የግብ እዳ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ ይገኛል።

Read 1548 times