Sunday, 28 May 2017 00:00

ባላጂ ማኑፋክቸሪንግ 9 ዓይነት ሞተርሳይክሎች በአገር ውስጥ ገጣጠመ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

  በሕንድ ባለሀብቶች ከሦስት ዓመት በፊት በ50 ሚሊዮን ብር ካፒታል ተመሥርቶ በዓመቱ በ2015 ሥራ የጀመረው ባላጂ ማኑፋክቸሪንግ (ቢኤምፒ) በሁለት ዓመት ውስጥ የኤሌክትሪክና የትራፊክ ፖሊሶች ሞተር ሳይክሎችን ጨምሮ ዘጠኝ ዓይነት የተለያዩ ሞተር ሳይክሎች በአገር ውስጥ መገጣጠሙን አስታወቀ፡፡
በአገር ውስጥ የገጣጠማቸውን ሞተርሳይክሎች ባለፈው ረቡዕ በሞዛይክ ሆቴል ባስተዋወቀበት ወቅት የኩባንያው ዳይሬክተር ሚ/ር ቪካስ አጋርዎል፣ የትራፊክና የኤሌክትሪክን ጨምሮ ለገጠር (ለእርሻ) የሚሆን፣ ለጭቃ፣ ለዳገትና ለኮረኮንች መንገድ የማይገበር፣ ከመሬት ከፍ ያለ ሞተርሳይክል መገጣጠማቸውን ተናግረዋል፡፡
ሞተርሳይክሎቹ፣ በአሁኑ ወቅት በገበያው ውስጥ ከሚገኙ ተመሳሳይ ምርቶች በጉልበትና በፍጥነት ይበልጣሉ፣ በዋጋ ደግሞ በእጥፍ ያንሳሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፤ እነዚህ በአገር ውስጥ የሚገጣጠሙት ለአብነት የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክሎች ፣ ዲጂታል ማሳያ ያላቸው፣ የአየርም ሆነ የድምጽ ብክለት የማያስከትሉ፣ አውቶማቲክ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ያላቸው፣ መለዋወጫቸው በቀላሉ የሚገኝ፣ በ100 ብር ነዳጅ 5000 ኪሜ ርቀት ለማካለል የሚያስችሉ፣ በጣም ፈጣንና ቀልጣፋ ናቸው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል በኤሌክትሪክ ሞተርሳይክሎች ምርት ጀምረው ከገበያው በጣም ጥሩና አጥጋቢ ምላሽ ስላገኙ ለከተማና ገጠር ተገልጋዮች፣ በነዳጅ የሚሠሩ ሞተርሳይክሎች ማምረት እንደጀመሩ የጠቀሱት ሚ/ር ቪካስ አጋራዎል፤ የሌሎች አገራት ዘመናዊ ሞተርሳይክሎች የሌላቸውን እጅግ ዘመናዊ የቅርብ ጊዜ ምርቶች በመጠቀም ለኢትዮጵያ ገበያ በማቅረባችን ኩራት ይሰማኛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አሁን በገበያ ላይ ያሉት ሞተርሳይክሎች በጋዝ ልቀታቸው ዩሮ-1 (በአውሮፓ የሚፈቀድ የጋዝ ልቀት) ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የእኛ ሞተር ሳይክሎች ዩሮ-3 ስለሆኑ ምንም በካይ ጋዝ ወደማያመነጭ ሁኔታ እየተጠጋን ነው ብለዋል፡፡
ለትራፊክ ፖሊሶች የተሰራው ባለ 250 ሲሲ ልዩ ሞተርሳይክል የትራፊክ ሞተሮች ያላቸውን ሁሉንም መገልገያዎች (ብልጭ ድርግም የሚል መብራት፣ የጩኸት ድምፅ፣ የተለያዩ መብራቶች፣ የድምፅ መነጋገሪያና ሌሎችም አስፈላጊ ነገሮች ያለው ሲሆን ከፍተኛ ፍጥነቱ በሰዓት 140 ኪ.ሜ፣ የነዳጅ መያዣው አቅም 15 ሊትርና የነዳጅ ፍጆታው በአንድ ሊትር 27 ኪ.ሜ እንደሚጓዝ ታውቋል፡፡
ሞተር ሳይክሎቹ የተለያየ አቅም ያላቸው ሲሆን፣ 250 ሲሲ የሆነው የውድድር (ሬስ) ሞተር ሳይክል ከፍተኛ ፍጥነት በሰዓት 140 ኪ.ሜ፣ የነዳጅ መያዥው አቅም 20 ሊትር፣ የነዳጅ ፍጆታው በአንድ ሊትር 28 ኪ.ሜ ይጓዛል፡፡ 180 ሲሲ የፈረስ ጉልበት ያለው ሶኒክ የተባለው ሞተር ሳይክል፣ ከፍተኛ ፍጥነት በሰዓት 100 ኪ.ሜ፣ የነዳጅ ፍጆታው በአንድ ሊትር በሰዓት 40 ኪ.ሜ፣ ለገበሬዎች ወይም ለገጠር ሰዎች ከመሬት ከፍ ብሎ የተሠራ ሬንጀር ባለ 200 ሲ.ሲ፣ ከፍተኛ ፍጥነት 100 ኪ.ሜ ሆኖ፣ በአንድ ሊትር በሰዓት 40 ኪ.ሜ ይጓዛል፡፡
ከከተማ ወጣ ብሎ ወይም ለገጠር አካባቢዎች ለትራንስፖርት የሚያገለግለው ሽንጠ ረዥሙ ባለ 150 ሲሲ  ሽያን፣ ከፍተኛ ፍጥነቱ በሰዓት 90 ኪ.ሜ ሲሆን የነዳጅ ፍጆታው ደግሞ በአንድ ሊትር በሰዓት 40 ኪሜ ይጓዛል፡፡
ቢኤምፒ ምርቶቹን ባስተዋወቀበት ወቅት በክብር እንግድነት የተገኙት የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ደለለኝ፣ ሥራ ጀምሮ ሁለት ዓመት ሳይሞላው የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክሎችን አምርቶ ያቀረበው ቢኤምፒ፤ ዛሬ ደግሞ ለከተማውም ሆነ ለገጠሩ ኅብረተሰብ (የገጠሩ ሕዝብ ከፍተኛ የሞተር ሳይክል ተጠቃሚ ሆኗል) ለሁሉም በሚስማማ መልኩ፣ የተለያዩ ሞተርሳይክሎችን በማቅረቡ በጣም ደስ ብሎኛል ብለዋል፡፡

Read 2292 times