Sunday, 28 May 2017 00:00

ዓለም አቀፍ የጥበቃና ደህንነት ኤክስፖና ባዛር ሊካሄድ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

   ከአውሮፓ፣ ከአፍሪካ፣ ከአሜሪካ፣ ከመካከለኛውና ከሩቅ ምሥራቅ በአጠቃላይ ከ23 አገሮች የተውጣጡ የደህንነትና የጥበቃ (ሴፍቲ ኤንድ ሴኩሪቲ) ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር ከሰኔ 18-20 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ቤታሆን አድቨርታይዚንግና ኢቨንት ኦርጋናይዚንግ አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ማንከልክሎት ባለፈው ማክሰኞ በሰፋዬር አዲስ ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ኤክስፖና ባዛሩ ለ3 ቀን ከሰኔ 18-20 በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ እንደሚካሄድ ጠቅሰው በየዓመቱ የሚቀጥል ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በደህንነትና ጥበቃ ዙሪያ በቴክኖሎጂ የላቀና የዳበረ ትልቅ ስምና እውቅና ያላቸው ድርጅቶች እንደሚሳተፉ የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፣ የኤክስፖው ዓላማ፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናና የተባበሩት መንግሥታት በርካታ ኤጀንሲዎች መቀመጫ ስለሆነች፣ ዓለም በጥበቃና ደህንነት ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ደረጃ ለማሳየትና ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመጀመሪያው የዘንድሮ ኤክስፖ ላይ ለመሳተፍ 25 አገሮች አረጋግጠዋል ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ 3,500 ጎብኚዎች፣ 5,132 ከፍተኛ እውቅና ያላቸው ተሳታፊዎችና 23 የሚዲያ ኩባንያዎች ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ጥበቃና ደህንነት ለሁሉም ክፍሎች የግድ አስፈላጊ ስለሆነ ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ የተውጣጡ በተለይም በባንክና ኢንሹራንስ (ፋይናንስ) አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ፣ አከፋፋዮች፣ ኤምባሲዎች፣ ዘይትና ጋዝ አዳዮች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ህግ አስፈጻሚዎች፣ መከላከያ ሰራዊት፣ ሲስትም ዘርጊያዎች፣ ኃይልና አገልግሎት ሰጪዎች፣ የግሉ ዘርፍ፣ ዲዛይነሮች፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው፣ የሆቴሎችና ቱሪዝም ድርጅቶች፣ የግል ደህንነት ድርጅቶች፣ አማካሪዎች፣ አርኪተክቶች፣ ፋሲሊቲ ማናጀሮች፣ ፋይናንሶች፣ የጤናና ደህንነት፣ የግንኙነት ባለሙያዎች፣ … በኤክስፖና ባዛሩ ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡
ዓላማችን በአገሪቷ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሀብቶች፣ ኢንቨስትመንታቸውን ለመጠበቅ የሚረዱ የደህንነት መሳሪያዎች ለማስተዋወቅ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በማስተዋወቁ ሂደት በወቅታዊ ቴክኖሎጂ፣ የመንግሥት ተደራሽነትንና የሲቪል ማኅበረሰቡን በዚህ ውስጥ ማካተት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ከኤክስፖው ጎን ለጎን በሚቀርቡ ፎረሞችና ኮንፈረንሶች ላይ በተለይ በባንክና ኢንሹራንስ በጥበቃና ደህንነት መሰረተ ልማት፣ … እንዲሁም የአንድ ለአንድ ውይይትና የልምድ ልውውጥ እንደሚካሄድ ዋና ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡ 

Read 1266 times