Sunday, 28 May 2017 00:00

የደራሲያን ማህበር የጥበብ ጉዞ ዛሬ ይጠናቀቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ- ከጎንደር
Rate this item
(2 votes)

  የደራሲ አቤ ጉበኛና የአለቃ ገ/ሀና አገሮች ተጎብኝተዋል
                    
       ከተመሰረተ 57 ዓመታትን ያስቆጠረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ለ5ኛ ጊዜ ያዘጋጀው “ህያው የጥበብ ጉዞ 5 ወደ አባይ ጣና ምድር የኪነ ጥበብ ጉዞ” ዛሬ ደብረታቦርና አካባቢዋን በመጎብኘት ይጠናቀቃል፡፡ ባለፈው ሐሙስ ግንቦት 9፣ ከ70 በላይ አንጋፋ ደራሲያንን፣ ጋዜጠኞችንና የፊልምና የሙዚቃ ባለሙያዎችን አካቶ፣ ከአዲስ አበባ የተጀመረው የኪነ ጥበብ ጉዞ፣ አባይ ማዶ ከወንዙ 100 ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ምንጭ ላይ የ”ፍቅር እስከ መቃብሯ” ዋና ገፀባህሪ ሰብለ ወንጌል፣አባ አለም ለምኔ ሆና ያደረችበት ቦታ ላይ የኪነ ጥበቡ የበኩር ክንዋኔ ተጀምሯል፡፡
በዚህ ቦታ ላይ ሰብለ ወንጌል መንኩሳ፣ በቦታው በማደር፣ከአውሬና ከጨለማ ጋር ስትታገል የነበረችበት የመፅሐፉ ታሪክ፤ በደራሲና ባለቅኔ አበረ አዳሙ የተነበበ ሲሆን ደራሲ፣ ዲዛይነርና ተዋናይት ንግስት ጎንፋ፣ በ30 ደቂቃ ዝግጅት ውስጥ አባ አለም ለምኔን ገፀ ባህሪ ወክላ በመተወን አድናቆትን አትርፋለች፡፡ በዚህ ቦታ ላይ የምስራቅ ጎጃም ዞን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ውድአለም አልማውና የባህል ቡድኑ ከደጀን ከተማ ድረስ በመምጣት ለተጓዦች ደማቅ አቀባበል አድርገዋል፡፡ በመቀጠል በደብረ ማርቆስ ከተማ የ2 ቀን ቆይታ የተደረገ ሲሆን በምስራቅ ጎጃም ዞን ስናን ወረዳ የሚገኘው ከ4100 ሜትር በላይ ከፍታ ያለውና የ273 ምንጮችና የ59 ወንዞች መነሻ የሆነው፣ ከ174 በላይ እጽዋት የሚገኙበትና ውርጫማው ጮቄ ተራራ፤ ጥቅጥቁ አባጃሜ ደንና የክቡር ዶ/ር አዲስ አለማየሁ ሀውልት እንዲሁም ሌሎችም ቦታዎች የተጎበኙ ሲሆን በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲና በጎዛመን ሆቴል ሁለት ትልልቅ የሥነ ጽሁፍ ምሽቶች ተካሂደዋል፡፡
በ3ኛው ቀን ወደ ባህርዳር ጉዞ የተጀመረ ሲሆን ባህርዳር ከመደረሱ በፊት ከምእራብ ጎጃን ዞን አንዱና የአባይ መፍለቂያ ወደ ሆነው ግሻባይ ሰከላ ወረዳ በመጓዝ፣ ምንጩ ተጎብኝቶ፣ በሰከላ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጊሸን አባይ ከተማ ለተጓዦች የምሳ ግብዣ ከተደረገ በኋላ በተለይ ‹‹አልወለድም›› በሚል መጽሐፉ የሚታወቀው ደራሴ አቤ ጉበኛ የትውልድ ስፍራ ተጉዘን፣ የደቡብ አቸፈር ወረዳ ዋና ከተማ ከሆነችው ዱር ቤቴ  በስተሰሜን 30 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ የሚገኘው ይስማላ ጊዮርጊስ፣ ለመታሰቢያው በስሙ የተቋቋመውን፣ አቤ ጉበኛ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትና ይስማላ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለው መቃብሩና ሀውልቱ ተጎብኝቷል፡፡
እሁድ ግንቦት 13 ቀን 2009፣ ከባህርዳር ወደ ደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ፣ ወረታ በመጓዝ ፈላስፋውና የፍትሀ ነገስት ዳኛ የነበሩት የአለቃ ገብረሃና ሀገር የተጎበኘ ሲሆን የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አቀባበል በማድረግ፣ ስለ አለቃ ገብረሀና ታሪኮች ገለፃ ሰጥቷል፡፡ በዘመናቸው ይለብሱት የነበረው ባለ ቀይ ጥለቱ (ጥንድ ድርብ) የተሰኘው ልብሳቸውም ለእይታ ቀርቧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአለቃ ገብረሃና 4ኛ የልጅ ልጅ የሆኑት ቄስ ገደቤ በስፍራው በመገኘት እነዚህ ትልልቅ ልሂቃን አለቃ ገብረሃናን ለማስታወስና የትውልድ ቦታውን ለመጎብኘት በመምጣታቸው፣ አለቃ ገብረሃናን በህይወት ያገኟቸው ያህል እንደተሰማቸው ገልፀው፤ አለቃ ገብረሃና ከቅዱስ ያሬድ በስተቀር የሚበልጣቸው ሊቅ እንዳልነበር ለተጓዦች ተናግረዋል፡፡ ቄስ ገደቤ አክለውም፤ እኚህ ሊቅ በወቅቱ ፍትሃ ነገስትን በመተርጎምና ዳኝነት በመስጠት ትልቅ ስራ ይሰሩ እንደነበር አስታውሰው፤ በተፈጥሮ ፀጋ አዋቂነትን የታደሉ እንጂ ፊደል ያስቆጠራቸው እንዳልነበረ፣ በቤተመንግስት ውስጥ ግን ተወዳጅ እንደነበሩ ገልፀዋል፡፡ አለቃ ገብረሃና በተለይም ‹‹ተክሌ አቋቋም›› የተባለውን ዝማሜ ጣና ላይ ከበቀለው ቄጤማ ውዝዋዜ ጋር በማጣመር እንደፈጠሩት የተነገረ ሲሆን ይህ የ”ተክሌ አቋቋም” የተባለው ፈጠራቸው በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ምርምር እየተሰራበት እንደመሆነም ተገልጧል፡፡
በጉዞው 5ኛ ቀን ግንቦት 13፣ ጠዋት፣ ንጋት በተባለችውና ከ550 በላይ ሰዎችን ማጓጓዝ በምትችለው ጀልባ፤ ጣናን አቋርጠን ወደ ማሀል ዘጌ የተጓዝን ሲሆን በ14ኛው ክፍለ ዘመን በፃዲቁ በትረማርያም የተመሰረተውንና በ2002 ዓ.ም ባልታወቀ ምክንያት ተቃጥሎ በመገንባት ላይ ያለውን መህል ዘጌ ጊዮርጊስን፣ ውራ ኪዳነምህረትንና ከ5 ዓመት በፊት ግንባታው ተጀምሮ ከ2 አመት በፊት በዘመናዊ መንገድ ስራ የጀመረውን፣ አጠገቡ የሚገኘውን ሙዚየም ጎብኝተን ስናበቃ፣ ከ1፡20 የጣና ላይ ጉዞ በኋላ ወደ ባህርዳር በመመለስ መጠነኛ እረፍትና የምሳ ቆይታ አደረግን፡፡ ወደ 10፡00 ገደማ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ባህር ዳር ቅርንጫፍ፣ በሙሉ አለም አዳራሽ የሥነ-ጹሁፍ ምሽት ያዘጋጀ ሲሆን በዚህ ምሽት ላይ የግጥም፣ቅኔና መሰል ዝግጅቶች ተከናውነዋል፡፡
ማክሰኞ ግንቦት 14፣ ጠዋት፣  ንጋት በተባለችው ጀልባ፣ ጣና ላይ ከሚገኙ ገዳማት ሰፊ ቦታን ወደሚሸፍነውና ከባህርዳር 72 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደሚገኘው የዳጋ ቅዱስ እስጢፋኖስ አንድነት ገዳም በመጓዝ፣ ገዳሙ የተጎበኘ ሲሆን ጉብኝቱ ለወንዶች ብቻ  የተፈቀደ ነበር፡፡ ይህ ገዳም በ1298 በአጼ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግስት፣ በጻዲቁ አቡሀ ሂሩተ አምላክ መመስረቱም ተገልጽዋል፡፡ ከ150 በላይ የህክምና ዶክተሮች፣ ፕሮፌሰሮች፣ በተለያየ የትምህርት ዓይነት የድግሪ ምሩቅ የሆኑ (ከእነዚህ መካከል ከ30 ዓመቱ ወጣት መነኩሴ አባ ገ/ስላሴ ጋር ያደረግነውን ቆይታ ሳምንት እናቀርባለን) ምሁራን፤ ዓለምን ንቀው በምንኩስና የሚገኙበት እንደሆነ ተገልጾልናል፡፡ በገዳሙ የአጼ ዘርዓያዕቆብ፣ የአፄ ዳዊትና የሌሎችም ነገስታት አጽም ሳይፈርስና ሳይበሰብስ እንደሚገኝ ያስረዱን የገዳም አባቶች፤ በርካታ ተዓምራት እንደተሰሩበትም ገልጸውልናል፡፡
በንጋት ጀልባ የመልስ ጉዞ በማድረግም፣ ወደ 46 ኪ.ሜ ርቀት ገደማ ተጉዘን፣ ጣናን በማቋረጥ ጎርጎራ ገብተናል፡፡ በጉዟችን ወቅት ያልተለመደ ነው የተባለ ከፍተኛ ማዕበል ተነስቶ የነበረ ሲሆን ካፒቴን ተስፋዬ፣ ማዕበሉ የተነሳበትን አቅጣጫ በመቀየር ጀልባዋ ዥዋዥዌ እየተጫወተችም ቢሆን በሰላም ገብተናል፡፡ ጎርጎራ ወደብ በደርግ ዘመነ መንግስት፤ በጀልባ ቅርጽ የተሰራ ሎጅ የሚገኝ ሲሆን በዚህ ሎጅ ውስጥ የደርግ መሪ ኮ/ል መንግስቱ ኃይለ ማርያማ ከትልልቅ ባለስልጣናት ጋር ጥሩ የእረፍት ጊዜ ያሳልፉበት እንደነበርና በአሁኑ ሰዓት ያለቅጥ ጉስቁልና ውስጥ እንደሚገኝ፣ የመብራት አገልግሎትም እንደሌለው ተነግሮናል፡፡ በዚህ ምሽት ዶ/ር የማነ ኮከቤ በተባሉ ባለሃብት፣ በኢትዮጵያ ባህል በተሰራ ባህላዊ ሎጅ፣ ጥቅጥቅ ባለ ጫካ ውስጥ “ሽፍታ ጥብስ” የተባለ የብረት ምጣድ ጥብስ ከጠላ ጋር እራት ተጋብዘናል፡፡
በነጋታው ጥዋት በአካባቢው የምትገኘው ጥንታዊቷ ደብረሲና ማርያም የተጎበኘች ሲሆን ቤተክርስቲያኗ በአንድ ወቅት ጣሪያዋ ቆርቆሮ ቢለብስም በአንድ ቀን ተገንጥሎ በማደሩ ወደ ቀደመ የሳር ክዳኗ ተመልሳለች። ይህች ቤተክርስቲያን “ጤዛ” ፊልም ላይ ሴትዮዋ በእንብርክክ ሄደው ስለት የሚያስገቡባት እንደሆነች በጉብኝታችን ወቅት ተገልጾልናል፡፡ ረቡዕ እለት በጉዞው ሰባተኛ ቀን፣ ከጎርጎራ 62 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው ጥንታዊ ጎንደር ከተማ ተጉዘን፣ እጅግ ውብ በሆነው ጎሃ ሆቴል ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ቁልቋል እያየን፣የማህበሩ አባል በሆነው አርክቴክት ሽፈራው በነጻ የተሰራው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ህንጻ ዲዛይን ይፋ ሲደረግ፣ ተጓዡ በሙሉ ደስታ ፈንድቆ ነበር። በህንጻው ይዘትና በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ ቢሻሻሉ ለተባሉ ሃሳቦች ምላሽ ተሰጥቶ የእለቱ ፕሮግራም ከምሽቱ 3፡00 ላይ ተጠናቋል፡፡ በጉዞው ስምንተኛ ቀን ላይ፣ ከትላንት በስቲያ፣ ደብረ ብረሃን ስላሴና በ16ኛው ክ/ዘመን የተሰራው የአጼ ፋሲል ግንብ የተጎበኙ ሲሆን ከሰዓት በኋላ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ለደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን መታሰቢያ የሆነ የሥነ-ጹሁፍ ዝግጅት ተካሂዷል፡፡ በዚህ የሥነ-ጹሁፍ ዝግጅት ላይ ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ፣ ሰርጸ ፍሬ ስብሃትና ሌሎችም በታዋቂው ደራሲ ሥራዎች ዙርያ ጽሁፎችን አቅርበዋል፡፡
አርብ ጠዋት ወደ ባህርዳር የተመለስን ሲሆን ከሰዓት በኋላ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ጹሁፍ ዝግጅትና በመጪው የኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ እጣ ፈንታ ላይ  በተካሄደ ውይይትም ፕሬዚዳንት ዶ/ር ባይሌ ዳምጤን ጨምሮ በርካታ የዩንቨርሲቲው አባላት ሳትፈዋል፡፡
ቅዳሜ ጠዋት ጉዞ ወደ ደብረ ታቦርና አካባቢዋ ተደርጎ የኪነ-ጥበብ ጉዞው የሚጠናቀቅ ሲሆን እሁድ ግንቦት 20፣ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ተጓዦች በጉዞው በጣም ደስተኛ እንደሆኑና እጅግ ታሪካዊና ለትውልድ ትልቅ አሻራ ትቶ ለማለፍ፣ በተለይ ለደራሲያን እድል እንደሚከፍት ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡ ጉዞው አስዳሳች፣ መሰልቸት የሌለበት እንደሆነም በመግለጽ፤ በተጓዦች መካከል የመግባባት ስሜት እንዲፈጠር የማህበሩ ፕሬዝዳንት የዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ በሳል አመራር፣ አባታዊ ፍቅርና ትዕግስት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል ሲሉ የጉዞው አባላት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በዚህ ጉዞ ላይ ደራሲና ሃያሲ አስፋው ዳምጤ፣ ደራሲ ሃያሲና ጋዜጠኛ አለማየሁ ገላጋይ፣ ኃይለመለኮት መዋዕል፣ ሲሳይ ንጉሱ፣ የዝና ወርቁ፣ ሜሪ ጃፋር፣ ውድአላት ገዳሙ፣ የቀድሞው የማህበሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው በለጠ፣ የሙዚቃው ባለሙያው ሰርጸ ፍሬስብሃት፣ የፊልም ባለሙያ ደሳለኝ ኃይሉና ሌሎችም አንጋፋና ወጣት ደራሲያንና ገጣሚያን የተሳተፉ ሲሆን አዝማሪ ዋኘው አሸናፊ፤ጉዞውን በማሲንቆ በማጀብና ተጓዡን በማዝናናት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ የየዞኑና የየወረዳው አስተዳደሮችና የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተለያዩ ኃላፊዎችም ከፍተኛ አቀባበልና መስተንግዶ ሲያደርጉልን ሰንብተዋል፡፡ ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

Read 1809 times