Sunday, 28 May 2017 00:00

በረመዳን ዋዜማ

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(4 votes)


       በፋርስ ግዛት በትረ መንግስዋን ጨብጣ ትገዛ የነበረችው ንግስት ሴሬና ያጋጠማት ችግር ለወትሮው ነገስታት የሚጋፈጡት አይነት ችግር አልነበረም፡፡ ህዝቡ በነቂስ ተቃውሞውን ያሰማው ንግስትዋ ባል ስላልነበራት ብቻ ነበር፡፡
ባል በሌላት አንመራም፣ ያለው ህዝቡ ብቻ አልነበረም፡፡ መኳንንቱና መሣፍንቱም ጭምር ነበር። ንግስትም ግን ለዚህ ተቃውሞ ጆሮ አልነበራትም፡፡ ልቧም በአላህ ህግ የፀና ነበርና የሱን ህግ ለማይጠብቅ ወንድ እጅዋን ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረችም፡፡ ይህ የፀና አቋሟም ከህዝቡ፣ ከመኳንንቱና ከመሣፍንቱ ጋር ሆድና ጀርባ ቢያደርጋትም ከሰባ በላይ አገሮችን እያስገበረች እንድትገዛ ያደረግዋት ጀነራሎችም ከሷ ጋር ስለነበሩ ተቃውሞው ከሃሜትና ከማጉረምረም ሊያልፍ አልቻለም፡፡
አሁን ግን ነገሩ እየከፋ መጣ፡፡ ትንሽ ቆይቶም ታማኝ ጄነራሎችዋም ሳይቀሩ በጉዳዩ ላይ የሐሳብ ልዩነት ማምጣት ጀመሩ፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ነበር የሶርያው ንጉስ ተወካይ ንግስቲቱን እጅ ለመንሳት መንግስትም ድረስ የመጣው፡፡ በእብነበረድ ተሽቆጥቁጦ በተሰራው የንግስቷ ቤተመንግስት ውስጥ ባለው አዳራሽ ከአምስት ሺህ ህዝብ በላይ ተሰብስቧል፡፡ መኳንንቱና መሳፍንቱ በአዳራሹ ፊት ለፊት ባለው ረድፍ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ የጦር ጄኔራሎች በሌላ ረድፍ፡፡ የአገሪቱ ታላላቅ ሰዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ከኋላ ረድፍ ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ በየእንግዶቹ ፊት ለፊት ባለው ጠረጴዛ ላይ የዶሮና የበግ አሮስቶ፣ትኩስ ፍራፍሬዎች፣ ጭማቂዎች ተደርድረዋል፡፡
ንግስት ሴሬና ከፍ ብሎ በተሰራው መድረክ ላይ ካለው የወርቅ ዙፋን ላይ የወርቅ ዘውዷንና የወርቅ በትርዋን ይዛ ተቀምጣለች፡፡ ደንገጡሮችዋ በዙሪያዋ ተቀምጠዋል፡፡ ህዝቡ ሁሉ እየበላ እየጠጣ ነበር፡፡ ድንገት የእልፍኝ አስከልካዩ ምልክት ሲያሳይ ከወገባቸው በላይ እራቁታቸውን የሆኑት ነጋሪት ጎሳሚዎች፤ አዳራሹን በሐይለኛ የታቡር ድምፅ አደበላለቁት፡፡ ወዲያው ግዙፍ የአዳራሹ በር፣ ሲከፈት ህዝቡ በሙሉ ፀጥ እረጭ ብሎ የመጣውን እንግዳ ለማየት ማንጋጠጥ ጀመረ፡፡
አንድ በሜዳልያዎች የተሽቆጠቆጠ፣ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሰና ጎራዴውን በጎኑ ያንጠለጠለ፣በጥንቃቄ የተላጨ ሪዝ ያለው መኮንን ወደ አዳራሹ ገባ፡፡ አዳራሹን አቋርጦ በቀጥታ ወደ ዙፋኑ አመራና እንደደረሰ ለጥ ብሎ እጅ ነሳ፡፡ ንግስትም እጅዋን ከፍ አድርጋ በማንሳት አፀፋውን መለሰች፡፡፡
‹‹ከገናናው የሶርያው ንጉስ አርኪያስሲ፤ እንደ ፀሐይ ለሚያበሩ ግርማዊነትዎ፤ የተላከውን ገፀ በረከት እንዲቀበሉኝ በታላቅ ትህትና እጠይቃለሁ›› አለና፤ እንደገና ለጥ ብሎ እጅ ነሳ፡፡ ንግስትዋ እጅዋን በማንሳት ፈቃደኝነትዋን ገለፀች፡፡ ሳጥን የተሸከሙ ሰዎች ወደ አዳራሹ ገቡ፡፡ ሃያ ሳጥኖችን የተሸከሙ ሃያ ሰዎች ነበሩ፡፡ ሳጥኖቹን ከንግስትዋ ፊት ለፊት አስቀመጡና ከፈተቱት፡፡ ህዝቡ በሙሉ በአድናቆት አጉረመረመ፡፡ ሃያዎቹ ሳጥኖች በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች የተሞሉ ነበሩ፡፡
መልእክተኛው እንደገና እጁን አነሳ፡፡ አስር ሳጥን የተሸከሙ አስር ሰዎች፤ ወደ አዳራሹ ገቡ። ሰይጣኖቹን ከንግስትዋ ፊት ሲከፍቱት ህዝቡ እንደገና በአድናቆት አጉረመረመ፡፡ ከርቤና እጣን የሞሉ ሳጥኖች፡፡ መልዕክተኛው ፈገግ ብሎ እንደገና እጁን አነሳ፡፡ ህዝቡ አርስ በራሱ ማንሾካሾክ ጀመረ። ሰላሳ ትልልቅ የዝሆን ጥርስ የያዙ ሰላሳ ሰዎች ወደ አዳራሹ ገቡ፡፡ የሁሉም ሰው ፊት ላይ አድናቆትና መገረም፣ ታየ፤ ንግስትዋ ቀኝ እጅዋን ስታነሳ አዳራሹ መርፌ እንኳን ቢወድቅ እስኪሰማ ድረስ ፀጥ እረጭ አለ፡፡
‹‹ንጉስ አርክያስስ ምንድነው የሚፈልገው?›› ጠየቀች ንግስትዋ፡፡
‹‹ገናናው ንጉስ አርክያሲስ፣ በፀሐይ አምላክ ስም ይሄን ገፀ በረከት እያበረከተ የክብርነትዎን እጅ ለጋብቻ ይጠይቃል” አለና፤ መልዕክተኛው አሁንም ጎንበስ ብሎ እጅ ነሳ፡፡ ንግስትዋ እጅዋን ስታነሳ እንደገና ፀጥታ፡፡
“እኔ የማምነው በአንድ አላህ ሲሆን በፀሐይ አምላክ ለሚያምነው ንጉስ ሚስት ልሆን አልችልም። ገፀ በረከቱ ተቀባይነት ስለሌለው ከምስጋና ጋር ለንጉሡ መልስ›› አለች ንግስትዋ፡፡ የአዳራሹ ፀጥታ ደፈረሰ፡፡ ህዝቡ በቁጭትና በንዴት መጉረምረም ጀመር፡፡ ሰዎቹ ይዘው የመጡትን ሲወጡ ጉርምርምታው እንደቀጠለ ነበር፡፡ ወዲያው ከጄኔራሎቹ አንዱ ቁመተ መለሎውና ቀጥ ያለ ቁመና ያለው መኮንን ተነሳና ንግስትዋን እጅ ነሳ፡፡
‹‹ግርማዊነትዎ የወሰኑት ውሳኔና የወሰዱት እርምጃ ታላቁ አላህ በልቦናዎ ያሳደረው እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ የእርስዎን እጅ ለጋብቻ ለመጠየቅ በዚህ አለም ውስጥ መብት ያለው አንድ ሰው ብቻ ሲሆን እሱም እኔ ብቻ ነኝ፡፡ እርስዎ ገና ብላቴና እያሉ ግፈኛውንና ጨካኙን ንጉስ ካምቢስስ፣ በማስወገድ ደጉንና አስተዋዩን የርስዎን አባት፣ ስልጣን እንዲይዙ አድርጌያለሁ›› አለና ተቀመጠ፡፡
የአብዛኛው ሰው ፊት ላይ ፈገግታ ይታይ ነበር። ነገሩ በሌላ ሳይሆን ጄኔራሉ እውነተኛ ጀግናው የነገስታት ዝርያ ስላለው የንግስት ሴሬና ባል ለመሆን ይመጥናል ተብሎ ስለሚታሰብ ነበር፡፡ ሁሉም ሰው፣ የንግስትዋን መልስ በጉጉት ይጠባበቅ ጀመር፡፡
‹‹ያልከው እውነት ቢሆንም ካምቢሰሰን በመግደልህ የአላህን፣ ህግ አልጠበቅክምና ጥያቄህ ተቀባይነት የለውም›› አለች ንግስት ቀኝ እጅዋን ከፍ ካደረገች በኋላ፡፡
የንጉሳዊ ቤተሰብ አባል የሆነው የዝነኛው ቱጃር መስፍን የጋብቻ ጥያቄ ደግሞ  በንግስቲቱ ውድቅ የሆነው መስፍኑ ሐብቱን ያከማቸው በአራጣ በመሆኑ ነበር፡፡ እሱም የአላህን ህግ አፍርሷልና በንግስቲቱ ልብ ውስጥ ቦታ አልነበረውም፡፡
‹‹ፀሐይዋ ንግስታችን ሺኅ አመት ይንገሱ፤ እኛ ንግስታችን ጋብቻ እንዲፈፅሙ እንፈልጋለን። በዚህ ምድር ላይ የአላህን ህግ የሚጠብቅ የለምና፤ ንግስታችን ማንን ሊያገቡ ነው›› ሲል ከህዝቡ መሃል አንዱ ሽማግሌ እጅ ከነሳ በኋላ ጠየቀ።
‹‹በዚህ ምድር ላይ የአላህን ህግ የሚጠብቅ ከሌለ የኔ ባል ከሰማይ ይወርዳል፡፡ አሁን ነገ የሚገባውን የሮመዳን ጾም የማሳልፈው እዚህ ቤተ መንግስት ስላልሆነ መናፈሻው ላይ ድንኳን ይጣልልኝ›› አለችና ንግስት ሴሬና ከዙፋንዋ ተነሳች፡፡ ህዝቡም በሙሉ ተነሳና ለጥ ብሎ እጅ ነሳ፡፡
* * *  
ያሲን ኢብኒ ዛይድ አረብያ በመዲና ከተማ ውስጥ ፍራፍሬ እየሸጠ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ የሚኖር ብላቴና ነው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ዛሬ ምንም አልሸጠም፡፡ የመቅርቢን ሰላት ከሰገደ በኋላ ለሱና ለአሮጊት እናቱ ማፍጠርያ የሚሆን አንድ ሩዝ ኪሱ ውስጥ በአደረ ሳንቲም ገዛና ወደ ቤቱ አቀና። ፍራፍሬ የሚጭንበትና የሚሸጥበትን ጋሪ የቃሲም ሱቅ ውስጥ ነው የሚያሳድረው፡፡ ምግቡን ይዞ ወደ ቤቱ እየተራመደ እያለ አንድ ያደፈ ልብስ የለበሱ አሮጊት፣ መንገዱ ላይ ቆመው እሱን ሲመለከቱ አስተዋለ፡፡
‹‹ጾመኛ ነኝና በአላህ ስም እሱን ምግብ ስጠኝ›› አሉ አሮጊትዋ፤ በሚንቀጠቀጥ ድምፅ፡፡
ያሲን ግራ ተጋባ፡፡ ምግቡ የሱና የእናቱ ማፍጠርያና እራት ነው፡፡ ይሄን ምግብ ለአሮጊትዋ ከሰጠ ጾማቸውን ማደራቸው ነው፡፡ ሰምቶ እንዳልሰማ አልፎዋቸው ለመሄድ ተራመደ፡፡
‹‹‹አላህን ፍራ!›› አሉ አሮጊትዋ
ያሲን መራመድ አልቻለም፡፡ ዞረና ምግቡን ለአሮጊትዋ ከሰጠ በኋላ ፊቱን አዙሮ ለመሄድ ተዘጋጀና እጁ ላይ የቀረውን ሁለት ብርቱካና ሁለት ሙዝ ጨምሮ ሊሰጣቸው አስቦ ዞሮ ሲመለከት በአካባቢው ምንም የሰው ዘር አልነበረም፡፡ ግራ እየተጋባ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ቤቱ ሲገባ አሮጊትዋ እናቱ አልጋ ላይ ጋደም ብለው ነበር፡፡
‹‹ማፍጠርያችንን ይዘህ መጣህ ያሲን ልጄ›› አሉ እናቱ፡፡
‹‹ዛሬ ስራ አልነበረም፡፡ አንድ ምግብ ገዝቼ ነበር፤ ለደሃ ሰጠሁት፤ምንም እህል ሳይቀምስ፣ ውሃ ብቻ ጠጣና እንቅልፉን ለመተኛት ጋደም አለ፡፡ በነጋታው አንድ ዲናር ሽጦ ነበር፡፡ እናቱ ለመካስ፣ አስቦ ሰለነበር ሁለት ሩዝና ሁለት ቁራጭ አሳ ገዝቶ ወደ ቤቱ አቀና። ቤቱ ደጃፍ ላይ ሲደርስ አንድ የተቀደደ ቁምጣና ከናቴራ የለበሰ ብላቴና መንገዱ ላይ ቆሞ ነበር፡፡
“የምበላው የለኝምና ለአላህ ብለህ እሱን ምግብ ስጠኝ” አለው፣ ልጅ አይኑ እንባ እያቀረረ፡፡
ያሲን የአላህን ስም ሲጠራ እሰማ ተራምዶት ማለፍ አልፈለገም፡፡ አንዱን ምግብ ሰጥቶት ሊሄድ ሲዘጋጅ፤ “እናቴም እህል ከቀመሰች ሶስት ቀንዋ ነውና፤ እሱንም ጨምረህ ስጠኝ” አለው ልጁ፡፡
ያሲን ምርጫ አልነበረውም፡፡ ሁለተኛውንም ምግብ ሰጠው፡፡ ትንሽ እንደተራመደ የልጁን የተራበች እናት አሰበና እጁ ላይ የነበሩትን ሁለት ቁራጭ አሳዎች ሊሰጠው ዞር ሲል የሰው ዘር በአካባቢው አልነበረም፡፡
ቤቱ ሲገባ እናቱ መስገጃው ላይ ተቀምጠው ነበር፡፡
“ዛሬም ማፍጠርያ የለንም ያሲን ልጄ” ሲሉ ጠየቁ፡፡
“ምግብ ገዝቼ ነበር፤ ነገር ግን ለድሃ ሰጠሁት” አለና ሁለቱን ቁራጮች አሳዎች ሰጣቸው፡፡
“ከኛ የባሰ ማን ደሃ አለ የኔ ልጅ?” አሉ በቅሬታ፡፡ ለሁለት ቀናት እህል አልቀመሱም፡፡ ማፍጠርያውን ለደሃ ይሰጣል፡፡ በነጋታው ደሞ ይውላል፡፡ ውሃ ጠጣና ተጠቅልሎ ተኛ፡፡
በሶስተኛው ቀን እንደተለመደው ሲጾም ዋለና ለሱና ለእናቱ ሁለት ምግብ ገዝቶ ወደ ቤቱ አመራ። እቤቱ ሊደርስ ትንሽ ሲቀረው፣ ነበር ሽማግሌውን ያየው፡፡ ያደፈና የተበጫጨቀ ልብስ ለብሰዋል፡፡
“ጾመኛ ነኝና በአላህ ስም እሱን ምግብ ስጠኝ” አለው፤ ሽማግሌው፡፡
ያሲን አልፎት መራመድ አልቻlም፡፡ አንደኛውን ምግብ ሊሰጠው ወደሱ ሲቀርብ አንድ ነገር አስተዋለ። የሽማግሌው ፊት፣ አዲስ ፊት እንዳልሆነ።
የሽማግሌውን እጅ አፈፍ አድርጎ ያዘና፤ “ማነህ አንተ?” ሲል ጠየቀው፡፡
“አትግደለኝ፤ ማንነቴን እነግርሃለሁ፡፡” አለ ሽማግሌው፡፡
“አሮጊትዋም ህፃኑም አንተ ነበርክ!”
“አዎ፤ እኔ ነበርኩ”
“ምንድነህ?”
“እኔ ጅኒ ነኝ፡፡”
“ምንድነው የምትፈልገው?”
“አንተን በፈተና ለማሰናከል ነበር የመጣሁት፡፡ ነገር ግን እምነት አድኖሃል፡፡”
“አሁን የወሰድከውን ሁሉ መልስ” አለ ያሲን፤ የሽማግሌውን እጅ አጥብቆ እንደያዘ፡፡
“የምሰጥህ ነገር የለኝም፡፡ ነገር ግን አንድ ትልቅ ነገር ላደርግልህ እችላለሁ” አለ ሽማግሌው፡፡
“ምንድን ነው እሱ?”
“ወደፈለግክበት አገር እየበረርኩ ይዤህ ልሄድ እችላለሁ፡፡”
ያሲን አሰበ፡፡ ይሄ ጂኒ አየር ላይ የመብረር ችሎታ አለው፡፡ ወደ ፋርስ ይዞት ቢጓዝ ይሄ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮው ሊቀየር ይችላል፡፡ አሮጊት እናቱንም በደንብ መጦር ይችላል፡፡ ይህን ነገር ሁልግዜ ያስበው የነበረ ሲሆን ወደዚያ ለመሄድ ብዙ ወራትና ብዙ ገንዘብ ስለሚፈጅ፣ እስካሁን ሊያደርገው አልቻለም ነበር፡፡
“ወደ ፋርስ ልትወስደኝ ትችላለህ?” ጠየቀ ያሲን።
“በአንድ ሰዓት ውስጥ ላደርስህ እችላለሁ” መለሰ ሽማግሌው፡፡
“በል ተከተለኝ” አለና ያሲን ሽማግሌውን ይዞ ወደ ቤት ገባ፡፡ ምግቡን እሱ እናቱና ሽማግሌው ከቀማመሱ በኋላ ያሲን ለክፉ ቀን ብሎ በከረጢት ጠቅልሎ፣ ጓሮ ቀብሮት የነበረውን አስራ አምስት ዲናር የወርቅ ሳንቲሞችን ከቀረቀረበት አወጣና ለእናቱ ሰጠ፡፡
“ምንድነው ይሄ?” ጠየቁ እናቱ፡፡
“እስክመለስ ድረስ እየቆጠብሽ ተጠቀሚበት፡፡ እኔ ከሰውየው ጋር ወደ ፋርስ ለትንሽ ጊዜ መሄዴ ነው” አለ ያሲን፤ የእናቱን እጆች ይዞ፡፡
“ይሁና፤ ለመሆኑ ሰውየው ማነው?”
“በአየር ላይ መብረር የሚችል ጂኒ ነው”
“ያሲን ልጄ፤ ነብያችን ከአጋንንት ጋር አትገናኙ ብለዋል”
“አልፈራውማ፤ እኔ ውስጥ ያለው አላህ ከሱ ይበልጣል”
ለእንግዳው ከተነጠፈለት በኋላ ሶስቱም ጎናቸውን አሳረፉ፡፡ ያሲን ሌሊቱን በሙሉ እንቅልፍ በአይኑ ሳይዞር ነጋ፡፡ ጠዋት ከሱብሒ ሰላት በኋላ ከሽማግሌው ጋር ከቤት ወጡ፡፡ ሽማግሌው ያሲንን በጀርባው አዘለና አንዴ ሲዘል፣ አየሩ ላይ መንሳፈፍ ጀመሩ፡፡ ወዲያው ሽማግሌው ይመስል የነበረው ጂኒ፤ ባለ ብዙ ክንፍ ግዙፍ በራሪ ጅኒ ሆኖ ተቀየረ። በትልልቅ ክንፎቹ አየሩን እየቀዘፈ፣ ከደመናው በላይ ለማመን በሚያስቸግር ፍጥነት ይበራል፡፡ ያሲን የጅኒውን ጀርባ በክንዶቹ ጠምጥሞ ይዞ፣ ልቡ እየመታ አብሮት ይበራል፡፡፡
የብሱን ጨርሰው ወደ ባህሩ ክልል ገብተዋል። ባህሩን ለማቋረጥ የፈጀባቸው እኩል ሰዓት ብቻ ነበር፡፡ ያሲን ፀሐይዋ የቀረበች መሰለው፡፡ ከደመናው በላይ እየበረሩ ከታች የፋርስን መልከአ ምድር ይታያቸው ነበር፡፡ ጅኒው ፍጥነቱን ቀንሶ ወደ መሬት መውረድ ሲጀምር ያሲን በድንገት ከደመናው በላይ የሚውለበለብ ቀይ እሳት ወደነሱ አቅጣጫ ሲምዘገዘግ ተመለከተ፡፡ ጅኒው ወደመሬት ሲምዘገዘግ፣ እሳቱ በሱ አቅጣጫ ይወረወራል፡፡ እሳቱ እየቀረበ ሲመጣ ያሲን ያየውን ማመን አልቻለም፡፡› ብዙ ክንፎች ያሉት በጣም የሚያምር፣ ቀይ መልአክ የያዘውን የእሳት ጦር፣ እሱ ላይ አነጣጥሯል። ያሲን ልቡ እንደ ውሃ ፈሰሰ፡፡
“ሐይልም ችሎታም የአላህ ነው በል፡፡ አለዚያ እወጋሃለሁ” አለው መልአኩ፡፡ ያሲን በፍርሃት ተንቀጠቀጠ፡፡ ይሄን ቃል ከተነፈሰ ተሸክሞት እየተንሳፈፈ ያለው ጅኒ ይጠፋል፡፡ ጅኒው ጠፋ ማለት ደግሞ ያለው እድል መሬት ላይ መፈጥፈጥ ሲሆን ቃላቱን ካልተናገረ ደግሞ መልአኩ በያዘው የእሳት ጦር ይወጋውና፣ ወደ አስከሬንነት ይቀይረዋል፡፡ ልቡ በፍርሃት እየመታ ሰውነቱ ተንቀጠቀጠ፡፡
“ለመጨረሻ ጊዜ አዝሃለው፤ ኃይልም ችሎታም የአላህ ነው በል፤ አለዚያ እወጋሃለው” አለ፤መልአኩ በታላቅ ድምፅ፡፡
ያሲን ምርጫ አልነበረውም፡፡ ሁለቱም ሞት ቢሆንም የአላህን ኃይል ሳይመሰክር፣ በእሳት ጦር ተወግቶ ከመሞት መስክሮ መሬት ላይ ተፈጥፍጦ ቢሞት መረጠ፡፡
“ኃይልም ችሎታም የአላህ ነው” አለ ያሲን፤የሞት ሞቱን፡፡ ወዲያው አዝሎት የነበረው ጅኒ በቅጽበት ሲሰወር መልአኩ ደግሞ እንደ መብረቅ ተተኩሶ፣ ከደመናው በላይ እየበረረ ከአይኑ ተሰወረ፡፡ ያሲን ግን ቁልቁል ወደ መሬት እየወረደ ነበር፡፡
ከታች ህንጻዎችና ቤቶች ይታዩታል፡፡ በህንጻዎቹ ዙሪያ በመናፈሻ ውስጥ ያለ ጥቅጥቅ ያለ ደንም እንዲሁ፡፡ ያረፈው መናፈሻው ላይ ባሉት ዛፎች ላይ ነበር፡፡ የአንድ ትልቅ ዛፍ ቅርንጫፍ ሲቀበለው ህመሙ ቢሰማውም፣ ፍጥነቱን ቀንሶ ነበር፡፡ የዛፉ ቅርንጫፍ ሲያፈናጥረው የሌላ አነስ ያለ ዛፍ ቅርንጫፍ ፍጥነቱን ሙሉ ለሙሉ አበረደውና፣ ወደ መሬት ሲጥለው የአንድ ትልቅ ድንኳን ጣርያ ላይ አረፈ፡፡
መናፈሻው ላይ ተሰብስቦ የነበረው ህዝብ፤ ይህን ጉድ አፉን ከፍቶ በመደነቅ ይመለከት ነበር። ያሲን ከድንኳኑ ጣርያ ላይ በዛፉ የተጎዳ ጎኑን ይዞ ለመውረድ ሲሞክር፣ንግስት ሴሬና ከድንኳኑ ወጣችና ሽቅብ እያየችው “ውዱ ባሌ፤ ለረጅም ግዜ ስጠብቅህ ነበር፡፡ እንኳን ወደ ቤትህ በሰላም መጣህ!” አለችው፤ ፈገግ ብላ፡፡ ህዝቡ ከሰማይ የወረደውን የንግስትዋን ባልና የፋርስ ንጉስ ለማየት ወደ ድንኳኑ ተሰበሰበ፡፡

Read 3400 times