Sunday, 28 May 2017 00:00

የትዝታችን ቅመም፣ የጥበባችን ችቦ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(5 votes)

 በዘመኑ ስለ ኪነትና ከያኒ እጅግ ብዙ መጣጥፎችን፣ ግጥሞችንና ሌሎችንም እንጉርጉሮዎች አንብቤያለሁ፤ አድምጫለሁ፡፡ ከናፍርት በሀዘኔታ ሲመጠጡ፣ በርካቶች በሀዘን ስሜት ሲመስጡ አስተውያለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ ለከያንያን ሞት እጁ የማያርፈው ነቢይ መኮንን፤ አሳዛኝና አስደማሚ ግጥሞቹን አስነብቦ፣ የሀሳብ ችግኞች በልባችን ተክሏል፡፡ … አንዳንዴ መንግስቱ ለማን፣ ዮናስ አድማሱን ወዘተ … ልቤ ሲናፍቅ አብሬ በትዝታ ለመመለስ ገፆች እገልጣለሁ፡፡
ለምሳሌ ነቢይ መኮንን “በስውር ስፌት ቁጥር 2” ለዮናስ አድማሱና ለትውልዳችን” በሚል መታሰቢያ ከግርጌው ያስቀመጠለት ግጥም ስሜቴን ይሰረስረዋል። “ባንተ በኩል ፈካች” ብሎ፡፡
የልቤን ማህደር ቆፍሬ ቆፍሬ
ያገር ውለታህን ልናገር አምርሬ፡፡
ምንም ቢደባለቅ ብስሉ ከጥሬ
የፊደል ልሳኑ ያው ይጮሃል ዛሬ፡፡
እኔ በዚህ መነፅር ውስጥ አሁን ህልፈቱ አመት የደፈነው፣ ወዳጄ አብደላ እዝራ ታየኝ፡፡ አብደላ ትምህርት ቤት ሆኜ የማውቀውና ጽሁፎቹን በፍቅር የምወድድለት፣ በቋንቋ አጠቃቀሙ የምመሰጥበት ሰው ነበር፡፡ በተለይ የቀደምት ደራሲያንን ስራዎች ሲገመግም በከፍተኛ ተመስጦ፣ ፍቅር ነበር የማነበው። በኋላም አጋጣሚ ሲያገናኘን እኔ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፍ ብዬ ስለነበር ያወራሁት በፍቅርና በተሻለ ማስተዋል ነበር፡፡ በፍቅር የነደደው ፊቱ ለጥበብ ዕድገት ባለው ፍፁም ንፁህ ቅናት፣ ሲንገበገብና፣ ቀይ ፊቱ ላይ ደም እየነደደ፣ ሲያወራኝ አይረሳኝም፡፡ … ይገርማል፤ አብደላ እዝራ፣ ዘር አያውቅም፣ ሃይማኖት አይለይም። … ልቡ መላው ሰው እንዲሞቀው የተለኮሰ ሻማ ነው። ከላይ የጠቀስኩት ግጥምም ከልቤ ጋር የተሳሳመው ለዚያ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ራሱን እንደ ጥበብ አፍቃሪና ተቆርቋሪ ቢቆጥርም፣ አብደላ እዝራ ግን ፈፅሞ ይለይ ነበር፡፡ ትኩረቱ ከራሱ ይልቅ ለጥበቡ ነው፡፡ ለአበቦች ይሳሳል፣ ለወጣቶች ተስፋን ማጫር ይመኛል!
ሌላው ቀርቶ ፒያሳ ለመጨረሻ ጊዜ ስንገናኝ ስፕራይቱን ጋብዞ፣ የሚያወራልኝ ይህንኑ ነበር፡፡ በተለይ በአንዳንድ ወጣቶች በሕዝብ መነዳት ጉዳይ በእጅጉ ቅር ተሰኝቶ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
“ጥሩ የሚፅፉ ልጆች በህዝብ ማዕበል እየተገፉ፣ ችክ ወዳለ አላስፈላጊ ጉዳይ ውስጥ እየገቡ ነው!” ሲል የተናገረው የድምፁ ቅዝቃዜ ስሜት፣ ዛሬም ልቤን ይበርደዋል፡፡ አብደላ ስለ ጥበብ ሲነሳ ትኩስ ነው። አዲስ አበባ አግኝቼው ትኩስ ነው፣ ሀዋሳ አግኝቼው ትኩስ ነው፣ ቡታጅራም ያው ነው፣ ነበልባል ነው፡፡
ቡታጅራ ከተማ ብራይት ሆቴል፣ ለመጨረሻ ጊዜ ከጓደኛው ከመምህር ጥላሁን ሽሁር ጋር፣ ሳገኘው እንዴት ባለ ደስታ አበባ ፊቱ ላይ እንደነሰነሰ አልረሳውም። እንዴት እንዳቀፈኝ፣ እንዴት ባለ ሁኔታ ወደ ሆቴሉ እንደሄድን ልረሳው አልችልም። ስንለያይም፣ ለጥላሁን ባለቤት ሙዝ፣ ለእኔና ለሌላ ወጣት፣ አንድ አንድ “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ገዝቶ ጋብዞ ነበር፡፡ መቼም አብደላ እዝራን አግኝቶ ሳይጋበዝ “ተለየሁት” የሚል ሰው ካለ፣ መኝታ ላይ ጧ! ያለ እንቅልፍ ወስዶት፣ ወይም ሕይወቱ አልፎ፣ ለመጨረሻ ጊዜ ባሸለበበት የፍፃሜ ቀን ብቻ ነው፡፡ … እኔ .. አንድም ቀን ማስታወስ አልችልም። እርሱ እኮ መጽሐፍ ይጋብዝሃል፣ ምሳ ይጋብዝሃል፣ ለስላሳ ይጋብዝሃል … ሁሌ ይጋብዝሃል፡፡ እምቢ ማለት እርሱ ዘንድ አያዋጣም፡፡
“ጠግቤያለሁ!” ብትለው
“ምንድነው የበላኸው ይልሃል?!”
“ቅቅል” ካልከው፣
“እዚህ ቤት የተለየ ዱለት፣” አለ ብሎ እየተወዛገብክ እያለ አዝዞ፣ ፊትህ ሲቀመጥ ታየዋለህ።
ማህበራዊ ህይወቱና ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር፣ ዳር የለውም፡፡ በተለይ በህብረተሰቡ ውስጥ ዝቅተኛ ቦታ ለተሰጣቸው ሰዎች ያለው መቆርቆሮ፣ ጠጋ ላለው ሰው ቢነገር ሊረዳው የሚችል አይመስለኝም። … ብቻ በብዙ ነገር፣ የተለየ ሰው ነው፡፡ እና አንዳንዴ አስበዋለሁ፡፡ ለሰው ልጅ እንዲህ መብከንከን፣ እንዲህ መንደድ፣ ዋጋው ምንድንነው? ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ … ለሀገሩ ጥበብስ የከፈለው ዋጋ ምን ወሮታ ተሰጠው? እያልኩ ውስጤ ያዝናል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት ይኸው ስሜቴ ተቆስቁሶ፣ ከጓደኛው መምህር ጥላሁን ሽሁር ጋር ረጅም ሰዓት አውርቼ፣ በልቤ የነደደውን ፍም መበተኔን አስታውሳለሁ፡፡ ደግነቱን ለማሰብ፣ መምህር ጓደኛውን ፍለጋ በየሀገሩ ያደረገውን መንከራተት ብቻ ማሰብ ይበቃል፡፡ … ሌላውን ምስጢር ደግሞ ከመምህሩ ለሰማ ሰው ለጋስነቱ ከአእምሮ ይሰፋል። …
ብቻ አብደላ እዝራ፣ ከልብ ውስጥ የማይጠፋ ፍም ነው፡፡ ምናልባት የጊዜ ዐመድ ሊሸፍነው ይችላል፤ ግን የትዝታው ንፋስ ረመጡን መቆስቆሱ አይቀርም፡፡ ነፍስን እንደ ሽንኩርት እየላጠ፣ እስከ ውስጥ የሚዘልቅ ህመም አለው፡፡ ግን ምን ይደረጋል? ብዬ ሳስብ፣ የደበበ ሰይፉ አንድ ግጥም በልቤ አደባባይ ግራና ቀኝ ትመላለሳለች፡፡
እንዲህ ተጫጭደን፣
እንዲህ ተጨናብሰን፣
ውሃ እንደለዘዘን፣
ከውሃ ተዋግተን --ተዋግተን … ተዋግተን …
ውሃን አሸንፈን፤
እሳትን ፀንሰን
እሳትን አምጠን … አምጠን … አምጠን
እሳትንም ወልደን፣
እሳትንም ሁነን፣
የክረምት ማገዶች
ካጨለጨልንለት የድሃውን ጎጆ፣ ቀሳ ካልጭራሮ
ካበስልንለት ዘንድ፣ የአርሶ አደሩን ንፍሮ፣  
የሰርቶ አደሩን ሕዝብ ለስስ ያለ ሽሮ፤
ዘመን ይመስከረው፤ የኛን ውጣ ውረድ፤
የእንግልት ነሮ፡፡
(“የክረምት ማገዶ” በሚል ከጻፈው ግጥም)
አብደላ እዝራ በጥበብ ሥራ፤ በተለይ በሥነ ጽሁፋዊ ስራዎች ጊዜንና ሕይወቱን ከመቁረስ በቀር ለራሱ አንዳች ያገኘው ነገር የለም፡፡ ምናልባት በስራውና በትጋቱ ከመርካት በቀር!... ወጣቶችንና ሥራቸውን ለመኮትኮት፤ ብርሃን ይዞ፣ ፊት ፊት፣በመሮጥ ያገኘው ነገር ፍቅር ብቻ ነው፡፡ … ፍቅር!... ከወራት በፊት በፌስ ቡክ ገጹ ላይ፣ ገጣሚ ዮሐንስ ሞላ፣ በአክብሮትና በፍቅር፤ አስታውሶት ነበር፡፡… አዎ የአብደላ ዋጋ፣ የጥበብ ቤተሰቦች ፍቅር ነው፡፡
ግና ቅር ያለኝን ነገር ማስታወስም አይከፋም፡፡ … በተለይ የቀብር ስነ ስርዓቱ በተፈፀመ ቀን!.. ጭር ያለ ነበር፡፡ የብዙዎቻችንን ህይወት አሙቆ፣ የጥበባችንን ባንዲራ አውለብልቦ፤ የሚውለበለብለት ልብ ማጣቱ፣ ትንሽ ያባባ ነበር፡፡ እንደዚያ ለሰዎች ለኖረ ሰው፤… ብድራቱ ነው ወይ የሚል ብሶት ያጭራል። ማን ነበር በጭርታ የተሸኘው ሩሲያዊው ደራሲ - እንደዚያ ሆድ የሚያባባ ስሜት ነበረው፡፡  
አብደላ እዝራ፤ ከተለየን አንድ ዓመት ሞላው፡፡ እናም ውለታውን እንዳንረሣ እንዲህ እንላለን፡-  
የዓይኖችህ ውስጥ እሳት፤
ፍቅር ያረገዘው፤
የአዕምሮህ ብርሃን
ጥበብን የሚያዘው፤
ያ-ጉልህ ምልከታ
አሻግሮ የሚጓዘው፤
ያ-ጠሊቅ ሕሊና
ረቂቅ የልብ እሣት
ሃያል ሰብዕና
የልብህ አቀበት
በዕውቀት የሚወጣው
ከመቸው ወርዶ- ነው
ከጉባዔው የታጣው
ያ ሁሉ ቸርነት
ያ ሁሉ ችሮታ
ምን ንፋስ አፈሰው፤
ከመቸው ተፈታ?
የጥበብህ ማዕበል
የቅኔ ሞገዱ፤
ቁመና ርቀቱ
የሙዚቃው ወርዱ
ከአድማስ ወዲያ ህልምህ
ምነው ተሰወረ፤
ጅማሬ ውጥንህ
እንዴት መንገድ ቀረ?!
--- እያልን የለኮሳቸውን ሻማዎች ሙቀት፤ ከትንንሽ ልቦች፤ ከአበቦች አጸድ ውስጥ እያጣጣምን፤ እናስታውሰዋለን፡፡ የህልፈተ ህይወት ሻማ፤ ነበልባል የሌለው ደረቅ ክር ቢሆንም፣ በምናብ ግን፣ ዛሬም የሚነድደውን የጥበብና የሰው ልጅ ፍቅሩን ከብበን እንሞቃለን!..
አብደላ እዝራ የትዝታችን ቅመም፣ የጥበባችን ችቦ ነዋ!

Read 3091 times