Sunday, 28 May 2017 00:00

የአንጋፋው ሃያሲ አብደላ እዝራ ማስታወሻ ገጽ

Written by  ዕዝራ አብደላ
Rate this item
(2 votes)

   ከአዘጋጁ፡-
አንጋፋው ሃያሲ አብደላ እዝራ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየን እንደዘበት አንድ ዓመት ሞላው፡፡ በዚህ አንድ ዓመት በእርግጥም ጥበብ ብዙ እንደጎደለባት በትክክል ተረድተናል - ተገንዝበናል፡፡ ይሄን ጊዜ የስንቱን ደራሲያንና ገጣሚያን የፈጠራ ሥራዎች ያስነብበን፣ ያስቃኘን ያስተነትነን እንደነበር ስናስብ ሀዘናችን ይበረታል፤ ቁጭታችም እንደዛው፡፡ ግን ምን ያደርጋል? እሱ አንዴ አርፏል፡፡ ግና ትንፋሹ እስክታቆም ድረስ ለጥበብና ለጠቢባን ዕድገትና መሻሻል ብዙ ለፍቷል- ከልቡ፡፡ አብደላ የጥበብ ጠበቃ ነበር፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ በዓይነትና በብዛት እንድታድግ፣ በሳምንት ሁለቴ እንድትወጣም ይመኝ ነበር፡፡ አዲስ አድማስን ይወዳት ነበር - ከልቡ፡፡ የአንደኛ ዓመት ሙት ዓመቱን ለመዘከርና ጥበባዊ ፍቅሩንና ትጋቱን እንዲሁም ውለታውን ለማስታወስ፣ የራሱን በህይወት ሳለ የወጣ አንድ የሂስ ፅሁፍና ደራሲ ደረጀ በላይነህ የከተበለትን “ጥበባዊ እንጉርጉሮ” ለአንባቢያን አቅርበናል፡፡ ገፁንም የአብደላ እዝራ
ማስታወሻ አድርገነዋል፡፡ ፈጣሪ ነፍሱን በመንግስተ ሰማያት ያኑርለት፡፡

                   “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ሂሳዊ ቅርበት
                  ዕዝራ አብደላ

      ስለ አዳም ረታ ልቦለድ ውበትና ጥልቀት በመጠኑ ነው የተነካካው። ከደራሲው ጋር በተደረገ ውይይት እና በጥቂት የጥናት ወረቀቶች በአመዛኙ ስለ አጻጻፍ ይትበሃልና ዘዬ ነው የተተኮረው። “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ሰባት ትረካዎች ያስነብበናል፤ ስድስቱ ሆላንድ ሳለ ነው የተፈጠሩት። (1987 ) በገፅ መጠን “መች ትመጣለህ?” አጭር ልቦለድ ነው፤ የተቀሩት እንደ novella እምቅ ናቸው። ሰባቱም ብርቅ ትረካ ስለሆኑ፥ እያንዳንዱ የግሉን ኮስታራ ቆይታ ይማጠናል። ይህ ሂስ-ቀመስ ጽሑፍ፥ ሀምሳ ገፅ በፈጀ የስብስቡ ርዕስ በሆነው “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ላይ ብቻ ያተኩራል። ከዚህ ልቦለድ የተወሰኑ ገጾች ተመርጠው የዘመኑን መንፈስ -zeitgeist- በተለይ በገፀባህሪይዋ ምስራቅ ህይወትና እንግልት ላይ ባሳደረው የልቡና ወረራ ላይ ያጠነጠነ የአብረሃም ገዛኸኝ ፊልም ተሰርቷል። “ሃሜት፥ ጥላቻ፥ ውሸትና ቅናት የሞራል ወንጀሎች ... ከግለሰብ አልፈው ... ሀገር የማፍረስ አቅማቸው” በፊልሙ ተስተውሏል። ትረካው ግን የዘመን መንፈስ ክስተቶች ውጤት አይደለም። የግለሰብ ማንነት አቅምና ረግረግነት፥ ብሎም የልጅነት ዳራ የጐልማሳን ዛሬነት ሲቧጥጥ፥ ሰው ለራሱም ለሌላውም ሰቆቃ ይሆናል።  ለማኅበረሰቡ እምነት ግለሰብ ሲገዛ -እንደ ታደሰ- እንግልት የሸሸገ ሰላም እስከ መላበስ ድረስ ትረካው ይፍታታል። የዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ልዩ አሻሚ መንቶ፤ ምስራቅ እና ሎሚ ሽታ ይነጠቁበታል። “እኔ ምኑን ተጐዳሁ፥ ላንቺ ይብላኝልሽ እንጂ / እንደ መንፈስ ውስጤ ሳኖርሽ፥ አካል ሆነሽ ስትሄጂ” እንደ ስዕል የመንፈስ ቢጋር ውስጥ መታጠር የመረጠችው ምስራቅ፥ መቃኑን ነቃቅላ አካል ሆና ነፃ ከወጣች ሎሚ ሽታ እኩል ተቀርፀዋል።   
ከጭብጦች አንዱ የሆነው የሰዋዊ ግንኙነት ረቂቅ ገፅታዎች፥ በተለይም የወንድ-የሴት ሰበቃ እስከ ውስጣዊ ሥነልቦናዊ ጓዳ የመጥለቅ ምትሃት፥ አዳም ረታ ተክኖበታል። የስምንት ሴቶች ልቦለድ (143 ገፅ የፈጀው) “ኩሳንኩስ” በተመስጦ ሲነበብ፣ የሀዲስ ዓለማየሁ ሰብለወንጌል፥ የበዐሉ ግርማ ሉሊት፥ ተሻግሮም የቶልስቶይ ገፀባህሪ አና ካራኒን ... ይደበዝዛሉ። ይህ “ይወስዳል መንገድ፥ ያመጣል መንገድ”  መጽሐፍ ውስጥ ያደፈጠው “ኩሳንኩስ” ወደፊት በሂሳዊ ንባብ ባባብለውም እነ ሰናይት፥ እትዬ ወርቄ፥ ሣራ ... ከምናቤ አይሰክኑም፤ እየተንጓለሉ ሰርክ እበረግጋለሁ። ከሰው ለላቀ ገፀባህሪ መደንገጥ ምን ይደንቃል? ዋሲሁን በላይ በአርምሞ አግኝቶታል። “ትበረግጋለች ነፍሴ በትንሽ ኮሽታ / ሠቀቀን ገደላት ጊዜው ላይ ተኝታ” ዝነኛው ባለቅኔ Ezra Pound ስለ ግጥም አጻጻፍ የመሰከረው ለአዳም ረታ የቋንቋ ጥበብ ይመጥነዋል። “Great literature is simply language charged with meaning to the utmost possible degree.”  የአብይ ሥነጽሑፍ አስኳል በትርጓሜ፥ በአንድምታ የተለበለበ ቋንቋ ነው እንደማለት። ጥቃቅን ግን ሌላው ግለሰብ ሊመሰጥበት ቀርቶ ልብ የማይለውን ምስል፥ እንቅስቃሴ ወይም የሆነ ድርጊት የአዳም ረታ ብዕር ሲፍቀው፥ ሲያሻሸው የሚፈልቅለት ውበት-አስቀያሚነት እስከ ፍፁም ንዝረት፥ እስከ አስደንጋጭ ግርምት ይረቃል፤ እሳቦትና ምናባችን ይታመሳሉ። ለአዲስ በኩር ክስተት አሁንም እንበረግጋለን። (በአስረጅ እመለስበታለሁ)። አዳም፥ በኑሮ ውጣ ውረድ ተጠምደው ሲያቃስቱ፥ ሲቦርቁ ገፀባህሪያት ቀረፀ እንጂ አንዱን እኩይ፥ ሌላውን በጐ በማለት አይፈርድም። አንባቢ ነው እንደ ብስለቱ፥ እንደ ገጠመኙ የባለታሪኮችን ህይወትና አቋም የሚመነዝረው። ለዚህም ነው ሎሚ ሽታ ለአንዱ አርአያ እንስት ስትሆን፥ ሌላው የሚያወግዛት። ደራሲው በገፀባህሪያት ድርጊት ሳይታቀብ ውስጠታቸውን ሲቦረቡር ገለጣው ስዕሉ ያስደምማል። አንድ መነኩሴ ለመምህሩ ያቀረበው ጥያቄ ይታወሰኛል። ስለ ስዕል የሚያትት መጽሐፍ ነው። “ብርሃን ማጤን፥ ጥላውን መሳል” ከሚል ምዕራፍ የተተረከ ነው።
“እኔ ምንድነኝ?” ብሎ ጠየቀ መነኩሴው።
መምህሩም መለሰ፤ “ከውስጥህ ያደባ ድብቅ ነገር አለ። ዘልቆህ የተሸሸገውን እንቅስቃሴ መላመድ አለብህ።”
መነኩሴው እውስጡ ስለተሰወረው ነገር እንዲብራራለት ተማጠነ። መምህሩ በሃሳብ ከነጐደ በኋላ ዞር ብሎ መነኩሴውን አስተዋለና አይኑን ገለጥ፥ ጨፈን ብቻ አድርጐ ሄደ። ይህን ድርጊት - አይንን መጨፈንና መግለጥ- የመሰለ አፍታ መፈልፈል የሚችለው፥ ለፈጠራ ድርሰት የሚያበቃው አዳም ረታ ብቻ ነው። “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ን በማዟዛር የተለያየ ገጾቹን በጥቂት ክፍሎች ለማንበብ እሞክራለሁ።
--- 1 ---
መገለል
ለስራ ወጥቶ ሲገባ ቀድሜው ከደረስኩ ጊዜው አያልፍልኝም ነበር። ኮቴውን ስሰማ እተቀመጥኩበት እደነግጥ ነበር። እቆምኩበት እደነግጥ ነበር። ዛሬ ድረስ የእርምጃው ዳና እንደ ሙዚቃ እንደ ከበሮ ቃና በጆሮዬ ውስጥ አለ። ከሶስት ከአራት ሰዎች መሃል የእግሩን አጣጣል መርጬ ማውጣት እችል ነበር። የሚያስቀና መልክ የሚያስቀና ቁመና ነበረው። በአልኮል እየፋቁ በሐሰት መረጃ እየተረተሩ እስኪያጠፉት ድረስ። ... ጠረኑ ልጄ ገና የተለቀመ ጥጥ ይመስል ነበር።
(ምስራቅ ለልጇ ለታደሰ፥ ስለአባቱ ፍቅረስላሴ ካወጋችዉ የተቀነጨበ)
    [እቴሜቴ ሎሚሽታ  ገፅ 105 ]
ምስራቅ ልቧ ትርክክ ብሎ ለፍቅረሥላሴ የተርበተበተችው ገና በአፍላ እድሜዋ ነበር። “... ከኬክ ቤት(ብርቅ ነበር ያንጊዜ) እሱ ሲወጣ እኔ ልገባ ስል ... በሩ ጋ ሳየው፥ እዚህ ልቤን መታኝ፥ የማላመልጠው ነበር። ... ሌላ ሰው አስጠላኝ። ልቤ ግብት አለ። ያን ቀን ማታ ቤቴ ገብቼ ሙሉ ምሽት ሳስበው ነበር። አልጋዬ ላይ በጀርባዬ ተኝቼ ፈዝዣአለሁ፤ ዝም ብዬአለሁ።” ፍቅር  አሸነፋት፤ ለባሌ ዳንስ ሃንጋሪ መሄድ ስትችል ቀረች። የህይወቷን አቅጣጫ የሚገራ ትምህርት፥ በመዳፏ ያለውን ተገን አሽቀንጥራ እንድትጥል የመውደድ ሃያልነት አስገደዳት፤ ከፍቅር ጉም በዳበሳ ተሰወረች። ከፍቅረሥላሴ ትዳር ይመስርታሉ። ፍቅሯን ሳታጣጥም ገና ነፍሰጡር ሳለች ባልየው በጓደኞቹ ወሬ ተደናቅፎ እየተገለላት፥ ስክሮ በውድቅት እቤት መመለስ ጀመረ። ፍቅረሥላሴ የረባ ስራ ነበረው። የተለያዩ ወንዶች ተኝተዋት እንደነበር አወሩለት፤ ልቡ ሻከረ። “ታድይ አባትህ ደም ስሩ ተግተርትሮ ሊፈነዳ ደርሶ ትልቅ ዕውነት ከሰማይ እንደ ወረደለት ሁሉ ... `አንዴ ጨዋ ነኝ ብለሽ የለ፥ ውሸትሽ ሲወጣ ለምን አትክጂ?` ይለኛል።” የቅድመ ትዳር ህይወቷን ነበር የሚያማው። የተወለደው ህፃን የሱን መልክ ስለወረሰ ለጥቂት ወራት ምስራቅ በፍቅር መፍካት ቻለች። ጥርጣሬው ግን አገርሽቶ ህፃኑ ታደሰ ገና ጡጦ ሳይጥል ፍቅረስላሴ ያርፋል። “አንድ ቀን ከገነት ሆቴል ወረድ ብሎ ቦይ ውስጥ ከቁሙ ወደቀና - ያየ ሲያወራ - የተሰበረ ቆሻሻ ጠርሙስ በአንገቱ ገባ። አለቀስኩ እንጂ ሲሞት። ... ሳንደሰት፥ እሱም በልጅነቱ እኔም ገና በልጅነቴ እንዲህ ምርር እንዳለን ሁሉ ነገር አለቀ።” ታደሰ የአባቱን ህልፈትና የጠባቸውን መነሻ   ስለማያውቅ እናቱ በምትተርክለት ብቻ አስተሳሰቡ ይቦካል።
ምስራቅ ለጥቂት ወራት አዝና ብድግ ብላ ቁዘማዋን ገፍፋ፥ አዲስ ሌላ ህይወት ለመጐንጐን አልባዘነችም። ተኮፍሳ ቀረች። በፍቅር የተሰበረ ልቧን መጠገን ተሳናት። የባሏን አሉባልተኛ ጓደኞች ጠልታ ራሷን አግልላ ማኅበረሰቡን ጭምር ተራገመች፤ አቄመች። ለነገዎቿ ከምታልም፥ ትናንቷን እየወለወለች ፈዘዘች። ታደሰን ለማሳደግ ግን በታይፒስትነት እየሰራች ዘለቀች። “ብትረባም ባትረባም ያንድ ገፅ ያልተበረዘች እሱን የማፍቀር ታሪኬን ይዤ አፈር እገባለሁ። ወደሥራዬ ስሄድና አስቤዛ ልገዛ ካልሆነ ለአስራ ሰባት አመታት ከቤት አልወጣሁም።” እንዴት ግለሰብ እንዲህ ሊሰበር ሊገለል ቻለ? የሰዓዳ መሀመድ አጭር ልቦለድ “የውድቅት ዕንባ” [ወንዞች እስኪሞሉ፥ 1998 ገፅ 109-127] ትዝ ይለኛል::  የሮቤል እናት ዩኒቨርስቲ የመግባት ነጥብ ብታመጣም ከድህነት ለመጠለል ትዳር ትመሰርታለች። ሆኖም የምታፍቅረው ባል ችላ ይላታል።
የመጀመሪያ ባሌን እወደው ነበር። ግን አሁንስ እጠለዋለሁ? ታድያ የመጀመሪያ ልጄ አይኖቹ የሚረብሹኝ ለምን ይሆን?...

Read 3559 times