Sunday, 21 May 2017 00:00

ቅዱስ ጊዮርጊስ በሻምፒዮንስ ሊግ ጉዞውን ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የ2017 ቶታል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ  የምድብ ፉክክር 25ኛ ዙር ወዘተ ቢሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ስታድየም የቱኒዚያውን ኤስፔራንስ የፊታችን ማክሰኞ ያስተናግዳል፡፡ ባለፈው ሳምንት የቀጠለው በምድብ  ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጭ ከደቡብ አፍሪካው ሜመሎዲ ሰንዳውንስ ጋር ተገናኝቶ 0ለ0 አቻ ሲለያይ፤ በምድብ 3  ሌላ የቱኒዚያው ኤስፔራንስ ዴቱኒስ በሜዳው የዲ.ሪ ኮንጎውን ኤኤስ ቪታ አስተናግዶ 3ለ1 አሸንፏል፡፡
ይህ በእንደህ እያለ ባለፈው ሐሙስ ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2009 የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ሻምፒዮናነት ክብሩን ያረጋገጠ ሲሆን ኤስፔራንስም በተመሳሳይ ቀን የቱኒዚያ ሊግ 1 አሸናፊነቱን አግኝቷል፡፡ ስለሆነም የፊታችን ማክሰኞ በአዲስ አበባ ስታድየም የሚደረገው የሁለቱ ክለቦች ፍልሚያ የሻምፒዮኖች ትንቅንቅ ይሆናል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈው ሰሞን ለምድቡ የመጀመርያ ጨዋታ ወደ ደቡብ አፍሪካዋ ከተማ ፕሪቶርያ ያቀናው 18 ተጨዋቾችን በመያዝ ወሳኙን የአጥቂ መስመር ተሰላፊ ሳላዲን ሰኢድ በዚህ ጨዋታ ላይ 1 ቅጣት አለማሰለፉ የግብ እድሎችን እንዳይፈጥር አድርጎታል። ይሁንና ኡጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ሮበርት አዶንካራ፤ እንዲሁም የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎቹ ደጉ ደበበ እና አስቻለው ታመነ ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ የቻሉበት ፍልሚያ ነበር። በፕሪቶርያ በሚገኘው የሜመሎዲ ሰንዳውንስ ስታድዬም በሺዎች የሚቆጠሩ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቅዱስ ጊዮርጊስ በህብረት በመደገፍ የፈጠሩትን ድምቀት ሚዲያዎች አድንቀውታል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ማርቲን ኖይ ከሜመሎዲ ሰንዳውንስ ጋር ከመጫወታቸው በፊት ለካፍ ድረገፅ በሰጡት አስተያየት የምድብ ፉክክሩ ላይ የሚገኙት ሁሉም ክለቦች የአፍሪካ ምርጦች እንደሆነ በመግለፅ ምንም አይነት ጨዋታ ቀላል አይደለም ብለው ነበር፡፡ ክለባቸው ከአምናው ሻምፒዮን ጋር  አቻ ሊወጣ የቻለው በሱፕር ስፖርት ስርጭት ስለሜመሎዲ ሰንዳውንስ ብዙ በማወቃችንና ልዩ ክትትል አድርገን በመዘጋጀታችን ነው ብለዋል፡፡‹‹ ሆላንዳዊ ነኝ፡፡ የጨዋታ ትንተና በዚያ አገር አሰልጣኝነት የተለመደ ነው፡፡ በተለያዩ የግንኙነት መረቦች መረጃዎች እንሰበስባለን፡፡ ያንን በመንተራስ ታክቲክ እነድፋለሁ›› በማለትም ለካፍ ኦንላይን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በአፍሪካ እግር ኳስ በአሰልጣኝነት ሲሰሩ 17 ዓመታን ያስቆጠሩት ማርቲ ኖይ በ2012 እኤአ ላይ በኬፕታውኑ ክለብ ሳንቶስ የሰሩበትም ልምድ ስላላቸው በርግጥም ስለደቡብ አፍሪካ ክለቦች እንግዳ አይደሉም፡፡
ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በተደረገው ጨዋታ በሜመሎዲ ሰንዳውንስ በኩልም ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ተጨዋች ኡጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ዴኒስ ኦንያንጎ ነበር፡፡ በደቡብ አፍሪካ ሊግ የወሩ ኮከብ ሆኖ ጨዋታውን የተሰለፈው የ31 ዓመቱ ዴኒስ ኦንያንጎ በ2005 እና በ2006 እኤአ ላይ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ መጫወቱ የሁለቱን ክለቦች ግንኙነት ልዩ አድርጎታል፡፡ የኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ሆኖ የሚያገለግለው ዴኒስ ኦንያንጎ በ2016 እኤአ ላይ አገሩን ከ38 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያበቃ፤ ከክለቡ ሜመሎዲ ሰንዳውንስ ጋር በ2016 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና የአፍሪካ ክለቦች ሱፕር ካፕ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ ሊግ ሻምፒዮን በመሆን 3 ዋንጫዎችን የሰበሰበ ነው፡፡ በተጨማሪም በ2016 በአፍሪካ ውስጥ የሚጫወት አፍሪካዊ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ በካፍ ሽልማት ያገኘ ነው፡፡ ዴኒስ ኦንያንጎ ከጨዋታው በፊት ለሱፕር ስፖርት በሰጠው አስተያየት ‹‹የቀድሞ ክለቤን የምገጥምበት አጋጣሚ በመፈጠሩ ደስ ብሎኛል፡፡ ስሜታዊ አይደለሁም፤ በፕሮፌሽናልነት የማገለግለው ክለቤን ነው ብሎ ነበር፡፡ የሜመሎዲ ሰንዳውንስ ዋና አሰልጣኝ ደግሞ የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድንን ሲያሰለጥኑ የነበሩት ፒትሶ ሞስማኔ ናቸው፡፡ በ2016 በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ምርጥ አሰልጣኝ ሆነው ለሽልማት የበቁት ፒትሶ ‹‹ የምንገኘው በሞት ምድብ ነው፡፡ ዘንድሮ የሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ፉክክር የሽልማት ገንዘቡ በማደጉ እና የቴሌቭዥን ስርጭቱ በመስፋቱ ጠንካራ ነው፡፡ የምንገኘው በሞት ምድብ ነው። ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ሞሲማኔ ክለባቸው በሜዳው ነጥብ መጣሉ አላስደሰታቸውም፡፡ ክለባቸው ባለፈው የውድድር ዘመን የአህጉሪቱ ሻምፒዮን ለመሆን ሲበቃ በመላው አፍሪካ በመዘዋወር ያደረጋቸው ጨዋታዎች በተጨዋቾቹ ላይ መዳከም መፍጠሩን ምክንያት አድርገውም ጠቅሰዋል። በዘንድሮ የደቡብ አፍሪካ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቡ የነበረበት የጨዋታዎች መደራረረብ ተፅዕኖ መፍጠሩንም ያማርራሉ፡፡ ሜመሎዲ ስንዳውንስ የአምና ሻምፒዮናነቱን ለማስጠበቅ ሊከብደው ይቻላል ያሉት አሰልጣኙ በ2ኛ ዙር ጨዋታ፡፡ ወደ ኪንሻሳ በመጓዝ ለምናስመዘግበው ውጤት ከተጨዋቾቼ ቁርጠኝነት እጠብቃለሁ ብለዋል፡፡ ኤኤስቪታ ክለብ በአርቴፊሻል ሜዳ ጨዋታውን በማስተናገድ ብልጫ ሊወስድ ስለሚችል ተጫዋቾቻቸው አዕምሯቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከምድቡ የመጀመርያ ጨዋታዎች በኋላ ኤስፔራስን ዴ ቱኒስ በ3 ነጥብ እና በ2 የግብ ክፍያ መሪነቱን ሲይዝ ሜመሎዲ እና ጊዮርጊስ በእኩል 1 ነጥብ ያለምንም ግብ ተከታታይ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ኤኤስ ቪታ ያለምንም ነጥብ በመጨረሻ ደረጃ ላይ ነው፡፡
የምድብ ፉክክሩ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች በሚቀጥለው ሳምንት ሲደረጉ ማክሰኞ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው የቱኒዚያውን ኤስፔራንስ ዴ ቱኒዝ ሲገጥም፤ የዲ.ሪ ኮንጎው ኤኤስ ቪታ  የአምናውን የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ  ሜሞሎዲ ሰንዳውንስ በኪንሻሳ ከተማ ያስተናግዳል፡፡

Read 1958 times