Saturday, 20 May 2017 13:10

ማራቶንን ከ2 ሰዓትበታች ለመግባት በናይኪ ሙከራ…

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 3 ማራቶኒስቶች፤ 20 ሳይንቲስቶች፤ 30 አሯሯጮች ተሳትፈዋል

      የአሜሪካው የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ናይኪ Breaking2 በሚል ስያሜ በነደፈው ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት  ልዩ ፕሮጀክት የመጀመርያውን ሙከራ ከሁለት ሳምንት በፊት አድርጓል፡፡ በሙከራ ውድድሩ ኬንያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ ለታቀደው ሰዓት በጣም በመቃረብ ሲሳካለት፤ ኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰ እና ኢትዮጵያዊው ሌሊሳ ዴሲሳ ግን አልተሳካላቸውም ነበር።
ናይኪ ከ2014 እኤአ ጀምሮ በፕሮጀክቱ ላይ በተለያዩ አቅጣጫዎች ሲሰራ ቢቆይም ስለመጀመርያው የሙከራ ውድድር ለመላው ዓለም  በይፋ በማስታወቅ የሰራው ከ6 ወራት ወዲህ ነበር፡፡
በናይኪ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች የመግባት Breaking2 ፕሮጀክት  ላይ 3 የዓለማችን ምርጥ ማራቶኒስቶች ተሳትፈዋል፡፡ በማራቶን የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሆነውና የ32 ዓመቱ ኬንያዊ አትሌት  ኤሊውድ ኪፕቾጌ፤ በማራቶን በዓለም ሻምፒዮና የነሐስ ሜዳልያ ያገኘው፣ የቦስተን ማራቶንን ለሁለት ጊዜያት ያሸነፈው የ27 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ እና የዓለም የግማሽ ማራቶን ክብረወሰን ባለቤት የሆነው የ35 ዓመቱ ኤርትራዊ አትሌት ዘረሰናይ ታደሰ ናቸው፡፡ ሶስቱ የማራቶን አትሌቶች በናይኪ ፕሮጀክት ስር በመታቀፍ ለመጀመርያው የሙከራ ውድድር ዝግጅት ሲያደርጉ ነበር፡፡ ለፕሮጀክቱ በሰጡት ትኩረትም በትልልቅ የማራቶን ውድድሮች በመሳተፍ የሚያገኟቸውን የሽልማት ገንዘቦች ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ትተዋል። ማራቶኒስቶቹ በፕሮጀክቱ ላይ በሚኖራቸው ተሳትፎ የትጥቅ ስፖንሰራቸው ከሆነው ናይኪ በይፋ ያልተገለፁ ክፍያዎችን እንዳገኙ ግን መረጃዎች አውስተዋል፡፡ በተለያዩ የሙያ እና የእውቀት መስኮች ከተሰባሰቡ የዓለማችን ምርጥ የአትሌቲክስ ስፖርት የባለሙያዎች ቡድኖች ጋር ዝግጅቶቻቸውን አድርገዋል። በስፖርት ሳይንስ፤ ስልጠና፤ ህክምና አዳዲስ አሰራሮችን በመመራመር በBreaking2 ፕሮጀክት ላይ የሰሩት  ከ20 በላይ ሳይንቲስቶች ናቸው፡፡ ይህም በፕሮጀክት አይነቱ ግቡ የባለሙያዎች ስብስብ ነው ናይኪ አዳዲስ የመሮጫ ጫማዎች እና ማልያዎችን ከማቅረቡም በላይ፤ በላቀ ደረጃ የሳይንስ፤  ቴክኖሎጂ፤ የአመጋገብ፤ የውሃ እና ሃይል ሰጪ መጠጦችን አዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ከ30 በላይ ምርጥ አሯሯጮችን በመመደብም በስፋት ተንቀሳቅሷል። ለዚሁ ሙከራ ተብሎ ዙም ሱፕርፍላይ ኤሊት የተባለ የመሮጫ ጫማን ለሶስቱ አትሌቶች በአዲስ መልክ ናይኪ ያመረተ ሲሆን በውድድሩ ወቅት ሰዓቱንና የአሯሯጭ እና የራጮቹን ፔስ የሚለካ የኤሌክትሪክ መኪናም ነበር፡፡
በፕሮጀክቱ ስኬታማነት የስፖርቱን የወደፊት እድገት ለማነሳሳትና ለፕላኔታችን ምርጥ አትሌቶች መነቃቃትን የመፍጠር ዓላማን ያነገበው ናይኪ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በፕሮጀክቱ በሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ ሚሊዮኖችን የሚያነሳሳ ውጤት  ይመዘገባል በሚል ተስፋ ነበረው፡፡
በBreaking2 የሙከራ ውድድሩን ፕሮጀክት ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት ናይኪ የመጀመርያ የሙከራ ውድድሩን ያደረገው በጣሊያኗ ከተማ  በሚገኘው  አውቶድሮሞ ናዚዮናሌ ሞንዛ በተባለ ዝግ ስታድዬም ነበር፡፡ የፎርሙላ ዋን የመኪና ሽቅድምድም መወዳደርያ ትራክ ላይ ነበር የአንድ ዙር መሙ ርዝማኔ 100 ሜትር የሆነው የስታድዬሙ ትራክ በመጠምዘዣዎቹ ምቹነት እና አካባቢ ተስማሚ የአየር ሁኔታ በናይኪ ተመራጭ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በማራቶን የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ ሶስተኛ ሆኖ የተቀመጠውን 2፡03፡05 በ2016 እኤአ ላይ በለንደን ማራቶን ሲያሸንፍ ያስመዘገበውና የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ኤሊውድ ኪፕቾጌ በፕሮጀክቱ የመጀመርያ ሙከራ ከባዱን ፈተና በአስደናቂ ብቃት በመወጣት ልዩ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ የማራቶኑን ርቀት ሲጨርስ የገባበት ሰዓት 2፡00፡25 ነበር፡፡ ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት  በ26 ሰከንዶች በመዘግየቱ አልተሳካለትም ፤ ይሁን እንጅ የመኪና መወዳደደርያ ትራኩን የ100 ሜትር መም 422 ጊዜ ሲዞር እያንዳንዱን ዙር በ17 ሰከንዶች መሸፈኑ ለብዙዎች የገረመ ብቃት ነበር፡፡ የዓለም ማራቶን ሪከርድ በ2014 የኬንያው ዴኒስ ኪሜቶ በበርሊን ማራቶን በ2፡02፡57 የተመዘገበው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በናይኪ ፕሮጀክት የተሳተፈው ኪፕቾጌ የገባበት ሰዓት ይህን የዓለም የማራቶን ሪከርድን በ2 ደቂቃ ከ32 ሰከንዶች ቢያሻሽልም በክብረወሰንነት ግን የሚመዘገብ አይደለም፡፡ የመጀመርያው ምክንያት የመወዳደርያው ትራክ በአይኤኤኤፍ እውቅና ያገኘ ባለመሆኑ ሲሆን በውድድሩ ላይ የተመደቡ አሯሯጮች እየተቀያየሩ መስራታቸው ሌላው ነው ፡፡ ኪፕቾጌ ከውድድሩ በኋላ ያስመዘገበውን ሰዓት ታሪካዊ ክስተት ብሎታል፡፡ በአጠቃላይ ግን  የናይኪ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች የመግባት ሙከራ የመላው ዓለምን ትኩረት የሚስብ ትልቅ ክስተት ሲሆን የዓለም ሚዲያዎች አውስተዋል፡፡ ከኤሊውድ ኪፕቾጌ ሌላ መብቃቱን ዘረሰናይ ታደሰ እና ሌሊሳ ዴሲሳ በተመሳሳይ ፕሮጀክት ታቅፈው እየሰሩ ቢሆንም አልሆነላቸውም፡፡ የዓለም ግማሽ ማራቶን ሪከርድ ባለቤት የሆነው የኤርትራው ዘረሰናይ  በ2፡06፡51 ሲጨርስ የኢትዮጵያ ሌሊሳ ደሲሳ ደግሞ በ2፡14፡10 ርቀቱን ሸፍኗል፡፡
ለታሪካዊው የማራቶን ከፍተኛ ውጤት በተለያዩ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ ግምት የሚያገኙት ከሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ኬንያና ኢትዮጵያ የሚወጡ ማራቶኒስቶች ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ በቆጂ በምትባለዋ የክልል ከተማ እንዲሁም በኬንያ ኤልዶሬት እና ኢቴን በተባሉት ከተማዎች እንደሚገኙ የብዙዎች እምነት ነው፡፡ በእነዚህ የምስራቅ አፍሪካ የገጠር ከተሞች በማራቶን ፈጣን ሰዓቶችን የሚያመዘግቡ እና ትልልቅ ውድድሮችን የሚያሸንፉ ሯጮች በብዛት እንደሚገኙ የሚታወቅ ነው፡፡ በየከተሞቹ ያሉት መልክዓምድራዊ ሁኔታዎች፤ የድህነት ኑሮ፤ የስኬታማ ማራቶን ሯጮች መብዛት፤ ባህላዊ የአመጋገብ ስርዓቶች ለማራቶን ስኬታቸው ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ከዚህ አንፃር በናይኪ Breaking 2 ፕሮጀክት ኤሊውድ ኮፕቾጌ ያስመዘገበው ውጤት ግምቱን ወደ ኬኒያ አትሌቶች እንዲያጋድል አድርጎታል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሌሊሣ ዴሢሣ የገባበት ሰዓት ከምርጥ ማራቶኒስቶች አማካይ ሰዓት የራቀ መሆኑ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ የሚያስቆም ነው፡፡  
ናይኪ በመጀመርያ የሙከራ ውድድሩ ከ2 ሰዓት በታች የመግባት እቅዱን ማሳካት ባይችልም በማርኬቲንግ እንቅስቃሴዎቹ ተሳክቶለታል፡፡ በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማህበራዊ ሚዲያዎች ያገኘው ትኩረት የስፖርት ትጥቅ አምራቹን ብራንድ ያሳደገ ነበር፡፡ ስለBreaking2 የሚለው የፕሮጀክቱ በሚሊዮኖች እየተጠቀሰ በመላው ዓለም በትልቅ የአትሌቲክስ ስፖርት ዘጋቢ ድረገፆች፤ መፅሄቶች፤ ጋዜጠኞች እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያዎች ተዋውቋል፡፡ ናይኪ በዚህ ፕሮጀክት ላለፉት 3 ዓመታት ሲሰራ ለማስታወቂያ የመደበው በጀት ከ800 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ ብራንድዎች የተባለ ተቋም ይፋ ባደረገው መረጃ በማህበራዊ ሚዲያዎች ስለሙከራው ከ600ሺ ጊዜ በላይ መጠቀሱን 400ሺ ጊዜ #Breaking2 የሚለው ቃል መፃፉን አስታውቋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአትሌቲክስ ዙርያ ትንታኔ የሚሰሩ ድረገፆች እና ኤክስፐርቶቻቸውም አድናቆት ሰጥተውታል፡፡ በላይቭ ስትሪሚንግ በኢንተርኔት ድረገፅ ውድድሩ ባገኘው ስርጭት በ2 ቀናት 5 ሚሊዮን ተመልካች ማግኘት ችሏል፡፡ እነ ኪፕቾጌ የሮጡበት ቫፖርፍላይ ኤሊት የተሰኘው የናይኪ የጫማ ምርት በ250 ዶላር የሚሸጥ ሲሆን የሙከራ ውድደሩ የምርቱን ገበያ አሟሙቆታል፡፡
ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት እንደሚቻል በማቀድ በፕሮጀክት ደረጃ የሚንቀሳቀሰው ናይኪ ብቻ አይደለም፡፡   ስኮትላንዳዊው ፕሮፌሰር ያኒስ ፒስተሊደስ በsub2hr ፕሮጀክታቸው ከጀርመኑ የትጥቅ አምራች ኩባንያ አዲዳስ ጋር በመንቀሳቀስ ፈርቀዳጅ ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች መግባትን አስመልክቶ በርካታ በአትሌቲክስ ላይ በሚያተኩር ዘገባቸው በሚታወቁ መፅሄቶች፤ ድረገፆች እና የመረጃ ሚዲያዎች በየጊዜው ትንታኔዎች መቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡ በአጀንዳው ላይ በማተኮር የተፃፉ ታዋቂ መጽሐፍትም አሉ፡፡ በተለይ በኤድ ሲዛር የተፃፈውን “The quest to Run Impossible Marathon መጥቀስ ይቻላል፡፡  
ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት በርካታ ወሳኝ ሁኔታዎችን እና አስተዋጽኦዎች ይኖራሉ፡፡ 1፡59፡59 ሰዓትን በማራቶን ለማስመዝገብ 1 ማይል ርቀትን በ4 ደቂቃ ከ34 ሰኮንዶች መሸፈን ግድ ይሆናል፡፡ ከወቅታዊ ሪከርድ በየማይሉ በ7 ሰኮንዶች በፈጠነ አሯሯጥ ነው። የስፖርቱ  ሳይንቲስቶች የማራቶን ርቀትን በሰው ልጅ የተፈጥሮ ብቃት ለመሸፈን የሚቻልበት የመጨረሻው የሪከርድ ሰዓት ወሰኑ 1፡57፡57 እንደሆነ የሚገልፁ ሲሆን ይህም ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት እንደሚቻል የሚያመለክት ነው፡፡  
ስፖይክ የተባለና ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ጋር የሚሰራ ድረገፅ በአንድ ወቅት  በሰራው ዘገባ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የሚያስፈልጉ 13 ወሳኝ ሁኔታዎችን ዘርዝሯል፡፡ ከሪኮርዱ 5 ደቂቃዎች ባለፉት 20 ዓመታት መቀነሳቸው፤ አሁን ከተያዘው ሪኮርድ ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የሚቀሩት ከ3 ያነሱ ደቂቃዎች መሆናቸው፤ ከ2 ሰዓት 05 ደቂቃዎች በታች የሚገቡ አትሌቶች ከ30 በላይ ማለፋቸው፤ በማራቶን የፈጣን ሰዓቶች ደረጃ በየዓመቱ እስከ 30ኛ ደረጃ አዳዲስ አትሌቶች በብዛት መግባታቸው፤ በመጀመሪያ ማራቶናቸው ከ2፡04 በታች የሚገቡ አትሌቶች መገኘታቸው፣ በትራክ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ አትሌቶች ወደ ማራቶን በመግባት ስለሚሳካላቸው የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በአትሌቲክስ ስፖርት አሰለጣጠን በሳይንሳዊና ቴክኖሎጂ የምርምር ተግባራት የተጋዙ ፕሮጀክቶችንም በትኩረት መስራትን ወሳኝ እንደሆነ የሚገልፁ አሉ፡፡
የሰው ልጅ በሚችለው ብቃት ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት  የስልጠና ሳይንስ እና ቴክኖሎጂም ለውጥ የሚፈጥሩም ናቸው፡፡ ከ40 አመት በፊት የነበረው ስልጠና አሁን በከፍተኛ ደረጃ በምርምሮች ማደጉ እንደ አጋዥ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችል ነው።  በአዲዳስ፤ በናይኪ እና በፑማ የትጥቅ አምራች ኩባንያዎች የሚቀርቡ የመሮጫ ማልያዎችና ጫማዎችም የሚኖራቸው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም። በማራቶን ውድድሮች የሚመደቡ አሯሯጮች ልዩ ብቃት እና በማራቶን ውድድሮች ዳጎስ ያሉ ሽልማቶች፤ የስፖንሰርሺፕ እና የቦነስ ክፍያዎች ከፍተኛ ገቢ መገኘቱ ሌሎቹ አስተዋፅኦዎች ናቸው፡፡
በመላው ዓለም ከሚካሄዱና የሪከርድ ሰዓት ህጋዊ ከሚሆንባቸው ትልልቅ  ውድድሮች መካከል ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት ዋና እጩዎች የሚባሉት በበርሊን እና ለንደን ከተሞች  የሚዘጋጁት ማራቶኖች ነበሩ፡፡ ናይኪ የመጀመርያ ሙከራን በመኪና ውድድር ትራክ ላይ ማድረጉ ብዙዎችን አላስደሰተም፡፡
ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች መግባት በተለያዩ ጥናቶች እና ትንታኔዎች እስከ 2028፤ 2035 ወይም 2041 እኤአ ላይ እንደሚሳካ ይገመታል፡፡ በናይኪ Breaking2 ፕሮጀክት በ2017 ለማሳካት ታቅዶ አልሆነም፡፡ ስኮትላንዳዊው ፕሮፌሰር ያኒስ ፒስታሊደስ በበኩላቸው ከአዲዳስ ጋር በሚሰሩበት በsub2hr ፕሮጀክታቸው እስከ 2019 እኤአ የሚገኝ ውጤት ነው በሚል ስራቸውን ቀጥለዋል፡፡

Read 1456 times