Saturday, 20 May 2017 13:12

በእርግዝና ጊዜ ከ9-16 ኪሎ ክብደት መጨመር?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንዲት ሴት ስታረግዝ በተለይም የእንግዴ ልጅ ከሚባለው ጋር በተያያዘ አዳዲስ ሆርሞኖች ስለሚመረቱ በሁሉም የሰውነትዋ ክፍሎች ላይ አዳዲስ ለውጦች ይታያሉ። ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ መምህርና የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ለዚህ እትም እንደገለጹት ለእርጉዝ ሴት የአካል ለውጥ ምክንያት የሚሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። እርጉዝ ኤት የሰውነትዋ ክብደት ይጨምራል። ይህ የሰውነት ክብደት መጨመር ደግሞ የሚፈለግና የሚጠበቅ ሲሆን አንዲት ሴት በአንድ የእርግዝና ወቅት ከ9-16 ኪሎ ትጨምራለች።ይህ ኪሎ ከሚጨምርበት ምክንያትም ዋናዋናዎቹ፡-
የሚያድገው ልጅ ጽንስ መኖሩ፣
እንግዴ ልጅ ፣
የሽርት ውሀ ፣
የራስዋ ደም መጠን መጨመር ቀይ የደም ሴል መጠን ፣የውሀው መጠን
የኩላሊት መጠን መጨመር ፣የሚያመርተው የሽንት መጠን መጨመር፣
የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ማደግየጡት መጨመር፣
የማህጸን ማደግ ማህጸን ከእርግዝና በፊት ከ70 እስከ 100 ግራም ሲሆን ልክ እርግዝናው ዘጠኝ ወር ሲደርስ አንድ ኪሎ ይደርሳል።ይህም ማለት ከአስር አጥፍ በላይ ክብደቱ ይጨምራል።
ከዚህ በተጨማሪም በአይን በቀላሉ የሚታዩ የሰውነት ለውጦች ይኖራሉ። ለምሳሌም በቆዳ ላይ መጥቆር ፣በሆድ መካከል የሚታይ ጥቁረት በሆድ ፣በታፋ እና በጭን አካባቢ የሚታዩ ሸንተረር መሰል ነገሮች ይታያሉ። ሁሉም እርጉዝ እናቶች ላይ ባይሆንም 80 % የሚሆኑት ላይ የእግር ማበጥ ይታያል። ብዙ ሴቶች የእግር ማበጥን እንደችግር ሊያዩት ይችላሉ። ነገር ግን ፊትና እጅ አብረው የሚያብጡ ካልሆነ በስተቀር ብቻውን እንደችግር ሊታይ አይገባውም። የእጅ እና ፊት እብጠት ከታከለ ግን ከደም ግፊት ጋር በተያያዘ ወይንም ሌላ ችግር ሊሆን ስለሚችል ስጋት ሊኖር ገባል።
አንዲት እናት ከእርግዝና በፊት የነበራት ክብደት በእርግዝና ወቅት ይጨምራል። ከወሊድ በሁዋላ ደግሞ በተወሰኑ ሳምንታት ውስጥ ሌላ አይነት ክብደት ይመዘገባል። ይም ሂደት የታወቀ ነው። ነገር ግን በምን መንገድ ነው ከእርግዝና በፊት ወደነበረችበት ክብደት መመለስ የምትችለው? ተብሎ ሲጠየቅ ብዙ ምላሾች ይኖሩታል። አንዲት ሴት ወፈርፈር ብላ ስትታይ ወልደሽ ነው እንዴ? የሚለው ጥያቄም የተለመደ ነው። ስለዚህ አንዲት ሴት ከእርግዝናና ከወሊድ በሁዋላ የነበረውን ክብደትዋን ቀድሞ ወደነበረበት ወፍራም ካልነበረች እንዴት ልትመልሰው ትችላለች ሲባል ከአመጋገብና ከአኑዋኑዋርዋ ጋር የተገናኘ ይሆናል። ብለዋል ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ።
ምግብን አለማስወገድ፡-
አንዳንድ እናቶች በእርግዝና ጊዜ የተከሰተውን ክብደት ለማስወገድ ሲሉ (diet) ምግብን ወደማስወገድ ደረጃ የሚደርሱ አሉ። ይህ ግን ስህተት ነው። አንዲት እናት በወለደቸበት ወቅት ልትመግበው ጡትዋን ልታጠባው የሚገባው ልጅ አላት። በዚህ ላይ ሌሎች የእናትነት ጭን ቀቶች ተደራርበው ምግብን ከማስወገድ ጋር ከፍ ያለ ጉዳት ሊያደርሱባት ይችላሉ። ከሚደር ሱት ችግሮች መካከልም ጭርሱንም ውፍረትን እንዲመጣ ማድረግ አንዱ ነው። ስለዚህም ምግብን ማቆም ሳይሆን ምግብን አመጣጥኖ መውሰድ ብልህነት ይሆናል። ለምሳሌም አትክ ልትና ፍራፍሬ ፣ቅጠላቅጠል ወይንም የእህል ዘሮች እንደ ስንዴ ገብስ የመሳሰሉ በቆሎ መልክ የሚዘጋጁ ምግቦችን መጠቀም ጠቃሚ ይሆናል።
ከፍተኛ ንጥረ ነገር ያላቸውን ምግቦች መመገብ፡-
የወለደች ሴት ከፍተኛ ንጥረ ነገር ያላቸውን እና ቀለል ያለ ፕሮቲን እና ቅባት ያላቸውን ምግቦች መመገብም አለባት።ለምሳሌም የ ኦሜጋ 3 ውጤት ባለቤቶች ከሆኑት እንደ አሳ ሰርዲን ቱና ከዚህም በተጨማሪ ወተት ፣እርጎ፣ የተፈጨ ስጋ፣ የዶሮ ስጋ እንዲሁም ባቄላ ነክ ነገሮችን በፕሮግራም በምግብ ውስጥ አካቶ መውሰድ ይጠቅማል። ከላይ የተጠቀሱትና መሰል ምግቦችን ከፍተኛ ቅባት የሌላቸውና ከፍተኛ ንጥረ ነገር ያላቸው በመሆናቸው ጠቀሜ ታቸው ለእናትየውም ጡት ለሚጠባው ልጅም ነው።
ጡት ማትባት፡-
ጡት ማጥባት ሌላው ክብደትን ለመቀነስ የሚረዳ ዘዴ መሆኑን አንዳንድ ጥናቶች ያስረዳሉ። አንዳንድ ጥናቶች ደግሞ ጡት ማጥባትና ክብደት ምንም አይገናኙም ይላሉ። ዋናው ነገር ጡት ማጥባት ለልጆች እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ ወላጆች ይህን እንዲፈጽሙ ይደገፋል።ስለዚህም እናቶች በጡት ማጥባት ወቅት ጥሩ ወተት እንዲኖራቸው በሚል ለክብደት የሚዳርግ ምግብ ከመመገብ ተወግደው ቅባትነት የሌላቸውን ምግቦች ማለትም ከላይ እንደተጠቀሰው የእህል ዘር ቅጠላ ቅጠል እና ፍራፍሬዎች እንደ እንጆሪ ብርቱካን የመሳሰሉትን መጠኑ ሳይበዛ እንቁላል ጭምር መመገብ ፣ቡናማ መልክ ያለው ሩዝ የመሳሰሉትን ቢመገቡ ይመከራል።
ውሀ መጠጣት፡-
ሌላው ክብደትን ለመቆጣጠር የሚያስችለው ዘዴ ውሀ መጠጣት ነው። ውሀ በደንብ መጠጣት ረሀብን አስወግዶ ብዙ ምግብ ከመውሰድም ሊያስቆም ስለሚችል ጠቃሚ ነው። በተያያዥም አንዳንድ ሕመሞችን ለማስወገድ ፣በሰውነት ውስጥ የሚፈጠሩ መርዛማ ነገሮችንም ለማስወገድ ስለሚረዳ በተጨማሪም ምግብን ለመፍጨት ስለሚያፋጥን ውሀ በቀን ቢያንስ እስከ ሁለት ሊትር መጠጣት ይመከራል። በቂ ውሀ ጠጥቻለሁ? ወይንስ አልጠጣሁም ? የሚለውን ለማወቅ አንዲት እናት የሽንትዋ ቀለም ውሀማ መሆኑን ወይንም በየ3 እና 4 ሰአት መሽናትዋን መከታተል አለባት።
የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ፡-
የሰውነት እንቅስቃሴ ወይንም እስፖርት መስራት ክብደትን ለመቆጣጠር አንዱ መንገድ ነው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የእናትየውን ክብደት ከመቀነሱም በላይ በእናትየውም ሆነ አዲስ በተወለደው ልጅ ላይ ሊኖር የሚችለውን ጭንቀት ያስወግዳል። ከዚህም በተጨማሪ የእንቅልፍ ሁኔታን ያስተካክላል። በእርግጥ አንዲት እናት ልጅ በወለደች በጥቂት ቀን ውስጥ ወደ እስፖርት ማዘውተሪያ መሄድ ላይጠበቅባት ይችላል። ነገር ግን በየቀኑ ልጅዋን ይዛ በቤት ውስጥ ወይንም በግቢው ውስጥ እርምጃ ወይንም ሶምሶማ በማድረግ መጀመር ትችላለች። በሳምንት ጊዜ ውስጥ የተለያዩ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን እስለ 150 ደቂቃዎች በመመደብ መፈጸም ተገቢ ነው። ከተቻለም ለወላድ እናቶች ፕሮግራም ወዳላቸው የእስፖርት ቤቶች በመሄድ እንቅስቃሴውን ማድረግም ይመከራል። አንዲት እናት የእስፖርት እንቅስቃሴ ከማድረ ግዋ በፊት በተለይም የቀዶ ሕክምና ተጠቃሚ ከሆነች ከሐኪምዋ ጋር መመካከር ይጠበቅ ባታል።
ጥሩ እንቅልፍ፡-
አዲስ ልጅ መወለዱን ተከትሎ በሚመጡ የተለያዩ ኃላፊነቶችና ግዴታዎች ምክንያት ልጅ ከመወለዱ በፊት እንደነበረው በቀን የስምንት ሰአት እንቅልፍ መተኛት ሊከብድ ይችላል።ነገር ግን አንዲት እናት ጥሩ እንቅልፍ ካላገኘች በወሊድ ምክንያት የመጣ ውፍረትን እንዳይቀንስ በማድረግ ረገድ እንደ አንድ ትልቅ እንቅፋት ሊቆጠር ይችላል። አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከ5 ሰአት በታች የሚተኙ እናቶች በቀን 8 ሰአት ከሚተኙት ጋር ሲነጻጸር ውፍረታቸውን መቀነስ እንደሚከብዳቸው ይገልጻል። ሙሉ ስምንት ሰአቱን በቀጥታ መተኛት እንኩዋን ባይቻል በተገኘው አጋጣሚ አጫጭር እንቅልፍ በመተኛት እረፍት በማድረግ ማካካስ እንደሚገባ ጥና ቶች ይመክራሉ።
በአጠቃላይም ልጅ ባረገዙ ጊዜ የሚከሰተውን ውፍረት ከወሊድ በሁዋላ ቀድሞ ወደነበሩበት ለመመለስ የህክምና ባለሙያዎችንና በተለይም የምግብ ስርአት አማካሪዎችን ማማከር ጠቀሜታው የጎላ ነው። የህክምና ባለሙያዎቹ በምን ያህል ጊዜ ምን ያህል ክብደት መቀነስ እንደሚገባና ምን አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ አስፈላጊውን ምክር ይለግሳሉ። የምግብ ስርአት አማካሪዎቹ ደግሞ ክብደትን ለመቀነስ ሲባል ምግብን ከመውሰድ መታቀብ ወይንም ( diet ) ውስጥ መግባት ትክክል አለመሆኑንና ይልቁንም በደንብ የተመጣጠነ የምግብ አይነትን መጠቀም ለእናትየውም ለተወለደው ልጅ ጡት አመጋገብም እንደሚረዳ ይመክራሉ። ምናልባት ከምግብ ሰአት ውጭ ባሉ ጊዜያት ረሀብ ቢሰማ በረሀብ ጊዜ ሊወሰዱ የሚችሉ በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ በቀላሉ የሚዘጋጁ ምግቦችን መመገብ ጠቃሚ ነው። ለምሳሌም በሀገራችን ከተለያዩ የእህል ዘሮች የሚዘጋጁ ቆሎዎችን መጥቀስ ይቻላል። ባጠቃላይም አንዲት እናት በእርግዝና ጊዜ የጨመረው ክብደትዋ ምን ያህል ነው? የሚለውን ሐኪምዋ አይቶ ይህ በአጭር ጊዜ ሊስተካከል ይገባዋል ወይንም በተወሰነ ጊዜ ማለትም እስከ 2 ወር ድረስ መቀነስ ይቻላል የሚለውን ማማከር ይችላል። ነገር ግን ክብደቱ ከእርግዝናም በፊት የነበረ ከሆነ ያንን ወደትክክለኛው የሰውነት አቋም ለማድረስ ከአመት በላይም ሊፈጅ ስለሚችል በትእግስት እርምጃ መውሰድ ከወላድዋ ይጠበቃል። እናቶች ምናልባትም ለተጨማሪ እርግዝና የሚዘጋጁ ከሆኑ አስቀድመው የሰውነት ክብደታቸውን ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል።

Read 7985 times