Sunday, 21 May 2017 00:00

በ2 አመታት 170 ሺህ ህጻናት ስደተኞች በአውሮፓ ጥገኝነት ጠይቀዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ባለፉት 2 አመታት ብቻ 170 ሺህ ያህል የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው ህጻናት ስደተኞች ወደ አውሮፓ አገራት በመግባት ጥገኝነት መጠየቃቸውንና በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በአለም ዙሪያ ያለ ወላጅ ወይም ረዳት ብቻቸውን የተሰደዱ ህጻናት ቁጥር ከ300 ሺህ በላይ መድረሱን ዩኒሴፍ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ የአለማችን ህጻናት ስደተኞች ቁጥር በአምስት እጥፍ ያህል ያደገ ሲሆን፣ እየተባባሰ በመጣው ደጋፊና ረዳት የሌላቸው ብቸኛ ህጻናት ስደተኞች ላይ የሚሳተፉ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች  በርካቶቹን ለባርነትና ለሴተኛ አዳሪነት እየዳረጉ ይገኛሉ፡፡
ባለፈው አመትና በዘንድሮው የፈረንጆች አመት የመጀመሪያ ወራት በጀልባ ተሳፍረው ወደ ጣሊያን ከገቡት ህጻናት ስደተኞች መካከል 92 በመቶ የሚሆኑት ብቻቸውን የተጓዙ ወይም ወላጅ ዘመዶቻቸውን በስደት ጉዞ ላይ ያጡ እንደሆኑና አብዛኞቹም የኤርትራ፣ ጋምቢያ፣ ናይጀሪያ፣ ግብጽ እና ጊኒ ዜግነት ያላቸው እንደሆኑ ዩኒሴፍ አስታውቋል፡፡
90 ሺህ ያህል የአፍሪካ ቀንድ አገራት ህጻናት በአገራቸው ውስጥና በአካባቢው አገራት ከተቀሰቀሱ የእርስ በእርስ ግጭቶች ለመሸሽ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ብቻቸውን ለመሰደድ እንደተገደዱም ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ በደቡብ ሱዳን የቀጠለውን የእርስ በእርስ ግጭት በመሸሽ በየቀኑ 100 ያህል የአገሪቱ ህጻናት ብቻቸውን ድንበር አቋርጠው ወደ ኡጋንዳ እንደሚሰደዱ ወርልድ ቪዥን የተባለው አለማቀፍ ተቋም ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እነዚሁ የአገሪቱ ህጻናት ያለምግብና መጠጥ እንዲሁም ደጋፊ ወላጅ ዘመድ ድንበር አቋርጠው ለቀናት በአስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚጓዙና ለተለያዩ የከፉ ችግሮች እየተጋለጡ እንደሚገኙም ዘገባው ገልጧል፡፡

Read 954 times