Sunday, 21 May 2017 00:00

ሱስ

Written by  በአለማየሁ ጌትነት (ኢብታ)
Rate this item
(16 votes)

 በነጭ ሸሚዙ ላይ ጠቆር ያለ ሹራብ ደርቦ  …ሱፍ ሱሪ ለብሶ …የሚያብረቀርቅ ቆዳ ጫማ ተጫምቶ፣  ተንቀሳቃሽ ስልኩን ጆሮው ላይ እንደሰካ  በኩራት ይራመዳል፡፡
“አዎ…. አዎ--- ከስራ እየወጣሁ ነው”  
“…መገናኘት እንችላለን….”
“…..አረ በጣም ናፍቀሽኛል …. እ...  እ… እንኳን እንዲህ ለቀናት ተለያይተን ቀርቶ….“
“ok!.. ok! 12 ሰዓት ….. የት?”
ድንገት የሆነ ነገር እጁን ቧጨረው…  ምን እንደተፈጠረ ከማስተዋሉ በፊት ... ስልኩን የነጠቀው ወጣት ቅያስ መንገዱን ይዞ ተፈተለከ።
መስፍን /ዘ ጀንትል ማን/ ተከትሎት መሮጥን ክብሩ ስላልፈቀደለት፣ ተንጠልጥሎ  የነበረ እጁን ወደ ኪሱ መልሶ ማሰብ ጀመረ…
መጀመሪያ...  ቤዛ!!  
እያያት እምትናፍቀው፣ እያቀፋት እሚመኛት ልዩ ሴት …ዝቅ አድርጋ እንደምትገምተው እያወቀ ከስሯ እንዳይጠፋ የምትስበው ፍጥረት … የሆነ ቀን በቃኸኝ እንደምትለው ባይጠራጠርም ተስፋ የማይቆርጥባት እመቤት … እንደ መምህሩ የሚቆጥራት፣ እንደ ፈጣሪው  የሚፈራት እንቁ   … ከፍ ዝቅ በሚለው የወጣቱ እጅ ውስጥ፤
 “ሄሎ….  ሄሎ……  መስፍኔ” እንደምትለው፤ አሰበ
ለጥቆ፤
“ስንገናኝ መልስ ያልሰጠሁሽ …. ብዬ የተፈጠረውን ስነግራት ምን ታስብ ይሆን”ሲል፤ አሰበ
ያች ሚስጢራዊ ሴት፤ ልቧን ይዛ ትስቅ ይሆናል……
በንዴት ጦፋ፤
“አንተ ወንድ አይደለህም፤ አላንጠለጠልክም፤ መንጠቁ ቢቀር ተነጥቀህ ትገባለህ!” ትለው ይሆናል….
“ጦስህን ይዞ ይሂድ አቦ!” ልትለውም ትችላለች…..
በንቀት እየገላመጠችው ፤
“አያያዙን አይተህ እንጎቻውን ቀማው አሉ” ብላ ትተርትበትም ይሆናል … ለሱ እምትለውን፤ እምታስበውን፤ እምታደርገውን ከማወቅ የምጽአት ቀንን በርግጠኝነት መናገር  ይቀለዋል።
አያድርገውና የሶስት ወር ተኩል ፍቅረኛህን ግለጻት ቢባል፤
“ቤዛ፤ ቀይ ቆንጆ፣ ተስማ ታቅፋ የማትጠገብ ሴት ናት” ከማለት የዘለለ መናገር አይችልም፡፡  …. አያውቃትም!
አንዳንዴ ደላላ ያላት፣ ከሀብታሞች ጋር ብቻ የምትወጣ ሴተኛ አዳሪ ትመስለዋለች፤ ብር ደሞ ጠይቃው  አታውቅም፤ በርግጥ ቅብጥብጥ ባደረጋት ቀን….
“ኦ ዛሬ የሆነች ልጅ አድርጋው ያየሁት ጫማ--”   ትለዋለች
“ምን አይነት?”
“ባለ እረዥም ተረከዝ ሆኖ….” ታስረዳዋለች  …ነግቶ እጁን አውለብልቦ እንደተለያት ... ደንበል ዘው ይላል፡፡
……. ሌላ ቀን በሌላ ቅብጠት ……
“ብታይ….. አዲስ የመጣ የራት ልብስ አለ፤ እንዴት ነፍስ መሰለህ ……..  መስፍኔ ሙት ያንን ለብሼ ብታየኝ መሞትህ ነበር”
“ለምን?”
“ካላገባሁሽ ሞቼ እገኛለሁ ትላለህ!”
“ብልስ?”
“እኔ ማግባት አልፈልግም ...ትዳር ያስጠላኛል”
በልቡ፤ “እኔን ማግባት!”  ይልና በአፉ “ምን አይነት?” ይላታል
…ሲለያዩ …ሸገርን ያዳርሳል …አመሻሽ ላይ የተጠቀለለ ነገር ይዞ የተቀጠረበት ቦታ ይገኛል፡፡
አንዳንዴ ባለ ቅኔ ትመስለዋለች፤ ግን ስትመሰጥና ስታነብ እንጂ ስትጽፍ አይቷት አያውቅም…
*   *   *
ሰው ቆም..  እንደ ማለት እያለ ‹ሚሮጠውን ወጣትና ምንም የማይናገረውን ሰለባ ያያል  …አሳቢው  …አስማት የሆነች ሀሳብ ተከስታለት፤   
“Yes!....” አለ
Yes! እኔ ሲሜን አወጣለሁ፤ እሷ ትደውላለች……
ሌላ መርገምት፤
“ሺት!! ሺት!!.. ይች የማትረባ ደደብ ገልቱ”
“ያዲስ አበባ መታወቂያ ስለሌለኝ ሲም ካርድ አውጭልኝ” ሲላት፤
“እሽ” ያለችውን…..  ደደብ
አሜሪካን ሀገር የመሄድ እድል አገኘሽ ሲሏት፤
 “እሽ” ብላ እብስ ያለችውን ገልቱ….  ሽማጫሽን ወረደባት
……..ቆሽቱ እርር ድብን አለ፡፡   
ቤዛን እንዴት ያግኛት፤
…ታክሲ ላይ ከተገናኙበት ቀን ጀምሮ አንድም ጓደኛ አስተዋውቃው አታውቅም፤ እንዲያውም ጓደኛ እንዳላት ስትናገር ሰምቷት አያውቅም፡፡
….እሱ ሊያወራት ዳር ዳር ካለ እንኳ፤
“ጓደኝነት ሰው እራሱን ማየት ሲፈራ የሚከለልበት ጥላ ነው  .. ልብ ካለህ የራስህ ጓደኛ ሁን …ድክመትህን ተቀበል እንጂ እሚሸፍንልህ አታነፍንፍ” ብላ ቀንዱን ትለዋለች፡፡
ማንነቷን ለማወቅ መስቀለኛ ጥያቄ ሲጠይቃት ... እግሯቿን አጣምራ  እንደተቀመጠች--- ውብ አይኖቿን ከቦርሳዋ በማይጠፋው እንቆቅልሽ  መጫወቻ ላይ  ሰክታ፤
“ምድር ሁሉን በውስጧ አምቃ ስለምትይዝ በሀይል የተሞላች ነች…   አፈትልኮ የሚወጣውን እሳተ ጎሞራ ግን ተመልከት፤ ሀይሉ በጊዜ የተገደበ ነው
… ወደ ተራ አለትነት ከመውረድ አያመልጥም…… ማንነትም እንደዛ ነው  .. ነገረ ስራህን ሚስጥር ስታደርገው፣ ወደ ውስጥህ ስታምቀው በሀይል ትሞላለህ… ስለዚህ ስለ እኔ አትቆፍር፤ ስለ አንተ አትዘባርቅ፤ በአብሮነታችን ዘና በል”  ብላ ስለምትዘጋበት ስለሷ አያውቅም  …. እሷ ደሞ ጭራሽ ስለሱ ማወቅ  አትፈልግም፡፡  
እጁን አውለብልቦ እንዲሸኛት የምትፈቅድለት ---- አንድ ቀን ወደ ገርጂ፣ ሌላ ቀን ወደ አየር ጤና፣ ሌላ ጊዜ ወደ አዲሱ ገበያ   …. ብቻ ውቃቤዋ ወደ መራት ላዳ ታክሲ ገብታ ----- ብን ነው፡፡
  ……..መገናኛችው መለያያቸው፣ በየሰፈሩ ---- በየጉራንጉሩ ---- በየሆቴሉ ያሉ አልጋ ክፍሎች!…… የታባቱ ያግኛት?!

Read 5069 times