Sunday, 21 May 2017 00:00

‹‹አንደኛ መውጣት በጣም ያስደስታል››

Written by 
Rate this item
(5 votes)

   ‹‹በዩኒቨርሲቲ ለማጥናት የመጀመሪያ ምርጫዬ ህክምና ነው፤ ካልሆነ ስፔስ ሳይንስ ባጠና አይከፋኝም››

     ኦልማርት ሱፐር ማርኬት ከቅድስት ማሪያም ዩኒቨርሲቲና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር “Excellence for Education” የተሰኘና በአዲስ አበባ የሚገኙ 20 የመንግስት መሰናዶ ት/ቤት ተማሪዎች
የሚወዳደሩበት የጥያቄና መልስ መርሀ ግብር አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ መርሀ ግብር ለ6530 ተማሪዎች እድል ተሰጥቶ ሚያዚያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም 3 ሺህ ተማሪዎች ለፈተና የቀረቡ ሲሆን ባለፈው ቅዳሜ ማጣሪያ ካለፉት 100 ተማሪዎች ምርጥ አስሩ ተለይተው፣ ባለፈው ሰኞ ምሽት በራዲሰን ብሉ ሆቴል ሽልማታቸውን ወስደዋል፡፡ በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ በውድድሩ 1ኛ ከወጣውና የአየር ጤና መሰናዶ ት/ቤት ተማሪ ከሆነው የ19 ዓመቱ ወጣት አቤል ሽፈራው ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

      ከመጀመሪያ አንስቶ አየር ጤና ነው ትምህርትህን የተከታተልከው?
አየር ጤና አካባቢ ባሉ ት/ቤቶች ነው የተማርኩት፤ የተወለድኩት ግን መሀል አዲስ አበባ አራዳ ክ/ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ቤተሰቦቼ በቤት ኪራይ ይኖሩ ስለነበር፣ ከዚያ ቤት ሰርተው ወደ ወለቴ ሄድን፣ አንደኛ ደረጃም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የቀጠልኩት ከ1-10ኛ ክፍል ካራ ቆሬ ረጲ 1ኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ሲሆን ለመሰናዶ ትምህርት ነው አየር ጤና መሰናዶ የገባሁት፡፡
የቤተሰብህ የኑሮ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ቤተሰቤ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ተቸግረው ነው ያስተማሩኝ፡፡ እነሱ በቅጡ ባልተማሩበትና ባልተደላደሉበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው ነው፣ እኔንም ሆነ ከእኔ በላይና በታች ያሉ እህትና ወንድሞቼን እያስተማሩ ያሉት፡፡ እነሱ ለእኔ አርአያዎቼ ናቸው፤ እኔም የእነሱ ውጤትና መገለጫ ነኝ፡፡ በጣም ነው የማመሰግናቸው፡፡
ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ እስካሁን በትምህርት ውጤትህ እንዴት ነህ?
የሚገርምሽ ከ1ኛ ክፍል ጀምሬ ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ፤ በተለይ ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ በከፍተኛ ትኩረት ነው ትምህርቴን ስከታተል የነበረው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሁሉም የትምህርት አይነት ጥሩ ውጤት በማምጣት የደረጃ ተማሪ ሆኜ ነው የቀጠልኩት፡፡ አሁንም ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት በዝግጅት ላይ ነኝ፤ የ12ኛ ክፍል ፈተናዬን በደንብ ለመስራት በመትጋት ላይ እገኛለሁ፡፡
እንደነገርከኝ እድሜህ 19 ዓመት ነው፡፡  16 እና 17 ዓመት ወጣቶች በአቻዎቻቸው ግፊት ወደ ብዙ ነገሮች የሚገቡበት እድሜ ነው፡፡ አንተ ይህን ተቋቁመህ ጎበዝ ተማሪ የሆንክበት ምስጢር ምንድን ነው?
በጣም ከባድ ጊዜ ነው፡፡ እንደምታውቂው ጊዜው የግሎባላይዜሽን ነው፡፡ ይህ ማለት ብዙዎቻችን በውጭ የኑሮ ዘይቤ ተፅዕኖ ውስጥ ነው ያለነው። ይህንን ተፅዕኖ ተቋቁሞ ማለፍ ራሱን የቻለ ሌላ ፈተና ነው፡፡ እኔ በበኩሌ፤ ከዚህ ፈተና ለማምለጥ ስል ከሚዲያ የራቅኩ ነኝ፡፡ ኢንተርኔትና ፌስቡክ ሁሉንም አልጠቀምም፤ ትኩረቴን ወደ ትምህርት ነው ያደረግሁት፡፡ ስልክ እንኳን ለመደወልና ለጥሪ ብቻ ነው የምጠቀመው፡፡ እነዚህን ነገሮች ልጠቀም ብዬ  ቤተሰቤን ብጠይቅ፣  የራሳቸውን ነገር ወደ ጎን አድርገው እንደሚያሟሉልኝ አምናለሁ፡፡ ግን በዚህ ወቅት ላይ ለእኔ አስፈላጊ ስላልሆነ አልፈልግም በሚል ወደ ትምህርቴ አዘንብያለሁ፡፡ በአጠቃላይ በትምህርቴ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ማንኛውንም ነገር ትቼ፣ ትምህርቴ ላይ ማተኮር ቅድሚያ የምሰጠው ተግባሬ ነው፡፡
ኦልማርት ያዘጋጀውን ውድድር እንዴት አገኘኸው ወይስ ኦልማርትን ከዚህ በፊት ታውቀው ነበር?
እውነት ለመናገር ኦልማርትን ከዚህ በፊት አላውቀውም፤ እንዲህ የሚባል ድርጅት ስለመኖሩም መረጃ አልነበረኝም፡፡ ውድድሩ ተዘጋጀ ተብሎ ለፈተና ልንቀመጥ ሲቀበሉን በጣም ነበር የገረመኝ። የሄድንበት አውቶቡስ፣ የአዘጋጆቹ ትህትና፣ በአጠቃላይ የሰጡን ዕድል ከእኔ ግምት በላይ ነው፡፡  በቀጣይ ትልልቅ ፈተና ለሚጠብቃቸው የመንግሥት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ይህ ፈተና መዘጋጀቱ ትልቅ ዕድል ነው፤ ምክንያቱም ለዋናው ፈተና ያነቃቃቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ሽልማቱና ከዚህ ሁሉ ሰው አንደኛ ሆኖ መውጣት ትልቅ እድልና በራስ  ይበልጥ መተማመንን ያጎለብታል። በሌላ በኩል ከተመለከትነው እኛ ይህን ዕድል በኦልማርት ማግኘታችንና እዚህ በመድረሳችን ለሌሎች ተማሪዎች መነቃቃትን ይፈጥራል፡፡ በጣም የገረመኝ ከ1-10 የወጣነውን የሸለሙን ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ውስጥ በትልቅ ክብር ነው፡፡ ይህንን ሁሉ ስመለከተው እንኳን 1ኛ ወጥቼ አይደለም ተሳታፊ ሆኜ ብሸኝ እንኳን ለእኔ ለቤተሰቤም ኩራት ነው። በአጠቃላይ ውድድሩ እንዲህ ደረጃውን የጠበቀ ይሆናል ብለን አልጠበቅንም፡፡ እኔም ሆንኩ ከኔ ቀጥሎ እስከ 10ኛ የወጡት ልጆች በጣም ደስተኞች ነን፡፡
አንደኛ እወጣለሁ ብለህ ጠብቀህ ነበር?
አልጠበኩም፡፡
ለምን አልጠበክም?
ምክንያቱም የሌሎች ጎበዝ ተማሪዎችን ውጤት መገመት ይከብዳል፡፡ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ ምርጥ 10ሮቹ ውስጥ መግባታችን ሲነገረን፣ ማንኛችን አንደኛ እንወጣ ይሆን በሚል ስጨነቅ ነበር፤ ሆኖም ምርጥ 10 ውስጥ መግባቴን ራሱ እንደ ቀላል ውጤት አልቆጠርኩትም፡፡ ለምን ቢባል መጀመሪያ ከሶስት ሺህ ተማሪ ምርጥ መቶዎቹ ውስጥ መግባት በራሱ ትልቅ ነው፡፡
ከዚያ ምርጥ አስሩ ውስጥ በመጨረሻም አንደኛ መውጣት በጣም ያስደስታል፡፡ ያልጠበቀኩት ነገር ስለሆነ እኔ ብቻ ሳልሆን ቤተሰቦቼ በጣም ተደንቀዋል፡፡ አባቴና ሌሎች ቤተሰቦቼ እዚህ አዳራሽ ይገኛሉ፡፡ መወዳደሬን ራሱ ምርጥ 10 ውስጥ ከገባሁ በኋላ ነው የነገርኳቸው፡፡ በተለይ አባቴ ደስታውን መቆጣጠር አቅቶታል፡፡ ቤተሰቦቼም እንዲህ ትልቅ ውድድር መሆኑንና አንደኛ ይወጣል ብለውም አልጠበቁም ነበር፡፡
የፈተናው ሂደት ምን ይመስል ነበር፡ የቅድስት ማሪያም ዩኒቨርስቲ የፈተና አወጣጥ እንዴት ነበር? ጥያቄዎቹ ከባድ ናቸው ቀላል? ምን ምን ያህል ጥያቄዎችና ምን ያህል ሰዓት ነበር የተመደበው? እስኪ ጠቅለል አድርገህ መልስልኝ?
ቅድስት ማሪያም ዩኒቨርሲቲ ጥያቄዎቹን ያወጣው የፈተኑን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ነው። ማንኛውም አገር አቀፍ ፈተና ስንፈተን የሚሟላው ነገር ተሟልቷል፡፡ በራሳቸው መምህራን ነው የፈተኑን፡፡ ፈተናውም ከታሸገበት እዚያው ፊት ለፊታችን ነው የተቀደደው፡፡ ፈተናዎቹ በጣም ደስ ይላሉ፡፡ ሌላ ፈተና ለመስራት ያነቃቃሉ፣ ከዝግጅታቸው ጀምሮ ጥሩ የፈተና ሂደቶችን እንድናልፍ አደርገዋል፡፡ ወደ መፈተኛ ቦታው ስንሄድ ራሱ የተጓጓዝንበት አውቶቡስ ያነቃቃ ነበር፤ ያለማጋነን ነው የምነግርሽ፡፡ የምሰጠው አስተያየት በተለይ የሂሳብ ጥያቄዎቹን ትንሽ ጠንከር አደርገው ቻሌንጅ ቢያደርጉን ጥሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም እዚህ ፈተና ላይ የተቀመጠው ሁሉም ተማሪ ብቃት ያለው ነው፡፡ ጥያቄዎቹ በእኔ እይታ ትንሽ ላላ ብለዋል፤ ይሄ የእኔ የግል አስተያየት ብቻ ነው፡፡ ጥያቄዎቹን በተመለከተ በተለይ ሁለተኛው ፈተና ላይ ውጤት ባይነገረንም ሂሳብ ምንም የከበደኝና የሳትኩት ጥያቄ እንደሌለ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እንግሊዝኛ ትንሽ ከበድ የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩት፡፡ የጥያቄው ብዛት እንግሊዝኛ መቶ ጥያቄ ሲሆን ሂሳብ 60 ጥያቄ ነው የቀረበልን፡፡ 2፡30 ለሂሳብ፣ ሁለት ሰዓት ደግሞ ለእንግሊዝኛ ተፈቅዶልናል፡፡ በዚህ ሰዓት ነው ሰርተን ያጠናቀቅነው፡፡ ትንሽ እንግሊዝኛ ላይ  ብዙዎቻችን የተቸገርን ይመስለኛል ምክንያቱም እርስ በእርሳችን የምንግባባው በአማርኛ ነው፡፡ በተረፈ ግን ይህ ፈተና ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባንን ዋናውን ፈተና በምን ያህል አቅምና ዝግጅት እንሰራለን የሚለውን ያሳየንና ራሳችንን የለካንበት በመሆኑ፣ አዘጋጁንና አጋሮቹን ደጋግሜ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት የውድድር እድሎች ገጥመውህ ያውቃሉ?
በፍፁም ተወዳድሬ አላውቅም፡፡ ይሄ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ በእርግጥ ወደ 10ኛ ክፍል እንዳለፍኩ ስኮላርሺፕ የሚሰጥ አንድ ድርጅት መጥቶ ውጤቴን አስገብቼ ነበር፤ የመፈተን እድል ግን አልገጠመኝም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው እንዲህ አይነት ቦታ መጥቼ ይህን እድል ያገኘሁት፡፡
ከትምህርት ውጭ ሌላ ምን ዝንባሌ ወይም ተሰጥኦ አለህ?
ሌላ ተሰጥኦ ለጊዜው የለኝም፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ ሙሉ ትኩረቴን የማደርገው ትምህርቴ ላይ ነው፡፡ በእርግጥ ት/ቤት ውስጥ ተሰጥኦም ባይባል ርዕሰ መምህራንንና መምህራንን ለማገዝ አንዳንድ ጥረቶችን አደርጋለሁ፡፡ አየር ጤና መሰናዶ ት/ቤት ውስጥ በጣም ብዙ ተማሪ ነው ያለው፡፡ መምህራንና ርዕሰ መምህራን ያንን ሁሉ ተማሪ ለመግራትና ብቁ ዜጋ ለማድረግ የሚወጡት የሚወርዱት መከራ፣ የሚያሳልፉት ስቃይ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ እውነት ለመናገር እንደነዚህ ያለ ለዜጋ የሚቆረቆሩ መምህራን አይቼ አላውቅም፡፡ እኔንም ለዚህ ስላበቁኝ ክብር ይገባቸዋል፡፡ ያበረታቱናል፤ በተቻላቸው አቅም የእኛን ባህሪና ውጤት ለማሻሻል ይደክማሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት ብዙ ነገር ባልተሟላበት የመንግስት ት/ቤት በመሆኑ ክብርና ሽልማት ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ ት/ቤት የሚወጡ ብዙ ተማሪዎች በጥሩ ውጤት ነው ትምህርታቸውን የሚጨርሱት፡፡ ይህ ሁሉ የመምህራኑና የማኔጅመንቱ ልፋት ነው፡፡
ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት የሚያስችልህን ፈተና ለመፈተን ጥቂት ቀናት ናቸው የቀሩህ፡፡ ምን ያህል እየተዘጋጀህ ነው?
በጥሩ ዝግጅት ላይ ነኝ፡፡ ት/ቤትም የሞዴል ፈተናዎችን እየተፈተንን ነው ያለነው፡፡ አሁን ተወዳድሬ ያለፍኩበትም ፈተና ጥሩ መነቃቂያ ሆኖልኛል፡፡
ዩኒቨርስቲ ስትገባ ማጥናት የምትፈልገው ምንድ ነው?
እግዚአብሔር ፈቅዶ ጥሩ ውጤት አምጥቼ ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ፣ ለማጥናት የመጀመሪያ ምርጫዬ ህክምና ነው፤ ይሄ የምንጊዜም ህልሜ ነው፡፡ ቢሳካልኝ ደስ ይለኛል፡፡ ይህ ካልሆነ ስፔስ ሳይንስ በጣም ስለምወድ እሱን ባጠና አይከፋኝም፡፡
በውድድሩ 1ኛ በመውጣትህ 15 ሺህ ብርና ለትምህርት የሚረዳ ታብሌት ኮምፒዩተር ተሸልመሀል፡፡ ብሩን ምን ልታደርግበት አስበሀል?
እኔ እንደዚህ አይነት ብር በእጄ ይዤ አላውቅም። ከብር ጋር የተነካካ ነገርም የለኝም፡፡ ያው ቤተሰቦቼ የሚፈልጉትን ሊያደርጉበት ይችላሉ። ግን በመሸለሜ ደስተኛ ነኝ፡፡ ታብሌት ኮምፒዩተሩ አሁን አያስፈልገኝም፡፡ ወደፊት ስለምጠቀምበት አስቀምጠዋለሁ፡፡
በመጨረሻ ማለት የምትፈልገው ካለ?
በመጀመሪያ ለዚህ ያበቃኝን ልዑል እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ በመቀጠል ብርቱዎቹን ቤተሰቦቼን አመሰግናለሁ፡፡ ታላላቅ ወንድሞቼ ለእኔ አርአያ ናቸው፡፡ ታላላቅ ወንድሞቼ በርትተው ተምረው ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ እኔም ውጤታማ እንድንሆን ለሚያደርጉት ድጋፍ አከብራቸዋለሁ፡፡
እናቴና አባቴ በጣም መልካም ሰዎች፣ ልጆቻቸውን በጥሩ ስነ ምግባር የሚያንፁ ናቸው፡፡ ያው እኔም ነፀብራቃቸው እንድሆን ለፍተዋልና አመሰግናለሁ፡፡ ይህንን ውድድር አመቻችቶ፣ በዚህ ሁኔታ የሸለመንን ኦልማርትንና አጋር ድርጅቶቹን አመሰግናለሁ፡፡ ኦልማርት በዚህ ረገድ በር ከፋች ነው፡፡ በቀጣይ ሚኒስትሪ ለሚፈተኑም የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ጭምር ይህን እድል ቢያመቻችላቸው ጥሩ ነው የሚል አስተያየት አለኝ ሁሉንም ግን አመሰግናለሁ፡፡   

Read 4842 times