Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Wednesday, 04 April 2012 09:54

ቦርጨቅ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

-በስብሃት ገብረእግዚአብሔር-

አቶ ዘነበ ሀብትም ሆነ ሹመት ወይም ዝና በምኞታቸው ገብቶ አያውቅም ነበር፡፡ አግብቶ፣ ልጆች ወልዶ አሳድጎ፣ አስተምሮ፣ በስተርጅና ጧሪ ደጋፊ ማግኘት፣ በልጆችና በልጅ ልጆች ተከቦ መድሀኔአለምን ተመስገን እያሉ መሞት፡፡ ይኸ ነበር ያቶ ዘነበ ምኞትና ተስፋ፡፡ ግን እግዜር ሳይለው ቀረና፣ ባንድ መስሪያ ቤት የቢሮ ተላላኪነት ተቀጥረው፣ ካመት አመት ሚስት አገኛለሁ እያሉ ተስፋ ሲያደርጉ፣ በልዩ ልዩ ምክንያት ካመት አመት ሳይሳካላቸው ሲቀር፣ ካመት አመት ጊዜ ትከሻቸው ላይ እድሜ ሲቆልል፣ እድሜው እየከበዳቸው እየጎበጡ ሄዱ፡፡ ተስፋቸው ከወጣትነታቸው እኩል እየመነመነ ሲሄድ፣ መድሀኔአለምን እየተሳለሙ “አንተ አምላክ ሳላውቅ በድዬህ ይሆን? ማረኝ ይቅር በለኝ” እያሉ በልባቸው ሲለምኑ፣ ሲፆሙ ሲፀልዩ ሲሰግዱ፣ እንዲህ ሲሉ ስድሳ አመት ሲሆናቸው ተስፋ ቆረጡ፡፡ ያ ሲያስጎመጃቸው፣ ሲያስጨንቃቸው የነበረ ተስፋ ጥሎአቸው ሲሄድ ጊዜ ቀለል አላቸውና ልባቸው አረፈ፡፡ መድሀኔአለንም እየተሳለሙ “አንተ ታውቃለህ እንጂ እኔ ምን አውቃለሁ? አንተ እንዳልከው ይሁን” ብለው እድላቸውን በሙሉ ልባቸው ተቀበሉ፡፡

በዚያን ሰሞን አንድ ጨካኝ ባለጌ አለቃ ተሾመባቸውና እያመናጨቀ፣ ክብራቸውን እየነሳ ያስጨንቃቸው ጀመር፡፡ “ወንድ ልጅ ወልጄ ቢሆን ኖሮ በስተእርጅናዬ ሰው እንደዚህ ይጫወትብኝ ነበር?” ብለው “አንተ ክንፉ የተሰበረውን ወፍ የምትጠብቅ የምትጠግን አምላክ፣ ለደከመ መንገደኛ የዛፍ ጥላ የምትሰጥ አምላክ፣ ለኔስ በስተርጅናዬ ሰላም አትሰጠኝም?” አሉት፡፡

ሁለት አመት ያህል እንዲህ ከተበሳጩ በኋላ፣ ያ ጥላ-ቢስ አለቃቸው ወደ ሌላ ተዛወረና አንድ ወጣት አለቃ ተሾመላቸው፡፡ እሱም አቶ ዘነበን በጨዋ ደንብ ክብራቸውን ጠብቆ ከማዘዙም በላይ፣ በስራው እሳት ስለነበረ በጣም ያደንቁት ጀመር፡፡ ልባቸው እንዳረጀ ወፍ ብር ብሎ ሄዶ “መድሀኔአለም ባይለው ነው እንጂ ይህን የመሰለ ሳተና ሊሰጠኝ ይችል ነበር” የሚል ሀሳብ ላይ ያርፍ ጀመር፡፡

እንዴት እንደሆነ ሳይታወቃቸው በአለቃቸው ኩራት እያደረባቸው፣ ቀስ በቀስ እንደ ልጃቸው ሲወዱት ይሰማቸው ነበር፡፡ አንዳንዴ ከሌሎቹ የመስሪያ ቤቱ ተላላኪዎች ጋር ሲያወሩ “የኔ አለቃ ዘንድ የተመራ ዶሴ ፍፃሜውን ሳያገኝ ያድራል ማለት ዘበት ነው” እያሉ መፎከር አመጡ፡፡ ልባቸው አለቃቸውን እየወደደ በሄደ መጠን ፍርሀት እየተሞላ ሄደ፡፡ ይኸ ነው የማይባል፣ መነሻው የማይታወቅ ፍርሀት፡፡ መድሀኔአለምን እየተሳለሙ በልባቸው “አንተ አምላክ፣ የልቡን ደግነት እያየህ ጠብቀው” ይሉ ነበር፡፡

ታዲያ አንድ ሰሞን ይህ አለቃቸው ስራውን እንደ ድሮው ማቀላጠፍ ትቶ፣ ከቢሮው አስር ጊዜ እየወጣ አስር ጊዜ ይመለስ ጀመር፡፡ የስራ ሰአት አሳልፎ የመምጣት በሽታ ተጋባበት፣ አልፎ አልፎም ፂሙን ሳይላጭ መግባት አመጣ፡፡ አንድ ወር ያህል ሌላ ሰው ሆኖ ትልቁ ጠረጴዛው ላይ በሃምሳ የሚገመት ዶሴ ተወዘፈ፡፡

የመድሀኔአለም እለት አቶ ዘነበ ወደ ቤተስኪያን ሄደው እየተሳለሙ በልባቸው “አንካሳ እድሌን እዚህ ልጅ ላይ አጋብቼበት ይሆን? አታረገውም አንተ መድሀኔአለም! ይህንንስ አታረገውም” አሉ፡፡ በነጋታው ጧት ወደ አምስት ሰአት ላይ አለቃቸው አይኑ ቀልቶ፣  ፀጉሩ ተንጨፍርሮ ያስር አመት ሰካራም መስሎ መጣና፣ እጅ ሲነሱት እንዴት አደሩ እንኳ ሳይላቸው ወንበሩ ላይ ዘጭ አለ፡፡ ራሱን ዴስኩ ላይ ደፋ፡፡ አቶ ዘነበ ተጨነቁለት፡፡ ግን አለቃቸውን መድፈር ስላልፈለጉ፣ እና ቢደፍሩትም ልባቸው ውስጥ ያለውን ሽብር ለሱ መናገር የማይቻላቸው ስለሆነ፣

“ጫማዎን ለሊስትሮ ልስጠው?” አሉት

“እ?” ብሎ ደንግጦ ከዴስኩ ቀና ብሎ አያቸውና “እርስዎ ነዎት ‘ንዴ?” አላቸው፡፡

“እኔው ነኝ ጌታዬ፡፡ ምን ላድርግልህ?” አሉት፣ አንተ ማለታቸው ሳይታወቃቸው፡፡ ተስፋ የራቀው የፈገግታ መልክ እያሳያቸው፣

“ቤተክርስቲያን ይስማሉ?” አላቸው፡፡

“አዎን”

“ማንን?”

“መድሀኔአለምን”

“እንግዲያውስ ለመድሀኔአለም ያስታውሱኝ”

“ሁልጊዜ ነው ‘ማስታውስህ”

“ምን አሉኝ?”

“በፀሎቴ ሁል ጊዜ አስታውስሀለሁ”

ቶሎ መልሶ ራሱን ደፋ፡፡ ሲያዩት ትከሻው ይንቀጠቀጥ ጀመር፡፡ ከዚያ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡

አቶ ዘነበ የሚጨብጡትን የሚቆሙበትን ስላጡ “ኧረ ጌታዬ አታልቅስብኝ! ምን በወጣህ ታለቅሳለህ? ይቅር ተወው ይቅር፡፡ በቃ ተወው ይቅር፡፡ ተወው በቃ” እያሉ አለቃቸውን ሳይሆን በልባቸው ያለውን ልጃቸውን ያባብሉት ጀመር፡፡

ለቅሶው ፋታ ሲሰጠው አለቃቸው ቀና ብሎ፣

“ቤተሰብ አለዎት?” አላቸው፡፡

“ብቻዬን ነኝ”

“እኔም ብቻዬን ነኝ፡፡ አይገርምዎትም?”

መልስ አላገኙለትም፡፡

“መጣሁ” አላቸውና እየተጣደፈ ወጣ፡፡ አቶ ዘነበ ግራ ገብቶአቸው ሲጨነቁለት ሲቁነጠነጡ ደጋግመው ወደ ላይ እያዩ “አንተ መድሀኔአለም ምን ማድረግ ይሻለኛል?” ሲለ ብዙ ከቆዩ በኋላ፣ አለቃቸው በሩን በርግዶ ገባና ቆልፎት ሲያበቃ፤

“እነሆ” አላቸው በላስቲክ የታሰረ ገንዘብ፡፡

ተቀበሉት ሊልካቸው መስሎአቸው፡፡ “አራት ሺህ ሶስት መቶ ብር ናት፡፡ ትንሽ ቦታ ተመርተው ትንሽ ቤት ይስሩባት፡፡ ሲያረጁ ማረፊያ ትሆንዎታለች፡፡ እና ለመድሀኔአለም ያስታውሱኛል”

አቶ ዘነበ ከመደንገጣቸውና ከመገረማቸው የተነሳ አልተናገሩም፡፡ አልተንቀሳቀሱም፡፡

አለቃቸው እንደገና በሩን በርግዶ ወጥቶ ብዙ ቆየ፡፡ ካሁን ካሁን ይመለሳል ብለው ሲጠብቁ ሰባት ሰአት ሆነና፣ ቢሮውን ቆላልፈው ገንዘቡን ይዘው ቤታቸው ሄዱ፡፡

በዘጠኝ ቢሮውን ከፍተው ዴስኩን ወልውለው፣ የተቆለሉትን ዶሴዎች አይተው ራሳቸውን በሀዘን ነቅንቀው፣ ዝናብ መትቶአቸው ስለነበረ ፀሀይ ሊሞቁ ወጡ፡፡ ወደ አስራ አንድ ሰአት ላይ ወሬው ደረሳቸው፡፡ አለቃቸው መኪናውን ጭቃ አዳልጦአት ገደል ገብቶ ሞተ፡፡

በልባቸው ውስጥ፣ ከጥልቀቱ የተነሳ ማንም ሊሰማው ወይም ሊጠረጥረው የማይችለው ጥልቀት ውስጥ “ልጄን! ልጄን! ልጄን!” ብለው አለቀሱ፡፡

ጠዋት ተነስተው ለቀብሩ ሲሄዱ ድንገት የልብሳቸው መናኛነት ታያቸውና “እንዴት አለቃዬን በመናኛ ልብስ እሸኘዋለሁ?” ብለው በፍጥነት ተመልሰው፣ ከሃያ አመት በፊት ያሰፉዋትን የክት ገበርዲን ልብሳቸውን ከሳጥናቸው አውጥተው ከጎረቤት ካውያ ለምነው ተኩሰው፣ ወጣ ብለው ከሱቅ አዲስ ሸሚዝ ገዝተው፣ በሚገባ አጊጠው ወጡ፡፡ ሊቀብሩ ሳይሆን ሊሰናበቱ፡፡

ጊዜም እንዳያልፍባቸው፣ ለጊዜው አባርቶ የነበረው ዝናብም እንዳይደርስባቸው ለመሄድ ቆረጡ፡፡ ሁለት ታክሲ ሞልቶ አልፎአቸው ሶስተኛውን ሲጠብቁ፣ አንዲት ፈጣን ቆንጆ መኪና እንደ ወንዝ እየፈሰሰች መጣችና ቦርጨቅ! አለፈች፡፡

ውሀው ከመንገዱ ተወርውሮ ተለጠፈባቸው፡፡ ገበርዲናቸውን ጭምልቅልቅ አደረገባቸው፡፡ የተቆረጠውን ትንፋሻቸውን ገና ሳይቀጥሉትና መተንፈስ ሳይጀምሩ፣ ከርካሳ መኪና ስትንገጫገጭ መጥታ ቦርጨቅ! ደገመቻቸው፡፡ አለፈች፡፡

“ገበርዲኔን! አዲስ ሸሚዜን! አለቃዬን!” እያሉ እየጮሁ ጎምበስ ቢሉ ድንጋይ አጡ፡፡

“አንዲት ድንጋይ እንኳ ብትሰጡኝ ምን ቸገራችሁ ነበር? አንዲት ድንጋይ፣ ገበርዲኔን የምበቀልባት?” እያሉ እያለቀሱ፣ በእግር መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ትንሽ ቆይተው “ገበርዲን ጊዜው አልፏል፡፡ ቆሻሻ ውሀ ካልደረቡበት አያምርም ተብሏል” እያሉ፣ ሌላም ልዩ ልዩ ንግግር እየተናገሩ፣ ሊወርድባቸው የጀመረውን ሃይለኛ ዝናብ ሳያስተውሉ ቤተክርስቲያን ደረሱ፡፡

አለቃቸው ሲቀበር እየሳቁ ለብቻቸው ያጉረመርሙ ነበር “ማዘን አያሻም፡፡ እሱ መች ሞቶ መሰላችሁ? ተሻግሮ ነው፡፡ እዚያ እንግዲህ የወርቅ ቢሮ ይሰጡታል፡፡ በል እንደ ልማድህ ስራውን አቀላጥፍልን! ይሉታል፡፡ የሚረባ ተላላኪ ካልተመደበልኝ ልሰራ አልችልም! ሲላቸው፣ ምረጥ ይሉታል፡፡ ዘነበን ስጡኝ ሲላቸው፣ እዚያኛው አለም ነው ይሉታል፡፡ ላኩበት ይላቸዋል፤ አለቃህ ይፈልግሀል፣ ልጅህ ልኮብሀል በሉት፡፡”

አቶ ዘነበ የብርድ በሽታ ያዛቸውና እያተኮሳቸው፤ እያንቀጠቀጣቸው በሶስተኛው ቀን አረፉ፡፡

(ከደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር “ቦርጨቅ” የአጫጭር ታሪኮች አዲስ መድበል የተወሰደ)

 

 

Read 3070 times Last modified on Friday, 06 April 2012 11:40