Sunday, 21 May 2017 00:00

ዲሞክራሲያዊ ጋብቻ ናፈቀኝ!

Written by  ዘካሪስ አትክልት
Rate this item
(7 votes)

 ሠላም እና ፍቅሩን ያብዛልን! ዛሬ የባህል ካባ የተጫነው ሰርጋችን ላይ ሙድ እንይዛለን፡፡ ሰሞኑን የሰርግ ወቅት ነው፡፡ በባህላችን መሰረት የሠርግ ማሟሟቂያ የሆነው ሽማግሌ መላክ ነው፡፡ ወንዱ ሽማግሌዎች መርጦ ሴቷ ቤተሰብ ጋር ይልካል፡፡
“… ልጃችሁን ለልጃችን!” ሽማግሌዎች
“አረፍ በሉና እንወያይበት!” የሴት ቤተሰቦች
“እሺታችሁን ካልሰጣችሁን አንቀመጥም፤ ልጃችን በአ.አ.ዩ በማህበራዊ ሣይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው፤ ወላጆቹና መንደርተኛው ቆንጥጦ ያሳደገው ምግባረ ሰናይ ነው …”
“ጥሩ! እንደምታውቁት ልጃችን ወርቅ የሆነ ባህሪ ያላት፤ ኮሌጅ የበጠሰች ተመራማሪ ናት …”
እንዲህ እያለ ድርድሩ ቀጥሎ በስተመጨረሻ ተስማምተው፤ የተዘጋጀውን ድግስ ይቋደሳሉ። ወገኛ የሴት ቤተሰብ ከገጠመ አይጣል ነው። ሽማግሌዎች የወንዱ ጠበቃ፣ የሴት ቤተሰቦች ሲሻቸው ዳኛ፣ ሲሻቸው መርማሪ ፖሊስ እየሆኑ ድርድሩን ያዘግሙታል፡፡
ማን ይሙት በዚህ ዘመን ሽማግሌ መላክ ተገቢ ነው? ተላምደውና ተፋቅረው መንፈሳቸው ለተሳሰረ ሌላ ፈቃጅ ያስፈልጋል? ማኪያቶና ቢራ ሲጋብዛት፣ ሲሸኛት፣ ሲደውል … አስፈቅዷቸው ነበር? እሺ! መቼም ባህላችን ነው እንበል፤ ለሴት ቤተሰቦች ሽምግልና ሲላክ ለወንድ ቤተሰቦች ሽምግልና እማይላከው ለምንድን ነው? ባህላችን የጾታ አድልዎ አለበት፡፡ “የሴቶች እኩልነት ይከበር!” እየተባለ ቤተሰባዊ ክብራችን መነካቱ አስቆጥቶናል፡፡
ይቺ ተለምዶ ናት፡፡ አባቶቻችን የማይተዋወቁ ህፃናት እርስ በእርስ ተፈቃቅደው አጋብተዋል። ተለምዶ በጊዜ እየተራባ ባህል ሆኖ ቁጭ! እንትን ለእንትን አብረህ አዝግም ዓይነት ነገር ሆነ፡፡
በቅርቡ የታደምኩት የቅርብ ወዳጄ ሰርግን ሳውጠነጥን ሙድ ገብ ሀበሾች ታዩኝ፡፡
ሙሽራው በሚዜ እና ወዳጆቹ ታጅቦ ሙሽሪት ቤት ደረሰ፡፡ “ጨሰ አቧራው ጨሰ …” እያልን ከመኪና አወረድነው (በዘመነ ኮብልስቶን አቧራው ጨሰ መባሉ ቀርቶ “የሞከራት ጨሰ” ቢባል አያዋጣም?) ሙሽራውን አጅበን ወደ ሙሽሪት ቤት ተጠጋን፡፡ የሙሽሪት ወዳጆች፤ አናስገባም ሰርገኛ እደጅ ይተኛ እያሉ በሩን ጥርቅም፡፡ እኛም፤ “ሀይሎጋው ሽቦ” እያልን ታግለን በር አስከፍተን ሙሽራውን አስገባን፡፡
ወዳጃዊ ስሜት አነሁልሎኝ ተጋፍቼ በሩን ለማስከፈት ብጥርም መለስ ብዬ ሳስበው አሳቀኝ። ስንት ቀን አብረን ቢራ የጠጣን፣ የተጫወትን አናስገባም ማለት ተገቢ ነው? ሙሽራው ከቤት በር አልፎ የልቧን በር መክፈቱን ረሱት? አይ ተለምዶ! መግደርደር ባህል መሆኗን ማሳያ ትሆን?
ሙሽሪትና ሙሽራውን ይዘን የመኪና ጡሩንባ እየነፋን መጓዝ ጀመርን፡፡ የመኪና ጡሩንባ የሰርግ ዲዎዶራንት ነው፤ መንገዱን ያውደዋል፡፡ “ሠርግ እና ሞት አንድ ነው” የሚለው የገባኝ መኪና ውስጥ ሆኜ ነው፡፡ ሠርግ ከመበላቱ በፊት አስክሬን ከመቀበሩ በፊት በጡሩንባ ይታወጃል፡፡
ወደ ሰርጉ አዳራሽ ስንገባ እድምተኛው ተነሳ፡፡ ከዚህ ቀደም እድምተኛ ሆኜ በተደጋጋሚ ብነሳም የዛሬው አነሳስ ገረመኝ፡፡ እውነትም ሰርግ እና ሞት አንድ ነው! ነገሩ እንዲህ ነው፤ ከሁለት ቀን በፊት ሀሳብ ደቁሶኝ፣ ኪሴ አላላውስ ብሎኝ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ ነበር፡፡ በድርድሩ ተቀምጬ ሳለ ከጎኔ የተቀመጡት ብድግ ብድግ አሉ፡፡ ግር ብሎኝ የተነሱትን ሳስተውል ከጀርባዬ የለቅሶ ድምፅ ሰማሁና ዞርኩ፤ አስከሬን ይዘው እዬዬ እያሉ ሲገቡ አየሁ፡፡ እኔም ነገዬን አስቤ ለአስከሬኑ ክብር ሰጠሁ። ያልታደለ ሰው በሰርግና በሞቱ ክብር ያገኛል፡፡ የሞተ ነገን ስለሚያስታውሰን ብንነሳ ለራስ ማሰብ ነው፡፡ አንድ ሰዓት ተኩል ላረፈደ ሙሽራስ? የሰርጉ ጥሪ ስድስት ተኩል፤ የደረሰው ስምንት ሰዓት ነው፡፡ እድምተኛው በሰዓቱ ቢታደም፤ ማን ያውቃል ሰርግ እበላ ብሎ ቁርሱን ሳይበላ ለመጣ፣ የቅዳሴ ሰዓት ማለቂያ ላይ መብላቱ አይደል! ሊያውም ወረፋ ከደረሰው፡፡
በአንድ ወቅት የዘመድ ሰርግ ገጥሞን ከአጎቴ ጋር ሄድን፡፡ የሰርጉ ጥሪ ሰባት ሰዓት ነበር፡፡ በአዳራሹ የታደምነው ስድስት ተኩል ላይ ነው፡፡ ብንጠብቅ ሙሽሮች አይመጡም፡፡ አጎቴ የሰዓቱ መንጎድ አሳስቦት ይቁነጠነጣል፡፡ አስር ጊዜ ሰዓቱን ያያል። ሰርግ እበላለሁ ብዬ እናቴ ያቀረበችልኝን ቁርስ ሳልበላ መምጣቴ እያበሳጨኝ፤ በሆዴ አካባቢ የተፈጠረ የረሀብ ደመና ሲያስገመግም እሰማለሁ። አጎቴ ጥሎ እንዳይወጣ ቤተሰብ የሚታዘብ ስለመሰለው ጊዜውን በከንቱ ላለማጥፋት ኪሱ አጣጥፎ የከተተውን ጋዜጣ አውጥቶ ማንበብ ጀመረ፡፡ ሌላኛው አጎቴ በንቀት ተሞልቶ አጠገባችን መጣና፡-
“ወዲ አትኸልቲ ነውር አይደል?” ብሎ አፈጠጠበት
“ምኑ ነው ነውሩ? የእህትህ ልጅ ሰባት ሰዓት ጠርታን ሳትመጣ ዘጠኝ ሊሞላ አይደል!” ብሎ ተነስቶ ወጣ፡፡
በልጅነት ልቦናዬ አጎቴ ስጋ በያይነቱ ያመለጠው ይመስለኝ ነበር፡፡ ጊዜ ደጉ! የማርፈድ ታጋይ መሆኑን አሳየኝ፡፡ ማርፈድ ባህል ሆኗል፡፡ በተለይ የሴት ቀጠሮ አክባሪና የከርሰ ምድር ነዳጅ ማግኘት ብርቅ ነው፡፡
ሙሽሮች እያዘገሙ ሲሄዱ፣ ታዳሚው ቆሞ ሲያጨበጭብ በሙሽሪት ላይ አይኖቼ አተኮሩ፡፡ ይሄ ሁሉ ሰው የቆመው “ሙሽራ ንጉስ ነው” ብሎ ነው ወይስ ሙሽራው በዕጮኝነት ዘመኑ የሙሽሪትን ማርፈድ ችሎ ለዚህ በመድረሱ?
የሰርጉ መርሀ ግብር ቀጥሏል፡፡ ሙሽሮችና ሚዜዎች ከተቀመጡበት መለስተኛ ማማ እየተነሱ ምግብ አነሱ፡፡ እኛ አጃቢዎች ቀጠልን፡፡ ከጥሬው፣ ከጥብሱ ከወጡ ዝቄ መለስተኛ ቡፌ ይዤ ጠረጴዛ ላይ ተሰየምኩ፡፡ ከአጠገቤ የተቀመጠው ወዳጄ የያዘውን ሳይ ግር አለኝ፡፡ አንድ ቁርጥ እንጀራ ላይ የዶሮ መረቅ ከአንድ እንቁላል ሰሀኑ ላይ ሰፍሯል። ጥቂት ጊዜ ስለተለያየን በቅርቡ የያዘው በሽታ መኖሩን ገመትኩ፡፡
“ሠላም ነው?” አልኩት ሰሀኑን እያየሁ
“እህ! አንተ ምን አለብህ!” አለ በምፀት
“እንዴት?”
“የሠርግን ጣጣ እኔ ነኝ እማውቀው!”
‹‹አልገባኝም?››
“በ2006 ዓ.ም ተበድሬ አግብቼ እስከ አሁን እየከፈልኩ ነው፤ እንዳንተ ዝቀው የበሉብኝን እዳ!›› አለ በምሬት፡፡
ወዳጄ ፈገግታ ቢጭርብኝ ሳይፈልግ የባህል ምርኮኛ መሆን አሣዘነኝ፡፡ ‹‹የሀገርም ድሩን ሠርግ በልቼ ልጄን ካልዳርኩ ምኑን ሰው ሆንኩ!፤” ‹‹ልጄ በቬሎ ካልወጣች ሞቻለኋ!›› በሚል ተለምዷዊ ካቴና ታስረው ከአቅም በላይ ለደገሡና ለሚደግሱ፤ አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው፤ ታላቅ ችሎታ ነው የምትለዋን፣ ዜማ ጀባ ማለት ነው፡፡
ምግቤን እያነከትኩ ሙሽሮችና ሚዜዎችን አስተዋልኩ፡፡ ያለ ምክንያት “ሙሽራ ንጉስ ነው” እንዳልተባለ ገባኝ፡፡ ሙሽራው አፄ፣ ሙሽሪት፣ እቴጌ፣ ሚዜዎች ፈታውራሪ፣ ግራዝማች ፣ ልዕልት… አስተናባሪው አጋፋሪ መሠሉኝ፡፡ ለካ ሠርግ የፊውዳሊዝም ተምሳሌት ነው፤ አፄያዊ ስርዓት ማሳያ ቅሪት፡፡ ሙሽሮች ሲገቡ ሰው ተነስቶ እጅ ይነሣል፤ በእድምተኞች ፊት በክብር ዙፋን ይቀመጣሉ፡፡ ለምግብ ሲነሡ እጅ ይነሣል፡፡ ጠግበው ሲጨፍሩ ተከትሎ ይጨፍራል፡፡ አዳራሽ /እልፍኝ/ ለቀው ሲወጡ በጭብጨባ ይሸኛል፡፡
በዚህ ዘመን ተጫጭተው፣ ተፋቅረውና ተጋባብተው ከጨረሡ በኋላ አይደል የሠርግ ስነ-ስርዓት የሚከናወነው? ታዲያ ተንጋሎ በዙፋን ላይ መቀመጥ ምን አመጣው? በመካከላችን እየሠረጉ “ተጋብተናል፤ ደስ ይበላችሁ! ብሉልን ጠጡልን” እያሉ ቢያስገናብሩ ምን አለበት፡፡ ኧረ ዲሞክራሲያዊ ሠርግ ናፈቀኝ! ሱፍ መልበስ ብርቅ ይመስል ካሜራ ደቅኖ ደቅና በመኳል ጊዜ ፈጅቶ ታዳሚ ማስጠበቅ ምን ይባላል? ያው ንጉሡ አይከሰስ ሠማይ አይታረስ ነው፡፡ ፊውዳላዊ ሙሽሮች ይማሩ! ዲሞክራሲያዊ ሠርግ ይስፈን! ‹‹ሙሽራ ንጉሥ ነው›› የሚለው ይውደም! ሙሽራ ወዳጅ ነው!
ወደ ቀደመው ጨዋታ ስመለስ፤ ምግብ ተበልቶ አልቆ ዳንስ ተጀመረ፡፡ የሠርግ ሙዚቃዎች እየተንቆረቆሩ ሙሽሮች በወዳጅ ዘመድ ታጅበው ዳንሡን ተያያዙት፡፡ በመሀል መብራት ተቋረጠ፡፡ ሙዚቃው ግን በሠው አፍ ቀጠለ፡፡
“የዛሬ ዓመት የማሙሽ አባት..” እያለ አንዱ አዜመ፡፡ ይቺ የሙዚቃ ግጥም ትንቢት ልትሆን ትንሽ ነው የቀራት፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ ካጋባኋቸው ጓደኞቼ መካከል ትንቢቱ ያልሰራው በሁለቱ ነው፤ የወለዱት ማሙሽን ትተው ሚጣን ነው፡፡ የግጥሟ ቀለማቶች  ትንቢተኝነታቸው አዲስ አበባ ውስጥ ቀብድ ሳይሰጥ (ቀብድ ያልኩት ጽንስ ሳያኖሩ) መጋባት ዘበት የሆነ እስኪመስል ድረስ ሸንቃጣ ማየት ተዓምር ሆኗል፡፡ ግጥሟን ምን አይነት ነብይ የሆነ ገጣሚ ነው የፃፋት እንዳልል የገጣሚው ብዕር የአልትራሣውንድ ጨረር እንዳለው ጾታ መለየቱ ቢያግደኝም ያለ ቀብድ ጋብቻ፣ ያለ ፍቀር ድግስ መደገሡ ይታሠብበት፡፡

Read 4521 times