Sunday, 21 May 2017 00:00

በስድስት ክ/ከተሞች ነጻ የደም ግፊት ምርመራ ተከናወነ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ጤና ቢሮ ከአስትራዜንካ ጋር በመተባበር በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በስድስት ክፍለ ከተሞች  ነፃ የደም ግፊት ምርመራዎችን አከናወነ፡፡ በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተካሄደው የነፃ ምርመራ አገልግሎት በአህጉራዊው ተቋም አስተርዜንካ ልዩ ፕሮግራም ሔልዚ ኸርት አፍሪካ (HHA) አማካኝነት ሲሆን በመላው ዓለም ከሚከበረው የዓለም የደም ግፊት ቀንን ምክንያት በማድረግ የተከናወነ ነው፡፡
“በደም ግፊት ማም ሰው መሞት የለበትም” በሚል መርህ የሚንቀሳቀሰው አስትራዜንካ፤ ከኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በአጋርነት ለመስራት ስምምነት ያደረገው ባለፈው ዓመት ሲሆን በኸልዚ ኸርት አፍሪካ ፕሮግራሙ፣የደም ብዛት በሽታን ለመዋጋት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለማገዝ እንዲሁም በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ የአሰራር መዋቅሮችን ከአገሪቱ የጤና አስተዳደር ጋር አጣጥሞ ለማከናወን ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል፡፡
በዚህ መሰረትም ከዓመት በፊት ከመላ አፍሪካ የተውጣጡ ታዋቂ የህክምና ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በአገር አቀፍ ደረጃ በመንቀሳቀስ ለሃኪሞችና ሌሎች የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም የህክምና ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫና የስልጠና መድረኮችን በማዘጋጀት ሰርተዋል፡፡ የአስትራዜንካ ኸልዚ ኸርት አፍሪካ ፕሮግራም ከኢትዮጵያ በፊት በጎረቤት  አገር ኬንያ ተግባራዊ በመሆን ከፍተኛ ውጤት እንደተገኘበትም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሰሞኑን ‹‹የዓለም የደም ግፊት ቀን››ን ምክንያት በማድረግ በተከናወነው ነፃ የደም ግፊት ምርመራ ተጠቃሚ የሆኑት የጤና ማዕከላት በየካ፤ በልደታና አብነት፤ በአዲሱ ገበያ፣ፒያሳና ቀጨኔ፤ በሩፋኤል ማዞርያ በቃሊቲና አቃቂ የሚገኙ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ አስትራዜንካ  የኸልዚ ኸርት አፍሪካ ፕሮግራምን በማከናወን ለ900 የጤና ባለሙያዎችና የህክምና ድጋፍ ሰጪዎች ስልጠና የሰጠ ሲሆን በሰባት የአገሪቱ ክልሎች በሚገኙ 12 ሆስፒታሎችና 36 የጤና ማዕከላት የተቀናጀ የአሰራር መዋቅርን መዘርጋቱ ታውቋል፡፡
ባለፈው አንድ ዓመት ለ100ሺ ሰዎች ነፃ የደም ግፊት ምርመራ በማካሄድ 13ሺ ግለሰቦች በሽታው እንዳለባቸው ለመጀመርያ ጊዜ ያረጋገጠው ፕሮግራሙ፤ከደም ግፊት ጋር በተያያዘ ደረጃውን የጠበቀ ህክምና፤ እንክብካቤና የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥበትን ሁኔታ በመላው ኢትዮጵያ ለማስፋፋት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የደም ግፊት ለልብ ህመምና ሌሎች ተያያዥ በሽታዎች የሚያጋልጥ ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚያመለክተው፤በአፍሪካ ከደም ግፊት ጋር በተያያዘ ያለው የግንዛቤ ማነስ በበሽታው የሚከሰተውን የሞት አደጋ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡  

Read 1791 times