Sunday, 21 May 2017 00:00

ኢትዮጵያ የራሷን የልማት ግምገማ ሪፖርት ለተመድ ልታቀርብ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  ሪፖርቱ ከተቃዋሚዎች ከፍተኛ ትችት ቀርቦበታል
                      
      የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን የኢትዮጵያን የዘላቂ ልማት ግቦችና የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ስኬቶች የግምገማ ሪፖርት ለተባበሩት መንግሥታት ለማቅረብ የተዘጋጀ ሲሆን በረቂቅ ሪፖርቱ ላይ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ውይይት ሪፖርቱ ጠንካራ ትችቶች ተሰንዝሮበታል፡፡   
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለአባል ሀገራቱ በ2030 እንዲያሳኳቸው 17 የልማት ግቦችን ያስቀመጠ ሲሆን ከነዚህ አጀንዳዎች ውስጥ ኢትዮጵያ ባለፈው 2 ዓመት በተመረጡ 6 የልማት ግቦች ላይ የደረሰችበትን ደረጃ የሚያሳይ ሪፖርት በፈቃደኝነት እንድታቀርብ መጠየቋን ተከትሎ ሪፖርቱ መዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡
የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽንም በዚህ መነሻነት፣ በመላ ሀገሪቱ የሁለት ዓመቱን የልማት ግምገማዎች አከናውኖ በማጠናቀቅ፣ ለሚኒስትሮች ም/ቤት አቅርቦ በማፀደቅ፣ ከ15 ቀናት በኋላ ሪፖርቱን ለመንግሥታቱ ድርጅት የፖለቲካ ፎረም ለማስረከብ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
የመንግሥታቱ ድርጅት ግምገማ እንዲካሄድባቸው የጠየቃቸው የትኩረት አቅጣጫዎች፡- ድህነትን ማጥፋት፣ ረሃብን ማጥፋት፣ ጤናማ ህይወትና ደህንነት፣ የስርአተ ጾታ እኩልነት፣ የመሰረተ ልማት ግንባታና ኢንዱስትሪ ፈጠራ እንዲሁም የውሃ ስነ ምህዳር ለዘላቂ ልማት መጠበቅ የሚሉት ናቸው፡፡
እነዚህን ለማሳካት የመንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዲሁም የመንግስትና ህዝብ ባለቤትነት ምን ያህል ነበር የሚለው የግምገማው ዋና መመዘኛዎች መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ባቀረበው የመንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማሳያዎች ላይ ያልተማከለ አስተዳደር ስርአት መገንባቱ፣ የመንግስት የደህንነት ተኮር ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ እቅዶችና ፕሮግራሞች እንዲሁም በኢትዮጵያ ያለው የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የተጠቀሰ ሲሆን በውይይቱ ወቅት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ከፍተኛ ትችት ተሰንዝሮበታል፡፡  
ኮሚሽኑ ለመንግሥታቱ ድርጅት ሊያቀርበው ባዘጋጀው ሰነድ ላይ በ2007 እና በ2008 ዓ.ም በአጠቃላይ የ8 በመቶ ሀገራዊ እድገት መመዝገቡን፣ ባለፉት 6 ዓመታትም በተከታታይ በአማካይ የ9.8 በመቶ እድገት በየዓመቱ ማስመዝገቡን በተለይም የመሰረተ ልማት በመላ ሀገሪቱ በከፍተኛ ፍጥነት መስፋፋቱ ተጠቅሷል፡፡
የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢም በ2002 ከነበረበት 377 ዶላር፣ በ2007 ወደ 691 ዶላር ከፍ ማለቱን እንዲሁም በ2008 ዓ.ም 794 ዶላር መድረሱንና ከ3 ዓመት በኋላ በ2012 ዓ.ም የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ወደ 1,177 ዶላር ከፍ እንደሚል በሪፖርቱ ተቀምጧል፡፡
መንግስት የተባበሩት መንግስታት ያስቀመጠውን የዘላቂ ልማት ግቦች ለማሳካት ሲል ከዋናው በጀት በተጨማሪ በየዓመቱ 12 ቢሊዮን ብር እየመደበ መሆኑን የሚጠቁመው ሰነዱ፤ በዚህም በመሰረተ ልማት፣ በማህበራዊ ልማትና በአካባቢ ልማት ስኬታማ ውጤት ተመዝግቧል ይላል፡፡ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችም የህዝብ ባለቤትነት እየተፈጠረባቸው መሆኑን ሪፖርቱ ያትታል፡፡ በ2008 ዓ.ም በሀገሪቱ የተከሰተው ድርቅ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሳያስከትል፣ ሀገሪቱ በራሷ አደጋውን መቀልበሷ የኢኮኖሚ እድገቱ ማሳያ መሆኑንም ይጠቅሳል፡፡  
ድህነትን ከማጥፋትና ብልፅግናን ከማስፋፋት አንፃር ያለው የድህነት ምጣኔና ስራ አጥነት አሁንም በጣም ሰፊ እንደሆነ፣ በተለይ የሴቶችና የወጣቶች ስራ አጥነት በጣም ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡ “የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ድህነትን ለማጥፋትና የዜጎችን ብልፅግና ለማስፋፋት ዋና ማስፈፀሚያ መንገድ ነው” የሚለው ሪፖርቱ፤ይሄን ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ያትታል፡፡
መንግስት በየዓመቱ ከሚመድበው በጀት 70 በመቶ ድህነትን ለማጥፋት ቁልፍ ሚና ባላቸው የግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና የመሳሰሉት ላይ እያዋለ መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በዚህም ሀገራዊ የድህነት ምጣኔ በ2003 ከነበረበት 29.6 በመቶ፣ በ2007 ዓ.ም ወደ 23.4 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቅሷል፡፡ ረሀብን ለማጥፋት መንግስት አረንጓዴ የግብርና ልማትን በመከተል ምርት እያሳደገ መሆኑን በመጠቆም፣ የዋና ዋና ሀገራዊ የሰብል ምርት ምጣኔ በ2002 ከነበረበት 180 ሚሊዮን ኩንታል፣ በ2009 ዓ.ም ወደ 288.5 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ እንደሚል የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ማመላከቱን ይጠቅሳል፡፡  
የጤና አገልግሎቱም በመላ ሀገሪቱ በ2008 የበጀት ዓመት 98 በመቶ መዳረሱን፣ አገልግሎት ያገኙ እናቶች ሽፋንም ወደ 73 በመቶ ማደጉን ለመንግሥታቱ ድርጅት ሊቀርብ የተዘጋጀው ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ የሴቶች እኩልነትን በተመለከተም በየደረጃው ባሉ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሴቶች  ከ38 እስከ 50 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የመሰረተ ልማት አቅርቦት በተለይ የውሃ አቅርቦት በመላ ሀገሪቱ ወደ 61 በመቶ ማዳረስ መቻሉን አመልክቷል፡፡
በተዘጋጀው የሪፖርት ሰነድ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ የኢኮኖሚ እድገትና የዲሞክራሲ እድገት እንዲሁም የሠብዓዊ መብት አጠባበቅ ተነጣጥለው የሚታዩ አለመሆናቸውን በመግለፅ፣ ሪፖርቱ የተጋነነና የሃገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ የማይወክል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በ2008 ዓ.ም በአብዛኛው በሃገሪቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት እንደነበር ያስታወሱት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ ኢንቨስትመንት የተቀዛቀዘበትና በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር ያልገቡበት፣ ሃገሪቱም ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተዳረገችበት ወቅት በመሆኑ ሪፖርቱ የተጋነና ከእውነታው የራቀ ነው ብለዋል፡፡ በሰው ሃብት ልማት ሃገሪቱ ገና ብዙ እንደሚቀራት የጠቆሙት ዶ/ር ጫኔ፤ በዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሃገሪቱ ስኬት እያስመዘገበች መሆኑ የተጠቀሰው ጉዳይ በተጨባጭ ያለውን እውነት ስለማያንፀባርቅና የተባበሩት መንግስታትም ሊቀበለው ስለማይችል ከሪፖርቱ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
የሃገሪቱ የዘላቂ ልማት ግቦች ግምገማም ሊካሄድ የሚገባው በመንግስት አካል ሳይሆን በገለልተኛ ቡድን እንደነበር ዶ/ር ጫኔ በአፅንኦት ገልፀዋል። የሃገሪቱ ዲሞክራሲ ባልዳበረበትና ሠብአዊ መብት ባልተከበረበት ሁኔታ እንዲህ ያለው ሪፖርት መቅረቡ ከተጨባጭ እውነታ ጋር የሚቃረን መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ የኢራፓ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሠብሮ በበኩላቸው፤ በሠብአዊ መብት፣ በዲሞክራሲና በሚዲያ ነፃነት ጉዳይ ሃገሪቱ ብዙ ሳትራመድ የቀረበው የልማት ሪፖርት ተቀባይነት እንደማይኖረው ጠቁመው፣መንግስት ሙስናን መግታት ባልቻለበት ሁኔታ፣ “መንግስት ለልማቱ ቁርጠኛ ነው” የሚል ሪፖርትን እንደማይቀበሉት ተናግረዋል፡፡
የኦብኮ ሊቀ መንበር አቶ ተስፋዬ ቶሎሣ በሰጡት አስተያየት፤”በሃገሪቱ ሙስና እና የመሬት ብዝበዛ በተንሠራፋበት፣ ዜጎች የዲሞክራሲና የሠብዓዊ መብት ጉዳይን እየጠየቁ ባሉበት ሁኔታ እንዴት ነው ፈጣን ልማት መጥቷል፣ የዘላቂ ልማት ግቡን እየመታ ነው ማለት የሚቻለው?” ሲሉ የጠየቁ ሲሆን ‹‹ረሃብን ተቋቁመናል›› እየተባለ በጎን እርዳታ እየተጠየቀ መሆኑም ከሪፖርቱና ከተጨባጭ እውነታው እንደሚቃረን ጠቁመዋል፡፡
የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ያዘጋጀው ሪፖርት፤ ሰኔ 1 ቀን 2009 ዓ.ም በሚኒስትሮች ም/ቤት ከፀደቀ በኋላ ሰኔ 7 ቀን 2009 ዓ.ም ለተመድ የፖለቲካ ፎረም ይቀርባል ተብሏል፡፡

Read 2530 times