Sunday, 21 May 2017 00:00

የቴዲ አፍሮ ቃለመጠይቅ የታገደበት የኢቢሲ ጋዜጠኛ በፈቃዱ ስራ ለቀቀ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

     የኢቢሲው ጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለ ከድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ ጋር ካደረገውና ባለፈው ሳምንት በእሁድ መዝናኛ ፕሮግራም ላይ ይቀርባል ተብሎ ከተዋወቀ በኋላ በድርጅቱ የስራ ሃላፊዎች ውሳኔ ሳይተላለፍ ቀርቷል ከተባለው ቃለመጠይቅ ጋር በተያያዘ በፈቃዱ ስራውን መልቀቁን አስታወቀ፡፡
ላለፉት 4 አመታት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ያገለገለው ጋዜጠኛ ብሩክ፣ ከድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ጋር በስራዎቹና በግል ህይወቱ ዙሪያ ያደረገው ቃለ መጠይቅ እንዳይተላለፍ መታገዱ ከፈጠረው ውዝግብ ጋር በተያያዘ በተቋሙ ውስጥ ለመቀጠል የሚያስችል ሞራላዊ አቅም እንደሌለው በመጥቀስ፣ ስራውን በገዛ ፈቃዱ ለመልቀቅ መወሰኑን ትናንት ለድርጅቱ በጻፈው ደብዳቤ ገልጧል፡፡
በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የቴዲ አፍሮ ቃለመጠይቅ በተያዘለት ፕሮግራም አለመተላለፉ ብዙዎችን ያሳዘነና ያስቆጣ ጉዳይ ሲሆን፣ ጋዜጠኛውም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከህሊናው ጋር እየታገለ ስራውን መቀጠል ስለማይችል፣ በገዛ ፈቃዱ ስራውን ለመልቀቅ መወሰኑን በፌስቡክ ገጹ ላይ ትናንት ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
“ጉዳዩ አንድን የኪነጥበብ ሰው የማቅረብና ያለማቅረብ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የጋዜጠኝነት ልዕልናንም የሚጋፋ ጭምር እንጂ፤ ብዙዎች መስዋዕትነት የከፈሉለትን ሙያ ክብር ለመስጠት ስል ስራዬን የመልቀቅ ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ” ብሏል፤ ጋዜጠኛው በዚሁ መረጃው፡፡
ከስራ ለመልቀቅ ሰበብ የሆነውን የቴዲ አፍሮ ቃለመጠይቅ በተመለከተ በቅርቡ ዝርዝር መረጃ እንደሚሰጥ የጠቆመው ጋዜጠኛው፤ ላለፉት አራት አመታት በድርጅቱ በነበረው የስራ ቆይታ መልካም ጊዜ ማሳለፉን በማስታወስ፣ ለድርጅቱ ሰራተኞችና በተለያዩ መንገዶች ከጎኑ ለነበሩ ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
ጋዜጠኛው በቴዲ አፍሮ መኖሪያ ቤት በመገኘት ከድምጻዊው ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ ባለፈው እሁድ በመዝናኛ ፕሮግራም ይተላለፋል የሚለው መረጃ በማህበራዊ ድረገጾች በስፋት ተሰራጭቶ ብዙዎች ዕለቱን በጉጉት እንዲጠብቁት ቢያደርግም፣ ቃለ መጠይቁ እንዳይተላለፍ መወሰኑን የሚገልጽ ሌላ መረጃ መውጣቱን ተከትሎ ደግሞ ጉዳዩ በድምጻዊው አድናቂዎች ዘንድ በማህበራዊ ድረገጾች ከፍተኛ ቅሬታንና ቁጣን መፍጠሩ ይታወሳል፡፡
“ኢትዮጵያ” የተሰኘውን አምስተኛ የሙዚቃ አልበሙን በቅርቡ ካወጣው ቴዲ አፍሮ ጋር የተደረገውን ቃለ መጠይቅ በተመለከተ በማህበራዊ ድረገጾች ከሚሰራጩ መረጃዎች በስተቀር የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አመራሮችም ሆኑ የዝግጅት ክፍሉ ሃላፊዎች በይፋ ያስታወቁት ነገር የለም፡፡


Read 11197 times