Sunday, 21 May 2017 00:00

መንዝ ላይ በጥይት የተገደሉት ወንድማማቾች ጉዳይ አስደንጋጭ ሆኗል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(8 votes)

ለገጣፎ የሚገኘው የወረኩማ ባርና ሬስቶራንት ባለቤት አቶ ደረጀ ሺበሺና የታላቅ ወንድሙ ሀሰን ሁሴን (ጫንያለው) በሰሜን ሸዋ ዞን መንዝና ማማምድር ወረዳ፣ ቆሎ ማርገፊያ ቀበሌ በጥይት መገደላቸው አስደንጋጭ ሆኗል፡፡ ፖሊስ የገዳዮቹን ማንነትና የግድያውን መንስኤ ለማጣራት ምርመራ መጀመሩን ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
ሟች ወንድማማቾች ወደ መንዝ የተጓዙት ወረኩማ ለተባለው ባርና ሬስቶራንት በሬ ለመግዛት እንደነበር የጠቆሙት ቤተሰቦቻቸው፤ ሐሙስ ግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም ከምሽት 3፡20 ላይ ባልታወቁ ሰዎች በጥይት መገደላቸውን ተናግረዋል፡፡  
የ35 ዓመቱ ወጣት ደረጀ ሺበሺ ወረኩማ ባርና ሬስቶራንት በመምራትና በማስተዳደር ስራ ላይ የነበረ ሲሆን የ55 ዓመት ዕድሜ ያለው ወንድሙ ሐሰን ሁሴን (ጫንያለው) ላለፉት 24 ዓመታት ኑሮውን በኬንያ አድርጎ፣ የራሱን የግል ኩባንያ ይመራ እንደነበርና ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተሰቡን ለማየት ከ20 ቀን በፊት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን የሟቾቹ ቤተሰቦች ገልፀዋል፡፡
የደረጀ ሺበሺ እጮኛ ከመጋባታቸው በፊት እንዳረገዘችና ለወሊድ እህቶቹ ጋር ካናዳ ሄዳ አንድ ወንድና አንድ ሴት መንታ ልጆች መውለዷን የተናገሩት የሟቾች ቤተሰቦች፤ ከወለደች ከሁለት ዓመት በኋላ ልጆቿን ይዛ ከመጣች 15 ቀን እንደሆናት ጠቁመው፣ በቀጣይ ሳምንታት ህጋዊ ጋብቻ ለመፈፀም እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት የሞት አደጋው በመድረሱ ሀዘናቸው እንደተባባሰ በምሬት ገልፀዋል፡፡
ደረጀና ሀሰን ወደ መንዝ ሲጓዙ ለከብት መግዣ 120 ሺህ ብር ይዘው እንደነበር፣ ሞተው በተገኙበት ቦታ ላይ የደረጀ የአንገት ሀብልና 8 ሺህ ዶላር ዋጋ ያለው ሮሌክስ ሰዓቱ መወሰዳቸውን፣ በኪሱ ተንቀሳቃሽ ስልኩና 2400 ብር መገኘቱን የጠቆሙት ቤተሰቦች፤ በታላቅ ወንድምዬ በሀሰን ሁሴን ኪስ ውስጥ 3500 ብር፣ ሰዓቱና ተንቀሳቃሽ ስልኩ እንደተገኘ ተናግረዋል፡፡  
በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት ወንድማማቾች፣ እሁድ ግንቦት 6 ቀን 2009 ዓ.ም ወዳጅ ዘመድ በተገኘበት በለገጣፎ እግዚአብሄር አብ ቤተክርስቲያን ስርዓተ ቀብራቸው ተፈፅሟል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝተን ያነጋገርናቸው የሟቾቹ እናት ወ/ሮ ሀገረወይን ሁሴን፤ ‹‹ከ24 ዓመት በኋላ አይኑን ያየሁትን የመጀመሪያ ልጄንና አሞላቅቄ በልዩ ፍቅር ያሳደግኩትን የመጨረሻ ልጄን በአንድ ደቂቃ ማጣቴ እድሜ ልኬን የማልወጣው ሀዘን ውስጥ ከትቶኛል›› ሲሉ እንባቸውን እያዘሩ፣ መሪር ሃዘናቸውን ገልፀውልናል፡፡ ‹‹ወላድ ይፍረደኝ፤ ፍትህ እሻለሁ›› ብለዋል-ሁለት ልጆቻቸውን ያጡት እኚሁ እናት፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ ም/ኮማንደር ከለላው ቦግያለ፤ ወንድማማቾቹ በጦር መሳሪያ መገደላቸውን ማረጋገጣቸውን ጠቁመው፤ ምን ላይ ተመቱ፣ በምን ያህል ጥይት ተገደሉ የሚሉትንና ተያያዥ ጉዳዮችን ለማወቅ አስከሬኑ ለዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ለምርመራ ተልኮ ውጤቱን እየተጠባበቁ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከዞኑ ፖሊስ፣ ከወረዳው ፖሊስና ከአቃቤ ሕግ መርማሪ ቡድን ተቋቁሞ፣ ገዳዮችን ለመያዝ ሌት ተቀን እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ም/ኮማንደር ከለላው፤ ጉዳዩ አሁን ባለበት ሁኔታ እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው ለማለት እንደሚያስቸግርና ውጤቱን በቀጣይ እንደሚያሳውቁ አክለው ገልፀዋል፡፡

Read 11039 times