Sunday, 14 May 2017 00:00

አንድን ንግድ አሥር ዓመት ውሃ ውስጥ ብታስቀምጠው አዞ አይሆንም!

Written by 
Rate this item
(14 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊት አጠቃላይ ስብሰባ ያደርጋሉ፡፡ ሰብሳቢው የዱር አራዊት ሁሉ ሊቀመንበር አያ አንበሶ ነው፡፡ ስብሰባው እንዲኖር ያዘዘው ግን የሁሉም የበላይ የሆነው አምላክ ነው፡፡
አራዊቱ ሁሉ ንቅል ብለው ከጫካው መጥተዋል፡፡ አያ አንበሶ በነብሮ አማካኝነት የምዝገባ ቁጥጥር እንዲደረግ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የስብሰባ መቆጣጠሪያ ላይ ሁሉም ተገኝተው ኤሊ ግን አልመጣችም፡፡ የኤሊን መቅረት ለማጣራት የተወሰኑ አራዊት ተሰማሩ፡፡ ዝንጀሮና ጦጣ አንድ ላይ አገኟት፡፡
“እመት ኤሊ”
“አቤት”
“ከስብሰባው በመቅረትሽ የዱር አራዊት ሁሉ ተቀይመውሻል፤ ማንን ተማምና ነው? እያሉ ነው!”
“እኔ የተማመንኩት ተፈጥሮን ነው፡፡ እዚህ የድንጋይ መከላከያ ዋሻ ውስጥ ሆኜ ማን ይነካኛል?” አለች፡፡
“እሺ ይሄንን መልስሺን ለአምላክ እንነግራለን!” ብለዋት ይሄዳሉ!
አምላክ የኤሊን ነገር ሲሰማ “ትምጣና ፍርዷን ትስማ” አለ፡፡
ኤሊ የግዷን እየተንጓፈፈች መጣች፡፡
አምላክም፤
“ለፈፀምሺው ከፍተኛ ድፍረት አንድ ከባድ ፍርድ ይገባሻል፡፡ በዚህም የዱር አራዊት ሁሉ ትምህርት ሊያገኙ ይገባል፡፡ በዚህ መሰረት እመት ኤሊ ከዛሬ ጀምሮ እሸሸግበታለሁ ያልሺውን ድንጋይ ለብሰሽ ኑሪ! ይህ ህግ የማይሻር የማይለወጥ ይሁን” አለ፡፡
ብዙዎቹ የዱር አራዊቶች የፍርድ ማቃለያ ጠየቁላት፤ አንዳንዶቹ፤ “አውቃ ሳይሆን ተሳስታ ነው” አሉ፡፡
ከፊሎቹ፤
“የድንጋይ ዋሻ የመጨረሻው መጠለያዋ መስሏት ነው” አሉ፡፡
ሌሎቹ፤ “ስለ አምላክ ታላቅነት ያላት ዕውቀት ውሱን በመሆኑ ነው” አሉና ተማፀኑ፡፡ አምላክ ግን “ትምህርት ማግኘት አለባት” አለ፤ ኮስተር ብሎ፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ኤሊ ዕድሜ ልኳን ድንጋይ እንደለበሰች ትኖራለች፡፡
*   *   *
በዚህም ሆነ በዚያ ከህግ መሸሽ ያስጠይቃል፡፡ ያስቀጣልም፡፡ ይግባኝ የሌለው ከባድ ቅጣት! ታስቦ፣ ወንጀል ልፈፅም ተብሎ፣ ሁነኛ ጥፋት ተደርጎ የተፈፀመ ድርጊት ነው! ማጣፊያው የሚያጥረውም ለዚህ ነው!
የየትኛውም ወገን የፖለቲካ ድርጅቶች እንዴት ትልቁን ስዕል (The Bigger Picture) ማየት እንደሚችሉ የገባቸው አይመስሉም፡፡ ብዙ ግትር የሚመስሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተንኮታኩተዋል! ያሉ ሲመስላቸው የሉም፡፡ ተፅዕኖ ያሳደሩ ሲመስላቸው ዜሮ ግፊት ብቻ (Zero degree pressure) ነው ያላቸው፡፡ የመግባባት አቅማቸው ደካማ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ሁኔታዎችን ጠንቅቆ አውቆ የመጠቀም ዘዴ ከቶም የእነሱ ባለመሆኑ ነው፡፡ የድንጋይ ምሽግ ይዣለሁ ብሎ መተማመንና ማን ይነካኛል ማለት “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” የሚለውን የጠዋት ተረት እየናቁ መውደቅ ነው፡፡ በወገናዊነት መረብ (በኔትዎርክ) አገር አይገነባም፡፡ ምክንያቱም ኔትዎርኩን ለመበጣጠስ ደፋ-ቀና ሲባል ሊሰራ የሚገባው ቁልፍ ቁልፍ ሥራ ሳይከናወን ይቀራል፡፡ አገር ወደ ኋላ ትቀራለች፡፡ የጉዳዮችን ቅደም ተከተል ማበጀት አንዱ ወሳኝ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህም ብልህነትን ይጠይቃል፡፡ የህዳሴው ግድብ ዐቢይ ራዕይ መሆኑን ማንም አይስተውም፡፡ ሆኖም ከሥሩ መከናወን ያለባቸውን ሌሎች ቁልፍ ተግባራት የምንሸፍንበት ወይም ድክመታችንን  ላለማሳየት ጭምብል የምናጠልቅበት (masking one’s own weaknesses) ዘዴ መሆን የለበትም፡፡ በየአደባባዩ መሪ መፈክሮችን በማስገርና ጠላቶቻችን ያልናቸውን በማውገዝ፣ የራሳችንን ጥፋት ለመከለል መሞከር አንድ ቀን መጋለጡ አይቀሬ ነው፡፡ (They shout at most against the vices they themselves are guilty of እንዲሉ ፈረንጆቹ) የቡድነኝነትም ሆነ የመንገኝነት ስሜት ለሀገር አሉታዊ እንጂ አዎንታዊ ግብዓት አይፈጥሩም፡፡ ይልቁንም የገነባነውን ይሸረሽራሉ፡፡
ዶ/ር  አበራ ጀምበሩ፤ ‹‹ብቸኛ ሰው›› ጽሁፋቸው ላይ ፀሐፌ ትዕዛዝ ተፈራ ወርቅ ኪዳነወልድ ቅሬታቸውን ሲገልጡ፤ ‹‹የሥራ ቅንነት፣ ትጋትና ግለት እየቀዘቀዘ መሄድ፤ ተረስቶና ሞቶ የነበረው የቤተ - መንግሥት ተንኮል እንደገና ነፍስ ዘርቶ፣ ለብዙ መልካም ስራዎች እንቅፋት መሆኑ፣ የወገን የመከፋፈል መንፈስ በብዙ ሰዎች ማደሩ ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ለመማር ዝግጁ ከሆንን አሁንም ጊዜ አለ፡፡ ውሃ ወቀጣውን እንተው፡፡ ሁልጊዜ የእነ እገሌ ጥፋት ነው ማለትን በርትተን እናስወግደው፡፡ ራሳችንን ለማዳን ኳሱን ወደ ሌሎች በመወርወር የተሻለ ፍሬ አናፈራም፡፡ ይልቁንም የወረወርነው ቀስት መልሶ ወደ ራሳችን ይመለስና ይወጋናል- ቡመራንግ (Boomerang)፡፡ አዳዲስ ሹማምንት ሥልጣን ላይ በተቀመጡ ቁጥር በአሮጌዎቹ ባለሥልጣናት ላይ እንከንና አቃቂር በማውጣት፣ የራስን ንፁህነት ለማሳየት መጣጠር ለጊዜው የዋሐንን ይማርክ እንደሆን እንጂ ዘላቂ የልማት መሳሪያ አይሆንም፡፡ ውስጣችን ከፊውዳላዊ አስተሳሰብ ሳይፀዳ ዲሞክራሲያዊነትን፤ ብሎም ፍትሐዊነትን ከዚያም ልማታዊነትን ማፍራት አይቻልም፡፡ በዘመነ በዛንታይን፣ የሮማን መንግሥት የካቶሊክ ስርዓት ፀሐፍት ሲተቹ፤ “The Holy Roman Empire is neither Holy nor Roman nor an Empire” ይሉ ነበር፡፡ ቅዱስ ሮማዊ ግዛት ተባለ እንጂ ቅዱስም አልነበረም፡፡ ሮማዊም አልነበረም፡፡ ግዛትም አልነበረውም ማለታቸው ነው፤ በስላቅ! ከውሃ ወቀጣው ግምገማ መውጣት አለብን፡፡ አዲስ አመለካከት እናምጣ፡፡ ለአስተሳሰብ ፈጣሪዎች (Thinkers) ዕድል እንስጥ፡፡ አለበለዚያ አሮጌው አመለካከት አረንቋ ውስጥ እንደተቸከልን እንቀራለን፡፡ ‹‹አንድን ግንድ አሥር ዓመት ውሃ ውስጥ ብታስቀምጠው አዞ አይሆንም›› የሚባለው ለዚህ ነው!

Read 3683 times