Sunday, 14 May 2017 00:00

‘የድፍረት ጡንቻ’ እና ‘የእውቀት ጡንቻ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በቀደም ነው አሉ፡፡ በአንዱ የከተማችን ክፍል ሁለት ሴቶች መኪኖቻቸው በስሱ ይነካካሉ፡፡ ሁለቱም ሴት ነብሮች ሆነውላችሁ ለገላጋይ አስቸግረው ነበር አሉ፡፡ ዘንድሮ እኮ ግራ የሚያጋቡን ነገሮች ከመብዛታቸው የተነሳ ለመዘርዘርም እያስቸገሩን ነው፡፡ ገና ለገና ‘መኪናዬ ተጫረች ብሎ የምን ‘አርበኝነት’ ነው!
እኔ የምለው..ሰው ሁሉ ጉልበቱን ከየት አምጥቶት ነው፡ የዘንድሮ ጠጅ እንደሁ እንኳን አንበሳ ሊያደርግ እንደ ሰመመን መስጫ መድኃኒት ሆኗል ነው የሚባለው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… በ (ለትዳሮች መፍረስ ሰመመን የሚያሲዘው ጠጅ አስተዋጽኦ ተጠንቶ ይነገረንማ!)
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በፊት እኮ ለገላጋይ የሚያስቸግር… አለ አይደል… “ተዉ፣ ግዴለም” ባይ በጨመረ ቁጥር ያዙኝ ልቀቁኝ ለሚያበዛው፣ “ተዉአቸው፣ ይለይላቸው…” የምትባል ነገር ነበረች፡፡ ያኔ ታዲያ ምን ይሆናል መሰላችሁ… “መንጋጭላህን የበር መደገፊያ እንዳላደርገው!” ፉከራ ወደ ስድብ ተለውጦ እስኪበቃቸው ተሰዳድበው ይለያያሉ፡፡
እናማ… አንዳንድ ጊዜ በየመንገዱ  ‘ቡራ ከረዩ’ የሚያበዙ ባለመኪኖችን “ተዉአቸው፣ ይለይላቸው…” ብሎ መልቀቅ፣ ‘በአደራዳሪ ማስፈለግና አለማስፈለግ’ ጭቅጭቅ ውስጥ ሳይገባ የችግር መፍቻ መፍትሄ ሊሆን ይችላል! ቂ…ቂ…ቂ…
እኔ የምለው… እግረ መንገዴን… “ተጣልተዋል፣” “ዘንድሮስ በቄስ ግዝትም የሚመለሱ አይመስልም፣”…ምናምን የሚባለው…እንዴት ነው ነገሩ? አሀ… ይነገረና፡፡ መቼም ለዚህ ብለን ግጥሙ የተለወጠ “ቁርጡን ንገሪኝ” ዘፈን አንዘፍን! (ከዛ ሰፈር ‘የትዊተር ገጽ የሚከፍት’ አንድ ሰው እንኳን ይጥፋ! ምናለበት…ኩረጃ እንደለመድነው፣ ግፋ ቢል “ከዶናልድ ትረምፕ ልምድ በመነሳት…” ምናምን ማለት ይቻላል፡፡)
‘የድፍረት ጡንቻ’ እየዳበረ፣ ‘የእውቀት ጡንቻ’ እየሰለለ ሲሄድ አሪፍ አይደለም፡፡
እናማ… በዚህ ‘በሰለጠነ’ ዘመን አእምሮ ይዞታውን ለቆ ጡንቻ ላይ ሲከመር አሪፍ አይደለም፡፡ እኔ የምለው…ከቻይና ሹካ የሰለለች ክንድ ሁሉ ጡንቻ ሆና በ‘ታቱ’ ተዥጎረጎረችሳ! ኸረ ቢያንስ፣ ቢያንስ የሚነቀሱት ነገሮች እኛን ይምሰሉ! ለነገሩ ታቱ ከጡንቻ፣ ከአንገት ምናምን ዘሎ ከሠራተኞች በስተቀር መግባት ክልክል ነው (ቂ…ቂ…ቂ…) ሊለጠፍበት የሚገባ ቦታ ላይ ሁሉ ደርሷል አሉ፡፡ ልክ ነዋ...ስንሰለጥን “ስቴፕ ባይ ስቴፕ ሂድ፣” “ከ‘ሀ’ ጀምረህ ‘ፐ’ ድረስ…” “የምትረግጠውን ድንጋይ እያየህ ተራመድ…” ብሎ ነገር የለማ! ማን ነበር… “በቅርቡ አዲስ አበባን ኒው ዮርክ እናደርጋታለን ያለው! ይልቅ ‘የተቦዳደሰው፣’ ‘የተከመረው፣’ ‘የተበተነው፣’ ‘የትዝረከረው፣’ ነገር ሁሉ ይስተካከልልን! በአንዴ ሰባ ሺህ መኪና ቢገባም… “እግረኛ መሆን ኃጢአት አይደለም፣” የሚል ‘ሲንግል’ ይለቀቅልንማ!
ታዲያላችሁ… እንደ ስቲፍን ሴጋል “በአምስት ደቂቃ የአምስት ወረዳ ህዝብ እረፈርፋለሁ፣” አይነት ‘ሄሮይዝም’ ቅሽምና ነው፡፡  እናማ… አንዳንድ ጊዜ… “ተዉአቸው፣ ይለይላቸው” ብሎ ዓለም ጦሽ ትል እንደሁ ማየት ነው፡፡
‘የድፍረት ጡንቻ’ እየዳበረ፣ ‘የእውቀት ጡንቻ’ እየሰለለ ሲሄድ አሪፍ አይደለም፡፡
እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የ‘ቡራ ከረዩ’ ነገር ካነሳን አይቀር… አለ አይደል…ምነው ‘መለያየት’ በዛሳ! (‘ላይ ሰፈር’ ሰላም ነው!) ምነው ‘ዓይንህ ለአፈር፣ ዓይንሽ ለአፈር’ በረከተ! ምነው ‘ዘመን እንኳን ከማያዳክመው’ ወዳጅነት ከመቅጽበት ወደ “መቃብሬ ላይ እንዳትቆም/እንዳትቆሚ” መንሸራተት በረከተ! ግለሰብ እርስ በእርሱ ተጣልቶ… የንግድ የምናምን ድርጀት እርስ በእርስ ተጣልቶ…  የፖለቲካ ማሀበር እርስ በእርሱ ተጣልቶ…እንዴት ነው ነገሩ!
ስሙኝማ…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…መጀመሪያ ግንኙነቱ ሲመሰረት…አለ አይደል… የ‘እነ ቶሎ፣ ቶሎ ቤት’ አይነት ነገር ነው፡፡ ልክ ነዋ…ድንገት ተገናኝቶ አራት ደብል ብላክ ሌብል ስለገዛ “ስማ፣ እንዴት አይነት ጥሩ ሰው እንደሆነ አታምነኝም!”
“በቃ፣ ጓደኛ ማለት እንዲህ ነው…” ምናምን አይነት ወዳጅነት በበረከተበት፣ ሁሉም የእምቧይ ካብ ነገር ሲሆን አይገርምም፡፡
ለነገሩ… “ምን ሰይጣን ገብቶ ነው ያጣላቸው!” ማለትም እየቀረ ነው፡፡ አሀ…ሰይጣን እኮ አይደለም እሷና እሱን፣ እነኚህንና እነኛን ሊያጋጭ ሌላ፣ ሌላ ቦታ ሥራ በዝቶበታል!
እንትናና እንትናዬ የሆነ ቦታ ይገናኛሉ፡፡ ‘የሆነ ቦታ’ ማለት እንደበፊቱ ‘እከሊት ሰርግ ላይ’ ‘እከሌ ለቅሶ ላይ’…ላይሆን ይችላል፡፡ በድምጽ ሁለት ፍጥነት ‘የሚበረው ስልጣኔያችን’ ምስጋና ይግባውና… ‘የትም’ ሊሆን እንደሚችል ልብ ይባልልንማ! አለ አይደል…የቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ መንገዶችም ሊሆኑ ይችላሉ! (ቂ…ቂ…ቂ… አይ እሱ ሰፈር! ለምን ‘ልዩ የምናምን ሰፈር’ የሚል ‘ኦፊሴላዊ’ ስያሜ አይወጣለትም!)
‘የድፍረት ጡንቻ’ እየዳበረ፣ ‘የእውቀት ጡንቻ’ እየሰለለ ሲሄድ አሪፍ አይደለም፡፡
ስሙኝማ… የከተማችን ‘ብራድ ፒት’ ነገር ነው፡፡ የእንትናዬዎች ‘ፕሮጀክት ፕሮፖዛሉን’ የሚያስበውም፣ የሚያጸድቀውም፣ የሚተገብረውም በደቂቃዎች ጊዜ ነው አሉ፡፡ ያያል፣ ያናግራል፣ እሺ ያሰኛል፣ ፎረስት ኬክ ያበላል፣ ‘ይዞ አረፍ’ ይላል…ይሸኛል፡፡ አለቀ፡፡
እናላችሁ…ከአንዷ ጋር ‘እነሆ በረከት’ ምናምን ላይ ‘ኮከባቸው ይገጥማል፣’ ቂ…ቂ…ቂ… (ዘንድሮ፣ ኮከብ ልግጠም ካለ ምን የማይገጥምበት ቦታ አለ!) እናላችሁ… ከዛም በየእኩል ሰዓቱ ‘ናፈቅኸኝ/ናፈቅሽኝ’ ይመጣል፡፡ የሆነ የሆቴልና የቱሪዝም ድርጅት ‘የመኝታ ቤቶች ብቃት ማረጋገጫ ሰጪዎች’ ያደረጋቸው ይመስል… ዓለም ዘጠኝ ይላላ፡፡ ከዛም ድንገት ሲንተከተክ የነበረው ‘ፍቅር’ ሳምንት ሳይሆነው በአፍ ጢሙ ይደፋል፡፡
እሱዬው ‘ደከመ’ አሉ፡ ቂ…ቂ…ቂ… (ሳምንት እንኳን ሳይሆነው!) ለነገሩ’ኮ…መጀመሪያም ዋናው ያቆራኛቸው ነገር… አለ አይደል… ‘እነሆ በረከቱ’ ነበር፡፡ እናማ… አሥር ጊዜ ‘ብረት ሲያነሳ’ ቢውል፣ አሥር ጊዜ ’ቪ’ ነገርዬውን ሲቅም ቢውል፣ አሥር፣ አሥራ አምስት ደብል ዳግም ሲቀነድብ ቢውል… መቼም የሰው ልጅ ሆኖ ‘ጉልበቱ የማይደክም’ የለም፡፡ ይኸው ዌይን ሩኒን የመሰለ እግረ ኳሰኛ ደክሞ የለ! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ… ወይ ደግሞ የግንኙነቱ ዋልታና ማገር፣ ጣራና ግድግዳ ‘ፈረንካ’ ይሆናል፡፡
“እሱ እኮ የሚወስዳት ቦታ ብነግርሽ ኡ፣ ኡ ነው የምትዪው…”
“የት ይወስዳታል?”
“የት አይወስዳትም ብትይ ይሻላል፡፡ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል በዪው፣ ሪዞርት በዪው፣ ናይት ክለብ በዪው…ዓለሟን እያስቀጫት ነው፡፡” ይህ በተባለ በወር ከአሥራ ሰባት ቀኑ…
“አንቺ እነኛ ሰዎች ተለያዩ እኮ!”
“እነማንን ነው የምትዪኝ!”
“ያቺ እንኳን…”
“ዓለሟን እያስቀጫት ነው አላልሽኝም ነበር!”
“እሱማ በፊት ነበር…አታምኚም…ቅዳሜ  እለት ቀበሌ መዝናኛ ይዟት ገብቶ አንድ ምግብ ለሁለት አያዝ መሰለሽ!”
“ምነው፣ ምን መጣ!”
“እንጃለት…ገንዘቡ አለቀበት መሰለኝ…”
“እና በዛ ምክንያት ተዋት እያልሽኝ ነው?”
“እሷ ነች የተወችው፣ ሌላ ባለቡቲክ ይዛለች አሉ…”
 የዘንድሮ ነገር በቃ ይኸው ነው፡፡
‘የድፍረት ጡንቻ’ እየዳበረ፣ ‘የእውቀት ጡንቻ’ እየሰለለ ሲሄድ አሪፍ አይደለም፡፡
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አሁን ለምሳሌ ‘ቦተሊከኞቹ’ ተጣሉ ሲባል፣ አፋችንን ሸፍነን ቂ…ቂ…ቂ… እንላለን፡፡ እንክት አድርገን ነዋ! ስሙኝማ…ይሄነ ካነሳን አይቀር፣ እኛ አገር ደስ የሚለው ነገር ምን መሰላችሁ… ‘ቦተሊከኛ’ ለመሆን ‘ቦተሊካ’ ማወቅ አያስፈልግም፡፡ አለቀ፣ ደቀቀ፡፡ ልክ ነዋ… አንዱን ‘ቦተሊከኛ’ አለ አይደል… “ሜንሼቪኮች እነማን ናቸው?” ብላችሁ ብትጠይቁት፣ “የማንቼ ተጫዋቾች ናቸዋ!” ሊላችሁ ይችላል፡፡
የምር ግን…“ስማ አንዲት እቁብ ጀምረናል፣ ለምን አትገባም…” እንደሚባለው አይነት፣ “ስማ የሆነች የፖለቲካ ድርጅት አቋቁመናል፣ ለምን አትገባም?” የሚባል ነው የሚመስለን፡፡ ስለሆነም… ‘ቦተሊከኛ’ ለመሆን የፈለገ ሰው፣ በ‘ፋስት ፎርወርድ’ መሆን ይችላል፡፡
ደግሞላችሁ… አንዳንዱ “ፖለቲካ አውቃለሁ፣ ጥርሴን የነቀልኩበት ነው…” ምናምን የሚለው… ቼ ጉቬራ አሁንም በቦሊቪያ ጫካዎች ያለ ይመስለዋል እንዴ! አሀ…አስተሳሰብ እንኳን ባይሻሻል ምን አለ ቋንቋው እንኳን ለወጥ ቢል! አለ አይደል… “ቺኬ ነች፣” የሚለው “ፕሮጀክቴ ነች፣” ወደሚለው እንደተለወጠ ማለት ነው፡፡
‘የድፍረት ጡንቻ’ እየዳበረ፣ ‘የእውቀት ጡንቻ’ እየሰለለ ሲሄድ አሪፍ አይደለም፡፡
የ‘እውቀት ጡንቻውን’ ያዳብርልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3611 times