Sunday, 07 May 2017 00:00

ዋና አሰልጣኝ አሸናፊለጋና ጨዋታ ዋልያዎቹን ለ10 ቀናት ብቻ ያዘጋጃሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2019 እኤአ ላይ ካሜሮን ለምታስተናግደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚያደርገውን የምድብ ማጣርያ ከወር በኋላ ቢጀምርም፤ አስፈላጊውን የተሟላ ዝግጅት በተያዘው እቅድ መሰረት ለማከናወን አልቻለም። አዲሱ ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለስፖርት አድማስ እንደገለፁት በመጀመሪያ ምርጫቸው ለብሔራዊ ቡድኑ 29 ተጨዋቾችን በመመልመልና የአንድ ወር የዝግጅት እቅዳቸውን ለፌደሬሽኑ ከሳምንት በፊት አቅርበው ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ፤ ከጥሎ ማለፍ እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ በተያያዘ ባሉት የጨዋታ መደራረቦች ሳቢያ እቅዳቸውን ሊተገብሩ አልቻሉም፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ባስተላለፈው ውሳኔ ግን ከጋና ጋር ከሚደረገው ጨዋታ በፊት ዋልያዎቹን ለ10 ቀናት ብቻ እንዲያዘጋጁ ወስኖባቸዋል፡፡ ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለፌደሬሽኑ ያቀረቡትን የ1 ወር የዝግጅት እቅድ እንዳብራሩት፤ 3 የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከከተማ ውጭ ለማድረግ፤ የተለያዩ የልምምድ መርሃ ግብሮችን ለመስራት፤ የተጨዋቾችን የጤና ሁኔታዎችና ወቅታዊ አቋም በመገንዘብ ቡድኑን ለማዋሃድና የመጨረሻ ቡድናቸውን ዝርዝር ለማሳወቅ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ይሁንና የክለቦች መልካም ፈቃደኝነት ባለመኖሩ የዝግጅት ጊዜው ከ1 ወር ወደ አስር ቀናት እንዲያጥር እንዲሁም የወዳጅነት ጨዋታዎች ብዛትም ከ3 ወደ አንድ እንዲቀነስ ግድ ሆኗል፡፡
ለ6 ወራት ያለአንዳች ውድድር ተበትነው የቆዩት  ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫው የምድብ ማጣርያ በምድብ 6 ከጋና፤ ከኬንያና ከሴራሊዮን መደልደላቸው ይታወቃል፡፡ ከወር በኋላ የመጀመርያ ጨዋታቸውን  የሚያደርጉት ከሜዳ ውጭ ከጋና ብሄራዊ ቡድን ጋር ይሆናል፡፡ ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለስፖርት አድማስ በሰጡት አስተያየት የብሄራዊ ቡድኑ ባለቤት ህዝቡ እና ሁላችን ነን ብለው፤ በቴክኒክ ኮሚቴ ፀድቆ የቀረበውን የ1 ወር የዝግጅት እቅዳቸውን የፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ወደ 10 ቀናት ለማሳጠር መወሰኑን በመቃወም በከፍተኛ ደረጃ መከራከራቸውን አስገንዝበዋል፡፡ ፌደሬሽኑ፤ የክለብ አሰልጣኞች እና አመራሮች፤ ሚዲያ እና ህዝቡ ለብሄራዊ ቡድኑ የሚሰጠውን ትኩረት ለማሳደግ   በጋራ  እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ያቀረቡት ዋና  አሰልጣኙ፤ የዝግጅት እቅዶች ተለዋዋጭ መሆን የለባቸውም ሲሉም ያሳስባሉ፡፡ ክለቦች በጠቅላላ ጉባኤ በጋራ የደረሱበት ስምምነት ላይም በድጋሚ ምክክር በማድረግ እንዲሰሩም ይመክራሉ፡፡
በሌላ በኩል ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የሚያደርገው ተሳትፎ በተወሰነ መልኩ ጫና መፍጠሩ አይቀርም የሚሉት ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኮንጎው ክለብ ኤኤስ ቪታ ጋር በሜዳው የሚያደርገው ሁለተኛ ጨዋታም ከዋልያዎቹ የጨዋታ መርሃ ግብር የሚደራረብበት ሁኔታ እንደሚያስጨንቃቸውም ጠቁመዋል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያውን ከሜዳ ውጭ ከጋና ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ መጀመራቸው ፈታኝ እንደሚሆን ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ ሲያስገነዝቡ የ10 ቀናት ዝግጅቱ ሙሉና ውጤታማ ቡድን ለመገንባት እንደሚያስቸግራቸው አልሸሸጉም፡፡ በብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ አጀማመር ስኬታማ ለመሆን በተለዋጭ እቅዶች እየተንቀሳቀስኩ ነው ግን ብለዋል፡፡ በተለይ የጋና ብሄራዊ ቡድን በቅርብ ጊዜያት ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎች ቪዲዮ በጥልቀት እንደተመለከትን በተለያዩ የዓለም ሀገራት ያሉ የጋና ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች እንቅስቃሴም ስከታተል ቆይቻለሁ ብሏል፡፡ ከምድብ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ከመደረጉ 1 ሳምንት በፊት ከኡጋንዳ  ብሄራዊ ቡድን ጋር የሚያደርጉት የወዳጅነት ጨዋታ ቋሚ ተሰላፊዎቻቸውንና፤ አጠቃላይ የቡድኑን ስብስብ ለመለየት የምጠቀምበት ይሆናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአዲሱ ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የብሄራዊ ቡድኑን ሙሉ ሃላፊነት  ካስረከባቸው  ሳምንታት አልፈዋል፡፡  በውል ስምምነቱ እንደተጠቀሰው የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ሆነው ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የሚሰሩ ሲሆን፤ በ2019 እኤአ ላይ ካሜሮን ለምታስተናግደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ማብቃት እንዳለባቸው ተገልፆላቸዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለዋና አሰልጣኙ ውላቸው በስምምነት እስካልተቋረጠ ድረስም ከስልክ፣ መኪና እና ሹፌር እንዲሁም የጤና መድህን ወጭዎችና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ጋር በወር ያልተጣራ 100000 ብር ደመወዝ እንደሚከፍላቸው ይታወቃል፡፡ ከሳምንት በፊት የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ እና ስራ አስፈፃሚው ባፀደቀላቸው መሰረት ዋና አሰልጣኙ ሁለት ረዳት አሰልጣኞች የቅዱስ ጊዮርጊሱ ምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ እና የመከላከያ አሰልጣኝ በለጠ ገብረኪዳን ናቸው፡፡  ፀጋ ዘአብ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ሆኖ ሲመደብ፣ ይስሃቅ ሽፈራው የብሄራዊ ቡድኑ ወጌሻ እንዲሁም ዶክተር አያሌው የቡድኑ ሃኪም ሆነው ይሰራሉ፡፡ የስነ ልቦና እና የስነ ምግብ ባለሙያዎችን የፌደሬሽኑ የህክምና ኮሚቴ ከስራ አስፈፃሚው ጋር በመመካከር የሚያሳውቁ ይሆናል፡፡
ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ትውልዳቸው በምዕራብ ሸዋ ዞን ኮደዱላ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ሲሆን፤ ለበርካታ ዓመታት እግር ኳስን ተጫውተዋል፡፡ ላለፉት 24 ዓመታት በተለያዩ ክለቦች በአሰልጣኝነት ያገለገሉ ናቸው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ባንኮች፣ መከላከያ፣ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ክለቦችን  በማሰልጠን  ሰፊ ልምድ ያካበቱ ሲሆን የፕሪሚዬር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ባይችሉም ጠንካራ ቡድን  በሚገነቡበት አሰራራቸው ይታወቃሉ፡፡ በ1995 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን በማሰልጠን የሰሩ ሲሆን ለሦስት ዓመት ከሉሲዎቹ ጋር ሲያሳልፉ ለሦስተኛ ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፉ በማድረግም ውጤታማ ነበሩ፡፡
ዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከፌደሬሽኑ ጋር ውሉን በፈረሙበት ወቅት ለ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ብቻ ሳይሆን ሩብ ፍፃሜ መግባት ዕቅዳቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተለያየ ምክንያት ከብሄራዊ ቡድኑ ያገለሉ ተጫዋቾችንም ወደ ቡድኑ ሊመለሱ  እንደሚችሉም አስታውቀው ነበር፡፡ ይህን አስመልክቶ ዋና አሰልጣኙ ለስፖርት አድማስ በሰጡት አስተያየት ከቀድሞ ተጨዋቾች ወደ ብሄራዊ ቡድኑ እንዲመለስ በተለይ ጥረት ያደረጉት የቅዱስ ጊዮርጊሱን አዳነ ግርማ በማነጋገር ነበር፡፡ ‹‹አዳነን  ወደ ቡድኑ እንዲመለስ ስጠይቀው በቅርበት አግኝቼው ነው። ሁሌም ለአገሩ ለማገልገል ፍላጎት እንዳለው ገልፆልኝ በተለያዩ የግል ምክንያቶች  ግን ወደ ቡድኑ ለመመለስ እንደሚከብደው አስረድቶኛል፡፡ እኔም ሙሉ ለሙሉ አቋሙን ተረድቼ ውሳኔውን ተቀብያለሁ›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ለብሄራዊ ቡድን በመጀመርያ ምርጫ የጠሯቸውን ተጨዋቾች ስም ዝርዝር እስካሁን ያላሳወቁት ዋና አሰልጣኙ፤ በውጭ ካሉ ተጨዋቾች በተለይ በግብፅ የሚገኙት የአጥቂ መስመር ተሰላፊው ኡመድ ኡክሪና አማካዩ ሽመልስ በቀለ ለብሄራዊ በድኑ ለመሰለፍ መልካም ፈቃዳቸውንና ጉጉታቸውን መግለፃቸውንም ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2019 እኤአ ካሜሮን ወደምታስተናግደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የምድብ ማጣርያ በምድብ ስድስት የሚገኙ ሌሎቹ ቡድኖች ወደ ካምፕ ገብተው በመሰባሰብ ባይሆንም በተለያያ መንገድ ዝግጅቶቻቸውን ከጀመሩ ሳምንታት ተቆጥረዋል። በተለይ ኬንያ ለምድብ ማጣርያው ከፍተኛ ትኩረት የሰጠች ሲሆን የመጀመርያውን የወዳጅነት ጨዋታ ከሳምንት በፊት ከማላዊ ብሄራዊ ቡድን  በናይሮቢ አድርጋ ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡ የሃራምቤ ኮከቦች የሚባለውን የኬንያ ብሄራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት የሚመሩት ስታንሊ አኩዋምቢ ናቸው፡፡ ሰሞኑን ለዴይሊ ኔሽን በሰጡት አስተያየት በአፍሪካ ዋንጫ እና የቻን ውድድር በሚኖራቸው ዝግጅቶች ስኬታማ መሆን የሚቻለው የፌደሬሽን እና የፕሪሚዬር ሊግ አስተዳደር ትብብርና ድጋፍ ሲሰጡ ነው ብለዋል፡፡ ለብሄራዊ ቡድኑ ጠንካራ እና የተሟላ ዝግጅት ሲባል የፕሪሚዬር ሊጉ አስተዳደር በጨዋታዎች መርሃ ግብር ላይ የተወሰኑ ሽግሽጎችን እንዲያደርግ የጠየቁት ስታንሊ አኩዋምቢ፤ ክለቦች ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን በአስፈላጊው ወቅት በመልቀቅ እንዲተባበበሩ እና በየወሩ ቢያንስ  የወዳጅነት ጨዋታ ፌደሬሽኑ እንዲያዘጋጅላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በሌላ በኩል ከምድቡ ሰፊ የማለፍ እድል እንደያዘ የሚነገርለት የጋና ብሄራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝነት የሚመሩት ኩዋሲ አፒያህ ሲሆኑ ወደ ሃላፊነቱ የመጡት ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ አሰልጣኙ የጋና ህዝብ በአፍሪካ ዋንጫ እና በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን አምበሉ  አሰሞሃ ጊያንም ተመሳሳይ መልዕክት ነበረው፡፡ አሳሞሃ ጊያን ለጋና ክሮኒክል በቅርቡ በሰጠው አስተያየት በጋና ፕሪሚዬር ሊግ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች  ለብሄራዊ ቡድኑ ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸው መክሯል፡፡ ከ2012 እስከ 2014 የጋና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት ኩዋሲ አፕያህ በድጋሚ ጥቋቁር ክዋክብቶችን እንዲመሩ ሲመረጡ የሁለት ዓመት የቅጥር ኮንትራት  ተፈራመዋል፡፡ የጋና ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫው ሻምፒዮን እንዲያደርጉ እና ለ2018 የራሽያ ዓለም ዋንጫ እንዲያሳልፉ የጋና እግር ኳስ ፌደሬሽን ይፈልጋል፡፡

                 የምድብ 6 ጨዋታዎች

• ጁን 9 ፤ 2017 እኤአ ጋና ከኢትዮጵያ - ሴራሊዮን ከኬንያ
• ማርች 23፤ 2018 እኤአ ኢትዮጵያ ከሴራሊዮን - ኬንያ ከጋና
• ሴምፕተምበር 5 ፤ 2018 እኤአ ጋና ከሴራሊዮን - ኢትዮጵያ ከኬንያ
• ሴፕቴምበር 9፤ 2018 እኤአ ሴራሊዮን ከጋና - ኬንያ ከኢትዮጵያ
• ኦክቶበር 12 ፤ 2018 እኤአ ኢትዮጵያ ከጋና - ኬንያ ከሴራሊዮን
• ኖቬምበር 9፤ 2018 እኤአሴራሊዮን ከኢትዮጵያ - ጋና ከኬንያ

Read 2021 times