Sunday, 07 May 2017 00:00

ቀዩ ቀበቶ

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(2 votes)

  የህይወት ትርጉም ምንድን ነው? በሚል ዘወትር እብሰለሰል ነበር፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህይወት ትርጉም ኖራት አልኖራት የራሷ ጉዳይ! በሚል ማሰቤን እርግፍ አድርጌ ትቼዋለሁ፡፡ በህይወት ውስጥ ያለኝ ሚና የተመልካችነት ከሆነ ሰነባበተ። እናም ለኔ ህይወት ማለት በምድር ላይ ለሚታይ ትርኢት የመግቢያ ትኬት ናት፡፡ ትርዒቱን በቀጥታ ሥርጭት አልጀዚራ እያሳየኝ ነው፡፡ የጦርነት ውጥረት፣ ግጭት ፣ ፍጭት .. ምድር እንደ ጧፍ ቦግ ብላ ሥትነድ! ድው! ቡም! ዶግ አመድ! እንደ ምፅአት ቀን ውርጅብኝ ሁሉም ነገር ድብልቅልቁ ሲወጣ… ዓለም ድምጥማጧ ሊጠፋ ጣር ላይ ናት አይባል ነገር… “ምሳ ቀርቧል፤ በተቀመጥክበት አሸለበህ እንዴ?” ስትል ቀለሟ ቀሰቀሰችኝ፤ ከገባሁበት የቀትር ቅዠት ብንን ብዬ ነቃሁ፡፡
….ቀለሟ ተመላላሽ የቤት ሠራተኛዬ ነች። ወደ 30 ዓመት የምትገመት፣ አንገቷ በንቅሳት የተዥጎረጎረ ብስል ቀይ፡፡ ህይወቷ የተከደነ ምስጢር ነው፡፡ ሥራዋን በፍፁም እርጋታ ከመሥራት በቀር፣ “ሀገሬ እዚያ ነው… ከዚህ መጣሁ… ከዚያ ፈለስኩ ቅብጥስዬ” ስትል አትደመጥም፤ ዛሬ ግን ያለወትሮዋ ፈጠን  ፈጠን እያለች……
“እባክህን ማመልከቻ ጻፍልኝ”
“የምን ማመልከቻ…”
“ሁለት የ6 ዓመት ልጆቼን የነፃ ትምህርት ለማስተማር ….”
“መንታ ናቸው እንዴ ?”
“…አዎ መንታ ናቸው …. ወንድ እወልዳለሁ ብዬ መልሶ ሴት ሰጠኝ…”
‘መልሶ ሰጠኝ’  ምን ማለቷ ነው፤አልኩ ግርም ብሎኝ
“ቀለሟ፤ ሌላ ሴት ልጅ አለሽ እንዴ ! ”
“አዎና ! ከአንድም ሁለት…”
…..ፃፍልኝ ያለችኝን ማመልከቻ በምትፈልገው መልኩ ፃፍኩላት፡፡
ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ህይወት እንደምትገፋ… የልጆቿ አባት በህይወት ስለሌለ ልጆቿን በክፍያ ለማስተማር እንደማትችል ---- የነፃ ትምህርት ዕድል ለልጆቿ እንዲፈቀድላት ….
“የልጆችሽ አባት ህይወቱ ያለፈው መቼ ነው?...”
“…ህይወቱ ስለ ማለፉ እርግጠኛ አይደለሁም፤ ከሁለት ዓመት ወዲህ ድምፁን ሰምተን አናውቅም”
… በዚህች የማትረባ መናኛ ደመወዝ 4 ልጆቿን ያለ አባት ማሳደግ ቀላል ነገር አይደለም። ከሁኔታዋ እንደተረዳሁት፣ ወንድ የመውለድ ምኞቷ የጋለ ነው፡፡ “ወንድ እወልዳለሁ” በሚል የልጆቿን ቁጥር እየጨመረች፣ ወደ ከፋ የድህነት አረንቋ ሊሰነቀር በቋፍ ያለ ህይወቷ አሳዘነኝ፡፡ ቀለሟ መመከር አለባት፡፡ ስለ ቅርብ ዘመዴ እትዬ ስንቄ አነሣሁባት፤ ወንድ እወልዳለሁ በሚል 10 ሴት ስለመውለዳቸው አጫወትኳት…
“….እናም ቀለሟ፤ ወንድ ልውለድ በሚል እልህ….”
አላስጨረሰችኝም “…ወንድ ልጆችማ አሉኝ..”   
“እዚህ አዲስ አበባ? ”
“ሀገሬ ላይ እንጂ!! ሁለት ወንድ ልጆች የወለድኩለት የ80 ባሌ መሸተኛ ሆኖ ነጋ ጠባ ሲደበድበኝ ወደ አዲስ አበባ ኮበለልኩ…. ምኑንም የማላውቅ አንድ ፍሬ ልጅ ነበርኩ”
የቀለሟ ልጆች ብዛት 6 ደርሷል፤ ግማሽ ደርዘን መሆኑ ነው፡፡
የልደታ እለት ደመወዟን ከተቀበለችኝ በኋላ፣ 200 ብር ቆጥራ በእጄ እያስጨበጠችኝ …
“ይህችን 200 ብር ለልጄ በባንክ ላክልኝ”
“የት? ለማንስ ብዬ ?”
“ዲላ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነው፤ ሁነኛው አናውጤ ጨርቆሴ ይባላል…”
“ከህግ ባለቤትሽ ከወለድሻቸው አንደኛው ልጅ ነውን ? ”
“አይደለም፤ ጎጆ ከመውጣቴ በፊት ከከንፈር ወዳጄ የወለድኩት የበኩር ልጄ ነው… ያኔ ምኑን አውቄው አንድ ፍሬ ልጅ ነበርኩ …”
ይገርማል እኮ ሰዎች… ‘ያኔ ምኑን አውቄው አንድ ፍሬ ልጅ ነበርኩ…’ እያለች ለዚህች የመከራ ምድር 7 ልጆችን አስቆጥራለች፡፡ ህይወት ማለት ቁጥር ትሆን እንዴ! መኖራችንን የምናውቀው ዕድሜያችንን ስንቆጥር ወይም በመንግስት ስንቆጠር ይመስለኛል፤ እናም የቀለሟን ልጆች የመቁጠር ግዴታ ያለበት መንግስት እንጂ እኔ አይደለሁም፡፡
አንበርብር አናውጤ ጨርቆሴ የሚለው አስፈሪ ስም ባሳደረብኝ የፍርሀት ተፅዕኖ ከራሴ አንድ መቶ ብር ጨምሬ 300 ብር በንግድ ባንክ ላኩለት፡፡…..
ሚያዝያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም ምሳዬን በዝምታ ተመገብኩ፤ ከቀለሟ ጋር መነጋገር አልፈለግሁም፡፡ የሆነ ርዕስ በተነሳ ቁጥር የቀለሟ ልጆች ከተደበቁበት ስውር ዓለም ብቅ እያሉ መቁጠሩ ታክቶኝ ነበር። ስራዋን አጠናቃ ወደ ቤቷ ለመሄድ እየተዘጋጀች …
“ዛሬ የመንታ ልጆቼ ልደት ነው - ከተመቸህ ብቅ በል” ብላኝ ወጣች ፡፡
ከስራ እንደወጣሁ ወደ አንድ መደብር ጎራ ብዬ ሁለት እሽግ ብስኩት ገዛሁና ወደ ልደት ጥሪዬ አዘገምኩ፡፡ ለአይን ያዝ ሲያደርግ ቀለሟ ቤት ደረስኩ፡፡
…ጠባቧ ክፍል በእንግዶች ጢም ብላለች፡፡ ህፃናቱ እንደ ጨረባ ተስካር ይንጫጫሉ፡፡ በርጩማ ላይ የተቀመጠ ጎልማሳ ሰውዬ እይታዬን ሳበው። እንደ ምፃተኛ ባይተዋር፣ ራሱን ነጥሎ በዝምታ ተክዟል፡፡ ቀለሟ ድፎ ዳቦና ኬኔቶ እያቀረበችልኝ…..
“ባለቤቴ ነው ---- ተዋወቀው” አለችኝ
“ጋሻው” ሲል ተዋወቀኝ
…..አፋር ክልል ውስጥ በሚገኝ ሲኦል መሰል የጨው ማምረቻ ውስጥ እንደሚሰራ … ለሁለት ዓመት ደብዛውን አጥፍቶ፣ በፋሲካ ዋዜማ ወደ ቤት መምጣቱን አጫወተኝ …..
ጋሻው ታሪከ ብዙ ነው፡፡ ጅማ ላይ ቡና ነግዷል….ጅጅጋ ላይ ኮንትሮባንድ ሰርቷል….. ወደ ሰላሳ ሺህ ብር የያዘ እቃ ሲወረስበት ለእብደት ተቃርቦ መመለሱን ….. ናዝሬት ላይ ሉካንዳ ቤት ከፍቶ በኪሳራ መዝጋቱን …. አጋሮ በልብስ ሰፊነት ….. ደሴ ላይ በአናፂነት…… አዋሳ በባሬስታነት መስራቱን ዘረዘረልኝ …. “ከሀገር ሀገር የሚያዞር አባዜ ነበረብኝ…. መሐል መርካቶ ሰልባጅ ስነግድ ነው ከቀለሟ ጋር የተዋወቅነው …. የእህል ውሃ ነገር ሆኖ ወልደን ከብደን …” በማለት ስለ ትዳሩ አቆራቆር አወጋኝ፡፡ “የእድሌ ደመራ አመድ ሆኗል…. ቤሳቤስቲን የለኝም… በምድር ለመኖር አምስት ደቂቃ ቢቀርህ እንኳን ገንዘብ ያስፈልግሀል” ለአፍታ ዝም ካለ በኋላ፤
“በገዛ እጣ ፈንታዬ ላይ ማመጽ የለብኝም … ውድቀቴን እንደ አመጣጡ እያስተናገድኩት ነው… ለሽንፈት እጄን አልሰጥም፤ ምናልባትም ወታደራዊ ህይወቴ …..”
 “ወታደር ነበርክ እንዴ?”
“ያውም 181 እስፓርታ ….. ከክፍሌ ተመልምዬ ለልዩ ስልጠና ወደ ኮሪያ ከተላኩት ምርጦች አንዱ ነበርኩ… በቴኳንዶ እስከ ቀይ ቀበቶ ደረጃ የተቀዳጀሁ…” ንግግሩን ቆም አድርጎ የሻጉራ አየኝ። ያወራልኝን ነገር ያመንኩት ስላልመሰለው….
“ቀለሟ፤ ያንን ቀይ ቀበቶ ለወዳጄ ላሳየው?!”
ቀለሟ ከሳጥን አውጥታ ሰጠችው፡፡ እንደ ኮብራ እባብ የተጠቀለለ ደማቅ ቀይ ቀበቶ …. ጋሻው የቀበቶውን ጥቅል ዘረጋው፤ መሀሉ ላይ በሜዳልያ የተሽቆጠቆጠ፣ ምትሀታዊ ቀበቶ። “የዚህን ቀበቶ ትክክለኛ ዋጋ … የከፈልኩለትን መስዋዕትነት … ልጆቼ በተረዱ ጊዜ ምን ያህል ታላቅ ኩራት እንደሚያጎናጽፋቸው ….” እያለ ቀበቶውን ኮቱ ላይ እንደ ዝናር ታጠቀው፡፡ ከነተበ ካፖርት መሳይ ኮቱ ጋር፣አስቂኝ የካርቶን ምስል ሆነና አረፈው፡፡
የልጆቹ መንጫጫት ጋብ ብሏል… ቀለሟ ከጎረቤቶቿ ጋር በሹክሹክታ እያወራች ነበር... “ይመስገነው፤ ት/ቤቱ ቀበሌ ያስመሰከርኩበትን ማመልከቻዬን ተቀበሉኝ፤ ሁለቱንም ልጆቼን በነጻ ሊያስተምሩልኝ ነው”
አይነ ፈጣጣ፣ ጥርሰ ገጣጣዋ ሴትዮ፤“እኔማ አባታቸው በህይወት የለም ብዬ ለመመስከር እንዴት ከብዶኝ ነበር !!… ለነገሩ ጋሻው ሁለት አመት ሙሉ እምጥ ይግባ ስምጥ ….”
ጋሻው የእነ ቀለሟን ወሬ ልቅም አድርጎ ሰምቷል። ቀለሟ ላይ አይኑን እያጉረጠረጠ፤ “በህይወት የሌለው አባት ማነው? ለምንስ ምክንያት?” ሲል በመስቀለኛ ጥያቄ አጣደፋት። ቀለሟ ሀቁን ፍርጥ አድርጋ ነገረችው፤ ጋሻው ለቀለሟ ምንም ምላሽ አልሰጣትም …… እንደተነፈሰ ከመነዳሪ ሙሽሽ አለ፤ የአይኖቹ ውጋገን እንደምትጠልቅ ጀንበር ስልምልም ሲሉ ያየሁ መሰለኝ፡፡ ... ጋሻው ወደ ሽንት ቤት ወጣ ባለበት፣ ቀለሟንና ያቺን ሾካካ ሴትዮ እየወቀስኳቸው ሳለ፣ በመሀል የአንዲት ሴት እሪታ ሰፈሩን አደበላለቀው። በጥድፊያ ከቤት ወጥቼ የምትጮኸው ሴትዮ አጠገብ ደረስኩ፤ እሪታዋን እያቀለጠች፣ ወደ ሽንት ቤቱ በአመልካች ጣቷ ጠቆመችኝ…. በደመነፍስ ተደናብሬ የሽንት ቤቱን በር እንደበረገድኩት…. ባየሁት ጉድ፣ ክው ብዬ ደነገጥኩ፤ ጋሻው በዚያ ቀይ ቀበቶ ራሱን ሰቅሎ ነበር……  

Read 3431 times