Sunday, 07 May 2017 00:00

እንደ ሀገር ባለውለታ፤ የመከበር መሥፈርቱ ምንድን ነው?

Written by  ጤርጢዮስ - ከቫቲካን
Rate this item
(2 votes)

  የታዋቂውን ኢትዮጵያዊ አስትሮፊዚስት፣ ዶ/ር ለገሠ ወትሮን የህልፈተ ህይወት መርዶ የሰማሁት ከአንድ የቅርብ ወዳጄ ነው፡፡ ስልክ ደውሎ፤ “ዶ/ር ለገሠ ወትሮ ማለፉን እገሌ ነገረኝ፣ ቀብሩ ነገ ነው፣ ቦታውም እንዲህ ነው፣ ከቀብሩ በፊት ግን ቤተ ክርስቲያን የሽኝት ፕሮግራም ተዘጋጅቶለታል። እኔ አልችልም፣ አንተ ግን ተገኝ” ብሎኝ ብዙም ወሬ ሳያበዛ ስልኩን ዘጋው፡፡ ንግግሩ ከልብ ማዘኑን ያሳብቅበታል፡፡ እኔም በጣም ደንግጬ ስለነበር፣ ከዚያ በላይ ምንም ማለት አልፈለግሁም። ሆኖም ቤት ዘግቼ ስለ አሟሟቱ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ዕድሜ ለቴክኖሎጂው ፈጣሪዎች፣ “ጎግል” ውስጥ ገብቼ መረጃ መጎልጎያ ቁልፎቹን ተጫንኩ፡፡ የዶክተር ለገሰ ወትሮን አሟሟት በተመለከተ በዕለቱ ከተደረደሩት የድረ ገፅ ምርጫዎች፣ የድሬ ቲዩብን ያህል ጥሩ ተደርጎ የተፃፈ ዘገባ አላገኘሁም፡፡
ድረ ገፁ የዶክተሩን ዜና ዕረፍት አስመልክቶ ባሰፈረው ዘገባው፤ ዶ/ር ለገሰ ወትሮ በዓለም የታወቀ ኢትዮጵያዊ አስትሮፊዚስት እና የኢትዮጵያ ስፔስ MST (Esss) መሥራች ስለመሆኑ ጠቅሶ ሴት ልጁ፣ ግቢው ውስጥ ባለ አትክልት ውስጥ ወድቆ እንዳገኘችውና የህክምና ሪፖርቱ፣ ከዚህ ቀደም ከልብ ጋር የተያያዘ ችግር እንደነበረው ማመልከቱን ይጠቁማል፡፡ ዶ/ር ለገሠ ወትሮ፤ በህይወት ዘመኑ ካከናወናቸው ተግባራት በርካቶቹን በዝርዝር ያስቀመጠው ድረ ገፁ፤ ከዶክተሩ ስራዎች ይግረማችሁ ያለውንና ለ460 ዓመታት ሳይፈታ የቆየን አንዳች ጂኦሜትሪካል እንቆቅልሽ ስለመፍታቱ ይጠቅሳል፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 ከአሜሪካ ባዮግራፊካል ኢኒስቲቲዩት (ABI) “የዓመቱ ሰው” ተሰኝቶ ሽልማት መቀበሉን ያወሳው ድሬ ቲዩብ፤ የሟቹን የቀብር ቀን፣ ቦታና ሰዓትም ጠቁሟል፡፡  
ይሁንና ከድረ ገፁ ያገኘሁት የቀብሩ ቦታ ጥቅማ     “መርዶ ነጋሪው” ባልንጀራዬ ከነገረኝ ጋር ልዩነት ነበረው፡፡ ምክንያቱም የቀብሩ ትክክለኛ ቦታ ጉለሌ አካባቢ በተለምዶ “የጴንጤዎች መቃብር” እየተባለ በሚጠራው ቅጥር ግቢ ውስጥ ስለነበር ማለቴ ነው፡፡ ለቀብር አፈፃፃሙ በወጣው መርሃ ግብር መሰረት፤ ከሶስት ሰዓታት በፊት የአስክሬን ሽኝቱ በሚከናወንበት ጉለሌ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን መገኘት ነበረብኝና ሦስት ያህል ታክሲዎችን አፈራርቄ በሰዓቱ ቦታው ደረስኩ፤ እንዲያ ተጣድፌም ያለማጋነን የቀደሙኝ ሰዎች ቁጥርም ቢሆን ከሦስት የሚበልጥ አልነበረም፡፡ ኋላ ላይ ግን በርካቶቹ ሰዎች አስክሬኑን አጅበው ለመምጣት ወደ መኖሪያ ቤቱ ማቅናታቸውን አስተዋልኩ፡፡
በመርሃ ግብሩ ቅደም ተከተል መሰረት፤ የመክፈቻ     ፀሎት በመጋቢ ፍቃዱ አይጋ ከተደረገ በኋላ ዶ/ር ለገሠ ወትሮ በህይወት ሳለ ከደረሳቸው መንፈሳዊ ዝማሬዎች መካከል ሁለት ያህሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዘምራን ተዜሙ፡፡ በእውነት ልብ የሚነኩና መሳጭ ናቸው፡፡ በመቀጠል የስነ መለኮት መምህርና መጋቢ የሆኑት ሰለሞን አበበ ገብረመድህን፤ ቃለ እግዚአብሔር ከማቅረባቸው በፊት “በፊዚክስ የሳይንስ ዘርፍ ተመራማሪ፣ የስነ ክዋክብት አስትሮኖሚና የስነ ፈለክ አስትሮፊዚክስ ጥናት ኮከቡ፤ ከህዋው በታች ውድቆ ከህዋው ባሻገር ሄደ፡፡ በኢትዮጵያ ክርስትና ታሪክ ውስጥ ቀደምት የወንጌላውያን መዝሙራት ከዋክብት አንዱ የነበረው ኮከብ፤ በዚህች ፕላኔት ላይ ለመኖር የተሰጠው ዕድሜ ተጠናቀቀ፡፡ ሀገር ስትሞቀው የኖረችው ኮከብ፤ የምድር ጉዞውን ጨረሰ፡፡ አንድ ሌላ ታላቅ ዋርካ ከኮረብታ በላይ ተሰበረ” በማለት ልብ የሚነካ ንግግር አደረጉ፡፡ በመዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ዘጠና ላይ የሰፈረው የወሌ ፀሎት ደግሞ የስብከታቸው ድርና ማግ ነበር፡፡ የሰውን ህይወት ጤዛነትና የነገ ተስፋ አስተሳስሮ የተወሳ ግሩም መልዕክት ነበር፡፡
ከዚያም የዶ/ር ለገሠ ወትሮ ባለቤት፣ ወ/ሮ አገሬ ደምሴና የበኩር ልጁ አቶ አርአያ ለገሠ፣ ሀዘንና ተስፋ የተቀላቀለበት ንግግር በማድረግ፣ ስለ ሟቹ ባልና አባት ስሜታቸውን ገለጡ፡፡ ሦስት ያህል ዶ/ር አብሮ አደጎች፣ የመንፈሳዊ አገልግሎት አጋሮችም፣ ከሟቹ ለገሰ ወትሮ ጋር ስለነበራቸው የህይወት ዘመን ቆይታም ምስክርነታቸውን ሰጡ፡፡ የቀብሩ ሰዓት እንዲጠበቅ የፈለጉት የቤተ ክርስቲያኒቱ መጋቢ፤ “በዚያ የሚጠብቁን እንግዶች ስላሉ ባይረፍድባቸው ጥሩ ነው” የሚል ማስታወቂያ ከተናገሩ በኋላ ጉዞ ወደ መካነ መቃብሩ ሆነ፡፡ በእርግጥም እንዲህ ዓይነቱ “የአገር ዋርካ” ሲሞት ሽኝቱ ላይ የሆነ ሰላማዊ ግርግር መኖሩ የሚጠበቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ይመጣሉ ተብለው ከሚጠበቁት ሰዎች አንዳንዶቹ የፀጥታ ጥበቃ ስለሚያስፈልጋቸው አካባቢው ላይ ሽርጉዶች ያበዛሉ፡፡ ለዚህም ነበር በወዳጄ ዶ/ር መሐሪ ታደሰ መኪና የመሳፈር ዕድል ማግኘቴን እንደ ጥሩ አጋጣሚ የቆጠርኩት። ምክንያቱም ቶሎ ስፍራው ላይ ደርሼ ነገሮችን ለመታዘብ በብርቱ ሽቼአለሁ፡፡ መጋቢ ሰለሞን አበበ “ተሰበረ” ያሉትን የሀገር ዋርካ መሰበር አስመልክቶ የሀዘን መግለጫ የሚሰጠውን የመንግስት ባለስልጣን ንግግር በቅርበት ሆኜ ለማዳመጥ ጓጉቻለሁ፡፡ ይሁንና እንደጠበቅሁት የሆነ ምንም ነገር አልነበረም፡፡ እውነታውም የዶ/ር ለገሠ ወትሮ የቀብር ሥነ ስርዓት እንደ ማንኛውም ሰው ቀብር መሆኑ ነበር፡፡
ገድለ ለገሠ ወትሮ
አሁን ዶ/ር ለገሠ ወትሮ ለ20 ዓመታት በመምህርነት ያገለገለበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተራ ነው፡፡ የህይወት ታሪኩ ፅሁፍ የተዘጋጀውም ሆነ የተነበበው በዩኒቨርሲቲው በኩል ነው፡፡ ያነበቡት ዶ/ር አሸብር ናቸው፡፡ “የዶክተር ለገሰ ወትሮ አጭር የህይወት ታሪክ” በሚል ርዕስ የቀረበው ፅሁፍ ረጅም በመሆኑ ሁሉንም መዘርዘር ባልችልም ለትዝብቴ ማነፃፀሪያነት ይረዳኝ ዘንድ ግን መጠነኛ በሆነ የራሴ አቀራረብ ገድሉን የመዘከር ግድ አለብኝ፡፡ እነሆም ታሪኩ ከብዙ በጥቂቱ የሚከተለውን ይመስላል፡- (አንቱታውን በአንተ የቀየርኩትም እኔ ነኝ)
ዶ/ር ለገሠ ወትሮ በቀድሞ አጠራሩ በአርሲ ክፍለ ሀገር፣ ልዩ ስሙ አርሲ ቢሬ በተባለ ቦታ በ1942 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ዕድሜው ለትምህርት እንደደረሰ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በኃይሌ አባ መርሳ ትምህርት ቤት ተከታተለ፡፡ በተለይ የሂሳብ ትምህርት ላይ ያለው ተሰጥኦ፣ ለአእምሮው ብሩህነት ምስክር ከመሆኑም በላይ በአንድ ዓመት ሁለት ክፍሎችን እየዘለለ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በሶስት ዓመት አጠናቆ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በራስ ዳርጌ ት/ቤት ተከታትሏል። 11ኛ ክፍል እንደደረሰ በመላው ኢትዮጵያ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተመረጡ ተማሪዎች ይገቡበት ወደነበረውና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደሚገኘው በእደ ማሪያም ትምህርት ቤት ለመግባት በቅቷል። በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ሂሳብና ፊዚክስ ማጥናት ምርጫው ስለነበረም የዩኒቨርሲቲው የፊዚክስ ዲፓርትመንት በመቀላቀል ዕድሜ ልኩን የተመራመረበትን የፊዚክስ ሙያ ተምሮ ወደ ሌሎች እርከኖች ተሸጋግሯል፡፡
ዶ/ር ለገሰ ወትሮ፤ ዩኒቨርሲቴ በቆየባቸው ዓመታት ጎበዝ የፊዚክስ ተማሪ ከመሆኑም ባሻገር በመንፈሳዊ ህይወቱም ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበረው የህይወት ታሪኩ ይገልፃል፡፡ በዩኒቨርሲቲ አራት ዓመት ቆይታው ብቻ ከ80 በላይ የሚሆኑ መንፈሳዊ ዝማሬዎችን ስለመድረሱ፣ ስለማቀናበሩና ስለመዘመሩም ያወሳል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መመረቁን ተከትሎ በነፋስ ስልክ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተመድቦ፣ ለሁለት ዓመታት ካስተማረ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ዲፓርትመንት ተዛውሮ በመምህርነት አገልግሏል፡፡
በዚህ የአገልግሎት ዘመኑም በሚሰራበት ዩኒቨርሲቲ፣ የድህረ ምረቃ ትምህርቱን በላቀ ውጤት በማጠናቀቅ የሳይንስ ማስተርስ ዲግሪ አግኝቷል፡፡ ዶ/ር ለገሰ ወትሮ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1979 ዓ.ም መጨረሻ ለፒኤችዲ ትምህርት እንግሊዝ አገር ወደሚገነው ሼፊልድ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት ሁለተኛ ማስተርስ ዲግሪውን ሲያጠናቅቅ፣ሁለት ጥናታዊ ፅሁፎችንም ለህትመት አብቅቷል፡፡ ሆኖም በእንግሊዝ አገር የፒኤችዲ ትምህርቱን ለመቀጠል የማያስችለው ሁኔታ የገጠመው ዶ/ር ለገሰ ወትሮ፤ ፊቱን ወደ ሀገረ አሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ እንደተገደደ ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው የህይወት ታሪኩ ይጠቅሳል፡፡ አሜሪካ ከገባ በኋላ በአሜሪካን አገር የሚሰጠውን ፈተና ማለፉም ብቻ ሳይሆን “ናሣ” ተብሎ የሚጠራው የአሜሪካ የጠፈር ምርምር መስሪያ ቤት፤ የገንዘብ ድጋፍ በሚገኝበት የምርምር ፕሮጀክት ላይ የፒኤችዲ ትምህርቱን ለመጀመር እንደተመረጠና በአሜሪካ ቆይታውም በትላልቅ አማካይነት ቴሌስኮፖችን ከመሬት ከባቢ ብዙ ሺ ሜትሮች ከፍታ በመላክ መረጃ የሚሰበስቡ ቴሌስኮፖችን የመደረዝ (ካሊብሬት የማድረግ) ኦሪጅናልና ወጥ የሆነ ስራ ስለማከናወኑ፣ ከብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ከፍታ በቴሌስኮፖች የሚሰበስቧቸውን መሳሪያዎች የሚተነትንና ምሥያዎች ተመልሰው የሚዋቀሩበትን ሂሳባዊ ቀመር ብቻ ሳይሆን ቀመሩ በኮምፒዩተር ላይ የሚሰራበትን ፕሮግራም በመጻፍ በዙሪያው ባሉ ሁሉና በዩኒቨርሲቲው አድናቆትና ሞገስ ያስገኘለትን ስራ ስለማከናወኑ ይተርካል፡፡
“የህዋ ሳይንስ ተመራማሪው ስንብት” በሚል ርዕስ የአዲስ ዘመኑ ብሩክ በርሄ በሚያዚያ 22 ቀን 2009 ዓ.ም “የህይወት እንዲህ ናት” ዐምድ ላይ በሰራው የትውስታ ዘገባ፤ ከወራት በፊት ከዶ/ር ለገሠ ወትሮ ጋር አድርጎት የነበረውን ቃለ ምልልስ በማስታወሻነት አቅርቧል፡፡ በዚያም ቃለ ምልልስ ወቅት ዶ/ር ለገሰ ወትሮ ስለ ምን የፒኤችዲ ትምህርታቸውን በአገረ እንግሊዝ መከታተል እንዳልቻሉና ወደ አሜሪካ እንዳቀኑ፣ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ለምን እዚያ ጥቂት ጊዜ ለመቆየት ፈልገው የመኖሪያ ፈቃድ እንደተከለከሉ፣ ታህሳስ 18 ቀን 2008 በወጣው የአዲስ ዘመን ዕትም የተናገሩትን አቅርቦታል፡፡
የእንግሊዝ አገሩ የፒኤችዲ የትምህርት ዕድል ከገጠማቸው አፍሪካውያን ተማሪዎች አንዱ ዶ/ር ለገሠ ወትሮ መሆናቸውን የጠቀሰው ጋዜጣው፤ ከአስተማሪዎቹ መካከል ጆንስ የተባለ ነጭ መምህር፣ ጥቁርን አብዝቶ ይጠላ ስለነበር፣ ዶ/ሩ ሁለተኛ ማስተርሳቸውን በሚሰሩበት ወቅት የረባ ድጋፍ ስላላደረገላቸው፣ “ጆንስ ምንም ስላልረዳኝ ለፒኤችዲ እንዲያሰለጥነኝ አልፈልግም” የሚል አቋም በመያዝ ወደ አሜሪካ ፊታቸውን ለማዞራቸው ምክንያቱ ይኸው እንደነበር ይገልፃል። አሜሪካን አገር የፒኤችዲ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁም በኋላ እዚያ ጥቂት ጊዜ ለመቆየት ያደረጉት ሙከራ ያልተሳካበትንም ምክንያት ብሩክ በርሄ እንደሚከተለው ተርኮታል፡-
“በሀሳብ ጭልጥ ብሎ ተጉዟል፡፡ ከአሜሪካው የስደተኞች ጉዳይ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ጎራ ብሎ የመስተንግዶ ተራውን እየተጠባበቀ ነው፡፡ ደግሞም የሚያብሰለስለው አንድ ጉዳይ በውስጡ ይንገዋለላል፡፡ መልሳቸው ምን ሊሆን ይችላል? ሲል ቢጠይቅም እራሱ ሊመልሰው ግን አልቻለም። ዓላማው በአገረ አሜሪካ የመሰንበቻ ዕድሜውን ለማራዘም ቪዛ ማሳደስ ነው፡፡ ይሁንና ቀደም ብሎ የሰማው ጭምጭምታ፣ የመስተንግዶውን ምላሽ ቀናነት በጥርጣሬ እንዲጠብቅ አድርጎታል። በወቅቱ የዶክትሬት ዲግሪውን ለማግኘት ያበቃው የምርምር ውጤት፣ በነጭ መምህራኑ ዘንድ በፅኑ ተፈልጓል፡፡ መምህራኑ ብቻ ሳይሆኑ በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም የምርምር ውጤቱ ትልቅ ትኩረት አግኝቷል፡፡ በወቅቱ ለ“ስጠን” ጥያቄያቸው፣ ምላሹ አዎንታዊ ይሆናል ብለው የተማመኑ አካላት፣ “የምርምር ውጤትህ ለተጨማሪ ስራ ያስፈልጋልና፣ ወዲህ በል” ሲሉ ቀጭን ትዕዛዝ ሰጡት፡፡
የእርሱ ምላሽ ግን ‹‹አሻፈረኝ›› ሆነ፡፡ ምላሹ ያልጠበቁት የሆነባቸው የዩኒቨርስቲው አካላት በጣም ተበሳጩ፡፡ ጉዳዩን ዝም ብለው ማለፍ አልወደዱም፡፡ በንዴት ‹‹ያስተማርንህ ለእኛ ጥቅምና አገልግሎት መሆኑን ዘነጋህሳ›› በሚል ስሜት፣ አገራቸውን ፈጥኖ እንዲለቅ ጫና ፈጠሩበት፡፡ ቪዛው እንዳይታደስ አደረጉ፡፡ ውሳኔያቸው ያስደነገጠው የቀመሩ ባለቤት፤ በወቅቱ ሁለት ምርጫዎችን በህሊናው ውስጥ መገላበጥ ጀመሩ፡፡ አንድም ጥናቱን አስረክቦ በአሜሪካ መቆየት አልያም ጓዙን ጠቅልሎ ወደ እናት ሀገሩ መመለስ፡፡ በሁለት ጫፎች የተወጠረ የፍላጎት ግጭት ገጠመው፡፡ በመጨረሻም ‹‹ከለከላቸው›› በማለት አስፍሯል፡፡
‹‹ ሳይንስ እና መንፈሳዊነት››
ዶ/ር ለገሠ ወትሮን ከክርስቲያናዊ እምነቱ አፋቶ፣ ሳይንሳዊ ተመራማሪነቱን ብቻ መግለፅ የሚቻል አይደለም፡፡ ለእርሱ ሁለቱም ሰምና ወርቅ ናቸው፡፡ ይህንንም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከመግለፅ ተቆጥቦ አያውቅም፡፡ ስለህዋ - ዓለሙ የትየሌለነትና የአደራደር ጥበብ በአድናቆት በሚያወራበት ልክ፣ እነዚህ ሁሉ ሰሪና ባለቤት እንዳላቸው ሳይጠቁም አያልፍም፡፡ እምነቱን ባገኘበት ቅዱስ መጽሐፍም ውስጥ፡- ‹‹የማይታየው ባህርይ እርሱም አምላክነቱ ከተሠሩት ታውቆ ግልፅ ሆኖ ይታያል›› የሚል ደግሞም በመዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 19፡1 ላይ፤ ‹‹ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይ ጠፈርም የእጁን ስራ ያወራል›› የሚል ቃል ተፅፎ ይገኛልና ለእምነቱም ቢሆን የሚያቀርበው መረጃ የሌለው አይደለም፡፡
ቀደም ብዬ ስሙን የጠቀስኩት የአዲስ ዘመኑ ጋዜጠኛም በዘገባው፤ ‹‹ሳይንስ እና መንፈሳዊነት›› ብሎ በሰየመው ንዑስ ርዕስ ዶ/ር ለገሠ ወትሮ ‹‹እኔ መንፈሳዊ ሰው ነኝ›› እንዳለው ጠቅሶ በብዙ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ሳይንስና ሃይማኖት፣ ውሃና ዘይት ተደርገው ሲወሰዱ ቢስተዋሉም እርሱ ግና ለሰው ልጅ የማሰቢያ አእምሮ የቸረው ፈጣሪ እስከሆነ ድረስ ያንን ለበጎ ዓላማ መጠቀም ከሃይማኖት ጋር ምንም ዓይነት ግጭት እንደሌለው እንዳጫወተው ይገልፃል፡፡
ይህ ሰው በሁሉም ሰፈሮች ደምቆ ሲያበራ የኖረ ኮከብ እንደነበር በሽኝቱ ላይ ስብከት ያቀረቡት መጋቢ፤ ‹‹ሀገር ስትሞቀው የኖረችው ኮከብ፤ የምድር ላይ ጉዞውን ጨረሰ፣ አንድ ሌላ ታላቅ ዋርካ ከኮረብታ በላይ ተሠበረ›› ማለታቸውም ይህንኑ ይጠቁማል፡፡
በመኪናው አሳፍሮ ከሽኝቱ ቦታ ወደ መካነ መቃብሩ የወሰደኝ ወዳጄ ዶ/ር መሐሪ ታደሰ አስተያየትም ይህን የሚመስል ነበር፤ ‹‹ዶ/ር ለገሠ ወትሮ እግዚአብሔር የሰጠው ብሩህ አእምሮና የተለወጠ ልብ አለው፡፡ በሙያውም ሆነ በመንፈሳዊ ፀጋው የአገርና የቤተክርስቲያን ታላቅ ባለውለታ ነው።›› በማለት የጀመረው ወዳጄ አክሎም፤ ‹‹አንዳንድ ሰው ወደ ሳይንሱ ዓለም ጠልቆ ሲገባ እምነቱን ይጥላል፣ ሌላው ደግሞ ወደ እምነት ጭልጥ ብሎ በገባ ጊዜ ከሳይንሳዊ እውነታ ጋር ሳይቀር ይፋታል፡፡ ዶ/ር ለገሠ ግን ሁለቱንም ጫፎች ያለ ተቃርኖ አስታርቆ መኖር የቻለ ሰው ነው፡፡ ቅድም ጓደኞቹ አዲሱ ወርቁ፣ ፕሮፌሰር ጥላሁን አደራና ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም ሲናገሩ እንደሰማኸው ይሄ ሰው በልቡ ውስጥ የተተከለውን እምነትና በስሌት የበለፀገውን አእምሮውን አስማምቶ ለመጓዝ ያልቸገረው ሰው ነው፡፡›› ብሎኛል፡፡
ወዳጄ ይህን ብቻ ብሎ አላቆመም፡- ‹‹ዶ/ር ለገሠ ወትሮ፤ በአገር ደረጃ ትልቅ አንጡራ ሀብት ነው፤ በእምነት ደረጃ ስትሄድ ደግሞ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዝማሬዎቹ ብስለት የተመሰገነና ለትውልድ ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡ ዝማሬዎቹ ዘመን ተሻጋሪና አጥቢያ ዘለል ናቸው፡፡ በነበረው ዕውቀትም ሆነ እምነት ተፅዕኖ ፈጣሪ ነበር። በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ የጠፈር ምርምር ጣቢያ (ናሣ) ውስጥ አሉ ከሚባሉት ሳይንቲስቶች አንዱ ዶ/ር ጥላዬ ታደሠ፣ የዶ/ር ለገሠ ወትሮ ተማሪ ነበር። የመመረቂያ ፅሁፍ (ቴሲስ) አማካሪ እርሱ ነበር። የምርምር ትኩረታቸውን በዋናነት ፀሀይ ላይ ካደረጉ ተመራማሪዎች አንዱ ዶ/ር ጥላዬ ነው፡፡ ይህ ሰው ሳይንሳዊ እውቀትን ብቻ ሳይሆን ክርስቲያናዊ ህይወትንም ከዶ/ር ለገሠ ወትሮ መቅዳቱን ስለ እምነቱ በሚሠጣቸው ምስክርነቶች ማረጋገጥ ትችላለህ፡›› ሲልም አጫወቶኛል፡፡
እንደ መደምደሚያ
የእምነትና መንፈሣዊነት ጉዳይ ምንም ስሜት የማይሠጣቸው በርካታ አንባብያን ስለሚኖሩ ያንን ተወት ላድርግና የጋራ ወደሆነው ጉዳይ ልግባ። ሆኖም እየፃፍኩ ያለሁት ስለ ዶ/ር ለገሠ ወትሮ ‹‹የህይወት ታሪክ›› እስከሆነ ድረስ ይህንኑ ማድረግ የግድና ተገቢ መሆኑን አምናለሁ፡፡ ዶ/ር ለገሠ ወትሮ ወደ እናት ሐገሩ ከተመለሠ በኋላ ለ20 ዓመታት በተመራማሪነት፣ በመምህርነት፣ በጥናትና ምርምር አሃድ መሪነትና በሞያ ማህበር መሪነት በመደበኛ ሰዓት ሳይውሰን ቀን ከሌሊት ሲያገለግል መኖሩን የሚጠቅሰው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀው የህይወት ታሪኩ፤ ቀደም ብዬ የጠቆምኳቸውን ተግባራት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም በቁጥር ተለይተው የተዘረዘሩ ወደ አሥር ያህል ተግባራቱንም ሠፍረዋል። ከእነዚህም ጥቂቶቹ በዋናው የፅሁፌ ርዕስ ላነሳሁት ጥያቄ ግብዓት ስለሆኑ ከነዚያ መካከል አንድ ሦስቱን ጠቅሼ ወደ መደምደሚያዬ ልዝለቅ፡፡
ዶ/ር ለገሠ ወትሮ በዩኒቨርሲቲው የማስተማር ቆይታው ከ5 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የፒ.ኤች.ዲ. ትምህርት አማካሪ በመሆኑ፣ ከ50 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን ደግሞ በማስተርስ አስመርቋል፡፡ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የፐልሰር አስትሮፌዚክስ መሪ ሳይንቲስትና የዓለም አቀፍ አስትሚ ህብረት አባል፤ እንዲሁም እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ተጠሪ ነበር፡፡ ዛሬ እንጦጦ ተራራ ላይ ተተክሎ አገራችንን በዓለም የህዋ ሳይንስ ካርታ ላይ እንድትገኝ ያስቻለው Space Observatory በ1990 ዎቹ የታፀነሰውም በዶ/ር ለገሠ ወትሮ አእምሮ ውስጥ ነበር፡፡ ይህ ተቋም ከህዋ ምልከታ ተቋምነት ወደ አገር አቀፍ የህዋ ጥናትና ምርምር ተቋምነት አድጎ ማየት፣ የዶ/ር ለገሠ የ1990ዎቹ ህልም የነበረ ሲሆን ያ ህልሙም እውን ሆኖ በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ ሲንቀሳቀስ ለማየት መታደሉን የዩኒቨርሲቲው “ገድለ- ለገሠ ወትሮ” ይገልፃል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ (ESSS) የበላይ ጠባቂ የሆኑት የኢ.ፌ.ድሪ መንግስት የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትር፣ የአዲስ አበባ ከንቲባና የአቅም ግንባታ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ፤ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ 11ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሪፖርት ማቅረባቸውን የጠቆመው የ‹‹ጊዜ›› መጽሔት (ሚያዝያ 2009 ቁ.36 ዕትም) ተፈራ ዋልዋ ከመጽሔቱ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሚከተውን ብለዋል፡- ‹‹የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ የተመሰረተው በ1996 ዓ.ም ነው፡፡” ያሉት ተፈራ ዋልዋ፣ መጀመሪያ አካባቢ የሚበላና የሚጠጣ ነገር በሚገባ ማሟላት ባልቻለ ህዝብ መካከል ስለ ህዋ የሚያስብ ማህበር ማቋቋም እንደ ዕብደት ይታይ እንደነበር ገልፀው፤ አሁን ላይ ግን ማህበሩ ያንን ሁሉ አልፎ ትልቅና የመንግሥትን ትኩረት የሳበ ስለመሆኑ ጠቁመዋል። ማህበሩን ለመመስረት ዓይነተኛ ሚና ከተጫወቱት ግለሰቦች መካከልም ‹‹ብቸኛው የህዋ ሳይንቲስት የነበረ›› በማለት የዶ/ር ለገሠ ወትሮን ስም ጠቅሰዋል። አሁን ላይ የኤሮስፔስ ሳይንስ በህግ መቋቋሙንና ምክር ቤት እንዳለው የጠቆሙት አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ ይሄ ምክር ቤት የሚመራው በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
እንግዲህ የዚህ ሁሉ ነገር ጠንሳሹ በወቅቱ ብቸኛው የህዋ ሳይንቲስት የነበረው ዶ/ር ለገሠ ወትሮ ቢሆንም መቃብሩ ላይ ተገኝቶ ለዚያ ዕውቅና የሰጠ የመንግስት ተዋካይ አላየሁምና በቀዳሚነት ‹‹እንደ ሀገር ባለውታ ተቆጥሮ የመከበር መሥፈርቱ ምንድነው?›› የሚለው ጥያቄ በአእምሮዬ ያጫረው እዚያው ቀብሩ ቦታ ነው፡፡
ይህ ጥያቄና ትዝብት ግን ‹‹የእኔና የቤተሰቤ ጋዜጣ›› ከምላት “አዲስ አድማስ” አንስቶ በርካቶቹን የሚዲያ አካላትንም ይመለከታል፡፡ ይልቁንም ያለፈውን ሳምንት የ“አዲስ አድማስ” እትም የተመለከተ ሰው፤ በአንድና ተመሳሳይ ጊዜ የህልፈት ዜናቸው ለተገለፁ ሁለት ሰዎች የተሰጠው የዘገባ ሽፋን የትየለሌ ልዩነት፣ ከፍ ብዬ የጠየቅሁትን ተመሳሳዩን ጥያቄ እንድጠይቅ አስገድዶኛል፡፡
ለዚህ ጥያቄዬ ከሁለቱም ሰፈር ምላሽ ባገኝም ደስ ይለኛል። ሆኖም ይህ ጥያቄዬ የተገቢነት እንጂ የመብት አለመሆኑም ይታወቅልኝ ዘንድ እሻለሁ።

Read 2106 times