Sunday, 07 May 2017 00:00

ድስትና ሰሐን

Written by  ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
Rate this item
(9 votes)

  “ድስቶች ለፍተው የሰሩትን ሰሃኖች ተውበው ያቀርቡታል”
                        
     እሳቱን ግር አድርገው አንድደው ይለበልቡታል፡፡ ዕዳው የጀመረው ‹ትንሽ እሳት ይስማው› ብለው የጣዱት ጊዜ ነው፡፡ እሳቱ ሞቅ ሲያደርገው ሽንኩርቱን አቀመሱት፡፡ ሽንኩርቱ ብቻውን አልመጣም፡፡ ወደል ማማሰያ ይዞ እንጂ፡፡ ባልተወለደ አንጀቱ ሆዱን ያተራምስለት ገባ፡፡ አንዴ እያማሰለ፤ አንዴም ሆዱን እየፋቀ የክብደት አንሽ እግር የሚያህለው ማማሰያ  ድስቱን ይፈቀፍቀዋል፡፡ ሽንኩርቱ አጋም ሲመስል ደግሞ ውኃውን ቸለስ አደረጉበት። እፎይ አለ ድስቱ። ግን ምን ዋጋ አለው እፎይታው የዘለቀው እስኪንፈቀፈቅ ድረስ ብቻ ነው፡፡
የድስቱ ዙሪያ መጀመሪያ ጠቆረ፣ ቀጥሎም ጥላሸት ተቀባ፡፡ በመጨረሻም ራሱ ከሰለ፡፡ ሁለቱ ጆሮዎቹ ከሥሩ የሚነደውን ገሞራ እያዩ ‹ማርያም ማርያም› ይላሉ፡፡ ሥጋው ከገባበት በኋላማ ከሥሩ ማገዶውን፣ ከሆዱ ማማሰሉን እያከታተሉ ስቃዩን አበዙት፡፡ ደግሞ የጉልቻው መከራ፡፡ ይቆረቁራል፡፡ ‹‹የእናት ሞትና የድንጋይ መቀመጫ እየቆዩ ይቆረቁራል›› እንዲሉ በአንድ በኩል የድንጋዩ ጉብጠት፣ በሌላ በኩል የድንጋዩ ትኩሳት፣ እንኳን ለመቀመጫነት ለሲኦልነት እንኳን ሲበዛበት ነው፡፡
ለአራት ሰዓታት ያህል በውስጥ በአፍኣ አሳሩን ሲበላ ቆይቶ እዚያው ምድጃው ላይ ተዉት፡፡ እርሱም ተንፈቅፍቆ - ተንፈቅፍቆ፣ በመጨረሻ በክዳኑ በኩል ትንፋሹ እያወጣ ያንኮራፋ ጀመር፡፡ እሳቱም እየደከመውና ዓይኑ እየተስለመለመ ሄዶ አሸለበ፡፡ አልፎ አልፎ ብቻ ቆይተን የዚህን ድስት መጨረሻ እናያለን ያሉ ጉማጆች የዐመድ ሻሽ ለብሰው፣ ዓይናቸውን ከፈት ከደን እያደረጉ ሙቀቱ ጨርሶ እንዳይጠፋ አድርገውታል፡፡ ጉልቻውም ዋናው እሳት የተወውን እኔ ‹ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ› አልሆንም ብሎ መቀዝቀዝ ጀምሯል፡፡
ድስቱ ግን ዕንቅልፍ ሊወስደው አልቻለም። ኳ - ኳኳ - ቂው - ቂው ቂው - ቻ - ቻቻ - የሚል ድምጽ ማዕድ ቤቱን ሞላው፡፡ እዚህና እዚያ የሚጣደፉ ሰዎች ይታያሉ፡፡ ይወጣሉ፤ ይገባሉ። ይከራከራሉ፤ ይነታረካሉ፡፡ ድስቱን ረበሸው። እንዲያም ሆኖ ድካሙ ስለበረታበት ክዳኑን አናቱ ላይ ጣል አድርጎ ሸለብ ማድረግ ሲጀምር - ኳ - የሚል የቅርብ ድምጽ ሰማ፡፡ ይበልጥ ያነቃው ደግሞ - ኳ - የሚለው ድምጽ እዚያው ድስቱ አካባቢ የተሰማ መሆኑ ነው፡፡
የድስቱ ክዳን ተነሣ፡፡ ‹እባብ ያየ በልጥ ይደነግጣል› እንዲሉ ለአራት ሰዓታት ያህል ያሰቃየው እሳት ደግሞ ሊመለስ ነው ብሎ ሰቀጠጠው፡፡ ግድንግዱ ማማሰያ መጥቶ ሊወቅጠኝ ነው ብሎ ሲጠብቅ አንዲት አንገቷ የሰለለ፣ አናቷ የሞለለ ጭልፋ ቀጫ ቀንቧ እያለች ስትመጣ ታየች፡፡ ‹ይቺ ደግሞ ምንድን ናት?› አለ ድስቱ፡፡ የሚገርመው ነገር ብቻዋን አልነበረችም፡፡ ሁለት ድንቡሽ ያሉ ወጣት ሴቶች አንዲት እንደነርሱ ድንቡሽ ያለች ሰሐን ይዘዋል። ዙሪያዋን በአበባ ምስል ተጊጣለች፡፡ ሁለመናዋ ነጭ ነው፡፡ አንድም የቆሸሸ ነገር አይታይባትም። እንዲያውም ከሁለቱ ወጣት ሴቶች ጀርባ ፎጣ ይዛ አንዲት ልጅ ትከተል ነበር፡፡  ያቺ ሰሐን አንዳች ነገር ጠብ ሲልባት ፈጠን ብላ ጠረግ ታደርግላታለች፡፡
ጭልፋዋ ወደ ወጡ ጎንበስ ስትል ድንገት አንዲት ፍንጣቂ ዘልላ ሰሐኗ ላይ ዐረፈች፡፡ ያቺ እንደ ደንገጡር ከኋላ የምትከተል ወጣት እንደ ጀት ፈጥና በያዘችው ፎጣ ጥርግ አደረገችላት፡፡ ድስቱ ተገረመ፡፡ አራት ሰዓት ሙሉ ሲንፈቀፈቅ፣ ከታች የሚመጣ እሳት፣ ከውስጥ የሚፈነጥቅ ወጥ እንዲያ ጥቁርና ቀይ ሲያደርገው ዘወር ብሎ ያየው የለም፡፡ ጠቁሮ - ጠልሽቶ -ከስሎ -  እንኳን ሌላ ራሱ ድስቱ ራሱን እስኪረሳው ድረስ - ካሉት በታች ከሞቱት በላይ ሆነ፡፡ ያን ጊዜ ቀርቶ ወጡ በስሎ ሲያልቅ እንኳን ልጥረግህ፣ ልወልውልህ ያለው የለም - አዬ ድስት መሆን፡፡
‹ደግሞ አንቺ ማነሽ?› አላት ድስት በሁለት ቆነጃጅት እጆች የተያዘችውን ሰሐን፡፡
‹የወጥ ማቅረቢያ ሰሐን ነኝ› አለችው ፈገግ እያለች፡፡
‹ምን ልታደርጊ መጣሽ?› አለ ከዚህ በፊት እዚያ አካባቢ አይቷት አያውቅም፡፡
‹ለእንግዶቹ ወጥ ልወስድ ነው› አለች የወጡ ፍንጣቂ እንዳይነካት ፈንጠር እያለች፡፡
‹ማን የሠራውን ማን ያቀርበዋል?› አለ ድስት እንደመፎከር ብሎ፡፡
‹ድስቶች ለፍተው የሠሩትን ሰሐኖች ተዉበው ያቀርቡታል› አለችውና ፍልቅ ብላ ሳቀች፡፡
‹የት ነበርሽ አንቺ ለመሆኑ? እሳት ከሥር፣ ማማሰያ ከላይ ሲኦል እንደገባ ኃጥእ ሲያሰቃዩኝ? ለመሆኑ ሽኩርቱ ሲቁላላ፣ ቅመሙ ሲዋሐድ፣ ሥጋው ሲወጠወጥ፣ ጨው ጣል ሲደረግ፣ ማማሰያው ሆዴን ሲያተራምሰው - ለመሆኑ አንቺ የት ነበርሽ? የመሥዋዕቱ ጊዜ የት ነበርሽ፣ የመከራው ጊዜ የት ነበርሽ፣ የችግሩ ጊዜ የት ነበርሽ፣ ሽንኩርቱ፣ ቅመሙ፣ ቅቤው፣ ሥጋው መልክና ስማቸውን ቀይረው ‹ወጥ› እስኪባሉ ድረስ የት ነበርሽ? አሁን ወጥ ሆኑ ሲባል ነው የምትመጭው› አላት ድስቱ ከጉልቻው ላይ እየተወዛወዘ፡፡
‹ስማ ድስቱ› አለችው ሰሐኗ፡፡ ‹ዋናው መሥዋዕትነቱ አይደለም፡፡ አቀራረቡ ነው። ሰውኮ ድስቱን ሳይሆን ወጡን ነው የሚፈልገው። ወጡ ደግሞ በእኛ በኩል ነው የሚቀርበው፡፡ በድስት ይሠራ፣ በበርሜል ይሠራ፣ በገንዳ ይሠራ፣ በጉድጓድ ይሠራ ማን ያይልሃል፡፡ ተጋባዦቹምኮ አዳራሹን እንጂ ማዕድ ቤቱን አያዩትም፡፡
ለመሆኑ ምግብ ቤት ገብቶ ‹አስተናጋጇ በደንብ አላስተናገደችኝም› የሚል እንጂ ‹ወጥ ሠሪዋ በሚገባ ለብሳ፣ ጤናዋን ጠብቃ፣ ከአደጋ የሚከላከል ልብስ አጥልቃ፣ አካባቢዋን አጽድታ አልሠራችውም› ብሎ የሚያማርር ተስተናጋጅ ሰምተህ ታውቃለህ? ወዳጄ ዘመኑ ለድስቶች ሳይሆን ለሰሐኖች ነው ዋጋ የሚሰጠው›› አለችው፡፡
ድስቱ አልተዋጠለትም፡፡ በተለይ ደግሞ አራት ሰዓት ሙሉ ከሥር ከላይ የከፈለውን መሥዋዕትነት ሲያስበው - እንኳን ሊዋጥለት፣ ሊጎረስለት አልቻለም፡፡
የለፋነው እኛ፣ የነደድነው እኛ፣ የተማሰልነው እኛ፤ መከራውን የቀመስነው እኛ - ለመሆኑ ከየት የመጣ ወጥ ነው ብሎ ነው ተጋባዡ የሚያስበው? ለመሆኑ ያለ አኛ እናንተ መኖር ትችሉ ነበር? ያንቺ ውበት የኔ መቃጠል ውጤት አይደለም? አንቺ በሁለት እልፍኝ አስከልካዮችና በአንዲት ደንገጡር እንድትከበቢ ያደረግንሽ እኛ አይደለንም? እኔና የወጥ ማማሰያ የከፈልነው መሥዋዕትነት እንዴት ቢረሳ ነው አንቺና ጭልፋ በመጨረሻ መጥታችሁ የምትሽረቀሩት››
ሁለቱ ሴቶች ወጡን እያወጡ ወደ ሰሐኗ ሲጨምሩ - ‹ስማ› አለቺው ሰሐኗ ‹አንተ የተናገርከው እውነቱን ነው፡፡ እኔ የምነግርህ የሚያዋጣውን ነው፡፡በዚህ ዘመን በሚፈለገውና በሚያስፈልገው መካከል ልዩነት መፈጠሩን አልሰማህም መሰል፡፡ በዚህ ዘመን ማራቶኑን የምትፈልገው ለጤና ከሆነ ዐርባ ሁለቱን ኪሎ ሜትር ሩጥ፤ ማራቶኑን የምትፈልገው ለሽልማቱ ከሆነ ግን ዐርባውን ሌሎች ይሩጡልህ፣ አንተ ግን ሁለት ኪሎ ሜትር ሲቀር ገብተህ ቅደም። ያን ጊዜ ልፋቱን ሌላው ይለፋል -ሽልማቱን አንተ ትወስዳለህ፡፡ እስኪ ለሀገራቸው ዋጋ የከፈሉትን፣ የተሠዉትን፣ የሞቱትን፣ የደከሙትንና ሀገሪቱን ሀገር ያደረጉትን አስባቸው፡፡ ምን አገኙ? እነርሱ እንዳንተ ማዕድ ቤት ውስጥ ተረስተው  ቀርተዋል። ስለ እነርሱ የሚደሰኩረውና የሚተርከው ግን ዛሬ የት ነው ያለው? ዘመኑ የዐርበኞች ሳይሆን የድል አጥቢያ ዐርበኞች ነው።››
ይህንን ስትነግረው ወጡ ተጠቃልሎ ወጥቶ ደንገጡሯ የተፈናጠቀውን እየጠረገች ነበር። በድስቱ ክዳን አናት ላይ ባለችው ቀዳዳ አበባ ተደረገባት፡፡ ሰሐንዋን የያዘችው ወጣት ለሌላዋ ወጣት ስትሰጣት እንደ አራስ ልጅ በባለ አበባ ጨርቅ አደግድጋ ተቀበለቻት፡፡ ጭልፋ የያዘችው ወጣት ከፊት እንደ እልፍኝ አስከልካይ እየመራች፣ ፎጣ የያዘችው ወጣት እንደ ደንገጡር እየተከተለች አጅባት ሄደች፡፡ ድስቱም ‹እዚህ ሀገር እንደ ጠረጴዛ አበባ ፊት  ሆኖ የሚታየውን እንጂ፣ እንደ ጄነሬተር ከኋላ ሆኖ የሚሠራውን የሚያየውና የሚያከብረው የለም ማለት ነው?›› አለ፡፡ ይህን ሲናገር ሁለት ወጠምሻ ጎረምሶች መጥተው፣ ከጉልቻው አውጥተው ድስቱን ዐመድ ላይ ጣሉት፡፡

Read 4058 times