Sunday, 30 April 2017 00:00

ጥሩነሽ ከኢትዮጵያ የማራቶን ሪከርድ በኋላ...

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 የ31 ዓመቷ ጥሩነሽ ዲባባ የዓለማችን የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሴት አትሌት ሆና ቀጥላለች፡፡ በኦሎምፒክ፤ በዓለም ሻምፒዮና ፤ በዓለም አገር አቋራጭ የሰበሰበቻቸው ሜዳልያዎችና አጠቃላይ ውጤቶቿ በረጅም ርቀት ታሪክ ከሚጠቀሱ የዓለም ምርጦች ተርታ ያሰልፉታል፡፡ ይህ ክብረወሰኗ በማራቶን ምርጥ ውጤቶች እየታጀበ የሚቀጥል ከሆነ የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሴት አትሌት ለሚለው የክብር ማዕረግ የሚቀናቀናት ታጣለች፡፡ በኦሎምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮና በተጎናፀፈቻቸው ሜዳልያዎች የኢትዮጵያ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበች ሴት አትሌት ናት፤ ጥሩነሽ ዲባባ
በሴቶች አዲሱ የኢትዮጵያ ማራቶን ሪከርድ…ከዚያም የዓለም ሪከርድ
ጥሩነሽ ዲባባ ያለፈው ሳምንት በተካሄደው 37ኛው የለንደን ማራቶን በሩጫ ዘመኗ ሁለተኛውን የማራቶን ውድድር ነበር የሮጠችው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ስትጨርስ ያስመዘገበችው 2፡17፡56  አዲስ የኢትዮጵያ ማራቶን ሪከርድ ነው፡፡ ከውድድሩ በፊት‹‹ የጎዳና ላይ ሩጫዎች በጣም ይከብዳሉ፡፡ በተለይ ማራቶን እጅግ ፈታኝ ነው፡፡ ውድድሩ ብቻ ሳይሆን ልምምዱም ከባድ ነው›› ብላ ነበር፡፡ የጥሩነሽ አዲስ የኢትዮጵያ የማራቶን ሪከርድ  በ2012 እኤአ ላይ በለንደን ኦሎምፒክ ቲኪ ገላና በ2፡18፡58  የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ሆና የወርቅ ሜዳልያ ስትጎናፀፍ ያስመዘገበችውን ሰዓት በ62 ሰከንዶች ያሻሻለ ነው፡፡ ከውድድሩ በኋላ‹‹ ገና በሁለተኛ የማራቶን ውድድሬ ያስመዘገብኩት ፈጣን ሰዓት ነው፡፡ ምርጥ ሰዓቴም ጭምር፡፡ በውጤቱም ረክቻለሁ፡፡›› በማለት ተናግራለች፡፡
ለጥሩነሽ ከአዲሱ የኢትዮጵያ የማራቶን ሪከርድ በኋላ በቁጥጥሯ ስር የሚገኙት የኢትዮጵያ  የረጅም ርቀት ክብረወሰኖች ብዛት 6 ደርሰዋል፡፡  በ25 ኪሜ እና በ30 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ የተመዘገቡት ሁለት አዳዲስ የኢትዮጵያ ሪከርዶች በ37ኛው የለንደን ማራቶን ላይ ያሳካቻቸው ናቸው፡፡
በ5ሺ ሜትር  14፡11.15 (2008 እኤአ ፤ በኦስሎ ኖርዌይ)
በ10 ኪሜ የጎዳና ሩጫ 30፡30 (በ2013 እኤአ ፤በቲልበርግ ሆላንድ)
በ15 ኪሜ የጎዳና ሩጫ 46፡27.7 (በ2019 እኤአ፤ በኒማንጄን ሆላንድ)
በ25 ኪ ሜ የጎዳና ሩጫ 1፡20፡51 (በ2017 እኤአ፤ በለንደን ማራቶን)
በ30 ኪ ሜ የጎዳና ሩጫ 1፡37፡23 (በ2017 እኤአ፤ በለንደን ማራቶን)
ጥሩነሽ ዲባባ በለንደን ማራቶን ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈችው በ2014 እኤአ ላይ ሲሆን በወቅቱ 3ኛ ደረጃ ነበር ያስመዘገበችው፡፡ በ2017 እኤአ  በተካሄደው 37ኛ የለንደን ማራቶን 2ኛ ደረጃ ካገኘች በኋላ 30 ሺ ፓውንድ፤ ከ2 ሰዓት 18ደቂቃዎች በታች በመግባቷ 100ሺ ፓውንድ  አግኝታለች፡፡ በአጠቃላይ የምትቀበለው የገንዘብ ሽልማት ከከ130 ሺ ፓውንድ በላይ ሲሆን፤ በተሳትፎ ክፍያ ፤ ሌሎች በይፋ ያልተገለፀ የቦነስ እና የስፖንሰር ክፍያዎችን የምታገኘውን ሳይጨምር ነው፡፡
በቀጣይ ከ4 ወራት በኋላ የለንደን ከተማ የምታስተናግደው 16ኛ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለጥሩነሽ ዲባባ በማራቶን ከፍተኛውን ውጤት የምታስመዘግብበትን እድል ይፈጥርላታል፡፡ ለዓለም ማራቶን ሪከርድ መጠበቋም የማይቀር ነው፡፡ በ37ኛው የለንደን ማራቶን ላይ ኬንያዊቷ ማሪ ኬይታኒ ስታሸንፍ ርቀቱን የጨረሰችበት 2፡17፡01 በሴቶች አሯሯጭነት አዲስ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ሆኖ እንደተመዘገበ ይታወቃል፡፡ ፓውላ ራድክሊፍ በ2005 እኤአ ላይ በሴቶች አሯሯጭነት ያስመዘገበችው 2፡17፡42 ነበር፡፡  ማሪ ኬይታኒ  በአርባ አንድ ሰከንዶች አሻሽላዋለች፡፡ በርግጥ የዓለም የሴቶች ማራቶን ሪከርድ ተብሎ የሚጠቀሰው ፓውላ ራድክሊፍ ከ13 ዓመታት በፊት በወንዶች አሯሯጭነት ያስመዘገበችው 2፡15፡23    ነው፡፡ ይህን ሰዓት ለመስበር አቅም ካላቸው አትሌቶች ጥሩነሽ ዲባባ ትገኝበታለች፡፡ ከሰሞኑ የለንደን ማራቶን ውጤት በኋላ አንዳንድ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች ከ2፡16 በታች እንደምትገባ ግምት ሰጥተዋል፡፡
የዓለማችን የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሴት አትሌት ለምን?
በ2016 እኤአ ላይ የብራዚሏ ከተማ ሪዮ ዲጄኔሮ ባስተናገደችው 31ኛው ኦሎምፒያድ 4ኛዋን ኦሎምፒክ ተሳትፋለች፡፡የተሳተፈችባቸው 4  የኦሎምፒክ መድረኮች  በ2004 እኤአ በአቴንስ፤ በ2008 እኤአ በቤጂንግ ፤ በ2012 እኤአ በለንደን እንዲሁም በ2016 እኤአ በሪዮ ዲጄኔሮ የተካሄዱት ናቸው፡፡   በዚህም የተሳትፎ ክብረወሰኑን ከአክስቷ ደራርቱ ቱሉ ጋር ተጋርታለች፡፡ በ31ኛው ኦሎምፒያድ በ5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ በማግኘቷም የምንግዜም ውጤታማዋ  የኢትዮጵያ ኦሎምፒያን ለመሆን በቅታለች፡፡ ይህም በተሳተፈችባቸው 4 ኦሎምፒኮች በ10 ሺ ሜትር ሁለት የወርቅና አንድ የነሐስ፤ እንዲሁም በ5 ሺ ሜትር አንድ የወርቅና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎች በመጎናፀፍ የሚመዘገብ ነው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በረጅም ርቀት  5 የወርቅና 1 የነሐስ   ሜዳልያዎች በመሰብሰብ የውጤት ክብረወሰን እንደያዘች ነው፡፡ 3 የወርቅ ሜዳያዎችን በ10ሺ ሜትር በ2005፤ በ2007 እና 2013 እኤአ እንዲሁም 2 የወርቅ ሜዳልያዎችን በ5ሺ ሜትር በ2003 እና በ2005 እኤአ ላይ ነበር፡፡
በአዋቂ ሴቶች ምድብ በግሏ አምስት፣ በቡድን ዘጠኝ የወርቅ ሜዳሊያዎች በአጠቃላይ በ14 ወርቅ ሜዳሊያዎች የዓለም አንደኛ ሴት አትሌት ናት፡፡ በረጅም ርቀት 8ኪሜ ለ3 ጊዜያት እንዲሁም በአጭር ርቀት በ4 ኪ ሜ ለ1 ጊዜ በማሸነፍ የኢትዮጵያን ትልቅ ውጤት ያስመዘገበች ሲሆን በአዋቂ ሴቶች የ8 ኪ.ሜ ውድድር ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው 9 የወርቅ ሜዳልያዎች 3 (በ2005፣በ2006፣ በ2008 እ.ኤ.አ) በእሷ የተገኙ ናቸው፡፡
7 የዳይመንድ ሊግ እና 9 የጎልደን ሊግ ውድድሮችን አሸንፋለች፡፡
ዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች የታሪክ እና የመረጃዎች አባሳቢ ማህበር ድረገፅ በሰፈረው መረጃ መሰረት በሩጫ ዘመኗ ከ85 በላይ ውድድሮችን በማሸነፍ ከ982ሺ 156 ዶላር በላይ የሽልማት ገንዘብ ሰብስባለች፡፡
የመጀመርያውን የሜዳልያ ድል ያስመዘገበችው በ18 ዓመቷ ሲሆን በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ነበር፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ብቻ ሳይሆን  ለኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ሜዳሊያ በማምጣት በእድሜ ትንሿ ኦሎምፒያን የሆነችው  እ.ኤ.አ በ2004 አቴንስ ኦሎምፒክ  3ኛ ወጥታ ባመጣችው የነሀስ ሜዳሊያ ነው።
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተከታታይ ለ3 ጊዜያት  በ10000 ሜ. በማሸነፍ የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት ስትሆን  ይህም እ.ኤ.አ በ2005 ሄልሲንኪ እና በ2007 ኦሳካ እንዲሁም በ2013 ሞስኮ ላይ ነበር።
እ.ኤ.አ በ2008 በ ቤጂንግ 29ኛው ኦሎምፒያድ ላይ በ5000 እና 10000 ሜ. ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች ድርብ አሸናፊ በመሆን የመጀመሪያዋ ሴት አትሌትና  ኢትዮጵያዊ አትሌት ነች፡፡
በ2008 እኤአ በቤጂንግ 29ኛው ኦሎምፒያድ እንዲሁም  በ2012 እኤአ በ ለንደን 30ኛው ኦሎምፒያድ በ10ሺ ሜትር አከታትላ የወርቅ ሜዳልያዎችን በማሸነፍ የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት ለመሆን በቅታለች።
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሰበሰበቻቸው 5 የወርቅ ሜዳልያዎች ብቸኛዋ ሴት አትሌት ለመሆን የበቃች ሲሆን በሁለቱም ፆታዎች በሚኖረው የከፍተኛ ውጤት ደረጃ የሚበልጣት 7 የወርቅ ሜዳልያዎች ያሉት ጃማይካዊው ዩሴያን ቦልት ብቻ ነው፡፡
በኦሎምፒክ  በ3 የወርቅ እና 2 የነሐስ ሜዳልያዎች ከፍተኛው የኢትዮጵያ ውጤት የራሷ ነው፡፡
 በ2005 እና በ2008 እኤአ በዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የዓመቱን ምርጥ ብቃት ያሳየች አትሌት ተብላ ሁለት ልዩ የክብር ሽልማቶችን ተቀዳጅታለች፡፡

Read 2166 times