Sunday, 30 April 2017 00:00

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ የክለቦች ታሪክ ፈርቀዳጅነቱ በተለያዩ ሁኔታዎች ይጠቀሳል፡፡ 80ኛ ዓመቱን በማክበር ላይ የሚገኘው ክለቡን በብሄራዊና አህጉራዊ ደረጃ አዳዲስ ምእራፎችን እየከፈተ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ተሳትፎ 50ኛ ዓመቱን ሲይዝ  በ2017 ቶታል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ገብቷል፡፡ ከደቡብ ፤ ከመካከለኛው እና ከሰሜን አፍሪካ ምርጥና የቀድሞ ሻምፒዮን ክለቦች ጋር የሚፋለምበት ደረጃ ላይ ነው፡፡
በ2017 ቶታል የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ 16 ክለቦች መሳተፋቸው በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ይህን ለውጥ በመፍጠሩ አድናቆት አግኝቷል፡፡ በተለይ በክለቦች ደረጃ ጠንካራ የሊግ ውድድር ያላቸው እነ አልጄርያ፤ ዛምቢያ፤ ሱዳን፤ ኬንያና የመሳሰሉት፤ እንዲሁም በምስራቅ፤ በደቡብ እና በመካከለኛው አፍሪካ ዞኖች ያሉ ክለቦች በምድብ ፉክክር ተሳታፊ የሚሆኑበትን እድል ፈጥሯል፡፡ በሌላ በኩል ባለፉት የውድድር ዘመናት በምድብ ፉክክሩ የሚገቡት ክለቦች 5 አገራትን ብቻ በተደጋጋሚ የሚወከሉበትን ሁኔታም ቀይሮታል፡፡ ዘንድሮ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የ13 አገራት ክለቦች ተሳታፊ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ሊጉ የምድብ ፉክክር አዳዲስ ክለቦች ከተለያዩ አገራት በብዛት ያሳተፈ በመሆኑ በአፍሪካ ደረጃ  የሚያገኘውን ትኩረት ያሳድገዋል፡፡
በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በካይሮ ከተማ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለ2017 የካፍ ቶታል ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ የምድብ ድልድሎችን  አውጥቷል፡፡ ኢትዮጵያን በመወከል የምድብ ፉክክር ውስጥ የገባው ቅዱስ ጊዮርጊስ በምድብ 3 ከደቡብ አፍሪካው ሜመሎዲ ሰንዳውንስ፤ ከዲ.ሪ ኮንጎው ኤኤስ ቪታ ክለብ እና ከቱኒዚያው ኤስፔራንስ ዴቱኒስ ጋር ተመድቧል፡፡ የምድብ የመጀመርያ ጨዋታዎች ከ2 ሳምንት በኋላ የሚጀምሩ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጭ ከደቡብ አፍሪካው ሜመሎዲ ሰንዳውንስ ጋር ይገኛል፡፡
በሌሎቹ ሶስት ምድቦች ከ1 ጊዜ በላይ የሻምፒዮናነት ድሎችን ያስመዘገቡት የሰሜን አፍሪካ ክለቦች ቀለል ያሉ ታጋጣሚዎችን አግኝተዋል፡፡ በምድብ 1 በ2007 እኤአ ላይ ሻምፒዮን የሆነው የቱኒዚያ ኤትዋል ደሳህል፤ የሱዳኖቹ አልሂላል እና አልሜሪክ እንዲሁም በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በምድብ ማጣርያው ተሳታፊ የሚሆነው የሞዛምቢኩ ፌዮቬራዬ ዴማፑቶ ይገኛሉ፡፡ በምድብ 2 የአምስት ጊዜ ሻምፒዮኑ የግብፁ ዛማሌክ፤ በቅድመ ማጣርያ ሃያሉን ቲፒ ማዜምቤ ጥሎ ማለፍ የቻለው የዚምባቡዌው ካፕስ ዩናይትድ፤ የአልጄርያው ዩኤስኤም አልጀር እና በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በቱኒዚያ የሚያደርገው የሊቢያው አልሃሊ ትሪፖሊ ተደልድለዋል፡፡ በምድብ 4 ደግሞ ለስምንት ጊዜያት የአፍሪካ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው የግብፁ ክለብ አልአሃሊ፤ ከሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ፤ የካሜሮኑ ኮተን ስፖርት እንዲሁም የዛምቢያ ዛናኮ ዩናይትድ ተመድበዋል፡፡
ብራዚላውያኖቹ ከደቡብ አፍሪካ
ሜመሎዲ ሰንዳውንስ የአምናው የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ነው፡፡ በ2016 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው በሚያስገርም አጋጣሚ ነበር፡፡ የዲ.ሪ ኮንጎው ክለብ ኤኤስ ቪታ ክለብ ተገቢ ያልሆነ ተጨዋች በማሰለፉ በቅጣት ከውድድሩ ውጭ ሲሆን ሜሞሎዲ ተክቶ በመግባት እስከ ዋንጫው ድል ተጉዟል፡፡ ሜሞሎዲ ሰንዳውንስን ማልያቸው ከብራዚል ብሄራዊ ቡድን ጋር ስለሚመሳሰል ብራዚላዊያኖቹ እያሉ ይጠሯቸዋል፡፡ ባፋና ባ ስታይል የሚሏቸውም አሉ፡፡ ከተመሰረተ 47 ዓመት የሆነው ክለቡ ስታድዬሙ በፕሪቶርያ የሚገኘውና 28ሺ ተመልካች የሚያስተናግደው ሎፍተስ ቬርስፊልድ ነው፡፡ ከ2016 ጀምሮ ማሊያው በናይኪ ስፖንሰር የሆነለትና፤ 3 የደቡብ አፍሪካ ግዙፍ ኩባንያዎች በአበይት ስፖንሰርነት የሚደግፉት ክለቡን በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ፓትሪስ ሞቴስፔ የተባሉ ባለሃብት ናቸው፡፡ ዋና አሰልጣኝ ደግሞ የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድንን ሲያሰለጥኑ የነበሩት ፒትሶ ሞስማኔ ናቸው፡፡በ2016 የዓመቱ የካፍ ምርጥ ክለብ የተባለው ሜሞሎዲ የ2017 የአፍሪካ ሱፕር ካፕንም ተቀዳጅቷል፡፡ በሌላ በኩል ከ1996 እኤአ ወዲህ የደቡብ አፍሪካ አብሳ ሊግን 7 ጊዜ ያሸነፈ ሲሆን በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ባለፉት 10 ዓመታ 37 ጨዋታዎች አድርጎ በ37 ድል፤ በ16 አቻ እንዲሁም በ15 ሽንፈት ገጥሞታል፡፡
ጥቁር ዶልፊኖች ከመካከለኛው አፍሪካ
የዲሪ ኮንጎው ክለብ ኤኤስ ቪታ ክለብ በ1973 እኤአ ላይ የአፍሪካ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃ ሲሆን  በቅፅል ስም ጥቁር ዶልፊኖች ብለው ይጠሯቸዋል፡፡ ከተመሰረተ 92 ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ ክለብ 80ሺ ተመልካች የሚያስተናግደውን ስታድ ዴ ማርታየርስ በሜዳነት የሚጠቀም ሲሆን የክለቡ ፕሬዝዳንት ጋብሬል አሲሚ ይባላሉ፡፡
ደምና ወርቅ ከሰሜን አፍሪካ
የቱኒዚያው ምርጥ ክለብ በሙሉ ስሙ ኤስፔራንሴ ስፖርቲቭ ዴ ቱኒዝ ተብሎ ቢታወቅም ቅፅል ስማቸው ደምና ወርቅ የሚል ነው፡፡ ከተመሰረተ 98ኛ ዓመቱን የያዘው ክለቡ በቱኒስ ከተማ የሚገኘውና 60ሺ ተመልካች የሚያተናግደውን ኦሎምፒክ ዴ ራዴስ ስታድዬም ይጠቀማል፡፡ የእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን፤ እጅ ኳስ፤ ቅርጫት ኳስ፤ መረብ ኳስ እና የራግቢ ቡድኖችን የሚያተዳድረው ክለቡን በሊቀመንበርነት የሚመሩት ሃመዲ ማዴስ ናቸው፡፡ ኤስፔራንስ የቱኒዚያን ሊግ ለ21 ጊዜ የቱኒዚያ ካፕን 15 ጊዜ ያሸነፈ ሲሆን የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግን በ1994 እና በ2011 እኤአ ከማሸነፉም በላይ ለ4 ጊዜያት በ2ኛ ደረጃ ጨርሷል፡፡ በ1998 እ.ኤ.አ ደግሞ የአፍሪካ ሱፕር ካፕን አሸንፎ ነበር፡፡
ፈረሰኞቹ ከምስራቅ አፍሪካ
የ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግን እየመራ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ  ዓመታዊ በጀቱ እስከ 20 ሚሊዮን ብር ይደርሳል፡፡   ከደጋፊዎች መዋጮ፤ ከስፖንሰሮች እና ከአጋር ድርጅቶች ፤ ከሜዳ፤ ከስፖርት ማህበሩ ክበብ፤ ከልዩ ልዩ የስፖርት ቁሶች ሽያጭ ከሚሰበስባቸው ገቢዎች የሚገኝ ነው፡፡ በማልያው ስፖንሰርሺፕ በየዓመቱ እስከ 6 ሚሊዮን ብር እየተከፈለውም ነው፡፡ በክለቡ ዘንድሮ   የአባልነት መዋጮ የሚከፍሉ ደጋፊዎች ብዛት ከ14ሺ 700 በላይ ሲሆን በተለያዩ የጥራት ደረጃዎች የተሸጡት ማልያዎች ከ10ሺ በላይ ናቸው፡፡  
ጊዮርጊስ በአገር ውስጥ የክለብ ውድድሮች ከ80 በላይ ዋንጫዎች የሰበሰበ ሲሆን፤ የፕሪሚዬር ሊግ 30፤ የጥሎ ማለፍ 13፤ የአሸናፊዎች አሸናፊ 10 ዋንጫዎች ይገኙበታል፡፡ በሀገር ውስጥ ውድድር ባስመዘገባቸው ተደጋጋሚ ድሎች ምክንያት ከኢትዮጵያ ክለቦች በአህጉራዊ ውድድሮች ተሳትፎው ከ50 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ ከዘንድሮ በፊት በአህጉራዊ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ያስመዘገበው በ1959 ዓ.ም በአፍሪካ ክለቦች ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ የገባበት እና በ2005 ዓ.ም በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ስምንት ውስጥ የገባበት ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ከ1967 እኤአ ጀምሮ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ስር በሚካሄዱ ውድድሮች፤ ለ12 ጊዜያት በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ፤ለ10 ጊዜያት በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ካፕ፤ 1 ጊዜ በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ፤ 1 ጊዜ በካፍ ካፕ እንዲሁም ለ3 ጊዜያት በካፍ የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድሮች  ነው፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣርያዎች ላይ (ውድድሩ በካፍ አዲስ መዋቅር መካሄድ ከጀመረበት ከ1997 እኤአ ወዲህ  ማለት ነው፡፡) ከዘንድሮ በፊት ለ12 ጊዜያት በነበረው ተሳትፎ  በአጠቃላይ ውጤቱ 61ኛ ደረጃ ላይ ነበር፡፡ ለ8 ጊዜያት ቅድመ ማጣርያውን በማለፍ ለመጀመርያ ዙር ሲበቃ ለ4 ጊዜያት ከውድድሩ የተሰናበተው በቅድመ ማጣርያ ነበር፡፡
የአቶ አብነት ተስፋ እና የአቶ አርሰናል ማነቃቂያ
በሙሉ ስማቸው ዴቪድ ባሪ ዲን ተብለው ይጠራሉ፡፡ የ73 ዓመት አንጋፋ የእግር ኳስ ባለሙያ ሲሆኑ በሊድስ ዩኒቨርስቲ ኢኮኖሚክስ አጥንተዋል፡፡ በ1983 እኤአ ላይ ወደ አርሰናል ሲቀላቀሉ በክለቡ እስከ 292ሺ ፓውንድ ኢንቨስት በማድረግ  16 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ገዝተው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ  በአርሰናል ክለብና በእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር ምክትል ሊቀመንበርነት ከ20 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡  በአርሰናል ክለብ ከፍተኛ ባለስልጣን ሆነው በቆዩባቸው ዓመታት በክለቡ በነበራቸው የአክሲዮን ባለድርሻነት ፤ የአሰልጣኝ ቅጥር እና የተጨዋቾች ግዢ፤ የስታድዬም ግንባታ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች  ጉልህ ሚናዎች በመጫወታቸው አቶ አርሰናል (Mr· Arsenal) እስከመባልም ደርሰዋል፡፡ በተለይም በአርሰናል ክለብ ዋና አሰልጣኝነት ሲሰሩ 21ኛ  ዓመታቸውን የያዙትን ፈረንሳዊ አርሴን ዌንገር በመቅጠር በክለቡ ታሪክ ጉልህ አስተዋፅኦ ለማበርከት መቻላቸው ይጠቀስላቸዋል፡፡  በ2007 ክለቡ የለቀቁት የነበራቸውን  የአክሲዮን ድርሻ በ25 ሚሊዮን ፓውንድ በመሸጥ ነበር፡፡    በሌላ በኩል በ1992 እኤአ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በአዲስ መልክ ተዋቅሮ፤ በትርፋማ አቅጣጫዎች እንዲንቀሳቀስ ካስቻሉ ባለሙያዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ  ናቸው፡፡ከወር በፊት  የቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀል ባደረጉት ልዩ ጥረት በሸራተን አዲስ በተዘጋጀ የግማሽ ቀን ሲምፖዚዬም ላይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ለሚንቀሳቀሱ ባለድርሻ አካላት የማነቃቂያ ንግግር አቅርበው ነበር፡፡  በዓመት እስከ 4.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ስለሚሆንበት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መዋቅራዊ አደራጃጀትና የእድገት ሂደት ፤ የክለቦችና የደጋፊዎች እንቅስቃሴ፤ በቴሌቭዥን የስርጭት መብት፤ በፕሮፌሽናል ተጨዋቾች የዝውውር ገበያ ያሉትን ጠቃሚ ተመክሮዎች  አጭር መግለጫ የሰጡበት መድረክ ነበር፡፡ በኢትዮጵያም የክለብ እግር ኳስ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተመክሮ እንዴት መተግበር እንደሚቻል  ያነቃቁበት መድረክ ነበር፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ አብነት ገ/መስቀል በ2017 የካፍ የክብር ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ዴቪድ ባሪ ዲንን ወደ አዲስ አበባ የጋበዙት እሳቸው ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ የክለብ እግር ኳስ ለውጥ የሚፈጥሩ ተመሳሳይ መድረኮችን ወደፊትም በመፍጠር ለመስራት እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር፡፡ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የኢትዮጵያ የክለቦች ውድድር በስፖንሰርሽፕ፣ በፕሮፌሽናል አደረጃጀት ትርፋማ እንዲሆን የሚያስችሉ የውይይት መድረኮችን ለመፍጠር ቃል ገብተው ነበር፡፡   

Read 1057 times