Print this page
Sunday, 30 April 2017 00:00

ጀንበሮቹ

Written by  በአለማየሁ ጌትነት (ኢብታ)
Rate this item
(15 votes)

 በአንድ ዘመን በሩቅና ሩቅ ቦታ …. ሁለት ጨቅላዎች …….. ከየአባታቸው ወገብ ተስፈንጥረው …… ከእናታቸው ስጋ … ስጋ ነስተው …… የአብ እስትንፋስን ወርሰው …….ወዲህ  መጡ - ወደ እናት ሀገር ጦቢያ፡፡
…….ሞሳዎቹ አፈሩን ፈጩ፣ ውሃዋን ተራጩ፤ ጥርሷን ነክሳ ከሌላት ሞጣ /አጣ ሳይሆን ያንች አይሆንም ተብላ/ … እልፍ አልፋ ጠብ ከምታደርገው የእውቀት መና  ….እነሆ መናውን ቆጥባችሁ ብቻ ሳይሆን አባዝታችሁ ተጠቀሙበት አለች፡፡  ...... እነሱቴ!  ይልቅ በገለጠችላቸው አይን ነውርሽን አየን አሉ፡፡ …….ዳርሽ አልሰለጠነም ሲሉም ተቹ።  ......እዚያ  እሷ …እዚህ  እሷ ብትሆንም፣ አንዱ ከአንዱ፣ ሌላኛውም ከሌላኛው ጥግ ወደ አማካኞች ፈረጠጡ።  እናት ናትና ተቀበለች፤ ቀረን ያሉትን ርዝቅም ባንድ መዓድ አቋደሰች፡፡
….በአይኖ  ስርም እንደ ተወዳጅ ያድጉ ነበር   …በአይኖ ስርም ክፉም ደግም ያደርጉ ነበር  …….ባይኖ ስርም ሳሉ፤ “ብላቴናዎችሽ ጎበዞች ሆነዋልና መንጋሽን ይጠብቁ፤ በመንጋዎችሽ ላይም በቅን ልቦና  ይፍረዱ፤ ዳኝነትም  ይቀመጡላቸው”  አሏት፡፡
እርሷም፤
“ቀበሮ ከበግ ግልገል ከተጫወተ ወይ ቁንጣን እስኪያስጨንቀው በልቷል  …አልያም የበግ ግልገል እንዲበላ አልተገለጠለትም …ልቦናውም ዋዥቷል።  ……አይኑ የተከፈተ ጊዜ ግን ወዮ! ለግልገል  ……ወዮላት ለናቷ” አለቻቸው
እነሱ ግን፤
“እናታለም፤ አየሽ የእርጅናሽን ስር መስደድ …አየሽ የሁሉ ነገርሽን መጃጀት ……እኛ ያልን ሌላ አንች ‘ምጠቅሽ ሌላ፡፡  …እናታለም ካንቺ የወረሱትን ድንቁርና እንግፈፍ …..ላያቸው ላይ ያጀፈጀፈውን ወግ አጥባቂነት እንሸልት …..ከነሱ ወጥተናል ….የራስ ጸጉራቸውን ቆጥረናልና ….መሻታቸውን እናውቃለን። ‘ሚፈልጉትንም አያውቁምና ‘ሚያስፈልጋቸውን ‘ንስጣቸው፡፡ ...የልዩነት አጋራቸውም ይራገፍ” …እና ሌላ ብዙ አሏት፤ አብዝተውም “መንጋውን ከኛ በላይ ያወቀው ላሳር”….ሲሉ እስክትደነቁር ነገርዋት። ..የመሰሎቻቸውም ቁጥር እንገሯን ጠብቶ በርክቷልና በፊቷ እንደ ባህር አሸዋ ፈሰሱ……ባንድነትም፤ “ኋላ ቀርነት ኋላ ይቅር! …ኢትዮጵያ ትቅደም!  ….የዘመን  ልጆች ገበሬ ወይፈኑን ባለሙያ ይሆን ዘንድ እንዲቆረቁብ  …..መንጋዎቹን ቆርቁበን በለምለሙ እናውላለን!!” አሏት እርሷም፤
“ፍየል ተራራው ትቦርቅበት ዘንድ ምቹዋ ነው!…የቁጥቋጦው እሾክም ያጠነክራታል …..ትቃርመው …ከሀሩርም ትከለልበት በቂዋ ነው፡፡ ….ዛዲያ ከመስኩ ምን አላት፤ …ለግመሎችስ የቀይ አፈር ሽታ ምናቸው ነው፡፡ ….ነጋ ጠባ ሽኮናቸውን ‘ሚያረሰርስ፣ ውሃስ ጥማትን ካጡ ምን ሊበጃቸው፤ …ልጆቸ ወፍ እንደ ሀገሯ ትዘምራለችና ዝማሬዋ ስላልጣማችሁ ብቻ አለቀሰች ትሏት አይገባም፡፡ …ከአፈር ‘ሚጋፋው ..ከአፈር ‘ሚላፋው ማረሻ ‘ንኳ ተፈጥሮበታልና ….አይሰለች አይደክመውም፤…..ላፈሩም እጅ አይሰጥም፡፡ ….በግብግቡም እንደ እባብ ቆዳውን እየሸለቀቀ ሲያበራ ይኖራል …..ያለ ተፈጥሮው ያስቀመጣችሁት……ያለ ግብሩ ያሳረፋችሁት ዕለት ግን…..ደረቱን የቀረደደው አፈር በተጋደመበት ሲሳብ ይመጣል ….እንደ አልባሌም ከጥቅም ውጭ ያደርገዋል፡፡  መንጎችም በመቀርደድ ‘ሚበረቱ ማረሻና…. በመቀርደድ ‘ሚፋፉ አፈር ናቸውና፤ ለይታችሁ አታውቋቸውም፡፡ …..ከነሱ ብትወጡም እነሱን አደላችሁም …ናቸው ያሏችሁን አንጠለጠላችሁ ‘ንጅ፣ አንዳች እንኳ አላስተዋላችሁም …..በደፈናው ትወጡባቸው፣ እንደ ዘንዶም ትውጧቸው ዘንድ አሰፍስፋችኋል” ….ስትል ሙግቷን አቀረበች፡፡
ግና በጀ አላሉም፤ እልፍና እልፍ እየሆኑ ሄደው ነበርና በምድሪቱ ስልጣኔን አፈሰሱ፤ ስርአትንም ዘረጉ።  …..ሁለቱ ማቲዎችም በመንጎቹ ላይ ሊፈርዱ በሸንጎ ተቀማጭ ሆኑ፡፡
…አንዱም በልቡ ያመነውን እንደዛው እያደረገ …..ወገቡ እስኪጎብጥ፣ አይኑም እስኪደክም መንጋዎችን ቆረቆበላት፡፡
….ሌላውም ልቡ የወደደውን እንደዛው እያደረገ …. ጨጓራው እስኪገጠብ ….. ደሙም እየጎሸ እስኪያብጠው ተጋ፡፡
*   *   *
የጮራነት እድሜያቸው ባከተመ፣ ቀትርነታቸውም ባለፈ ጊዜ  ….ጀንበሮቹ ሳይጠልቁ እናታቸውን ይገናኙ ዘንድ ወደዋልና ወደ እሷ መጡ።
እንደ ልቡ ያደረገው ቀጭን ሰውም ስለሱ፤
“በርግጥ ዋርካው የፍቅር ዋርካ ነው …. ቢሆንም ዘመኑን የጨረሰው በቃጠሎ ነውና ግንድ እንጂ ቅርንጫፍም ሆነ ቅጠል የለውም፤ ከብርድም ይከላከል ዘንድ አይቻለውም … ምድሪቱም ባጋተች ጊዜ ውሃ ለራሱ አልደበቀምና መልሶ ያገግም አይቻለውም ….ሊያምኑት ‘ንጅ ሊታመኑበት አይቻልም …አውሎ ንፋስም በመጣ ጊዜ በፊቱ ቅጥር አልተበጀምና አቅሙን ሰልሎ መነቀል እስኪቃጣው ይነቀንቀዋል …. በዙሪያው እጉም ብለው በተኮለኮሉትም ይበረታል …እንደ ርጉምም ይቀጠቀጣሉ ...ዛፉም ከማዘን የዘለለ ፋይዳ አያመጣም” ተብሏልና  በደሉ ጉሮሮውን ተናንቆት ….ምላሱ ጋር ተከማችቶልና አፉን ከፈተ….
“እናታለም….. ሌሎች ጸደይ ይኖሩ ዘንድ  የተኖረን በጋ መንጎችሽ ስለምን እንደ ጥፋት ይመዛሉ  ….ዋርካው እያንዳንዱን ቅጠል ለሌሎች ምቾት…እያንዳንዱንም ዝንጣፊ ለሌሎች ደህንነት … .በፍቅር መሰዋቱስ ስለ ምን  ግድ አይሰጣቸውም፡፡  ….ማንም ከድርሻው ካልዘለለ ተቀማጭ እንዳይኖረው…ከፋንታ ማለፍም …ለራስ ጥፍር የሌላ ሳንባ መቀርጠፍ መሆኑስ  ስለ ምን አይከሰትላቸውም”  አላት እናቱም መለሰች፤
“አንተ በኔም በመንጎቼም የተወደድክ ሆይ፤ አንተ መንጎችን ወደ ለምለሙ በሀቅ የነዳህ!…. በበርሃ ጥማት ስትቃጠል ካስገኘሀቸው ውሃ በፍኝህ ያልነካህ ሆይ… በ’ውኑ በመንጎች እንዳንተ የተወደደ.. እሚታመን አለን? …መንጎችስ ካንተ ውጭ አርጩሜ እንደያዘ ጠባቂ ሳይሆን ከመቀመጫው ሰፋ ብሎ ጉርብጥብጥ በማውጣቱ የሞተ ጸጉራቸውን ለማራገፍ እንደሚመቻቸው የሾላ ዛፍ የሚተሻሹት ይኖር ይሆን?  …….ካንተ ሌላስ የእጁን ወደ አፋቸው እንጂ ያፋቸውን ወደ እጁ እንዳያደርግ አውቀው መጎምዠት ወደ ፊታቸው ከቶ እማይመጣ መንጎች ያሉት ይኖር ይሆን?
“….ዛዲያ በመረጥከው መንገድ ከመፈቀርና  ከመታመን ያለፈ …ፍስሀህን እሚያነሳሳ …ተድላህን ‘ሚጠራ ምን ይኖርና ነው …ፊትህ መከስከሱ …ምላስህ ክፉ ታወራ ዘንድ ከአፎቷ መውጣቷ”   አለችው …..እርሱም፤ ”እናታለም አሁንም በድሮ በሬ ታርሳለችና …ከሷ ማውጋቱ ጉንጭ ማልፋት ነው …….ልትረዳም አትችልም” ሲል ተከዘ፡፡
የልቡን መሻት የፈጸመው ወፍራም ሰውም ተራው ሆኗልና፤
“እናታለም” አላት
“እነሆ!... አለሁ የምወድህ ልጄ” ባለችው ጊዜም
በመንጋው ተከቦ ብቸኝነት ተጫውቶበታል ….ጭፍራ አስከትሎ ፍርሀት ልቡን ደፍሮታል   ….በሃይል ተሞልቶ አለመቻል አላግጦበታልና …ማይስቁ ግን ያገጠጡ ጥርሶች፣ ሁሌም ከሁሉም አሰልችተውት ……በፍርሃት እሚሸሹ አይኖች  ….እሚንቀጠቀጡ እጆች ታክተውታልና …እፍኝ ጥሬ ለመደበቅ ዳሽንን ያክል የችግር የመከራ ተራራ ሲገነባ መስማት አማሮታልና ….. መበደሉ አንገሽግሾት  እንዲህ አላት፤
“እናታለም፤ እውን እንቦሳው ይጠባ ዘንድ ጥገቷ መመገቧ ሀጢያት ነው ….ያትክልት ቦታው ይጠበቅ ዘንድስ ቅጥሩን በተረፈ ምርቱ ማጠር ነውር ነው ….የበጎች መንጋስ በሰላም ያሸልብ ዘንድ ተኩላዎችን ማሳደድ ወንጀል ነው፡፡ …ከነብር  የታደጓት ፍየልስ እንባ ታክል ወተት ብትለግስ ነፍስዋ ከስጋዋ ትለያለች? ….በቁጥቋጦ ገብቶ መውጫ በማጣቱ ያላዝን የነበረ ግመልስ፣ ነጻ አውጥተው ቢቀመጡት ሻኛው  ይቀልጣል፡፡ ….ከእረኛ ውሾች መሀል  እያበራገገ ግጦሹን ያስተጓጎለውን መገሰጽ ክፋት ነው …. እንደ ልዩ ፍጥረት ያስቆጥራል፤ ……..ጨካኝ  እኩይስ ያስብላል”
ምላሱም ከመናገር በተገታች፣ አንደበቱም በቀዘቀዘ ጊዜ እናቱ በእርጋታ መለሰች ..አለችም፤
“የምወድህ ልጀ!....  በኔም በመንጎችም ሃይልህ  የታመነ ሆይ! …..አንተ ጠማማውን አቅኝ ….አለቱን በርቃሽ ….ሆይ!  …በውኑ እንደ አንተ በመንጎቹ ‘ሚከበር ይኖር ይሆን …..እንደ አንተስ ቃሉ ‘ሚሰማ  ….ትዕዛዙ ‘ማይሻር ከቀደሙት ተነስቶ ይሆን  ….እንደ አንተስ ‘ሚታመኑበት …የታመኑበትንስ ‘ማይጥል ……ያንበሳ ደቦልን በግራ እጁ ‘ሚሰብር …..በቀጠረው ቅጥር ወጀብ ‘ሚመክት …..በተሸበረ ከተማ የድህነት ደሴት ‘ሚያበጅ  በውኑ ይኖር ይሆን፡፡
…..ዛድያ በመረጥከው መንገድ ከሀይልና መታመኛ ከመሆን የዘለለ ምን የከንፈርህን ጥግ ሊያላቅቅ ይችልና ነው ...ሳቅህ እንደ ሰማይ የራቀው፣ ፈገግታህ የጨነገፈው”  አለችው፡፡
እርሱም….  እንደቀደመው ልትረዳ አትችልም ሲል በልቡ ተከዘ፡፡
(ተፈጠመ)
*   *   *                                
 ጀንበሮቹ ከትካዜያቸው በተመለሱ ጊዜም  ድምጻቸውን ዘለግ አድርገው እንዲህና እንዲያ በማለት ወደ መነሻቸው ተጓዙ …..ጀንበሮቹ ጠለቁ፡፡
©  ማድረግ ያለበትን በማድረግ የሚስቱን አፍ ዘግቶ፣ የልጆቹን ከርስ ሞልቶ፣ በምቹ አልጋው ‘ሚያንኮራፋ አባወራ የተባረከ ይሁን።  …..በፈንታው ከጓደኞችህ አንሰህ አሳነስከን በሚል ሰበብ የሚገላመጥ ….በነካሽኝ ሰበብ በሚስቱ ‘ርግጫ ከ’ንቅልፉ ‘ሚናጠብ ባል የተረገመ ይሁን።
©  በምቹ ምኝታው እንቅልፍ የተኮረፈው …በቀን ‘ሚቃዥ …ከመንጋው ጥቃትን ‘ሚሰጋ እረኛ የተረገመ ይሁን፡፡  ……በፈንታው በመንጏቹ መሀል ንጹህ ህሊናውን ትራስ አድርጎ ‘ሚያንቀላፋ እረኛ የተባረከ ይሁን፡፡
©  መንጎቹ በሃይሉ ‘ሚታበዩበት፣ ስለ ሃይሉም ‘ሚከበር እረኛ የተባረከ ይሁን። …..በፈንታውም በምሳሌነት እሚጠቀስ፣ ምሳሌነቱን  ሊከተሉት ‘ማይሹት እረኛ የተረገመ ይሁን፡፡
©   መንጎቹ በፍቅሩ የተነደፉለት፣ ስለ ፍቅሩም ‘ሚከበር እረኛ የተባረከ ይሁን፡፡  ……በፈንታውም በፍርሀታቸው ውስጥ ትንሽ ፍቅርን ሽቶ ‘ሚቅበዘበዝ እረኛ የተረገመ ይሁን።
©  ሰናዩን ጎዳና ሲያመላክት ላንተ ምን እንደበጀ ‘ሚባል፣ በአጓጉል ቸርነቱና ደረቅ ሀቅ፣ ልጆቹን ከጓደኞቻቸው በታች ያደረገ አባት የተረመ ይሁን።
©  ቀናውን ጏዳና ይይዙ ዘንድ ሲመክር “‘ምን  አንተ” እሚባል፣ ውርሱ እንደ ሀጢያት ‘ሚቆጠር፣ ስሙን ለመጥራት ‘ሚያፍሩበት አባት የተረገመ ይሁን፡፡
©  ……ህሊናውን ሳይነቅል፣ ጥርስ የነቀሉ ልጆችን ያመጣ አባት የተረገመ ይሁን፡፡  
©  ባልጠግብ ባይነቱ ልጆቹን የጓደኞቻቸው መጠቋቆሚያ ያደረገ አባት የተረገመ ይሁን፡፡

Read 3755 times