Sunday, 30 April 2017 00:00

ዝክረ - አሰፋ ጫቦ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

 አቶ አሰፋ ጫቦ በሀሳቦቹ ጥልቀት፣ በፖለቲካ ፍልስፍናው፣ በጨዋታ አዋቂነቱ፣ የበርካቶችን ቀልብ መሳብ የቻለ ጎምቱ ጸሐፊ፣ የህግ ባለሙያና የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ መሆኑን ይመሰክራሉ - በቅርበት የሚያውቁት፡፡ አሰፋ ጫቦ አዲስ አድማስን ጨምሮ በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ በውብና ማራኪ የአጻጻፍ ክህሎቱ፣ በሳል ሃሳቦቹንና ዕይታዎቹን ለአገሩ ልጆች አጋርቷል፡፡ እስከ መጨረሻው ህይወቱ ድረስም በተለይ በአዲስ አድማስ ጋዜጣና በራሱ ድረ-ገጽ ላይ ስለ ሀገሩ የሚቆረቆርባቸውን ጉዳዮች ሲሞግትና ሲከራከር ነው የኖረው፡፡ የተለያዩ ዕውቅ የሥነ ጽሁፍ ምሁራንና ደራሲያን ስለ አሰፋ ጫቦ ሰብዕናም ሆነ የጽሁፍ ሥራዎች የሚያውቁትን አጋርተውናል፤ ምስክርነታቸውን ሰጥተውናል፡፡ ለዚህ ነው ርዕሱን “ዝክረ አሰፋ” ያልነው፡፡ እንዲህ ተጠናቅሮ ቀርቧል፡፡
         (ከአዘጋጁ፡- የአዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍልን
      ጨምሮ ለብዙዎች የአሰፋ ጫቦ ህልፈት ድንገተኛና አስደንጋጭ ነበር፡፡ በእጅጉ አዝነናል፡፡ ፈጣሪ ነፍሱን ይማረው፡፡ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ መጽናናትን እንመኛለን፡፡)
                 
      “አቶ አሰፋ የሃገር ኩራትም ነበሩ”
 አቶ ጌታቸው በለጠ (ደራሲ)
አቶ አሰፋ ጫቦን ለረዥም ጊዜ አውቃቸዋለሁ። ከፖለቲካ አቋማቸው ይልቅ እኔ ሁልጊዜ የሚመስጠኝ ህይወትን የሚያዩበት መንገድ፣ አዕምሯቸው የተሸለመው የእውቀት አቅም ነው። ያን አቅማቸውን ደግሞ የመጡበትን ብሔር አክብረው፣ የመጡበትን ብሔር አድንቀው፣ የመጡበትን ብሄር ሰብዕና፣ ውብ ቀለማት፣ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያስተሳስሩበት መንገድ አስደናቂ ነው፡፡ በሚፅፉት ፅሁፍ የሀሳብ መሸከም አቅማቸው ቁልጭ ብሎ ይታያል፡፡ አዕምሯቸው ውስጥ ያለውን ሀሳብ እንዳለ በፅሁፋቸው እናያለን። አንዳንድ ሰው አዕምሮው ውስጥ የተሸከመውን ሀሳብ በፅሁፍ መግለፅ ይቸግረዋል ወይም ደግሞ በፅሁፍ የሚገልፀውን አዕምሮው ላይሸከመው ይችላል፤ እሳቸው ግን አዕምሯቸው የተሸከመውን የሃሳብ ልክ በፅሁፋቸው ውስጥ እናነበዋለን፡፡
 በተለይ በቅርቡ ያሳተሙት “የትዝታ ፈለግ” መፅሐፋቸው ማን እንደሆኑ ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ በዚህ ብቻም አይደለም፡፡ በሙያቸውም የተከበሩ ሰው ናቸው፡፡ የሚገርመው ነገር በህግ ባለሙያነታቸው የረቀቀ አቅምና እውቀት ቢኖራቸውም፣ ብዙ ነገር ሲናገሩ በተማሩበት የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው አይደለም፡፡ ‹‹እኔ’ኮ የህግ ሰው ነኝ›› እያሉ አይደለም የሚፅፉትና የሚናገሩት። እንደ ማንኛውም ሰው ሃሳብ ይሰጣሉ፡፡ የህግ እውቀታቸውን ለማስፈራሪያነት  ወይም ደግሞ ለማደናበሪያነት አይጠቀሙበትም፡፡ በእውነቱ እሳቸው ለሙያ የተወለዱ ሰው ነበሩ፡፡ በሰላም ግብራቸው፣ የሰብዕና ክብራቸውን ጠብቀው የኖሩ ናቸው፡፡ በሚፅፉት ሁሉ የማወላወል ሃሳብ ሳያሳዩ፣ በፀና አቋም ዘልቀዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚፅፏቸውን፣ ውጭ ሃገርም የሚወያዩዋቸውን ነገሮች አይቻለሁ፡፡ በእውነት ልናከብራቸው የሚገቡ ትልቅ ሰው ናቸው። በህይወት ሳሉ የበለጠ ብናከብራቸውና አክብሮታችንን ብንገልፅላቸው ደስ ባለኝ ነበር፡፡
እኔ ሁልጊዜ እሳቸውን ሳስብ የተፈጠሩበት የጋሞ ምድር፣ ጨንቻን አስታውሳለሁ፡፡ ለበርካታ ጊዜያት ጨንቻ አካባቢ ለስራ እመላለስ ነበር፡፡ እዚያ አካባቢ ሄጄ ተራሮችን ሳይ፣ እሳቸው ነበሩ እንደ ሃውልት ገዝፈው የሚታዩኝ፡፡ አቶ አሰፋ የትውልድ አካባቢያቸው ብቻ ሳይሆን የሃገር ኩራትም ናቸው። እንደነዚህ አይነት ዜጎች መታሰቢያ ቢቆምላቸው፣ ሌጋሲያቸው የሚተረክበት መድረክ ቢመቻች መልካም ነው እላለሁ፡፡
እኔ የሚቆጨኝ በርካቶች የነካኩትን የመንግስት ለውጥ ዘመን ከሳቸው አንደበት አለመስማታችን ነው፡፡ ከሳቸው አንደበት ብሰማ ወይም ከብዕራቸው ባነብ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ እሳቸውና ወዳጆቻቸው በወቅቱ የመሰረቱት አንዱ የፖለቲካ ክንፍ፣ በወቅቱ ተደማጭና ተፅዕኖ ፈጣሪ ነበር፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በደንብ ከሳቸው መስማት እፈልግ ነበር፡፡ ያንን ዘመንና ትውልድ፣ ከእሳቸው አንፃር ብናየው ጥሩ ነበር፡፡ ሌላው በደንብ ባውቀው ብዬ የምመኘው፣ በእነሱ ዘመን የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው እንዴት ነበር? ከአቻዎቻቸው ጋር እርስ በእርስ ይግባቡ ነበር ወይ? የሚለውን ነው፡፡ አሁን በሃገራችን ካለው ፖለቲካ አንፃር፣ በነሱ ዘመን መቻቻል ነበር ወይ? የሚለውን ማወቅ እፈልግ ነበር፡፡ ያ መቻቻል ስለጠፋ ነው፣ አንዱ አንዱን ያጠፋው፡፡ በዚህ ረገድ ክፍት ቦታ ትተውብን አልፈዋል፡፡

“ተሟጋች፣ ተጋፋጭና ተጋላጭ የብዕር ሰው ነው”
እንዳለጌታ ከበደ (ደራሲ)
ከጋሽ አሰፋ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ከፈጠርን ሁለት ዓመት አይሆነውም፤ ግን ለብዙ አመታት ሳነበው ቆይቻለሁ፡፡ ምንም እንኳ ከ1980 አጋማሽ ጀምሮ በ”ጦቢያ” እና “ኢትኦጵ” መፅሄቶች ላይ እንዲሁም በ”አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ የሚፅፋቸውን ፖለቲካዊ መጣጥፎች፣ የጉዞና የባህል  ማስታወሻዎች፣ እንዲሁም ወጎች ሳነብ የቆየሁ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ አሰፋ ጫቦ መፃፍ የጀመረው ከ1950ዎቹ ጀምሮ እንደነበር ለመገንዘብ ችያለሁ። አዳዲስ መፅሐፎች በሚወጡበት ሰዓት ትችት በማቅረብ፣ምልከታውን በማሳየት ቀዳሚ ከሆኑ ሰዎች መካከል አንዱ እንደሆነም ይታወቃል። ጋዜጦቹም ምስክሩ ይሆናሉ፡፡   
ጋሽ አሰፋ በእኔ እይታ ተሟጋች፣ ተጋፋጭ እንዲሁም ተጋላጭ የሆነ የብዕር ሰው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለብዙ ጊዜ ስናምናቸው የቆየናቸውን አስተሳሰቦች በመናድ እንደገና ደግሞ ልክ አይደሉም ብሎ በመካድ፣ አወይይና አነታራኪ የሆኑ መጣጥፎችን ይፅፋል፡፡
ከእሱ ፅሁፎች በአብዛኛው ደስ የሚሉኝ የጉዞ ማስታወሻዎቹና የዶርዜን ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ የተጠቀመበት መንገድ ነው፡፡ ፅሁፎቹ ለህይወት እጅግ በጣም ቅርብ ናቸው፤ ልብ ይነካሉ፣ ስሜት ያሞቃሉ፤ ልክ ልብወለድ የማንበብ ያህል ቀለል ባለ መንገድ ነገሮችን ይተርካቸዋል፡፡ ከምንም በላይ እኔ ስለ ጋሽ አሰፋ ሳስብ፣አንድ ጉዳይ ጨርሶ አይረሳኝም፡፡ ይኸውም የኢትዮጵያ አንድነትን በተመለከተ ደርግ የተጫወተውን ሚና ልንክድ እንደማይገባን፣ ኢህአዴግ ደግሞ በተቃራኒው የቆመ እንደሆነ ለመናገር ያልሰነፈ ሰው መሆኑ  ነው፡፡ አንድ ሰው ከ10 ዓመት በላይ በእስር ቤት ስላሰቃየው ጠላቱ፣ በእንዲህ አይነት መንገድ ሲመሰክር መስማት ይገርመኛል፡፡ ከ10 ዓመት በላይ ታስሮ፣ ከ25 ዓመት በላይ በስደት ቆይቶ፣ ህልፈቱ ሲሰማ የሚፈጥረው ስሜት ከባድ ነው፡፡
የናፈቃትን ጨንቻን ሳይመለከት፣ የናፈቀውን ኢትዮጵያዊ ወገኑን ሳያይ፣ እንደ ልቡ የጠቀሳቸውን ሰዎች ሳያገኝ እንደወጣ መቅረቱ የሚፈጥረው ስሜት ቀላል አይደለም፡፡ በስልክም በኢ-ሜልም በምንገናኝበት ጊዜ፣ የህይወት ዘመኑ መጨረሻ እንደሆነ እንደሚሰማው አውቅ ነበር፡፡ እኔና እሱ እንድንተዋወቅ ምክንያት የሆነን፣ በአንድ ወቅት አንድ መጣጥፍ ፅፌ ነበር፡፡ እዚያ መጣጥፍ ላይ በኢትዮጵያ የወግ አፃፃፍ ላይ ሳነባቸው እጅግ በጣም ስሜት ከሚሰጡኝ ሰዎች መካከል ብዬ፣የአሰፋ ጫቦንና የመስፍን ወ/ማሪያምን ስም ጠቅሼ፣ እግረመንገዴንም “የት ነው ያለኸው? ምን ሆነህ ነው የጠፋኸው?” የሚል ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ነው እየተገናኘን መተዋወቅ የጀመርነው፡፡ አንድ ሰው በሚፅፋቸው ሁሉ፣ ሁሉም ይስማማል ወይም ሁሉንም ይቀበላል ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡
ጋሽ አሰፋ ደግሞ ተጋላጭ ነው፤ የተሰማውን ፊት ለፊት የሚፅፍ ነው እንጂ ሀሳቡን ስሜቱን ጨቁኖ የሚይዝ አይደለም፡፡ እንደመታደል ሆኖ ደግሞ ከተለያዩ ሰዎች ጋር የመተዋወቅና የመግባባት እድል ገጥሞት ነበር፡፡ ዛሬ የት እንደወደቁ የማናውቃቸውን የእስር ቤት ጓደኞቹን በሚያነሳበት ጊዜ ሰብአዊ ስሜታቸውን ነው እንድናውቅና እንድንረዳ የሚያደርገው፡፡ በጥቅሉ ነገርን አጣፍጦ የማቅረብ ችሎታ አለው፤ ችሎታውንም ደግሞ አሳይቶናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁኔታዎች ቢመቻቹ፣ ጤናው የተጠበቀ ቢሆን፣ በሚወደው አካባቢ መኖር ቢችል ደግሞ የተሻለ ይሰራ ነበር፡፡
በመጨረሻ የህይወት ምዕራፉ ሲፅፋቸው የነበሩ ፅሁፎቹ፣ የተናዳፊነት ባህሪ የሚስተዋልባቸው ሲሆኑ ጠንካራ ትችቶችም ነበሩ፡፡ ዶርዜን የማውቀው በእሱ አይን ውስጥ ነው፤ ይሄ ትልቅ መታደል ነው፡፡ ደግሞ ሲፅፍ ነፃ ሆኖ ነው፡፡ የዚያ ማህበረሰብ ተወላጅ መሆኔን አልተወውም፤ ደግሞም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ነው፡፡ ቅኝቱ ይሄ ነው፡፡ እኔን የሚገርመኝ አንድ አገላለፅ አለው፡፡ “የኢትዮጵያ ህዝብ የማይመጣን ነገር የመጠበቅ የረዥም ጊዜ ልምድ አለው” ይላል፤ አንድ ፅሁፉ ላይ፡፡ የማይመጣን ነገር የመጠበቅ - የሚለው በጣም ይገርመኛል፡፡
እንዳጋጣሚ እኔም መጣጥፌን ስፅፍ፣“የማይመጣን ነገር መጠበቅ” በሚል ርዕስ ነው፡፡ ሊመጣ እንደማይችል እሙን ነው፤ ከዚህ መንግስት ጋር አልተጣጣመም፡፡ ደግሞ እውነት ነበረው፡፡ ወታደሩ ለምን ይበተናል፡፡ የደርግ ወታደር ለምን ለማኝ ይሆናል እያለ ሲሟገት የኖረ ሰው ነው፡፡ በዚህ አቋሙ በመንግስት ዘንድ ሊወደድ አልቻለም፡፡ እንደነቃፊና ዘላፊ ነበር የተቆጠረው፡፡ በዚህ ምክንያት ተሰደደ ወጣ፤ በዚያው ቀረ፡፡ እኛም ቢመጣ እያልን ------ የማይመጣን ነገር ስንጠብቅ ቆየን ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነንም፣ የማረፉን መርዶ ሰማን፡፡ ያስቆጫል!!

“የራሱን አዕምሮ የሚናገር ሰው ነው”
አያልነህ ሙላት (ገጣሚና ጸሃፌ ተውኔት)
አሰፋን ካወቅሁት ጊዜ ጀምሮ የራሱ የሆነ ሰው እንደሆነ ነው የተረዳሁት፡፡ የራሱን አዕምሮ የሚናገር ሰው ነው፡፡ የማንም ተፅዕኖ የሌለበት ሰው ነው፡፡ የትኛውም ፓርቲ የራሱም ቢሆን ተፅዕኖ አያደርግበትም፡፡  
የኢትዮጵያ ምሁራን በተለይ በፖለቲካ ህይወት ውስጥ ያሉ ምሁራን ከሱ ብዙ የሚማሩት ነገር አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ አንደኛ የቆመለትን ፓርቲ ወይም ድርጅት ከማንኛውም በላይ አግዝፎ በማየት ፓርቲውን ከእውነትና ከህዝብ በላይ አድርጎ መገንዘብ እንደማያስፈልግ ከአሰፋ መማር ይቻላል። ሁልጊዜ የህዝብ አገልጋይነትን በወረቀት ላይ ሳይሆን በተግባር መግለፅ የእሱ አይነተኛ ባህሪ ነው፡፡ ፓርቲንና ሀገርን ነጣጥሎ ማየት እንደሚገባ ከአሰፋ መማር ይቻላል፡፡
ሌላው ትልቁ ነገር አሰፋ፤ የሀገር ፍቅር በትልቁ በውስጡ የሰረፀ ትልቅ ሰው ነው፡፡ አንድ ጊዜ የሆነ ክርክር ላይ ሲከራከር፣ ”ኢትዮጵያ በድላናለች፤ እንዲህ ሆነናል” ለሚሉ የተወሰኑ ሰዎች የሰጠውን መልስ መቼም አልረሳውም፡፡ ሀበሾች እንዲህ ይላሉ ብሎ አንድ ተረት ተረተ፤ “ተው ማነህ ተው ማነህ የተኛ ሰው አለ ትቀሰቅሳለህ” አለና፣ “ይሄንን እናንተ የምትሉትን በደል፣ መሪዎቿና ኢትዮጵያ በድላለች ካላችሁ፣ ከዚያ የበለጠ የተበደለ ሰው አለ። ተበዳይ ነን የምትሉ ሰዎች ደግሞ የበደላችሁት በጣም ከፍተኛ ህዝብ አለ፤እና ተዉ የተኛ ሰው አለ ትቀሰቅሳላችሁ፤ ያ ቢነሳ ደግ ትልቅ ተአምር ነው የሚፈጥረው” ብሎ አስገራሚ መልስ ነበር የሰጠው። አሰፋ ማለት እንደዚህ ነው እንግዲህ፡፡
ወደ ሥነ ፅሁፍ ከመጣን፣ አሰፋ በአማርኛም በእንግሊዝኛም ሲፅፍ ፅሁፎቹ ውብ ናቸው። የሚናገራቸውን በሙሉ ነው የሚፅፈው። የሚናገራቸው ለዛ ያላቸው በመሆኑ ነው፣ የሚፅፋቸውም ለዛ ያላቸው የሆኑት፡፡ ለአብዛኛው ሰው የፖለቲካ ፅሁፍ ማንበብ ከባድ ነው፡፡ አሰፋ ግን ለፅሁፉ ስሜት ሰጥቶ፣ ፍቅር ሰጥቶ፣ እውቀት ሰጥቶ ነው የሚፅፈው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለፅሁፎቹ የሚጠቀመው አማርኛ፣ ሌላ ቋንቋ የሚችል ሁሉ አያስመስለውም፡፡ ዘይቤው፣ ለዛው፣ ገፀ ባህሪ አሳሳሉ ከፍተኛ የሥነ ፅሁፍ ችሎታ ያለው መሆኑን ይመሰክራል፡፡ የሥነ ፅሁፍ ስራዎቹ ተነበው የማይጠገቡ፣ ውበት ያላቸው ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፅሁፎቹ ልክ እንደ ልቦለድ ነው የሚነበቡት፡፡
“የአንድ ዜጋ ስራ ከምንለው በላይ ሰርቷል”
ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ (የሥነ ፅሁፍ ምሁር)
አሰፋ ጫቦ ህይወቱን ለሚያምንበት ነገር የሠጠ ሰው ነው፡፡ ከመጀመሪያ አንስቶ ለሚያምንበት ነገር ወደ ኋላ የማይል ሰው ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በሚፅፈው ነገር አንባቢው ሊስማማም ላይስማማም ይችላል፤ ነገር ግን በሚፅፈው ነገር ሙሉ ሃሳቡን ለመግለፅ ወደ ኋላ አይልም፡፡ እሱን የሚደግፉትን ወገኖች ሳይቀር ያስቆጣ ፅሁፎች ፅፎ አይተናል፡፡ ደጋፊው የነበሩትን ነቃፊው ያደረጉ ፅሁፎች ፅፏል። ነቃፊው የነበሩትን ደጋፊው ያደረጉ ፅሁፎችን ፅፏል። ይሄ ሰው ከመሆን የሚመነጭ ነገር ነው፡፡ ሰው ከሆንክ አንድ ጽንፍ ይዘህ ልትሄድ አትችልም። የኛን ሃገር ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ አመለካከት ስንቃኝ፣ በአብዛኛው አንድ ፅንፍ የያዘ ነገር ነው፡፡ እንደ ሃይማኖት ማለት ነው፤ ሃይማኖት አይጠየቅም አይመረመርም፡፡ ከቤተሰብ ተወርሷል፤ በዚያ ይቀጥላል፡፡ ሰው ከሆንክ ግን ይህን አካሄድ ትለውጣለህ፡፡
ስራዎቹ በመጨረሻ ሰአት ተሰብስበው መታተማቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሌላው የማንክደው ነገር አሰፋ አማርኛ የመጀመሪያ ቋንቋው አይደለም፤ ነገር ግን በአማርኛ የመግለፅና ምስል የመከሰት የቋንቋ ችሎታው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ለአማርኛ ቋንቋ ያለው አመለካከት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ አሰፋ አቅሙን አሉታዊ ጉዳይ ላይ አያባክንም፡፡ ለምሣሌ “አማራ ነው የጎዳኝ፤ አማርኛ በሌሎች ቋንቋዎች ላይ የበላይ ሆኗል” የመሳሰሉ ነገሮችን አይልም። በእንዲህ አይነት አመለካከት ቋንቋውን እስከ መጥላት የሚደርሱ አሉ፡፡ ቋንቋውን በመጥላት በእንግሊዝኛ ወይም በሌላ ቋንቋ ካልሆነ አንፅፍም የሚሉ አሉ፡፡ ይሄ ችግርን ወደ ሌላ ነገር ማሳደግ ነው፡፡ እሱ እዚህ ውስጥ የለበትም፡፡ ያመነበትን ትክክልም ይሁን አይሁን በዚህ መንገድ ሲናገር ሲፅፍ የኖረ ሰው ነው።
እሱ ያመነበትን ፅፏል፣ በህይወቱም ለሃገሩ ቀናኢ ነበር፡፡ ሃገሩንና የፖለቲካ ስርአቱን በተመለከተ በጽሁፍ ያንጸባረቃቸው ሃሳቦች፣ ያመነበትን ነገር እንዳደረገ ምስክሮቹ ናቸው፡፡ ህይወቱን ላመነበት ነገር የሰጠ ሰው ነው፡፡
ዛሬ ብዙ ሰው ታዋቂ ሲሆን “ይሄን ብናገር ህዝብ ይጠላኛል” ብሎ ይፈራል፡፡ ፀሃፊ ከሆንክ ግን ያመንክበትን ከህዝብ ፊት ቀድመህ ፅፈህ፣ “ይሄ ነው መንገዱ” በማለት፣ ሰው አንብቦ እንዲከተልህ ማድረግ ነው ያለብህ፡፡ አብዛኛው ሰው የሚፈልገውን ነገር ብቻ አጉልተህ፣ “ይሄ ነው መንገዱ” የምትል ከሆነ ግን አንተ ከሰው ኋላ ነህ ማለት ነው፡፡ በዚህ ደግሞ አሣቢ ፀሃፊ ልትባል አትችልም፡፡፡ አሰፋ ጫቦ አሣቢ ፀሃፊ ነው፡፡ ለሃገሩ የአንድ ዜጋ ስራ ከምንለው በላይ ሰርቷል፡፡
አንድ ሁለት ጊዜ በአጭር መልዕክት ተነጋግረን ነበር፡፡ ስራዬ ተሰብስቦ ታትሞ ባይ ይል ነበር፡፡ አንድ ልጅም እዚህ አለችው፤ የሷ ጉዳይ ያሳስበው ነበር። ይህን ሳስታውስ ምናልባት ለህይወቱ የሚያሰጋ በሽታ እንዳለበት ያውቅ ይሆን ብዬ እጠራጠራለሁ። እነ እንዳለ ጌታ ከበደ ብዙ ረድተውት፣ ፅሁፎቹ በተወሰነ መልኩ ተሰብስበው ታትመውለታል። መፅሃፉ ታትሞ ማየትና የልጁ ጉዳይ በጣም እንደሚያሳስቡት ይናገር ነበር፡፡
አሰፋ በየጋዜጣና መፅሄቱ የፃፋቸው ፅሁፎች በመፅሃፍ የታተሙት ብቻ አይደሉም፡፡ ከዚያም በእጅጉ ያልቃሉ፡፡ እንኳን እሱ ረጅም ዘመን የፃፈው ቀርቶ እኛም 100 እና ከዚያ በላይ ፅፈናል፡፡ ሃላፊነት ተሰምቶት የሚሰራ ሰው ከተገኘ፣ ቅፅ 2 መፅሃፍ ሊኖረው ይችላል፡፡
እኔ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ አይነት ነገር ሲፈጠር ሃዘን ነወ የሚሰማኝ፡፡ ሃገር የሁላችንም ናት፡፡  አንዱ ለሃገሬ የሚበጀው ይሄ ነው ይላል፤ ሌላውም የራሱን ያስቀምጣል፡፡ ዋናው ነገር ያገባኛል ብሎ ስለ ሃገር መናገር መቻል፣ ለሃገር የሚበጀው እንዲህ ነው ብሎ መናገርና የውይይት አጀንዳ መፍጠር ነው፡፡ መሃል ላይ ያለና አጀንዳ የሚፈጥር ነው የሚያስፈልገን። እነኚህ ሰዎች ደግሞ ለእንዲህ አይነቱ ውይይት ህይወታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የሚያምኑበት እየፃፉ ኖረዋል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መማር ያለብን፣ የሰውን ሃሳብ አክብረን የራሳችንን መግለፅ መቻልን ነው፡፡

Read 5645 times